ግልፅ ደብዳቤ ለጠ/ሚ ኃ/ማሪያም፡ “በሕዝብ ላይ ጦርነት አውጀዋል”

ክቡር ጠ/ሚኒስተር ኃ/ማሪያም ሰላምና ጤና ከእርስዎ ጋር ይሁን። ስሜ ስዩም ተሾመ ይባላል። በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የወሊሶ ካምፓስ መምህር ነኝ። በትርፍ ግዜዬ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የትንታኔ ፅሁፎችን እፅፋለሁ። በእርግጥ መፃፍ የጀመርኩት ከዘጠኝ ወር በፊት ሲሆን እኔ በምኖርበት ወሊሶ ከተማ የታየውን ከፍተኛ የሕዝብ ተቃውሞ በማስመልከት ነው። ከዚያ በኋላ ከ50 በላይ ፅሁፎችን በድረገፅ ላይ አውጥቼያለሁ። ከፅሁፎቼ ውስጥ “በቀውሱ የህዳሴን መንገድ ይቀይሱ – ለጠ/ሚ ኃ/ማሪያም) የሚል ይገኝበታል። ይህ መፃፍ የጀመርኩበት አጋጣሚና የፅሁፎቼ ዓላማ መንግስትና ሕዝብን የማሳወቅ እና የመፍትሄ ሃሳቦችን መጠቆም እንደሆነ እንዲያውቁልኝ ስለፈለኩ ነው። ይህን ፅሁፍም ከዚሁ አንፃር ተመልክተው፣ በፅሁፉ ለምዳስሰው ችግር አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጡት በቅድሚያ ለማሳሰብ እወዳለሁ።

በቀጥታ ወደ ጉዳዩ ስገባ፣ ማክሰኞ ነሃሴ 24/2008 ዓ.ም በቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ፤ “ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ አዝዣለሁ” ማለትዎ ይታወሳል። አንዳንድ ወገኖች ይህን ዓ.ነገር “በሕዝብ ላይ ጦርነት ታወጀ!” በማለት አስተያየት ሲሰጡ ነበር። በእርግጥ ያስተላለፉት ትዕዛዝ ወቅታዊ ስለሆነ፣ እርስዎ ዓ.ነገሩን ከተናገሩበት አውድ ውጪ ሊወሰድና የተለየ ትርጉም ሊሰጠው እንደሚችል በመገመት ትኩረት አልሰጠሁትም ነበር። ነገር ግን፣ “በአማራና ኦሮሞ ሕዝብ ላይ ጦርነት ታውጇል” የሚባለው ነገር እየተደጋገመ ቀጠለ። ይሄ ነገር እኮ ሲደጋገም እውነት ይመስላል” አልኩና በጉዳዩ ላይ ለመፃፍ አንዳንድ ማጣቀሻ የሚሆኑ ፅሁፎችን ማንበብ ጀመርኩ።

መቼም በእንዲህ ያለ ጉዳይ ላይ የሚቀርብ ትንታኔ በተቻለ መጠን በተረጋገጠ መርህ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት። መጀመሪያ ላይ ለመፃፍ ስነሳ በጉዳዩ ዙሪያ ያለውን ግራ መጋባትና የተዛባ አመለካከትን ለመቅረፍ የሚያስችል አሳማኝ ፅሁፍ ለማውጣት ነበር። መጨረሻ ላይ የደረስኩበት ድምዳሜ ግን ለእኔ ራሱ በጣም ነው ያስደነገጠኝ። በእርግጥ እርስዎ ጠ/ሚኒስተር የሆኑት ሕዝብን ለማገልገል ካለዎት ቀና እሳቤ እንደሆነ ፍፁም ጥርጥር የለኝም። እኔም ከዚህ ድምዳሜ ላይ እደርሳለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም። ይሁን እንጂ እውነቱ ሁለታችንም እንዳሰብነው አይደልም። ክቡር ጠ/ሚኒስተር “በሕዝብ ላይ ጦርነት አውጀዋል!”

