“በጠብታ ውሃ ውስጥ ጉማሬ አየን” የሚሉ “እውነትን” ያረጋግጣሉ!

ከላይ የተጠቀሰው አባባል የተለየ ቅጥፈት ወይም የተጋነነ ውሸትን ለመግለፅ የሚውልና የጋዜጠኞችን የስነ ምግባር ብልሹነት የሚገልፅ ነው። ነገር ግን፣ ያ በቢላ የማይደፈረው የጉማሬ ቆዳ የፀሃይ ብርሃን ሲነካው ስለሚሰነጣጠቅ ቀን-ቀን ሙሉ አካሉን በውሃ መሸፈን አለበት። ማታ ላይ ደግሞ ሳርና ቅጣላ-ቅጠል ለመመገብ ይወጣና ሲነጋጋ ተመልሶ ወደ ውሃው ይገባል።

ለምሳሌ እኔ “በጠብታ ውሃ ውስጥ ጉማሬ አየሁ!” ብል ሊከተል የሚገባው ጥያቄ “ነገሩን ያየኸው ቀን ወይስ ማታ?” የሚል መሆን አለበት። በዚህ መልኩ፣ ማታ ላይ ዝናብ እየዘነበ ሳለ ጉማሬው ምግብ ፈለጋ ሲወጣ በዝናቡ ጠብታ ውስጥ ስላየሁት ያልኩት ትክክል ነው። ነገሩ የሆነው ቀን ላይ ከሆነ ግን ያልኩት ነገር ተዓማኒነት አይኖረውም። በመሆኑም፣ አንድ ጋዜጠኛ/ፀሃፊ እውነት ሲፅፍ እውነትነቱን ያረጋግጣል፣ ማህብረሰቡን ያሳውቃል። በተመሳሳይ፣ የፀፈው ውሸት ከሆነ አሁንም የነገሩን እውነትነት ከማረጋገጥ የዘለለ ሚና አይኖረውም። ምክንያቱም፣ የተፃፈው ነገር ውሸት ከሆነና ይህንን በበቂ መረጃ ላይ ተመስርቶ ውድቅ የሚያደርግ ሌላ ፅሁፍ እንዲፃፍ ስለሚያደርግ፣ አንድ ጋዜጠኛ/ፀሃፊ ውሸት በመፃፉ እውነት እንዲታወቅ ያደርጋል፣ በዚህም ማህብረሰቡን ያሳውቃል።

ከዚያ ይልቅ፣ አንድ ጋዜጠኛ/ፀሃፊ የፃፈው ነገር ውሸትም ሆነ እውነት “ፀረ-ሰላም…ፀረ-ልማት…ከተለያዩ የአሸባሪ ድርጅቶች…ከፀረ-ሰላም ሃይሎች ጋር ግንኙነት………” ወዘተ በሚሉ ውንጀላዎች እስር-ቤት የምገባ ከሆነ፣ ከማንም የሚጎዳው “እውነት” ራሱ… እውነትን ማወቅ ያለበት “ህዝብ” እንደ ህዝብ፣ በእውነት ላይ ተመስርታ መመራት ያለባት “ሀገር” እንደ ሀገር…ሁሉም ይጎዳሉ። አሁን በእስር ቤት ያሉ ጋዜጠኞች፣ ፀሃፊዎች እና ጦማሪያ ይፈቱ የምንለው እንደ ህዝብና እንደ ሀገር ሁላችንም ስለምንጎዳ፣ …እየተጎዳንም ስለሆነ ነው።

ethiothinkthank.com