አመፅ የማን ልጅ ነው፡ የልማት ወይስ የአምባገነንነት?

በተለያዩ አከባቢዎች አመፅና ተቃውሞ ሲነሳ አንዳንድ የኢህአዴግ ባለስልጣናት የሀገሪቱ ልማት ያስከተለው ችግር እንደሆነ ሲናገሩ ይደመጣል። በእርግጥ የሀገር ልማት ለአመፅና አለመረጋጋት መንስዔ ሊሆን ይችላል? አመፅ የልማት ወይስ አምባገነንነት ተግባር ውጤት ነው? በዚህ ፅሁፍ እነዚህንና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን በዝርዝር እንመለከታለን።

በቅድሚያ ልማት ምንድነው የሚለውን በአጭሩ መመልከት ያስፈልጋል። ልማትን “ሰላም፥ ጤና፥ ትምህርት እና መሰረተ-ልማት” በማለት በአጭሩ መግለፅ ይቻላል። እነዚህ አራት መሰረታዊ ነገሮች የዳበረ ማህበራዊ ግንኙነት እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር በማስቻል የዜጎችን ኑሮና አኗኗር እንዲሻሻል ያስችላሉ፣ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ያደርጋሉ። ስለዚህ፣ ልማት ከቦታና ግዜ አንፃር የዜጎችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ፈጣንና ቀልጣፋ ከማድረግ ጋር የተያያዘ ነው።

“ፖለቲካ” ማለት ደግሞ ግለሰብ፥ ቡድንና ማህብረሰብ እርስ-በእርስ ወይም አንዱ ከሌላው ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት የሚመራበት ስርዓት ነው። ስለዚህ ፖለቲካ የሕዝቡ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት የሚመራበት ሥርዓት ነው። ልማት ደግሞ ይህን ስርዓት ወደ ላቀ ደረጃ ከማሻሻል ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። በዚህ መሰረት በአንድ ሀገር ውስጥ ልማት እስካለ ድረስ ፖለቲካዊ ስርዓቱን በበላይነት የሚመራው መንግስት አብሮ መቀየር መቻል አለበት።

በመሰረቱ፣ ማንኛውም የልማት ስራ ዓላማው ብዙኑን የሕብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ማድረግ ነው። ምክንያቱም፣ በአንድ ሀገር ውስጥ ልማት ሊኖር የሚችለው በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ሰላምና ደህንነት ሲኖር፤ የጤና፥ ትምህርትና ሌሎች ተቋማት አገልግሎት ተደራሽ ሲሆኑ፤ የመንገድ፣ ውሃ፥ መብራት፥ ቴሌኮምዩኒኬሽን መሰረተ-ልማት አውታሮች ሽፋን ሲጨምር ነው። ስለዚህ፣ ልማት ብዙሃኑን የሕብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ በማድረግ እኩልነት (equality) እንዲረጋገጥ ያስችላል።

“Anthony Giddens” የተባለው ምሁር ማንኛውም መንግስት የበለጠ ዴሞክራሲያዊ የመሆን ግዴታ አለበት ይገልፃል። “democratising democracy” በሚለው ፅሁፍ፣ ሌላው ቀርቶ የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ያላቸው ሀገራት ቢሆኑ እንኳን የበለጠ ዴሞክራሲያዊ እየሆኑ መሄድ ይጠበቅባቸዋል። በተለይ አምባገነናዊ ወይም ፊውዳላዊ የሆኑ መንግስት ከቀድሞ ግዜ በተሻለ ዴሞክራሲያዊ እየሆነ መሄድ አለባቸው። ምክንያቱም፣ ከግዜ ወደ ግዜ ለውጥና መሻሻል ከሌለ አመፅና ረብሻ፣ እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች እንደሚከሰቱ ይጠቅሳል።