ከላይ በጠቀስኩት ምክንያት በዚህ ፅሁፍ የሚቀርበው ትንታኔ ከወቅታዊ ማስረጃዎች ይልቅ በታሪክ ፍልስፍና (Philosophy of History) ላይ የተመሰረተ ነው። ለዚህ ደግሞ በዘርፉ ፈር-ቀዳጅ የሆነው ሩሲያዊ የታሪክ ፈላስፋ ሊዮ ቶልስቶይ (Leo Tolstoy) “War and Peace” በተሰኘው መፅሃፉ የሰጠውን ትንታኔ መሰረት ያደረገ ነው። ሊዮ ቶልስቶይ በዚህ መፅሀፍ የአንድ ሀገር መንግስት በሌላ ሀገር ወይም በራሱ ሕዝብ ላይ ለምንና እንዴት ጦርነት እንደሚያውጅ፣ በጦርነት ወቅት ለምን ሰው ጨካኝ እንደሚሆን፣ እና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ትንታኔ ሰጥቷል።

ወደ ዝርዝሩ ከመግባታችን በፊት በቅድሚያ “ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ አዝዣለሁ” የሚለውን ዓ.ነገር ሦስት ቦታ መክፈል ያስፈልጋል። በዚህ መሰረት፣ 1ኛ) “ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች” – የዕዝ ሰንሰለት (Chain of commands)፣ 2ኛ) “አዝዣለሁ” – የማዘዝ ስልጣን (Commanding Power) እና 3ኛ) “የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ” – ምክንያት (Justification) በማለት ሦስት ቦታ ተከፍሏል። ከዚህ በመቀጠል፣ የእርስዎ፥ የክቡር ጠ/ሚ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ትዕዛዝ፣ በፀጥታ ኃይሎች እየተወሰደ ያለው እርምጃ፣ እንዲሁም እንዴት በሕዝብ ላይ የታወጀ ጦርነት ሊሆን እንደቻለ እንደሚከተለው በዝርዝር ቀርቧል።

1ኛ) የዕዝ ሰንሰለት (Chain of commands)
“ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች” የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የክልል ልዩ ፖሊስ እና ሌሎች የፀጥታና ደህንነት መስሪያ ቤቶችን ያካትል። እነዚህ ተቋማት የሚመሩት ድርጅታዊ መዋቅርን በተከተለ የዕዝ ሰንሰለት (Chain of commands) መሰረት ነው። ከፀጥታና ደህንነት ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም የአስተዳደርና ቢዝነስ ተቋማት ስራና አመራራቸው በአንድ መሰረታዊ የአሰራር ሕግ ላይ የተመሰረተ ነው። በማንኛውም ድርጅት ውስጥ በተለያየ የእርከን ደረጃ ላይ ያሉ ሰራተኞች እና አመራሮች የስራ ድርሻቸውና የኃላፊነት ደረጃቸው የሚወስነውን በዚህ ሕግ መሰረት ነው። ሊዮ ቶልስቶይ በመፅሐፉ ይህን ሕግ እንደሚከተለው ይገልፀዋል፡-

“[M]en combine in such relations that the more directly they participate in performing the action the less they can command and the more numerous they are, while the less their direct participation in the action itself, the more they command and the fewer of them there are; rising in this way from the lowest ranks to the man at the top, who takes the least direct share in the action and directs his activity chiefly to commanding.” Leo Tolstoy, War and Peace, P.1157

