በፅሁፍ ፍርሃት፥ ዕውቀትና ዘላለማዊነትን አሸንፋለሁ!

ምሳ ሰዓት ላይ ወደ ቤት ስገባ ስለ አንድ ነገር መፃፍ እንዳለብኝ እያሰብኩ ነበር። ነገር ግን፣ መፃፍ እንዳለብኝ እንጂ ስለ ምን እንደምፅፍ አላሰብኩበትም ነበር። ታዲያ፣ ኮምፒውተሬን ከከፈትኩ በኋላ ስለምን መፃፍ እንዳለብኝ ባስብ…ባስብ አንድም የፅሁፍ ሃሳብ ጠብ አልል አለ። ከሁለት ሰዓት በላይ ስለ ምን መፀፍ እንዳለብኝ ማሰቡ ደከመኝ። “ዛሬ ባይፃፍስ…” ብዬ በመስኮት ወጪ-ወራጁን መመልከት ጀመርኩ። ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ፤ “ስለ ምን ልፃፍ?” የሚለው ጥያቄ “ለምን እፅፋለሁ?” ወደ የሚል ተቀይሮ አገኘሁት። “ስለ ምን እንደምፅፍ” ሳላውቅ ስቀር “ለምን እንደምፅፍ” መጠየቅ ጀመርኩ። ለመጀመሪያው ጥያቄ አንድ’ም ሃሳብ እንዳልጠፋ፣ ለሁለተኛው ጥያቄ ምላሽ ለመሆን መዓት ሃሳቦች ተግተለተሉ። እኔ’ም እነዚህን ሃሳቦች በደርዝ-በደርዝ አድርጌ እንዲህ አሰናዳዋቸው።

“ለምን እፅፋለሁ?” ብዬ ራሴን ስጠይቅ፣ ቀድሞ ወደ ሃሳቤ የመጣው፣ በማህበራዊ ድረገፆች፤ በተለይ ፌስቡክ (Facebook)፣ በጦማር ገፄ እንዲሁም ከቅርብ ግዜ ወዲህ በhornaffairs ድረገፅ ላይ የማወጣቸውን ፅሁፎች አንባቢያን ባገኙኝ ቁጥር የሚጠይቁኝ “ለምን ትፅፋለህ?” የሚለው አወዛጋቢ ጥያቄ ነው። ታዲያ ጓደኞቼና የስራ ባልደረቦቼ ጭምር በፅሁፎቼ ዙሪያ ያላቸውን አስተያየት በስልክ፣ በመዕልክት ወይም በአካል ሲያገኙኝ ብቻ ነው የሚጠይቁኝ። በዚያው ፅሁፎቼን ባወጣውባቸው ድረገፆች ላይ የአስተያየት መስጫ ቦታ ያለ ቢሆንም፣ ሃሳብና አስተያየታቸውን ግን በፅሁፍ ለመግለፅ አይደፍሩም። አብዛኞቹ ሃሳብና አስተያየታቸውን በይፋ ለመግለፅ ይፈራሉ። ይህ የፍርሃት ድባብ፣ ለዚህ ፅሁፍ መነሻ ለሆነው፣ “ለምን እፅፋለሁ?” ለሚለው ጥያቄ የመጀመሪያ ምላሽ ነው።

በአለም ላይ አስከፊ የሆኑ ነገሮች የተከሰቱት ወደፊትም የሚከሰቱት የፍርሃት ቆፈን በሰፈነበት ማህብረሰብ ውስጥ ነው። አምባገነንነት፣ ጦርነት፣ ጨቆና፣ ሽብር፣… ወዘተ መሰረታዊ አላማና ግባቸው በሕብረተሰቡ ዘንድ የፍርሃት ድባብን (Climate of fear) መፍጠር ነው። ምክንያቱም፣ ከፍርሃት ነፃ በሆነ ማህብረሰብ ዘንድ የዜጎች ነፃነት፣ ፍትህና እኩልነት ይረጋገጣል፣ ግልፅነት፣ ተጠያቂነትና የሕግ-የበላይነት ይሰፍናል። ፍርሃት በነገሰበት ማህብረሰብ ውስጥ በግልፅ መያየትና መነጋገር አይቻልም፣ ዜጎች መብትና ግዴታቸውን ለይተው አያውቁም። አንዱ የሌላውን ሃሳብና አስተሳሰብ፣ ባህልና እሴት፣ ልማድና ደንብ፣ አመለካከትና ስነ-ልቦና፣… በጥልቅ ለመረዳትና ለመገንዘብ ከፍርሃት ነፃ በሆነ መልኩ መናገርና መፃፍ አለበት። ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ግልፅ የሆነ የጋራ የውይይት መድረክ በሌለበት፤ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ አይኖርም፣ በጋራ ግንዛቤ የተመሰረተ ሀገራዊ መግባባት አይዳብርም። ከዚህ ይልቅ፣ አለመተማመን ይነግሳል፣ በሀገራዊና ታሪካዊ እውነቶች ዙሪያ መግባባት ይሳነናል፣ ተግባራዊ እንቅስቃሴያችን በጠባብ አስተሳሰብና ጭፍን ጥላቻ ይመራል፣ በማህበራዊ ሕይወታችንና ግንኙነታችን በዘረኝነት፣ ጎጠኝነት፣ አክራሪነትና ፅንፈኝነት ይመራል።

