ነጭ-ሽብር ተጀምሯል፣ ቀይ-ሽብር ይከተላል!

“ቆይ ግን፣ መንግስት ለምድነው እንዲህ የሚፈራው?” ይህ ጥያቄ ትላንት ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ከሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና በኋላ አንዳንድ የኢንተርኔት አገልግሎቶች በዚያው ተቋርጠው መቅረታቸውን አስመልክቶ ስንወያይ ያነሳሁት ነው። ከቅርብ ግዜ ወዲህ መንግስት እየወሰዳቸው ያሉት እርምጃዎች የፍርሃት ይመስላሉ፤ “በነጭ-ሽብር ዘመን እንደነበረው ዓይነት ፍርሃት…” አልኩና ለራሴ ደነገጥኩ። ጓደኛዬም “በትክክል…‘መንግስት ልክ በነጭ-ሽብር ዘመን የነበረው ዓይነት ፍርሃት ውስጥ ነው” ብሎ ሃሳቡን ሲደግመው የባሰ ደነገጥኩ። ይሄን ጉዳይ ሙሉ ትኩረቴን ሰጥቼ ማጥናት እንዳለብኝ አመኜ የተለያዩ መረጃዎችን በማሰባሰብ፣ በ1968 ዓ.ም እና በ2008 ዓ.ም መካከል ያለውን ሁኔታ ለማነፃፀር ስሞክር፣ ነገሩ ከማስደንገጥ አልፎ አስፈራኝ። ከአርባ ዓመት በኋላ የነጭ-ሽብር ጥቃት አይናችን ስር እየተካሄደ እንደሆና ቀይ-ሽብር ደግሞ ከዚህ ቀጥሎ ሊመጣ እንደሚችል ማሰቡ በራሱ በጣም ያስፈራል። እስኪ ድሮና ዘንድሮን በንፅፅር እንመልከት።

ከሕዳር ወር 2008 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በተከሰተው የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴ ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። በተለይ በኦሮሚያ ክልል የታየው የአመፅና ተቃውሞ አንቅስቃሴ በዋናነት በተማሪዎች የተቀሰቀሰ ሲሆን በሂደት ወደ ተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተስፋፍቷል። በዚህም፣ የኢትዮጲያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው ሪፖርት መሰረት፣ በክልሉ ለ173 ሰዎች ሕይወት መጥፋት እና በ261 ሰዎች ላይ ከባድ የመቁሰል አደጋ ድርሷል። እንደ ሪፖርቱ፣ ከሟቾቹ ውስጥ 14ቱ የፀጥታ አስከባሪዎች፣ 14ቱ “የመንግስት ኃላፊዎች” ሲሆኑ፣ ከፍተኛ የመቁሰል አደጋ ከደረሰባቸው ውስጥ 110 የፀጥታ አስከባሪዎች መሆናቸው ታውቋል። በተመሣሣይ፣ ሰሞኑን በጎንደር ከተማ በተከሰተው ችግር ምክንያት በ20 ሰዎች እና በ11 የፀጥታ አስከባሪዎች ላይ የሕይወት መጥፋት አደጋ ተከስቷል። በአጠቃላይ፣ ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች 25 የፀጥታ አስከባሪዎች እና በ14 የመንግስት ባለስልጣናትን ላይ የሞት አደጋ ደርሷል።

ከመስከረም ወር 1968 ዓ.ም ጀምሮ በተማሪዎች አባላቱ ላይ ጠንካራ እርምጃ መውሰዱ በመጀመሩ ተከትሎ ኢህአፓ (የኢትዮጲ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲ) በደርግ አባላትና ደጋፊዎቹ ላይ የኃይል እርምጅ መውሰድ ጀመረ። የነጭ-ሽብር ጥቃቱን የተጀመረው በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ በመንግስቱ ኃ/ማሪያም ላይ የግድያ ሙከራ በማድረግ ሲሆን ቀጥሎ ከፍተኛ የመንግስት ካድሬ የነበረውን አቶ ፍቅሬ መርድን በመግደል ነበር። በቀጣይ ሁለት ወራት ውስጥ 10 ከፍተኛ የደርግ ባለስልጣናትንና 15 የፀጥታ አስከባሪዎች በኢህአፓ ተገድለዋል። በ“African Watch Report” መሰረት፣ ኢህአፓ በደርግ አባላትና ደጋፊዎች ላይ እየወሰደ የነበረው የኃይል እርምጃ እስከ አመቱ አጋማሽ ድረስ የቀጠለ ሲሆን በዚህም በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። ደርግ የአፀፋ እርምጃ መውሰድ የጀመረው በተመሣሣይ ወቅት ከመስከረም ወር ጀምሮ ቢሆንም የጅምላ እስርና ግድያ የጀመረው ግን ከየካቲት ወር በኋላ መሆኑን በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