ከላይ ከሀገሪቱ ጠ/ሚ ጀምሮ እስከ ታችኛው እርከን ላይ ያሉ ወታደሮች እና ፖሊሶች በሥራቸው ላይ ያላቸው ተሳትፎ፣ የማዘዝ ስልጣንና የሰራተኞቹ ብዛት በዚህ ሕግ ይወስናል። በዚህ መሰረት፣ ከታች ያለው ተራ ወታደር ወይም ፖሊስ በቁጥር በጣም ብዙ ነው፣ በስራው ላይ ያለው የማዘዝ ስልጣን በጣም ውስን ነው፣ ፀጥታን በማስከበሩ ሥራ ላይ ግን ቀጥተኛ ተሳታፊ (ፈፃሚ) ነው። የሀገሪቱ የጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ የሆኑት ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ደግሞ፤ በቁጥር አንድ ግለሰብ ናቸው፣ ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች የማዘዝ ስልጣናቸው ሙሉ ነው፣ ፀጥታን በማስከበር ረገድ ያላቸው ቀጥተኛ ተሳትፎ ግን ምንም (ዜሮ) ነው። በተራው ወታደር/ፖሊስ እና በጠ/ሚኒስትሩ መካከል ያሉ አዛዦችና ኃላፊዎች ፀጥታን በማስከበሩ ረገድ ያላቸው ቀጥተኛ ተሳትፎ፣ ብዛትና የማዘዝ ስልጣን እንደ የስልጣን ደረጃቸው እየጨመረ ወይም እየቀነሰ ይሄዳል።

2ኛ) የማዘዝ ስልጣን (Commanding Power)
የስልጣን (Power) ፅንሰ-ሃሳብ ከላይ አንደኛ ላይ በተጠቀሰው ድርጅታዊ መዋቅር ውስጥ በተዘረጋው የዕዝ ሰንሰለት መሰረት በሚደረግ ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ነው። ጠ/ሚ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ “ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ አዝዣለሁ” የሚለውን ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ በዕዝ ሰንሰለቱ ውስጥ ያላቸውን የስልጣን ደረጃ በግልፅ ይጠቁማል። የሁሉም ፀጥታ ኃይሎች የበላይ አዛዥ ናቸው። በተራ ወታደር/ፖሊስ እና በጠ/ሚ ኃ/ማሪያም መካከል የተዘረጋው የስልጣን እርከን ዓላማና ተግባሩ – ትርጉሙ ምንድነው? በዚህ ላይ ሊዮ ቶልስቶይ የሚከተለውን ምላሽ ይሰጣል፡-

“Power is the relation of a given person to other individuals, in which the more this person expresses opinions, predictions, and justifications of the collective action that is performed, the less is his participation in that action.” Leo Tolstoy, War and Peace, P.1157

እንደ ቶልስቶይ አገላለፅ፣ በታችኛው የስልጣን እርከን ላይ የሚገኙ ወታደሮችና ፖሊሶች ያለባቸው ኃላፊነት ትዕዛዝን ተቀብሎ መፈፀም ነው። እንደ ጠ/ሚ ኃ/ማሪያም በከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ የሚገኝ ሰው ኃላፊነትና ተግባሩ በፀጥታ ኃይሎች የሚፈፀሙ ተግባራት አግባብነትና አስፈላጊነት ላይ አሳማኝ ምክንያት ማቅረብ ነው።

በስልጣን እርከኑ ከላይ ወደታች እወረድን በሄድን ቁጥር አስተያየት፣ ትንበያና ምክንያት የማቅረብ ኃላፊነቱ እየቀነሰ፣ በፀጥታ ማስከበር ተግባሩ ያለው ቀጥተኛ ተሳትፎ እየጨመረ ይሄዳል። በመጨረሻ እርከን ላይ ያለው ተራ ወታደርና ፖሊስ በፀጥታ ማስከበር ተግባራት አግባብነትና አስፈላጊነት ላይ የራሱን አስተያየትና ምክንያት የመስጠት ስልጣንና ኃላፊነት የለውም። በተቃራኒው፣ የላይኛው የሥልጣን እርከን ላይ የሚገኙ ባለስልጣናት ደግሞ ሥራና ኃላፊነታቸው የፀጥታ ኃይሎች ለሚፈፅሙት ተግባራት አስፈላጊነትና አግባብነት ምክንያት (Justification) ማቅረብ ነው።