በብዙሃን መገናኛ መድረኮች ላይ የግል ሃሳብ እና አመለካከትን በነፃነት መግለፅ ከስጋት ነፃ ነው እያልኩ አይደለም። ብቻውን ሆኖ እንኳን በነፃነት የማያስብ፣ ወይም ያሰበውን ለመናገር በሚፈራ ማህብረሰብ ውስጥ፣ በነፃነት መፃፍ፥ ሃሳብን በአደባባይ መግለፅ እንደ ወንጀል ቢወስድ አይገርምም። ከላይ በተጠቀሱት ማህበራዊ ድረገፆች ላይ ያወጣኋቸውን ፅሁፎች ጠቅሶ በግል የሚያስፈራራኝ ሰው ብዙ ነው። ማስፈራሪያዎቹን ፈርቼ ግን መፃፍ አላቆምም። በእርግጥ፣ በማህብረሰቡ ዘንድ ያለው የፍርሃት ስሜት በመቅረፍና ማህበራዊ መግባባት በማስፈኑ ረገድ የጎላ አስተዋፅዖ የለኝም። ሆኖም ግን፣ “ፍርሃት የግሌን አስተዋፅዖ ከማበርከት ሊያግደኝ አይገባም” የሚል ፅኑ እምነት አለኝ። ስለዚህ፣ መቼም ቢሆን፤ በነፃነት ከማሰብ፣ መናገርና መፃፍ ወደኋላ አልልም።

“ለምን እፅፋለሁ?” ለሚለው ጥያቄ ሁለተኛው ምክንያት በግል የማገኘው ልዩ ጥቅም ነው። እንዲህ ያሉ ፅሁፎችን እንድፅፍ ኣረዓያ የሆነኝ፣ ጓደኛዬ ሃብታሙ አለባቸው፣ “መፃፍ ምሉዕ ያደርጋል” ይለኝ ነበር። ስለ አንድ ነገር ማሰብ ግንዛቤን ይፈጥራል፣ ያሳቡትን መናገር ግንዛቤን ያዳብራል፣ ያሰቡትን መፃፍ ግንዛቤን ያበለፅጋል። በእርግጥ፣ ከማሰብና መናገር ባለፈ መፃፍ ግንዛቤን ምሉዕ ያደርጋል። ስለ አንድ ሃሳብ ስንፅፍ ፅንሰ-ሃሳቡ በውስጣችን ይሰርፃል። ከሌሎች ሃሳቦች ጋር አያይዘን ለመገንዘብ እድል ይፈጥርልናል። ተጨማሪ ዕውቀት ሃሳባችንን ያዳብረዋል። ፅሁፍ ደግሞ ይህንና ቀድሞ ከነበረን ዕውቀት ጋር አያይዞን ለመረዳት ያስችለናል። በዚህ፣፣ ግንዛቤያችንን ይበልጥ ያበለፅገዋል። ማንኛውም ሰው፣ ስለ አንድ ነገር አዘውትሮ ስለሚያስብና ስለሚናገር ብቻ ምሉዕ የሆነ ግንዛቤ ሊኖረው አይችልም። ወደ ሌላ መሄድ ሳያስፈልግ፣ በዚህ ፅሁፍ በማቀርበው ሃሳብ ዙሪያ ብዙ ሰዎች በተደጋጋሚ ጠይቀውኛል። ነገር ግን፣ እስካሁን ከተዘረዘሩት ሃሳቦች ሩብ ያህሉ በውስጤ ስለመኖራቸው እንኳን አላውቅም ነበር። ከሁሉም በላይ ግን፣ እስካሁኗ ቅፅበት ድረስ የማላውቀው ነገርና ለዚህ ፅሁፍ መነሻ ለሆነው ጥያቄ ሦስተኛውና የመጨረሻው ምክንያት ነው።

ከመግባባትና ዕውቀት በተጨማሪ፣ መፃፍ ዘላለማዊነትን ያቀዳጃል። ከጥንታዊ ግብፃዊያን ፓፒረስ እስከ የግሪክ ፊደላት፣ ከላቲን ቋንቋ እስከ የወረቀት ማተመያ፣ ከኮምፒውተር ቴክኖሎጂ እሰከ ዘመናዊ ደረገፆች፣… ወዘተ እያለ ፅሁፍ ዘላለማዊነትን ያቀዳጃል።የግብፅ፣ የግሪክና የሮማ ስልጣኔዎች ከወደቁ በኋላ ስለመኖራቸው ማረጋገጫ ዋስትና የሆናቸው በፅሁፍ ከትበው የተውት ታሪካቸው ነው። በዚህ የኮምፒውተርና ኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ዘመን፣ ቀድሞ በወረቀት ፅሁፍ ላይ ከቦታና ግዜ አንፃር የነበረው ውስንነት ተወግዷል። ለምሳሌ፣ ይህ የምፅፈው ፅሁፍን ከዛሬ አምስትና አስር ሺህ አመታት በኋላ ተፈልጎ ይገኛል። ቢያንስ ለዚያን ዘመን ሰዎች ፅሁፉ ይሄ ነው የሚባል ቁም-ነገር ባይኖረውም፣ ለፈለገው ሰው ግን ተፈልጎ ይገኛል። ነገር ግን፣ በፍርሃት ቆፈን ተይዞ፣ ሃሳብና አስተሳሰቡን በፅሁፍ ለማስፈር ድፍረት ያጣ ሰው፣ ከፓፒረስ በፊት ይኖሩ እንደነበሩ ሰዎች ታሪክ-አልባ ነው። ስለዚህ፣ “ስዩም ተሸመ” የሚባል ሰው ይኖር እንደነበር ማረጋገጫ ይሆነኝ ዘንድ መፃፌን እቀጥላለሁ።   

ethiothinkthank.com