ልማት የሕዝብ ነው፣ መንግስት ጥገኛ ነው

አብዛኞቹ የኢህአዴግ ባለስልጣናት በሀገሪቱ ታይቶ የማይታወቅ ልማትና እድገት እያስመዘገቡ እንደሆነ ያስባሉ። ነገር ግን፣ እነሱ እንደሚሉት በሀገሪቱ ታይቶ የማይታወቅ ልማትና እድገት እያስመዘገቡ አይደለም። ይሄን ያልኩበት ምክንያት “ኢህአዴግ ልማት አምጥቷል/አላመጣም” ወደሚለው ጉንጭ-አልፋ ክርክር ለመግባት ፈልጌ አይደለም። የኢህአዴግ መንግስት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ሁሉም መንግስታት በራሳቸው የልማትና እድገት ምንጭ ሊሆኑ አይችሉም። ምክንያቱም መንግስት በሀገር ልማትና እድገት ውስጥ ከደጋፊነት የዘለለ ሚና ሊኖረው አይችልምና።

ፅንሰ-ሃሳቡን በተጨባጭ እውነታዎች ላይ ተመስርተን እንመለከታለን። በእርግጥ ኢህአዴግ ራሱን የልማትና እድገት ዋና ተዋናይ አድርጎ እንደሚመለከት ግልፅ ነው። ለዚህ ደግሞ ለከፍተኛ ትምህርት ማህብረሰብ ሥልጠና የተዘጋጀውን ሰነድ ውስጥ“የሃያ አምስት አመታት ጉዞ የስኬት ምንጮች” በሚል የተጠቀሰው እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል፡-

“የዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግስት አስተሳሰብ በትክክለኛ ፖሊሲ፣ እስትራቴጂ፣ ፈፃሚና አመራር የፖሊሲ ነፃነት በማስከበር ያሳካው ድል መሆኑ፣… ህዝባችንን ከድህነት የሚያላቅቅልን ርዕዮት በቂ ሳይንሳዊ ትንተና በማድረግ ከሌሎች ልማታዊ መንግስታት ተሞክሮ በመማርና ከልምዳችን ችግሮቻችንን በማረም ያሳካነው ውጤት መሆኑ፣ መንግስታዊ ስልጣን ለህዝብ ጥቅም እንዲውል ለማድረግ የሚያስችል የፖለቲካ ስርዓት በመፍጠር የተገኘ ውጤት መሆኑ” የከፍተኛ ትምህርት ማህብረሰብ ሥልጠና ለ2009 ትምህርት ዘመን ዝግጅት ምዕራፍ ማጠናቀቂያ፣ ትምህርት ሚኒስቴር፥ መስከረም 2009፥ ሰነድ-አንድ፥ Slide-14.

 

እንደ ኢህአዴግ አገላለፅ፣ ላለፉት 25 ዓመታት የተመዘገቡት አንኳር አገራዊ ለውጦች የመንግስታዊ ስርዓቱና የመንግስት ተግባራት፤ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ አቅጣጫዎች እና አስተዳደር ውጤቶች ናቸው። ነገር ግን፣ መንግስታዊ ስርዓትና ተግባራት ለሀገር ልማትና እድገት ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባሻገር የስኬት ምንጭ ሊሆኑ አይችሉም። በዚህ ጉዳይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ችግሩ በብዙ ታዳጊ ሀገሮች ላይ እንደሚስተዋል ይገልፃሉ።

“Many developing nations discovered the hard way the obvious truth that no government can develop a nation. Nations are developed by their people. …. People develop themselves. It is the role of government to foster and support that process of self-development. …Society is the whole of which economy is only a part. Economy is the whole of which money is a part. Society creates jobs, not economy or money.” Employment, Individuality and Development, MSS Research, Feb 14, 2010.