3ኛ) ምክንያት (Justification)
የሰው ልጅ ምክንያታዊ አስተሳሰብና የሞራል ስብዕና ያለው ፍጡር ነው። እንያንዳንዱ ግለሰብ ከዚህ በፊት ያደረገውን፣ አሁን እያደረገ ያለውን እና ወደፊት የሚያደርገውን ነገር አግባብነትና አስፈላጊነት የሚወስንበት የራሱ የሆነ ምክንያታዊ አስተሳሰብ እና የሞራል እሳቤ አለው። በዚህ መሰረት፣ ማሰብና ማገናዘብ የሚችል ሰው በሌላ ሰው ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊት አይፈፅምም። ይህን የሚፈፅም ከሆነ ግን ጤናማ አዕምሮ የሌለው፤ ምክንያታዊ አስተሳሰቡን እና/ወይም የሞራል እሳቤውን ያጣ ሰው መሆን አለበት። ነገር ግን፣ ላለፉት ዘጠኝ ወራት እንዳየነው የሀገራችን የፀጥታ ኃይሎች በቀላሉ ሊስተናገዱ የሚችሉ ጉዳዮችን ሁሉ በጥይት፣ በዱላና በእስር ለመፍታት ይሞክራሉ።

ክቡር ጠ/ሚ፣ ባለፉት ሃያ አምስት አመታት ባልታየ መልኩ በዘንድሮ አመት ብቻ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለሞት፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ደግሞ ለአካል ጉዳትና ለእስር ተዳርገዋል። ማህበራዊ ድረገፆችን የሞላው የሀገራችን የፀጥታ አስከባሪዎች ጭካኔና ማንአለብኝነት በሚያሳዩ ምስሎች ነው። ከሕዝብ በተሰበሰበ ታክስ ደሞዝ የሚከፈላቸው ፖሊሶችና ወታደሮች ሰላምና ደህንነቱን ከማስጠበቅ ይልቅ ለምን ይገድሉታል? ለምን ያለ አግባብ ይደበድቡታል? ለምን ያለ ፍትህ አስረው ያሰቃዩታል?

ክቡር ጠ/ሚ እኔ በሰብዓዊነት (humanity) ላይ ፅኑ እምነት አለኝ። እርስዎም ሆኑ እያንዳንዱ ወታደር እና ፖሊስ እንደ ሰው ሰብዓዊ ስሜትና ርህራሄ አላቸው ብዬ አምናለሁ። ከምንም በላይ ደግሞ ተግባርና እንቅስቃሴያቸው በምክንያታዊ አስተሳሰብና በሞራል ስብዕና እንደሚመራ አምናለሁ። ነገር ግን፣ በራሳቸውም ሆነ በሌላ ሰው ላይ እንዲደርስ የማይፈልጉትን ነገር በኦሮሞ፣ አማራ፣ ኮንሶ፣…ወዘተ ነዋሪዎች ላይ ዘግናኝ የሆነ በደልና ጭቆና ሲፈፅሙ ይስተዋላል። እንደ ግለሰብ የማያደርጉትን ነገር በአለቃዎቻቸው ሲታዘዙ ግን ያደርጉታል። እንደ ሰው ያላቸውን ምክንያታዊነት (rationality) እና የሞራል ስብዕና ያሳጣቸዋል። ለዚህ ደግሞ ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች አሉ።

አንደኛ፡- የፀጥታ ኃይሎች እንደ ሰው ያላቸውን ምክንያታዊ አስተሳሰብ የሚያጡት በፀጥታ የማስከበር ሥራቸው ላይ በነፃነት የማሰብም ሆነ የመወሰን ስልጣንና ኃላፊነት ስለሌላቸው ነው። ምክንያቱም፣ እንደ ሰው የማሰብ ነፃነቱን ወይም ኃላፊነቱን ለበላይ አለቆቻቸው አሳልፈው ሰትተዋል። እንደ ሊዮ ቶልስቶይ አገላለፅ፡-

When a man works alone he always has a certain set of reflections which as it seems to him directed his past activity, justify his present activity, and guide him in planning his future actions. Just the same is done by a concourse of people, allowing those who do not take a direct part in the activity to devise considerations, justifications, and surmises concerning their collective activity.

ሁለተኛ፡- በግዳጅ ላይ የተሰማሩ ወታደሮችና ፖሊሶች ስለተግባራቸው ምክንያታዊነት ወይም አግባብነት የማሰብ ስልጣንና ኃላፊነት የላቸውም። ስለዚህ፣ የማሰብ ነፃነት የሌላቸው ሰዎች ምክንያታዊ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው መጠበቅ አይቻልም። ነገር ግን፣ ምክንያታዊ አስተሳሰብ ባይኖራቸውም፣ እንደ ሰው የሞራል ስብዕና አላቸው። ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ዜጎችን ያለ ርህራሄ የሚደበድቡ፣ የሚያስሩና የሚገድሉ ፖሊሶችና ወታደሮች የሞራል እሳቤ የላቸውም። ምክንያቱም፣ በየበላይ ባለስልጣናት የሚቀርቡ ምክንያቶች (justifications) የፀጥታ ኃይሎችን ሞራል የጎደለው፥ ኢሰብዓዊ ድርጊት እንዲፈፅሙ ከሞራል እዳ ነፃ ያደርጋቸዋል። በድጋሜ ሊዮ ቶልስቶይ ባለስልጣናትና ኃላፊዎች በሚሰጧቸው ምክንያቶች በፀጥታ ኃይሎች የሞራል ስብዕና ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ እንዲህ ይገልፀዋል፡-

“These justifications release those who produce the events from moral responsibility. These temporary aims are like the broom fixed in front of a locomotive to clear the snow from the rails in front: they clear men’s moral responsibilities from their path. Without such justification there would be no reply to the simplest question that presents itself when examining each historical event. How is it that millions of men commit collective crimes- make war, commit murder, and so on?” Leo Tolstoy, War and Peace, P.1156

በአጠቃላይ፣ 1ኛ) በዕዝ ሰንሰለት (Chain of commands) ሕግ መሰረት ከታች ያሉት ወታደሮች እና ፖለሶች በፀጥታ ማስከበር ተግባሩ ላይ በቀጥታ ተሳታፊዎች ናቸው። 2ኛ) በፀጥታ በማስከበር ተግባሩ በቀጥታ ተሳታፊ የሆኑት ወታደሮችና ፖሊሶች በፀጥታ ማስከበር ሥራቸው ላይ የማዘዝ ስልጣን (Commanding Power) የላቸውም። 3ኛ) በፀጥታ አስከባሪዎች ተግባር አግባብነትና አስፈላጊነት ዙሪያ በባለስልጣናት የሚሰጡ አስተያየቶች እና ምክንያቶች (Justifications) የወታደሮች እና ፖሊሶችን ከምክንያታዊ አስተሳሰብና የሞራል ስብዕና ያጠፋዋል። በዚህ መሰረት፣ ዘወትር እንደምናየው በየከተማው ለግዳጅ የተሰማሩ ወታደሮችና አድማ በታኝ ፖሊሶች በዜጎች ላይ ስለሚፈፅሙት ድብደባ፣ እስርና ግድያ አግባብነት በጥልቀት እንዳያስቡ እና ሰብዓዊ ርህራሄ እንዲያጡ አድርጓቸዋል። ምክንያቱም፣ ፀጥታ የማስከበር ተግባሩ አስፈላጊነትና አግባብነትን በተለመለከተ አሳማኝ ምክንያት የማቅረብ ስልጣና እና ኃላፊነት ያለበት የበላይ አዛዡ ነው።