“Garry Jacobs” የተባለው ምሁር ደግሞ “Employment, Individuality and Development” በተሰኘ ፅሁፉ ዴሞክራሲ ሦስት ዓይነት የእድገት ደረጃዎች እንዳሉት ይገልፃል። አንደኛ፡- “ስነ-ልቦናዊ ዴሞክራሲ” (psychological democracy) የሚባለው ሲሆን፣ ሰላማዊ፥ ጤናማና የተማረ ዜጋ ከሌሎች ጋር እኩል ነኝ ብሎ የሚያስብበት፤ ሁለተኛ፡- “ኢኮኖሚያዊ ዴሞክራሲ” (economic democracy) – ከሌሎች ጋር እኩል ሀብትና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥበት፤ እና ሦስተኛ፡- “ፖለቲካዊ ዴሞክራሲ” (political democracy) – ከሌሎች ዜጎች ጋር እኩል መብትና ነፃነት የሚጎናፀፍበት። ስነ-ልቦናዊ ዴሞክራሲ ከሌለ ኢኮኖሚያዊ ዴሞክራሲ አይኖርም፣ ኢኮኖሚያዊ ዴሞክራሲ ከሌለ ፖለቲካዊ ዴሞክራሲ ሊኖር አይችልም።

ፈረንሳዊው ፈላስፋ “Montesquieu” በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ደግሞ የዜጎችና የመንግስት ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚመራበት መርህ “እኩልነት” (equality) ነው። እንደእሱ አገላለፅ፣ እኩልነት የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባላት ሀገር ውስጥ የዜጎች እና የመንግስት ተግባራትና እንቅስቃሴዎች የሚመራበት መርህ ነው። “ልማት” በሰላም፥ ጤና፥ ትምህርት እና መሰረተ-ልማት ዜጎችን እኩል ተጠቃሚ ማድረግ ነው። “ዴሞክራሲ” በአመለካከት፣ ኢኮኖሚና መብት አንፃር በዜጎች መካከል እኩልነት እንዲሰፍን ያስችላል። በመሆኑም፣ ልማት እኩልነትን ለማረጋገጥ የሚከናወን ሲሆን ዴሞክራሲ ደግሞ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት ነው።ስለዚህ፣ ዴሞክራሲ የልማት የመጨረሻ ግብ ነው። በሌላ አነጋገር ልማት ዴሞክራሲን ይወልዳል።

የኢህአዴግ መንግስት በሀገሪቱ እየታየ ላለው የሕዝብ አመፅና ተቃውሞ መንስዔው ላለፉት 25 ዓመታት ሀገሪቱ እያስመዘገበችው ልማት እንደሆነ ይጠቅሳል። ነገር ግን፣ ከላይ በዝርዝር እንደተመለከትነው፣ ልማት ዴሞክራሲ እንጂ አመፅና ተቃውሞን አይወልድም። ስለዚህ፣ አንዳንድ የኢህአዴግ ባለስልጣናትና ደጋፊዎቻቸው የሕዝቡን የተቃውሞ አንቅስቃሴ “ልማቱ ያስከተለው ችግር ነው” ማለታቸው ስህተት ነውን?

በመሰረቱ፣ ልማት ዴሞክራሲን የሚወልደው በዜጎች መካከል ከኑሮና አኗኗር ዘይቤ አንፃር ያለውን “ልዩነት” በማጥበብ ነው። ስለዚህ እኩልነትን ለማረጋገጥ በቅድሚያ በዜጎች መካከል ያለው ልዩነት (Inequality) መጋለጥና መታወቅ አለበት። በዚህ መሰረት፣ የልማት የመጀመሪያው ግብ በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ያለው ልዩነት ማጋለጥ ነው። ይህ የልማቱ አካል በሆኑት የመገናኛና ኮሚዩኒኬሽን አውታሮች አማካኝነት የሚከናወን ይሆናል።

