ከአገር አልባዎች የተላከ

ውድ ባለ-አገሮች፣…እንዴት ይዟችኋል? አገር-ሰፈሩ፥ አየር-ምድሩ ሰላም ነው? …ዘመድ-አዝማድ አማን ነው? ባለሃብትና ባለስልጣናት እንዴት ናቸው? እናንተ እንዴት ናችሁ፣ እኛ “አለን’ም”…”የለንም”…እንዲያ እንኳን ብንል ሰሚ የለም፣… ሰሚ ቢገኝ አማኝ-ታማኝ የለም። ሰምተው አያዳምጡንም፣ አይተው አይቀበሉንም።

ባላአገሮች…”የለንም” እንዳንል አፍ አለን፣ “አለን’ም” እንዳንል ሰሚ የለንም። ግራ እንደተጋባን፣ ሳንሰማ ተስማምተን፣ ሳይገባን ተግባብተን፣ በሆነው-ባልሆነው እየተወዛገብን፤ …ስንገድል-ስንሞት፣ ስናስር-ስንፈታ፣ ትወልድ በትውልድ፣ መንግስት በመንግስት ቢተካም በእኛ ዘንድ ለውጥ የለም … እኛ እንደው አለን’ም-የለንም፣…ቁርጣችን አይታወቅም፣ አድራሻ የለንም፣ መድረሻ የለንም። እኛ’ኮ አገር-አልባዎች ነን። 

ባለ-አገሮች እንዴት ናችሁ’ሳ? እኛ እንደው አለን’ም-የለንም። እንደ እናንተ ከሁለት አንድ አንመርጥም። አያችሁ? …እኛ አገር አልባዎች ነን። እንደ እናንተ ሰው፣ መሬትና መንግስት ቢኖረንም፣ አገር ግን የለንም። አገር-አልባ ሰው የትስ ውሎ የት ቢገባ ምን ሊረባ?

በነፃነት የማሰብ ተፈጥሯዊ ባህሪውን የተገፈፈ ሰው ስሙ እንጂ ምን ቀረው? በራሱ የማያስብ ግዑዝ ፍጥረት ነው። የነፃነትን ትርጉምና ፋይዳ የማያውቅ ሰው ምኑን “ሰው” ነው? ሰብዓዊነት እኮ ከነፃነት ጋር ተጣብቆ የተሰጠ ክብር ነው። ነፃነቱን ያጣ ሰው ሳይታረድ ቆዳው እንደተገፈፈ በግ ነው፣ …ሳይሞት የሚያጣጥር ግዑዝ ፍጡር…። እንዲህ ያለ ፍጡር፣ ሰው ቢመስልም አይደለም። የሰውነት መለያ ነፃነትን ተገፏል፣ ሰው መሆኑ አብቅቷል፣…እንዴት አገር ይኖረዋል?

በእውን ለሌለ ሰው አገር ምን ያደርግለታል? ሰው እንዴት፣ በግዴታ አስቦ በግድ ይናገራል? ለራሱ ያልሰማውን ሃቅ ማን’ስ ሰምቶ ያምነዋል? እሱ ራሱ ሳይኖር “አለሁ” ቢል ማን ያምነዋል… ለራሱ የሌለ ሰው “ሀገር አለኝ” ቢል ማን ነው የሚያምነው? ለራሱ የሌለ ሰው መቼ አገር ይኖረዋል?

መሬት እኮ አለን… እንደ እናንተ አይደለም ደጋ’ማ ወይም ጭጋጋማ…መሬት’ማ ነበር ቆላ…ደጋ…ወይንደጋ፣ አንዴ’ም ሰላም የለው፣ ወይ አይረጋጋ። ሰው’ም ዞር-ዞር ብሎ ካልሰራ መሬት ምን ይጠቅማል? መሬት መስሪያ እንጂ መቼ በራሱ ይሰራል? መሬት፣ በነፃነት ሄደው ካልሰሩበት ምን ይረባል?

ሰው በመሬት ላይ ቆሞ “በአሜሪካ ዛፍ ሆኜ ልብቀል” እያለ ይመኛል። ታዲያ፣ ከሰውነት ዘፍ መሆን የተመኘ አገር አገኘ-አላገኘ ምን ይረባል? ከሰውነት ይልቅ ግዑዝ ነገር መሆን መርጧል፣ ምን ይጠቅማል? ድህነትና ድንቁርና ሃሳቡን ድኩማን አርጎታል…አገር ቢኖረውን ምን ያደርጋል? አገር ቢያጣ ምን ይቀርበታል?

ባላአገሮች ሆይ…እኛ ምንድነን? …ምን’ስ ነን? የራሳችን መንግስት እኛን የሚገድለን። በነፃነት እንድንኖር፣ በነፃነት እንድንሰራ የሰጠንውን አደራ፣ ቀርጥፎ የሚበላ መንግስት ባለበት፣ እያሰረን…እየገደለን “ይቅርታ” የሚለን ጉልበተኛ መንግስት ያለበት ሜድር “ሲዖል” እንጂ “ሀገር” ይባላል?

ውድ ባለ-አገሮች…እናላችሁ፣ እኛ ሰው እንጂ ነፃነት የለም። እኛ መሬት ቢኖረንም በነፃነት አንቀሳቀስም። እኛን መንግስታችን እየገደለን…እያሰረኝ…እያሰቃየን…ነፃነት ከሌለን ምን ቀረን? ሰው…መሬት…መንግስት ቢኖረንም አገር የለንም። እኛ አለን’ም…የለንም።

ethiothinkthank.com

Advertisements

ምላሽ ይስጡ

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s