በአጠቃላይ፣ በ2008 ዓ.ም ከሕዳር ወር ጀምሮ 25 የፀጥታ አስከባሪዎች እና 14 የመንግስት ባለስልጣናት ተገድለዋል። በተመሣሣይ፣ በ1968 ዓ.ም በጥቅምትና ሕዳር ወር ውስጥ ብቻ 15 የፀጥታ አስከባሪዎች እና 10 የመንግስት ባለስልጣናት ተገድለው ነበር። በሁለቱም አጋጣሚዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ሕይወት የጠፋበት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ግጭት እንደመከሰቱ በፀጥታ ኃይሎች ላይ የደረሰውን የሞትና የመቁሰል አደጋ መገመት ይቻል ይሆናል። ምክንያቱም፣ ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡ ነዋሪዎችና የፀጥታ አስከባሪዎች በግጭቱ ቀጥተኛ ተሳታፊዎች እንደመሆናቸው መጠን፣ በእነዚህ አካላት ላይ የሚደርሰው የሞትና የመቁሰል አደጋ የግጭቱ ስፋት ይጠቁማል። በተመሣሣይ፣ የ1997 ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ በተከሰተው አመፅና ብጥብጥ የተገደሉትን ሰዎች ብዛት መንግስት የ54 ብቻ ነው ሲል፣ አንዳንድ ወገኖች 193 እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ሆኖም ግን፣ በወቅቱ የደረሰው የሞትና የመቁሰል አደጋ በዋናነት በሰላማዊ ዜጎችና ፀጥታ አስከባሪዎች ላይ እንጂ በመንግስት ባለስልጣናት ላይ አልነበረም። በመሆም፣ ከዘንድሮው ጋር ተመሣሣይ ነው ማለት አይቻልም።

በዘንድሮ አመት፣ ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ ብቻ 14 የመንግስት ባለስልጣናት ተገድለዋል። በአመፅና የተቃውሞ እንቅስቃሴው ቀጥተኛ ተሳታፊ ከሆኑት ዜጎችና የፀጥታ አስከባሪዎች በተለየ፣ የመንግስት ባለስልጣናት መገደላቸው የሚጠቁመው የግጭቱን ስፋት ሳይሆን የግጭቱን ዓይነት ነው። ከዚህ አንፃር፣ የዘንድሮ ግጭት በዓይነቱ ከ1968ቱ የነጭ-ሽብር ጥቃት ጋር ይበልጥ ተመሣሣይነት አለው። በሁለቱም አጋጣሚዎች የመንግስት ባለስልጣናት ከፀጥታ አስከባሪዎች እኩል የተቃዋሚ ኃይሎች ኢላማ ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪ፣ ሃሳብን ይበልጥ ለመረዳት እንዲቻል ሰሞኑን በግሌ የታዘብኳቸውን ሁለት አጋጣሚዎች እንደ ማሳያ ለመጥቀስ እሞክራለሁ።

አጋጣሚ-1፡- ባለፈው ሳምንት በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ ቱሉ-ቦሎ ከተማ ውስጥ ከተማዋ የቀድሞ ከንቲባ ማንነቱ ባልታወቀ ሰው በጥይት ተመትቶ መሞቱን ሰማሁ። እዚያ የሚኖር ጋደኛዬ ጋር ስልክ ደውዬ ስለ አሟሟቱ ስጤቀው ሰውዬው የተገደለው በስህተት እንደሆነ ነገረኝ። ነገሩ ገርሞኝ፤ “ጦር መሳሪያ ይዞ…፣ ሰው ለመግደል ጥይት ተኩሶ ሲያበቃ፣ እንዴት ነው “በስህተት” ሊባል የሚችለው የሚል ጥያቄ አስከተልኩ። “ሰውዬው የተገደለው በዕለቱ አንድ ከኦሮሚያ ክልል ቢሮ የመጣ ባለስልጣን ስለነበረ፣ ገዳዩ እሱን ያገኘ መስሎት ነው በስህተት የገደለው” በማለት የግል ግምቱን ነገረኝ።

አጋጣሚ-2፡- በቅርቡ በጎንደር ከተማ የነበረውን ሁኔታ አስመልክቶ በፌስቡክ ገፄ ላይ “በትግራይ ብሔር ተወላጆች ላይ የሚፈፀመው ጥቃት ይቁም!” የሚል ፅሁፍ ለጥፌ ነበር። በተለይ በንብረት ላይ የደረሰውን ጥፋት አስመልክቶ በተደጋጋሚ ሲሰጥ የነበረው፤ “ጥቃት የደረሰባቸው ‘የወያኔ/ህውሓት አቃጣሪዎች’ ናቸው” የሚለው አስተያየት ሲሆን ይህም ልክ እንደ ሚዛናዊ አስተያየት በብዙዎች ዘንድ ሲደጋገም ታዝቤያለሁ።