ሀገራት በፍጥነት እያደጉ በሄዱ ቁጥር የመገናኛና ኮሚዩኒኬሽን አውታሮች ለአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ስለሚሆኑ፣ በዜጎች መካከል ያለው የመረጃ ልውውጥ በዚያኑ ያህል እየጨመረ ይሄዳል። ይህም በዜጎች ኑሮና የአኗኗር ዘይቤ ረገድ የነበረው እና እየተፈጠረ ያለው ልዩነት ለማወቅ ያስችላቸዋል። በመቀጠል፣ በተለይ በልማቱ እኩል ተጠቃሚ ባልሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ እንዲነሳ ምክንያት ይሆናል።

ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የልማት መሰረታዊ ዓላማ አብዛኛውን የሕብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ማድረግ ነው። በዚህም፣ የዜጎች እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ያስችላል። ልማት ባለበት ሁሉ የዴሞክራሲ ጥያቄ ይከተላል። ስለዚህ፣ ሀገራት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ሲጀምሩ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች በብዙ እጥፍ ይጨምራሉ። ከዚህ ቀጥሎ ያለው ትንታኔና ሰንጠረዥ ከ1993 – 2003 ዓ.ም (እ.አ.አ) የቻይና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እና በሀገሪቱ የተከሰቱትን የፀጥታና አለመረጋጋት ችግሮች በንፅፅር ያሳያል፡-

“In an age of mass communication, rising prosperity in one section of the population raises expectations of a better life everywhere. Indeed, a global revolution of rising expectations has been a major driving force for change over the past five decades. Television carries images of luxurious life in the metropolis and overseas to impoverished urban slums and outlying rural villages. When this growing awareness is not accompanied by growing opportunities, it gives rise to increasing frustration, social tensions and violence, as expressed by the increasing incidents of violence in China and India, the two fastest growing major economies in the world.” Human Capital and Sustainability, Sustainability Journal, Volume 3 Issue 1.

Mass incidents of social unrest in China 1993–2003.

ምንጭ፡ mssresearch.org

ከዚህ መረዳት እንደሚቻው፣ ልማት የዴሞክራሲ ጥያቄን ይወልዳል። ነገር ግን፣ እነዚህ ከሕዝቡ የሚነሱ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎችን በኃይል ለማፈን መሞከር ግጭትና አለመረጋጋትን ያስከትላል። በመሰረቱ የሕዝብን ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ በኃይል ለማፈን መሞከር “አምባገነንነት” ነው። በመሆኑም፣ ልማት የዴሞክራሲ ጥያቄን ሲወልድ፣ አምባገነንነት ደግሞ የሕዝብን አመፅ ይወልዳል። በዚህ መሰረት፣ የልማት ልጅ ዴሞክራሲ አንጂ አመፅ እንዳልሆነ መረዳት ይቻላል።

በአጠቃላይ፣ ልማትን ተከትሎ የሚነሱትን የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች በኃይል ለማፈን መሞከር ዴሞክራሲ እንደ ማጨናገፍ ሊቆጠር ይገባል። አሁን የኢህአዴግ መንግስት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ያለውን ተስፋ የሚያጨልም ነው። ከዚህ አንፃር መንግስት ከብዙሃን መገናኛ ተቋማትንና ሌሎች የመረጃ ምንጮችን በመቆጣጠር በሕዝቡ ዘንድ የተቀሰቀሰውን አመፅና ተቃውሞ ለማፈን እያደርገ ያለው ጥረት ፍፁም ስህተት እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። እንደ “Anthony Giddens” አገላለፅ፣ እንደ ኢህአዴግ ያሉ መንግስታት በሕዝቡ የተነሱትን የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ተቀብሎ በአስቸኳይ ምላሽ ከመስጠት ውጪ ሌላ ምንም አማራጭ እንደሌለው እንዲህ ገልፆታል፡-

“Information monopoly, upon which the political system was based, has no future in an intrinsically open framework of global communications. A deepening of democracy is required, because the old mechanisms of government don’t work in a society where citizens live in the same information environment as those in power over them.” Anthony Giddens: Runaway World – Democracy