ከመምህር ፓስተር ስትመርጡ…በቃኝ!

የሙርሲ እናት፣ የሙርሲ ቆንጆ፣ የሙርሲ ጉብል፣….እናንተ ሙርሲዎች፣… አንቺ ኢትዮጲያ፣.. እስኪ ልጠይቃችሁ። ኧረ እንደው ለመሆኑ የሰማሁት ነገር እውነት ነው? ከምር ግን፤ “ከዘመናዊ ትምህርት በፊት የወንጌል ስብከትን አስቀደማችሁ፣ ከመምህር ፓስተር መረጣችሁ” የሚባለው እውነት ነው እንዴ? ከትምህርት ቤት – መዝሙር ቤት፣ ከጤና ጣቢያ – ቤተ-ክርስቲያን ያስፈልጋል” ሲባል “በደስታ ጮቤ ረገጣችሁ” መባሉ ቅንጣት ያህል እውነትነት አለው? እንዲህ ከሆነ’ማ… የእናንተ ነገር በቃኝ!

የሙርሲ እናት፤
እኔ እኮ ሞኝ ነኝ። የሙርሲዎች እምነት “የእውነት” ይመስለኛል። አየሽ፣… እምነትሽ ለፈጣሪ የሚሰጥ ዘላለማዊ ክብር እንጂ ለወንጌል ስብከት መዳረሽ፥ ማቆያ አይመስለኝም ነበር። የአምልኮ ሥነ-ስርዓቱ ለፈጣሪሽ ያለሽን ከብርና ምስጋና የምትገልጪበት መንገድ እንጂ፣ የወንጌል ሰባኪ ፓስተሮች እና ወንጌል ተቀባይ ባለስልጣናቶች እንደሚያስቡት፣ ባለማወቅ የምታደርጊው የባዕድ አምልኮ አይመስለኝም ነበር። ችግሮችሽ ሁሉ በወንጌል ስብከት ፈውስ እንደሚያገኙ፣ ለዚህም ደግሞ 50ሺህ ቤተ-ክርስቲያን በአጥቢያሽ ሊገነባልሽ እንደሆነ ባለግዜዎች በኩራት ሲናገሩ ሰማሁ። እውነት ግን፣ ለዘመናት ያመንሽበትን እምነት “ስህተት”፣ አምልኮሽ’ም “የውሸት” መሆኑን በአደባባይ ከሚያውጁ ባለግዜዎች ጋር አብረሽ እኔ’ን ችላ ካልሽኝ እኔ ምን ቀረኝ? …በቃኝ! 

image

የሙርሲ ቆንጆ፤
“ከከንፈርሽ ላይ ያለው የሸክላ ጌጥ ያስዉባል እንጂ አያሳፍርም! እንደ የትግራይ ሴት የእጅ ላይ ንቅሳት፥ እንደ የጎንደር ሴት የግንባር ላይ ንቅሳት፥ እንደ የጎጃም ሴት የአንገት ላይ ንቅሳት፥ እንደ የኦሮሞ ሴት የጉንጭ ላይ ንቅሳት፣ እንደ የጋምቤላ ወንድ የግንባር ላይ ነቅሳት፥… እንደ መላው ኢትዮጲያዊ ያንቺም ከንፈር “በንቅሳት” የተዋበ ነው። ማንም ከማንም የበለጠ አያምርም፥ አያስጠላም…” እያልኩ በቁንጅናሽ ብወራረድ፣ “የከንፈርሽን ንቅሳት እንደ የወላይታ “በቄ” አያምርም” ለሚል ፓስተር ደግፈሽ አስረታሽኝ? በቃኝ!

የሙርሲ ጉብል፤
“አንተ ያለ ልብስ እርቃንህን የምትሄደው ሰውነትህ በስብ የታጨቀ፥ ተንዘረጠጠ፣…በጨርቅ መሸፈን ያለበት አስቀያሜ ገላ ስላልሆነ ነው፣ …ከዚያ ይልቅ፣ በፀሃይ ሙቀትና በተፈጥሮ ወዝ ያማረ፣ እንደተወለወለ መስታዎት የፀዳ ጥቁር ገላ ስላለው ነው፣… እንደ ክርስቲያኑ የጎጃም ገበሬ “ቁምጣ”፣ እንደ ሙስሊሙ ሶማሌ “ሽርጥ”፣… በአየር ፀባዩና አኗኗሩ ላይ የተመሰረተ ‘የአለባበስ ስልት’ ነው፤ … ከ20-30 ሺህ ብር የሚያወጣ ክላሽንኮፍ መሣሪያ ከእጁ የማይለየው የሙርሲ ጎልማሳ ለብጫቂ ጨርቅ መግዢያ የሚሆን ገንዘብ አያጣም…” እያልኩ በኩራት ስናገር፣ እርቃን ገላህን ለማየት ተፀይፎ አይኑን ከጨፈነ ፓስተር ጎን ቆምክ?… በቃኝ!