ከላይ በተጠቀሱት ችግሮች ዙሪያ በሚመለከተው አካል እየተደረገ ስላለው የማጣራት ስራ ዝርዝር መረጃ የለኝም። በእርግጥ የእኔ ትኩረት ዝርዝር መረጃ ላይ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ በሁለቱም አጋጣሚዎች ላይ ስለሚንፀባረቀው የተሳሳተ እሳቤ ነው። ይህም፣ የመንግስት ኃላፊዎች እና ደጋፊዎች ሕይወት እና ንብረትን ማጥፋት ተገቢና ተቀባይነት ያለው ተግባር ተደርጎ መቅረቡ ላይ ነው። ልክ እንደ ነጭ-ሽብር ዘመን፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የማንኛውም ዜጋ ሕይወትና ንብረት መጥፋት የለበትም የሚለው የሕግ-የበላይነት መርህ እንደዋዛ እየተሸረሸረ መሄዱ በጣም አሳሳቢ ነው።

በእርግጥ በ“ነጭ-ሽብር” እና “ቀይ-ሽብር” ዘመን በኢትዮጲያኖች ላይ የተፈፀመው ጅምላ ጭፍጨፋ ሀገሪቷን ዕውቀት መሃን አድርጓታል። በወቅቱ የተፈፀመው ጥፋት ግን በዋናነት በቃላት እንጂ በጥይት አልነበረም። ይህ በሀገራችን ታሪክ አሰቃቂ የሆነው ዘመን ሲመጣ ነጋሪት እያስጎሰመ አልነበረም። ከዚያ ይልቅ፣ በጥላቻና ስሜታዊ ግብዝነት በታጨቁ ቃላት እየተጎተተ ነው የመጣው። የሀገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን በተለያዩ መድረኮች የሚናገሯቸው ቃላት፣ ብዙሃኑን በአንድ ጎራ ማሰባሰብ ብቻ ሳይሆን ማሰብ እንዲያቆም ሊያደርጉት ሁሉ ይችላሉ (words that bind us also blind us)።

በ1968 ዓ.ም የኢህአፓ ጥቃት ከተጀመረ ከስምንት ወር በኋላ ጓድ መንግስቱ ኃ/ማሪያም በኢህአፓ ሲሰነዘርበት የነበረው ጥቃት “ነጭ-ሽብር” የሚል ስያሜ በመስጠት፣ አፀፋውን “ቀይ-ሽብር” ብሎ አወጀ። ይህን ተከትሎ፣ ሌ/ኮ አጥናፉ አባተ “በነጭ-ሽብር ለተገደለ አንድ አብዮተኛ አንድ ሺህ ፀረ-አብዮተኞች ይገደላሉ” (for every revolutionary killed, a thousand counter-revolutionaries executed) ብሎ ቃል በመግባት “የአብዮት ጥበቃ ጓዶችን” (Defense of the Revolution Squads) ማደራጀት ጀመረ። “መጥፎ ቀናት” (Evil Days) በሚል ርዕስ በ1983 ዓ.ም በወጣው የሰብዓዊ መብት ሪፖርት፤ “The promised ratio was not to be much of an exaggeration” በማለት፣ “በነጭ-ሽብር ለተገደለ አንድ የደርግ አባል አንድ ሺህ ተቃዋሚዎች ተገድለዋል” ቢባል ማጋነን እንዳልሆነ ይገልፃል።

በተመሣሣይ፣ የዘንድሮው አመፅ ከተከሰተ ከስምንት ወራት በኋላ፣ በተለይ በቅርቡ በጎንደር ከተማ በፀጥታ አስከባሪዎች (ፖሊሶች) እና ዜጎች ላይ ከደረሰው አደጋ ጋር ተያይዞ መንግስት የሚወስደው እርምጃ ችግሩን እንዳያባብሰው እሰጋለሁ። ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ በተለይ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች እየታየ ያለው የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴ “የነጭ-ሽብር ተጀምሯል” ለማለት ያስደፍራል። በተመሣሣይ፣ የመንግስት ግብረ-መልሱ ልክ እንደ ደርግ በስሜታዊ ግብዝነትና ፍርሃት የሚመራ ከሆነ “ቀይ-ሽብር ይከተላል”። ስለዚህ፣ ሁሉም አካላት ነገሮችን ከማባባስ እንዲቆጠቡና በመንግስት የሚወሰዱ እርምጃዎች በጥሞና ሊታሰብባቸው እንደሚገባ ለማሳሰብ እወዳለሁ።

One thought on “ነጭ-ሽብር ተጀምሯል፣ ቀይ-ሽብር ይከተላል!

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