ክቡር ጠ/ሚ ኃ/ማሪያም፣ የሀገሪቱ የጦር ኃይሎች አዛዥ እንደመሆንዎ፣ የሁሉም የፀጥታ ኃይሎች ለሚፈፀመው ተግባር አግባብነትና አስፈላጊነት የመጨረሻውን ቃል የሚሰጡት እርስዎ ነዎት።

4ኛ) ጦርነት (War)
ስለዚህ የአንድ ሀገር መንግስት በሌላ ሀገር ሕዝብና መንግስት ላይ ጦርነት እንዲያውጅ የሚያደርገው፣ ወይም ደግሞ በራሱ ዜጎች ላይ ጭካኔ የተሞላው ተግባር የሚፈፅመው እንዴትና ለምንድነው? የአንድን ሀገር መንግስትና ሕዝብ ወደ ጦርነት የሚያስገባው የባለስልጣናት ትዕዛዝ፣ የወታደሮች ፍላጎት ወይስ የፖለቲካ ልሂቃን ግፊት ነው? አብዛኛዎቹ የታሪክ ምሁራን የባለስልጣናት ውሳኔና የምሁራን ግፊት እንደሆነ ይገልፃሉ። ነገር ግን፣ እንደ ሊዮ ቶልስቶይ አገላለፅ፣ የአንድ ሀገር መንግስት በሌላ ሀገር ላይ ወይም በተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍል ላይ ጦርነት የሚያውጅበትን ምክንያት እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፡-

“The movement of nations [war] is caused not by power, nor by intellectual activity, nor even by a combination of the two as historians have supposed, but by the activity of all the people who participate in the events, and who always combine in such a way that those taking the largest direct share in the event take on themselves the least responsibility and vice versa.” Leo Tolstoy, War and Peace, P.1157

ከላይ በጥቅሱ ውስጥ እንደተገለፀው፣ ጦርነት በአንድ ወይም በሁለት አካላት ውሳኔና እንቅስቃሴ ምክንያት የሚጀመር ክስተት አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ በሁሉም አካላት ጥምር ተሳትፎ ምክንያት የሚከሰት ነው። ከሁሉም በላይ የጦርነት ዋና መነሻ ምክንያት በጦርነቱ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸው፤ ወታደሮች፣ ፖሊሶች እና ሌሎች የፀጥታና ደህንነት ኃይሎች በውጊያ ላይ ለሚፈፅሙት ኢሰብዓዊ ድርጊት ኃላፊነት እንዳይሰማቸው የሚያደርገው አሰራር እንደሆነ ተገልጿል።

በአጠቃላይ፣ ጦርነት እጅግ በጣም መጥፎ ነገር ነው። የሰው ልጅ ምክንያታዊ ግንዛቤ ይጋርዳል፣ የሞራል ስብዕናን ያወርዳል። በዚህም ሰውን ከሌላ ተራ እንስሳ እኩል ያደርጋል። ጦርነት ምንም ጥሩ የለውም። አንዳንድ የዘርፉ ምሁራን፣ ለምሳሌ፡-የሩዋንዳ ዘር ማጥፋት (Rwanda Genocide in 1994)፣ የአይሁዳዊያን ዘር ማጥፋት (The Holocaust)፣ የዩክሬን ችጋር/ቸነፈር (The Holodomor)፣ የአሜሪካ ዘር ማጥፋት (The Armenian Genocide of 1915)፣ እና የመሳሰሉት የዓለም አሰቃቂ ክስተቶች የተፈፀሙት ጦርነት ጥላ ስር እንደሆነ ይገልፃሉ።

“The strategic rationale for genocide is never based on emotion — not prejudice, not hatred, not sexual aggression, not personal greed, not religious belief — but is rather always based on the cold calculus of war. Nearly every genocide or atrocity or massacre around the world in the last hundred years occurred in the context of war, and was a planned act of military strategy.” Philosophy Weekend: Can A Person Be Guilty Of Genocide?

