ምክር ቤቱ ሶስት ዳኞችን በስነ ምግባር ችግር አሰናበተ

አዲስ አበባ ጥር 28/2008 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስነ-ምግባር ችግር የታየባቸውን ሶስት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች አሰናበተ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው ልዩ ስብሰባ እንዲሰናበቱ ያደረጋቸው ዳኞች የህግ ጥሰት በመፈጸምና ለህገመንግስቱ ታማኝ ባለመሆን በፈፀሙት የስነ- ምግባር ጉድለት ነው።

ምክር ቤቱ እንዲሰናበቱ ያደረገው በዛሬው እለት ከዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የቀረበለትን ማስረጃ መሰረት በማድረግ ነው።

ከዳኝነት ስራቸው እንዲሰናበቱ ምክር ቤቱ ቅጣት ያስተላለፈባቸው ዳኞች አቶ ግዛቸው ምትኩ፣አቶ ሀብታሙ ሚልኪ እና አቶ አብረሐ ተጠምቀ ናቸው።

ምክር ቤቱ አቶ ግዛቸውን ከዳኝነት ሥራቸው እንዲሰናበቱ ያደረገው “ህገ-መንግስቱ እንዲሻሻል በተደጋጋሚ የሚጠቅሱ በመሆኑ፣ለህገ-መንግስቱ ታማኝ ባለመሆናቸው፣ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አባል ያልሆነችው መንግስት ተደጋጋሚ የመብት ጥሰት ስለሚፈጽም ተጠያቂ ላለመሆን ነው፣በኢትዮጵያ የብሔር እኩልነት አልተረጋገጠም” በማለታቸው እንደሆነ ተገልጿል።

እንዲሁም በጀት ከሚመለስ ለምን እቃ አይገዛም ወይም ለምን ዳኞች እንዲከፋፈሉት አይደረግም የሚል የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት የሚያራምዱ ለመሆናቸው ለምክር ቤቱ ቀርቧል።

ህገመንግስቱን በታማኝነት ሙሉ ለሙሉ ባለመቀበላቸውና የዳኝነት ነጻነትና ገለልተኝነት የጎደለባቸው በመሆኑ ምክር ቤቱ ከስራቸው እንዲሰናበቱ አድርጓል።

አቶ ሀብታሙ ሚልኪ ደግሞ “በተከራካሪዎች ላይ የስነ-ምግባር ግድፈት በመፈፀም፣በግልጽ አሰራር፣በዳኝነት ነጻነት ችግርና በፍርድ ቤቶች ተዓማኒነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖን የሚያሳርፍ ከባድ ጥፋት ፈፅመዋል” የሚል ማስረጃ በመቅረቡ ነው።

ዳኛው በሰሩት የስነ ምግባር ግድፈት በአስተዳደሩ ከተመደቡበት ስራ ውጭ የሌላ ችሎት መዝገብ ስበው በማየትና ትእዛዝ በመስጠታቸው፣ የተለያዩ ተደራራቢ ድንጋጌዎችን መተላለፋቸው፣በተመሳሳይ ደረጃ ባለ ዳኛ ከተሰጠ ትእዛዝ በተቃራኒ ትዕዛዝ በመስጠታቸው እንደሆነ ተገልጿል።

በምክር ቤቱ እንዲሰናበቱ የተደረጉት ሦስተኛው ዳኛ አቶ አብርሐ ተጠምቀም በዓቃቤ ህግ በኩል እንዳያዩት አቤቱታ የቀረበበትን መዝገብ ማየት መቀጠላቸው ከቀረቡባቸው አምስት የስነ ምግባር ግድፈቶች አንዱ ነው።

ዳኛው ከተከሳሽ ወገን ዝምድና ያላቸው በመሆኑ ከአዲስ አበባ ወደ ጋምቤላ እንዲዘዋወር በሌላ ደኛ ቀጠሮ የተላለፈበት ችሎት በአዲስ አበባ እንዲታይ ትእዛዝ ለውጠው ሰጥተዋልም ተብሏል።

በሌላ ዳኛ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፎበት ውሳኔ ተሰጥቶበት ለቅጣት ያደረ መዝገብ ወስደው ቅጣቱን በመወሰናቸውና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ሲታይ የነበረ የወንጀል ጉዳይ እንዲቋረጥ ጉዳዩን በሚያዩ ዳኞች ላይ ተጽዕኖ በመፍጠራቸው መሆኑን ተገልጿል።

ማስተባበያ እንዲቀርብለት የተያዘ የቅሬታ ነጥብ በተዘዋዋሪ ችሎት በደቡብ ክልል ሲታይ በነበረው የወንጀል ክርክር በዓቃቤ ህግ የቀረቡ ምስክሮችን ያለ አግባብ በማዋካብና ገለልተኛ ባለመሆናቸው ምክር ቤቱ አሰናብቷቸዋል።
****
Featured, 07 Feb 2016|ፖለቲካ
www.ena.gov.et

ethiothinkthank.com