#Adigrat_for_Sale!

አፄ ሚኒሊክ ለፈረንሳይ መንግስት ጁቡቲን ለ100 ዓመት በሊዝ መሸጣቸው፣ በተለይ በትግራይ እና በኦሮሞ ተወላጆች ዘንድ፣ እንደ ከፍተኛ የሀገር ክህደትና ወንጀል ተደርጐ ሲጠቀስ መስማት የተለመደ ነው። መቼም ታሪክን አለማወቅ ለጭፍን ፍርድ ያመቻልና፣ አፄ ሚኒሊክን ብቻ ተወቃሽ ማድረግ የአላዋቂ ፍርደ-ገምድልነት ነው።

የታሪክ እውቀት አንድን ክስተት ጠቅሶ በዚያ ላይ መንጫጫት አይደለም። ከክስተቱ ጀርባ ያለውን ነባራዊ እውነታ መረዳት፣ በገሃድ የታየውን ብቻ ሣይሆን ‘ሊሆን ይችል የነበረና በተለያዩ ምክንያቶች እውን ሳይሆን የቀረን’ ጭምር መገንዘብ ይጠይቃል። የኢትዮጲያን ታሪክ ከዚህ የታሪክ እሳቤ አንፃር ካየነው፣ እርግጥ “የኢትዮጲያን መሬት ቆርሶ መሸጥ ብርቅ ነው’ዴ” ያስብላል?

ለዚህ ፅሁፍ ርዕስ መነሻ የሆነኝና ላነሳሁት ሃሳብ አይነተኛ ማሳያ የሚሆነውን፣ በትግራይ ክልል የዓዲ-ግራት አከባቢን፣ “የአጋሜ አውራጃ” በመውሰድ እ.ኤ.አ ከ1840 -1889 ዓ.ም በነበረው ግዜ ውስጥ በማንና ለማን ተሸጦ እንደነበር የታሪክ መዛግብትን እያጣቀስን ብንመለከት የታሪክ ቁስልን እንደማከክ ይሆናል። እስኪ ይህን አስቀያሚ የታሪክ ቁስላችን አከክ…አከክ እናድርግ።   

ጳውሎስ ኞኞ፣ “አጤ ቴዎድሮስ” በሚለው መፅሃፉ #እቴጌ_መነን ኢትዮጲያን እየከፋፈሉ ሊሸጡ ካስማሙ ባላባቶች አንደኛይቱ እንደነበሩ ይነግረናል። ጳውሎስ እንደፃፈው “…በአልክሳንድርያ የቤልጅግ መንግስት ቆንስል የነበረው ኤድዋርድ ብሎንዲል ከእቴጌ መነን (የራስ አሊ እናት) ጋር በመነጋገር #አጋሜንና_እንጣሉን በ15000 ማርትሬዚያ ብርና በሶስት ሺህ ጠመንጃ ለመግዛት ተስማምተው ነበረ። ለዚህም ጉዳይ ኢትዮጲያዊው አባ ገብረ ማሪያም ለኢትዮጲያ መንግስት ኃላፊ ሆነው ለሽያጩ ተግባር ዋና ደላላና ተዋዋይ ነበሩ።”

“… አባ ገብረ ማሪያም ካይሮ ውስጥ ከቤልጅጉ ቆንሲል ከብሎንዲል ጋር የተዋዋሉት ውል እንዲህ የሚል ነበር። “በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም። እኔ ገብረ ማሪያም የኢትዮጲያ እጨጌ፣ በኢትዮጲያ ገዢ በራስ አሊ ስም የሚከተለውን ተስማምቻለሁ። #ለቤልጅግ_ንጉሥ ግርማዊ ቀዳማዊ ሊዎፖልድና ለእሳቸው ወራሾች ሁሉ እንዲሆን #የአጋሜን_አውራጃ_በሙሉ ከአዲግራት እስከ ባህሩ ድረስ ሰጥተናል” የሚል ነበር።
(ጳውሎስ ኞኞ፥ 1985፥ አጤ ቴዎድሮስ፥ ገፅ 40 – 41)

ከዓዲግራት እስከ ቀይ ባህር ድረስ ያለውን የኢትዮጲያ መሬት ቆርሶ ለመሸጥ ከቤልጅግ ቆንፅላ ጋር ውል ተገብቶ የነበረ ቢሆንም የሽያጭ ስምምነቱ ውድቅ የሆነው በሌላ ምክኒያት ሣይሆን ገዢው አካል ጥናት አድርጐ ቦታው አዋጭነት እንደሌለው ስላመነ ነበር። ከላይ በተጠቀሰው መፅሃፍ እንዲህ ይላል፣ “የቤልጅግ መንግስት ጉዳዩ እንዲጠና አደረገ።…በጥናቱ መሰረት የቀይ ባህርን አከባቢ መያዝ እንደማይጠቅም ታወቀ። …ምክንያቱም ያኔ የስዊዝ ቦይ አልተቆፈረ ስለነበረ በመርከብ ወደ ቀይ ባህር ለመምጣት በደቡብ አፍሪካ ዞሮ በመሆኑ ወጪ እንደሚያስወጣና ጉዞው ረጅም በመሆኑ አያስፈልግም ተብሎ ተወሰነ (ጳውሎስ ኞኞ፥ 1985፥ አጤ ቴዎድሮስ፥ ገፅ 42)።