5ኛ) “በሕዝብ ላይ ጦርነት አውጀዋል?”
ክቡር ጠ/ሚ፣ እንደ የኢፊዴሪ ጠቅላይ ሚኒስተርና የጦር ኃይሎች አዛዥነትዎ፤ “ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ አዝዣለሁ” በማለት ያስተላለፉት መልዕክት በሕዝብ ላይ ጦርነት እንደማወጅ ይቆጠራልን? በሊዮ ቶልስቶይ የታሪክ ፍልስፍና መሰረት ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል እርስዎ የተናገሩትን ዓ.ነገር ከፋፍሎ መመልከት ያስፈልጋል።

በዚህ መሰረት፣ 1ኛ) “ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች” በሚለው ሐረግ የሀገሪቱን ፀጥታና ደህንነት መስሪያ ቤቶች “የዕዝ ሰንሰለት” (Chain of commands) በመጠቀም፣ 2ኛ) “አዝዣለሁ” በሚለው ቃል ደግሞ እንደ ጠቅላይ ሚኒስተርና የጦር ኃይሎች አዛዥ በሕግ የተሰጥዎትን “የማዘዝ ስልጣን” (Commanding Power) መሰረት በማድረግ፣ እና 3ኛ) “የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ” በማለት የፀጥታ ኃይሎች በሕዝቡ ላይ ለሚፈፅሟቸው አሰቃቂ በደሎች፤ ግድያዎች፣ ድብደባዎችና እስራቶች ምክንያት (Justification) በማቅረብ፣ በህዝብ ላይ ጦርነት አውጀዋል።

አዎ… ክቡር ጠ/ሚ፣ “ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ አዝዣለሁ” በማለት በሚመሩት ሕዝብ ላይ ጦርነት አውጀዋል

በፅሁፉ መግቢያ ላይ እንደገለፅኩት፣ የእኔ ጥረት በተቻለኝ አቅም ሕዝብና መንግስትን ማሳወቅና የመፍትሄ ሃሳቦችን መጠቆም ነው። በሀገራችን የተከሰተው ግጭትና አለመረጋጋት አሁን ካለበት አስከፊ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት “በቀውሱ የህዳሴን መንገድ ይቀይሱ – ለጠ/ሚ ኃ/ማሪያም) በሚል ርዕስ ምክር አዘል ፅሁፍ ማቅረቤን በመግቢያዬ ላይ ጠቅሼያለሁ። በፅሁፉ ያቀርብኩት ሃሳብ ለችግሮቹ ሁሉ መፍትሄ ይሆናል እያልኩ አይደለም። ነገር ግን፣ በወቅቱ ላነሳኋቸው ችግሮች ተገቢ ትኩረት ተሰጥቶ ቢሰራ ኖሮ አሁን ካለንበት ደረጃ ላይ አንደርስም ነበር።

አሁንም ቢሆንም “ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ አዝዣለሁ” የሚል ትዕዛዝ በማስተላለፍ በሕዝብ ላይ ጦርነት አውጀዋል። አስቸኳይ የመፍትሄ እርምጃ ካልተወሰደ ግን፣ በጦርነት ጥላ ስር የሚፈፀሙ ዘግናኝ ድርጊቶች በሕዝባችን ላይ መድረሳቸውን በማስመልከት በምፅፈው ቀጣይ ደብዳቤ ዳግም እንደምንገናኝ እርግጠኛ ነኝ። በዜጎች ላይ የሚደርሱ አሰቃቂ በደሎችና ጭቆናዎች መሰረታቸው ለስልጣን ጭፍን ተገዢ መሆን (blind obedience to authority) ነው።

ከሠላምታ ጋር
ስዩም ተሾመ (MBA)
አምቦ ዩኒቨርሲቲ ወሊሶ ካምፓስ
ወሊሶ
Email: seyee123@gmail.com
Blog Address:ethiothinkthank and Hornaffairs