ሙርሲዎች፤
የ“Arkansas corporate” ተቋም ኃላፊ ከአሜሪካ ድረስ ተጉዞ የመጣው እንደ እኔ ሊጎበኛችሁ አይደለም። እሱ፣ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጲያ የመጣው፣ ከአዲስ አበባ ተነስቶ የኦሞ ሸለቆ ድረስ የመጣው፤ ወግ፥ ባህልና አኗኗራችሁን ሊያደንቅ አይደለም። በእርሱ ዘንድ እናንተ የራሳችሁ እምነት፣ ልማድና ደንብ የሌላችሁ “ኋላቀር ጎሳዎች” (primitive tribes) ናችሁ። ሃይለየሱስ አባተ (Haileyesus Abate) ከሰፈራችሁ እንደ ደረሰ አምረው፥ ተውበው በድሰታ እየተፍለቀለቁ አቀባበል ያደረጉለትን ዘመዶቻችሁን አይቶ ውበታቸውን ለማድነቅ አልታደለም። ከዚያ ይልቅ፣ እነሱን በማየቱ ብቻ እምባ አውጥቶ ነው ያለቀሰው። ወደ አሜሪካ ተመልሶ ከሄደ በኋላ’ም፣ የሙርሲዎች ምስል በዓይነ-ህሊናው እየመጣ ተቸግሯል። እምባውን ጠራርጎ ዙሪያ ገባውን ሲመለከት፣ በዚያ ለውጥና መሻሻል በራቀዉ ሰፈር ውስጥ ለእሱ ጎልቶ የታየው ነገር የመሰረተ-ልማት ግንባታ አስፈላጊነት ሳይሆን የእስልምና ሃይማኖት መስፋፋት ነበር። ሙርሲዎች፣… ከዕውቀት ስብከት በልጦ፣ ከመምህር ፓስተር ከመረጣችሁ፣..በቃኝ! 

ኢትዮጲያ፤
በድህነት አረንቋ ለዘመናት የዳከርሽ ልማትና እድገት አጥተሸ እንጂ እምነት-ሃይማኖት ቸግሮሽ አይመስለኝም። በድህነት ሰቆቃ የኖርሽው ምርጫና አማራጭ አጥተሸ እንጂ በፆም-በፀሎት ስላልተጋሽ አይመስለኝም። ለዘመናት ከአለም ተቆራርጠሸ፣ እይታሽ ከሰፈር እርቆ ያልሄደው የመጓጓዣ መንገድ፥ የመገናኛ ዘዴው ጠፍቶሽ እንጂ እምነት-ሃይማኖት ቸግሮሽ አልመሰለኝም። በአጉል-ልማድ ተተብትበሽ፣ በጎጂ-ባህል የታሰርሽው፣ ተምሮ የሚያስተምርሽ እንጂ ተተብትቦ የሚተበትብሽ ጠፍቶ አይመስለኝም።

እኔ፤ ፕሬዘዳንት ወይም ጠ/ሚኒስትር፣ አፈ-ጉባኤ ወይም አምባሳደር፣ ፓይለት ወይም ፓስተር አይደለሁም። ስልጣን ዕውቀትን በሚጠየፍባት፣ ዕውቀት ለስልጣን በሚያሸረጉድባት ሀገር ዕውቀትን የሚያስተምር፣…ስልጣን ሆነ ገንዘብ የሌለኝ፣… ባለስልጣንና ባለገንዘብ ከቁብ የማይቆጥሩኝ መምህር ነኝ። የህዝቤ ችግር የማይገባኝ፥ ስቃዩ የማይታየኝ ብኩን ነኝ። የድህነት መንስዔ ያልገባኝ፥ መፍትኄው ያልተገለፀልኝ ከንቱ ነኝ። “የኢትዮጲያ ችግር በትምህርትና ዕውቀት እንጂ በስብከትና ጥምቀት አይፈታም” እያልኩ ኖሬ፣ መምህር ከእጅ-ወደ-አፍ እየኖረ በከፈለው ግብር ለፓስተር የአየር ትኬት ሲገዛለት፣ ለመምህር ግዜ የሌለው አምባሳደር ፓስተርን በክብር እንግዳነት ሲያስተናግድ፣ መምህር ከሀገር እየተሰደደ ባለበት ሀገር ፓስተር ቤተ-መንግስትና ፓርላማ ድረስ ገብቶ ወንጌል ሲሰብክ ባየሁ ግዜ፣…እኔ በመምህርነቴ አፈርኩ። እናንተ ከመምህር ፓስተር ስትመርጡ፣… ያ(እ)ኔ በቃኝ!!!

ethiothinkthank.com