በመቀጠል፣ “ማን ማንን ሸጠ?” የሚለውን የጭፍን ብሔርተኞችን ጥያቄ እናንሳ። የሽያጭ ስምምነቱ “በኢትዮጲያ ገዢ በራስ አሊ ስም የሚከተለውን ተስማምቻለሁ” እንደማለቱ በሺያጭነት የሚጠቀሱት ራስ አሊ ናቸው። #ራስ_አሊ_አሉላ ማን ናቸው? የጎንደርን መሳፍንት አገዛዝ የጀመሩት ትልቁ ራስ አሊ ልጅ ራስ ጉግሣ፣ የራስ ጉግሣ ልጅ አሉላ፣ የራስ አሉላ ልጅ ራስ አሊ። እንግዲህ፣ የዘር ሀረጉ እንደሚያሳየን ራስ አሊ የራስ አሉላ እና እትጌ መነን (በትክክለኛ ስሟ “ፋጡማ“) ልጅ ነው። ራስ አሊ የአጎታቸውን የራስ ዶሪን ሞት ተከትሎ በ1822 ዓ.ም በ12 ዓመታቸው የኢትዮጲያ ገዢ የነበሩ ሲሆን የትውልድ አገራቸው #የጁ ነው። በዚህ መሰረት፣ የኢትዮጲያን መሬት ቆርሶ ለባዕዳን በገንዘብና በቁስ ከሸጡ የሀገር ገዚዎች ውስጥ ራስ  አሊ አንዱ ሲሆኑ የዘር ግንዳቸው ሙሉ-በሙሉ የየጁ #ኦሮሞ ነው። 

የሽያጩን የብሔር ማንነት ካወቅን፣ (አሁንም ከፅንፈኞች እይታ አንፃር ለማቅረብ ካልሆነ በስተቀር የሚከተለው ጥያቄ ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ድምፀት እንዳለው አሳስባለሁ) ‘ማንን ነው የሸጠው?” ብለን ስንጠይቅ የአጋሜ አውራጃን ነዋሪ፣ የአጋመ/አጋሜ ማህብረሰብ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።

እንግዲህ የታሪክ ቁስልን የማከክ ውጤቱ ይሄ ነው! በብሔር፣ ብሔረሰቦች ላይ የተመሠረተ የአስተዳደርና ፖለቲካ መዋቅር የሚመፃደቁና መዋቅሩ በአፄ ሚኒልክ ተቀርፆ የተዋቀረና በመለስ ዜናዊ ተደርሶ የቀረበ መሆኑን መገንዘብ ተስኗቸው፣ አፄ ሚኒልክን በ”ሀገር ሺያጭነት!” ሲፈርጁ የሚውሉ አንዳንድ የትግራይ እና ኦሮሞ ተወላጆች፣ ይሄው በዚህ ታሪካዊ እውነታ ራሳቸውን ሺያጭና ተሺያጭ ሆነው ያገኙታል።

ነገር ግን፣ አንድ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ ያደረሰው ታሪካዊ በደል ተደርጐ ሊወሰድ አይገባም። ለምሳሌ፣ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ፣  “የየጁ ኦሮሞ ትግራይን ለባዕዳን ሸጠ” ለማለት እንደማይቻል የሚያሳይ ሌላ የታሪክ እከክ ልጥቀስ።

“ዓፄ ሚኒልክ እና የኢትዮጲያ አንድነት” በሚለው መፅሃፉ ተክለ-ፃዲቅ መኩሪያ በግልፅ እንዳስቀመጠው፣ የአከባቢው ገዢ  የነበሩ ሰውች ከጣሊያን ጋር በማበርና ለወራሪ ሃይል መሣራያ በመሆን ራሳቸውንና ሀገራቸውን አሳልፈው ሸጠዋል። “…የየጣሊያን ጦር አስመራ ከገባ በኋላ #የአጋሜው_ደጃች_ስብሐት እና የአካለ ጉዛዩ ደጃች ባሕታ ሐጎስ ለኢጣልያ ታመኝ ሆነው ስለገቡለት፣ በማናቸውም ረገድ የኢጣሊያን አቅም ለጊዜው እየበረታ ሔደ…”
(La Prima Guerra D’Africa –R Battaglia pp 355 – 360)።

በመጨረሻ፣ በብሔር ተደራጅቶ፣ በብሔር እያሰበ፣ በብሔር እየጠላ፣ በብሔር እየተጋባ፣ ብሔርን አስቦ፣ ፈቅዶና መርጦ ያገኘው መገለጫ ባሕሪው ላደረገው ይህ ትውልድ፣ አስቀያሚውን ያለፈ ታሪክ በብሔር ከፋፍሎ ቁስል መለጣጠፍ ከተጀመረ መጨረሻው አሰቃቂ ይሆናል። ግለሰብ እንጂ ብሔር አድራሻ የለውም። ብሔር ስም አለው እንጂ የግል ስብዕና የለውም። በስሙ ግፍና ወንጀል ይሰራል እንጂ ብሔር በአካል ቀርቦ አይከስም፣ አይከሰስም። ተጠያቂነት መውሰድ ለማይችል “ብሔር” የሚባል አካል የሰጠንው ሃላፊነት በመጨረሻመዓት ይዞብን ይመጣል!!!
******
ስዩም ተ.

ethiothinkthank.com