ህዝቡ በተቃውሞው ያነሳው ጥያቄ ምን ነበር?

ሰሞኑን በኦሮሚያ እየተካሄደ ያለው የሕዝብ ተቃውሞ፣ በተለይ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ በወሊሶ ከተማ እና በዙሪያዋ ባሉ የገጠር ከተሞች የታየው የህዝብ ተቃውሞ እጅግ በጣም አስገራሚና ሥር-ነቀል ነበር። በዚህ ረገድ የእንቅስቃሴው አስተባባሪዎች’ም ሆኑ እንቅስቃሴውን ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት አካላት ክስተቱ ከጠበቁት በላይ እንደነበር እሙን ነው። ነገር ግን፣ ከታህሳስ 03/2007 ዓ.ም ጀምሮ የመከላከያ ሠራዊት አከባቢውን ከመቆጣጠሩ ጋር ተያይዞ የህዝቡ ተቃውሞው እንቅስቃሴ የተለየ ገፅታ እየያዘ መጥቷል። ከጠላት ጋር ለመዋጋት ብቻ ሰልጥኖ በክፍተኛ ደረጃ የታጠቀ ብዛት ያለው ሠራዊት አከባቢውን ተቆጣጥሮ ባለበት ሁኔታ ህዝቡ በተለመደው መልኩ የተቃውሞ እንቅስቃሴ እንዲቀጥል ማነሳሳትና ጥሪ ማድረግ የብዙሃንን ሕይወት ለህልፈት ከመዳረግ በዘለለ ህዝቡ ባቀረበው ጥያቄ ላይ የሚጨምረው ነገር አነስተኛ እንደሆነ መገመት አያዳግትም። ከዚህ ባሻገር፣ በህዝቡና በጦር ሠራዊቱ መካከል ግጭቶች እያየሉ በሄዱ ቁጥር የህዝቡ እንቅስቃሴ ወደ ያልታሰበ አቅጣጫ ሊሄድና ከቁጥጥር ውጪ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ይፈጠራል። በመሆኑም፣ ቀጥሎ መሆን ያለበት ነገር የህዝቡን የለውጥ ጥያቄ እና ድምፅ በግልፅ መለየትና ለባለድርሻ አካላት ማሳወቅ ነው። ለዚህም ደግሞ የማህብረሰቡ የፖለቲካ ልሂቃን ህዝቡ በተቃውሞ ሰልፉ ያስተላለፈውን መልዕክት በግልፅ ለይቶ በማስቀመጥና በማሳወቅ ረገድ ጠንክረው መስራት ይጠበቅባቸዋል። እኔ በግሌ፤ ‘ህዝቡ ከአዲስ አበባ ማስተር-ፕላን በተጨማሪ በመልካም አስተዳደር እና ፍትህ ዙሪያ ሥር-ነቀል ለውጥ እንደሚሻ ግልፅ የሆነ መልዕክት አስተላልፏል’ የሚል እምነት አለኝ። እናንተስ…?  
#Woliso #OromoProtesters

ethiothinkthank.com

Advertisements