ከላይ እንደተጠቀሰው፣ መንግስት ሀገርን አያሳድግም። ከዚያ ይልቅ፣ ሀገር የሚያሳድገው ህዝብ ነው። እዚህ ጋር የመንግስት ድርሻ፣ ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ሕዝቡ ራሱን በራሱ ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት መደገፍ ነው። ነገር ግን፣ በትኛውም የፖለቲካ ሥርዓት የመንግስት ተግባርና ኃላፊነት ለሕዝቡ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ድጋፍ ከማድረግ የዘለለ ሊሆን አይችልም። መንግስት በኢኮኖሚው ዋና ተዋናይ ከሆነና ልክ እንደ ኢህአዴግ ራሱን የስኬት ምንጭ አድርጎ የሚቆጥር ከሆነ ፍፁም ስህተት ነው። ምክንያቱም መንግስት ያለ ኢኮኖሚና ገንዘብ የሥራ እድል መፍጠር ሆነ መሰረተ-ልማት መገንባት አይችልም። እንዴትና ለምን የሚለውን ከገንዘብ በመጀመር እንመልከት።

የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ እና የገንዘብ እንቅስቃሴ የሚወስነው በሕብረተሰቡ (Society) እንጂ በመንግስት ውሳኔና ፖሊሲ አይደለም። “Carl Menger” በ1892 (እ.አ.አ) “On the Origins of Money” በሚለው መፅሃፉ እንዲህ ይላል፡- “In its origin money is a social, not a state institution”። በዚህ መሰረት፣ ገንዘብ በሕብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አማካኝነት እንጂ በመንግስት ፍቃድ የተፈጠረ አይደለም። ይህንንም ፀኃፊው “Money has not been generated by law” በማለት ይገልፀዋል።

ከገንዘብ (money) በተጨማሪ መንግስት የሕብረተሰቡን የኢኮኖሚ አንቅስቃሴ በበላይነት መቆጣጠር አይችልም። የአንድ ሀገር ኢኮኖሚን ለማንቀሳቀስ የቋሚ ሃብቶች (fixed capitals) እና ጥሬ-ሃብቶች (resources) ያስፈልጋሉ። የሥነ-ምጣኔ ፈር-ቀዳጅ የሆነው አዳም ስሚዝ መሰረት አራት አይነት ቋሚ ህብቶች ያሉ ሲሆን፣ እነሱም፡- መሬት (land)፣ መስሪያ ቦታ (buildings)፣ የመስሪያ ማሽን (machinery) እና የሰው ሀብት (human abilities) ናቸው። ከእነዚህ በተጨማሪ፣ ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ሌሎች የተለያዩ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ግብዓቶች ጥቅም ላይ ይውላሉ። ነገር ግን፣ ሁሉም ሀብቶችና ግብዓቶች ያለ የሰው ልጅ ዕውቀትና ክህሎት ፋይዳ-ቢስ ናቸው።

Ludwig von Mises” የተባለው የሥነ-ምጣኔ (Economics) ምሁር ዘርፉን “Economics is not about goods and services; it is about human choice and action” በማለት ይገልፀዋል። በዚህ መሰረት ኢኮኖሚያ በሰዎች ምርጫና እንቅስቃሴ እንጂ በሸቀጣ-ሸቀጦች እና አገልግሎቶች አቅርቦት ላይ የተመሰረተ እንዳልሆነ እንረዳለን። በአጠቃላይመ የአንድ ሀገር ለኢኮኖሚያዊ አንቅስቃሴው መሰረት የሆኑት ቋሚና ጥሬ ሀብቶች በራሳቸው የሰው-ልጅ እሳቤና ግንዛቤ ውጤት ስለመሆናቸው እንደሚከተለው ተገልጿል፡-

“The very notion of capital is a human conception. In this sense, anything becomes a resource by the action of the human mind. Resources are perceived and developed. Materials exist in nature, but anything becomes a resource only when its potential value is recognized by the human mind. Human mental activity creates resources by discovering new productive relationships between existing elements.” Human Capital and Sustainability, Sustainability Journal, Volume 3 Issue 1.

በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን በመሰረተ-ልማት ግንባታ ረገድም ጭምር መንግስት ራሱን ችሎ ምንም ነገር የመስራት እቅም የለውም። ምክንያቱም በመሰረታዊ የሥነ-ምጣኔ መርህ መሰረት ገንዘብ የሕብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊ አንቅስቃሴ ውጤት እንጂ በመንግስት ፍቃድ የሚመነጭ ነገር አይደለም። ሕብረተሰቡ የጋራ ጥቅሙን ለማረጋገጥ በግብር መልክ (tax) ለመንግስት ገቢ ከሚያደርገው ውጪ መንግስት በራሱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አድርጎ ገቢ ማመንጨት አይችልም። ስለዚህ፣ መንግስት በገቢ ረገድም በሕብረተሰቡ ፍቃድና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ጥገኛ ነው። በመሆኑም፣ ከሕዝብ ፍቃድና ድጋፍ ውጪ መንግስት በራሱ የልማትና እድገት ምንጭ ለመሆን የሚያስችል አቅም የለውም።

ኢህአዴግ ባለፉት 25 ዓመታት ለተመዘገቡት አንኳር ሀገራዊ ለውጦች መንግስታዊ ስርዓቱና የመንግስት ተግባራት፤ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ አቅጣጫዎች እና የአስተዳደር ተግባራት እንደ ዋና የስኬት ምንጮች ጠቅሷል። ከላይ በዝርዝር ለመግለፅ እንደተሞከረው የሀገር ልማትና እድገት ሊመጣ የሚችለው በሕብረተሰቡ ነፃ እንቅስቃሴና ምርጫ እንጂ በመንግስት አማካኝነት እንዳልሆነ አይተናል። ስለዚህ፣ ኢህአዴግ ራስን እንደ የስኬት ምንጭ አድርጎ ማየቱ ከተሳሳተ እሳቤ የመነጨ ነው። ይሁን እንጂ፣ ይህ እሳቤ በኢህአዴግ ላይ ብቻ ሳይሆን በብዙ የበለፀጉ ሀገሮች ዘንድም የሚስተዋል ችግር ነው። ከዚህ አንፃር፣ የዓለም አቀፉ የምግብና ሰላም ከሚሽን (International Commission on Peace and Food (ICPF)) ችግሩን እንዲህ እንደሚከተለው ይገልፀዋል፡-

“for millennia we have tended to overlook or, at best, grossly underestimate the greatest of all resources and the true source of all the discoveries, inventions, creativity and productive power found in nature, the ultimate resource, the human being”

በአጠቃላይ ከላይ የተነሳውን ሃሳብ፤ “Man himself is the beginning and the end of every economy” በሚለው አባባል ማጠቃለል ይቻላል። አዎ… የእያንዳንዱ ኢኮኖሚ መነሻና መድረሻ ሰው ነው። የኢትዮጲያ ልማትና እድገት መነሻና መድረሻ የሀገሪቱ ሕዝብ ነው። እንደ መንግስት ከሕዝቡ በሰበሰበው ግብር ማህበራዊ ግንኙነቱንና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን የሚያቀላጥፉ መሰረተ-ልማቶችን መገንባት አለበት። ስለዚህ፣ እንደ ማንኛውም መንግስት ኢህአዴግ “ለሀገሪቱ ልማትና እድገት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የደጋፊነት ሚናዬን በአግባቡ ተወጥቼያለሁ” ማለት ወግ ነው። ነገር ግን፣ የለውጥ መሰረት የሆነውን ሕዝብ ወደ ጎን ትቶ ራሱን በስኬት ምንጭነት የሚጠቅሰው ኢህአዴግ ምን ይባላል? በእርግጥ የአምባገነንነት በተግባር ያልሆኑትን በግድ ነኝ ብሎ ከማሰብ ይጀምራል። ስለዚህ፣ የኢህአዴግ የስኬት ምንጭነት የራሱን አምባገነንነት ከመመስከር ያለፈ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም።