ኢህአዴግ ካልታደሰ አይወድቅም

አብዛኞቹ ተቃዋሚዎች “ኢህአዴግ በቅርቡ ይወድቃል” ሲሉ፣ ደጋፊዎቹ ደግሞ “በቅርቡ ይታደሳል” እያሉ ይገኛል። ከመቼውም ግዜ በላይ በሀገሪቱ ፖለቲካ ለውጥ ስለማስፈለጉ ግን ሁለቱም ወገኖች አምነው የተቀበሉት ይመስላል። ይህ ለውጥ ደግሞ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ከኢህአዴግ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። የሀገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እንደ መንግስት በኢህአዴግ ላይ ውድቀት ወይም ተሃድሶ ሊያስከትል ይቻላል። ታዲያ እዚህ ጋር ቁልፉ ጥያቄ “ኢህአዴግ ይወድቃል ወይስ ይታደሳል?” የሚለው ነው። የጥያቄው መልስ፣ ከጭፍን ተቃውሞና ድጋፍ ባሻገር፣ በተጨባጭ እውነታ ላይ የተመሰረተ ትንታኔ ይጠይቃል። በዚህ ፅሁፍ ዝርዝር ትንታኔውን ይዘን ቀርበናል።  

በመሰረቱ፣ በሕዝቡ እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እስካልተሰጣቸው ድረስ ግጭትና አለመረጋጋቱ እየጨመረ ይሄዳል። ለዚህም በ2008 ዓመት መጀመሪያ ላይ በተወሰኑ የአማራና ኦሮሚያ አከባቢዎች የተጀመረው የአመፅና ተቃውሞ በአመቱ መጨረሻ ላይ የት እንደደረሰ ማየቱ ብቻ በቂ ነው። የሚፈለገው ለውጥ እስካልመጣ ድረስ በቀጣይ አመትም በተመሳሳይ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች መከሰታቸው የማይቀር ነገር ነው። ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ከዕለት ወደ ዕለት ከቦታና ግዜ አንፃር እየሰፋና እየጨመረ ቢሆንም፣ በመንግስትና ተቃዋሚዎች ጎራ “ኢህአዴግ ይወድቃል ወይም ይታደሳል” ከሚል ፉከራ የዘለለ በተጨባጭ የሚታይ ለውጥ የለም።

በቅድሚያ ግን “የፖለቲካ እንቅስቃሴው በዚሁ ከቀጠለ ምን አይነት ጉዳት ያስከትላል?” የሚለውን በአጭሩ ማየት ያስፈልጋል። በፖለቲካ እንቅስቃሴው ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆኑት አካላት፡- ሕዝብ፣ መንግስትና ተቃዋሚዎች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ሕዝቡ ብቻ ነው ወደፊት እየተራመደ ያለው። መንግስትና ተቃዋሚዎች ግን ባሉበት እየረገጡ ይገኛሉ። በእርግጥ ኢህአዴግ አሁን ባለበት ሁኔታ ከቀጠለ በትንሽ ግዜ ውስጥ ይወድቃል። ይህ ግ በዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል፣ በፖለቲካውም ትልቅ ኪሳራ ያስከትላል። 

መንግስት ሕዝቡ እያነሳቸው ላሉት የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በኃይል ለማፈን የሚደረገው ጥረት ሀገሪቱን ወደለየለት ግጭትና አለመረጋጋት ያስገባታል። የኢህአዴግ ባለስልጣናት ሥራና አሰራራቸውን ከማሻሻል ይልቅ ፖሊሶች፣ ወታደሮችና የደህንነት ሰራተኞች በመላክ ሕዝቡን ለሞት፣ ጉዳትና ለእስራት የሚዳርጉት ከሆነ ባለስልጣናቱ በሕዝቡ ዘንድ ያላቸውን ቅቡልነት፣ እንደ መንግስትም ያላቸውን ተቀባይነት ከግዜ ወደ ግዜ እያጡ ይሄዳሉ። በዚህም፣ አንደኛ፡- መንግስት በሕዝቡ ዘንድ ያለውን የማስተዳደር ስልጣን ይገፈፋል፤ ሁለተኛ፡- ሕዝቡ ራሱን-በራሱ ማስተዳደር መብቱን ተጠቅሞ የጋራ ሰላምና ደህንነቱን በራሱ ለማስከበር ጥረት ያደርጋል። ይህን ተከትሎ የመንግስት ባለስልጣናትና የፀጥታ ኃይሎች በሕዝብ ላይ የሕይወትና ንብረት ጉዳት ሲያደርሱ ሕዝቡ ደግሞ በሁለቱም አካላት ላይ የአፀፋ እርምጃ መውሰድ ይጀምራል። 

በመሰረቱ የሕዝብ እርምጃ በተለያዩ መንገዶች ተቃውሞውን መግለፅ ነው። በመንግስት ኃይሎች የሚወሰደው እርምጃ በዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት እየከፋ በሄደ ቁጥር ግን ተቃውሞው ባህሪውን እየቀየረ ይመጣል። በእርግጥ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞውን መግለፅ ይቀጥላል። ከዚህ ጎን-ለጎን ግን መንግስትን በኃይል ለመጣል የሚታገሉ ኃይሎችን በውስጡ መደበቅ ይጀምራል። ከመንግስት ጋር የትጥቅ ትግል የሚያደርጉ ኃይሎች በስደት ከሚኖሩበት ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ይጀምራሉ። 

የኢህአዴግ መንግስት ራሱ ለረጅም ግዜ “ሞቷል” ሲለው የነበረው የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) እና “የኤርትራ ተላላኪ” የሚለው ግንቦት7 ባሳለፍነው የ2008 ዓመት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ግጭትና አለመረጋጋት እጃቸው አለበት ማለት ጀምሯል። ከዚህ በፊት እነዚህ ኃይሎች በመንግስት ላይ ጫና የማሳደር አቅማቸው ውስን ነበር። ይህ የሆነበት ምክንያት ሕዝቡ በውስጡ ከመንግስት ኃይሎች ሊደብቃቸው ፍቃደኛ ስላልነበር ነው። ዛሬ ላይ ግን፣ በኦሮሚያና በአማራ ልጆቹ በመንግስት ኃይሎች የተገደሉበት፣ የተጎዱበትና የታሰሩበት ቤተሰብ የኦነግ ወይም የግንቦት7 ተዋጊ ከቤቱ ቢደብቅና ስንቅ ቢያቀብል ሊገርመን አይገባም። 

ቁጥራቸው በጣም ጥቂት የሆኑ ግን ከሕዝቡ ውስጥ የተደበቁ የአማፂ ቡድን አባላት በመንግስት ኃላፊዎችና በፀጥታ ኃይሎች ላይ ጥቃት መፈፀም ሲጀምሩ የፖለቲካ ሁኔታው ፍፁም ይቀየራል። የመንግስት ባለስልጣናትና የፀጥታ ኃይሎች በጋራ ሕልውናቸው አደጋ ላይ ይወድቃል። ሕዝብ ጥቅጥቅ ያለ ደን ነው። በባለስልጣናትና የፀጥታ ኃይሎች ላይ ጥቃት ፈፃሚው ማን እንደሆነ በቀላሉ መለየት አይቻልም። በዚህ መልኩ በመንግስት ኃላፊዎችና የፀጥታ ኃይሎች ላይ የሚፈፀም ጥቃት በደርግ ዘመን እንደነበረው “ነጭ-ሽብር” ያስከትላል። መንግስትና የፀጥታ ኃይሎች ራሳቸውን ለመከላከል የሚወስዱት የአፀፋ እርምጃ ደግሞ “ቀይ-ሽብር” በመባል የሚታወቀውን ጅምላ ጭፍጨፋ ያስከትላል። በደርግ ዘመን በነጭ-ሽብር ጥቃት የተገደሉት 10 የደርግ ባለስልጣናትን እና 15 የፀጥታ አስከባሪዎችን ነበሩ። ከታህሳስ እስከ መጋቢት 2008 ዓ.ም ባሉት አራት ወራት ብቻ 14 የኢህአዴግ ባለስልጣናት እና 14 የፀጥታ አስከባሪዎች መገደላቸው ወደ የት እያመራን እንደሆነ በግልፅ ይጠቁማል። ስለዚህ፣ በደርግ ዘመን የደረሰው አስከፊ ጭፍጨፋና ጦርነት በሀገራችን ተመልሶ እንዳይመጣ አስቸኳይ ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል። 

ሕዝቡ እየጠየቀ ያለው ለውጥና መሻሻል እንዲመጣ “ኢህአዴግ ይውደቅ ወይስ ይታደስ?” የሚለውን ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል።በእርግጥ መውደቅም ሆነ መታደስ ሁለቱም ለውጥ ናቸው። ነገር ግን፣ ለውጥ (Change) ሁለት አይነት ነው፡- አፍራሽ (Destructive) ወይም ገንቢ (Constructive)። ከአፍራሽ ይልቅ ገንቢ ለውጥ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ይሰጣል። ኢህአዴግን የጠለፈው የአመራር ወጥመድ በሚለው ፅሁፍ ላይ በዝርዝር ለመግለፅ እንደሞከርኩት፣ ኢህአዴግ ራሱን በራሱ ለማደስ የሚያስችል አቅም የለውም። ኢህአዴግና ፅንፈኞች፡ ባለበት የቆመና ባለፈው የቆዘሙ በሚለው ፅሁፍ ደግሞ ከሕዝቡ የለውጥ ፍላጎት ጋር አብሮ ለመሄድ የተሳነው ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚዎች ጭምር እንደሆኑ በዝርዝር ይገልፃል። ስለዚህ፣ በአጠቃላይ፣ ለውጥ የሚያስፈልገው ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚዎች ጭምር ናቸው። 

ሁለቱም ወገኖች አስፈላጊና ተገቢ የሆነው ለውጥ ማምጣት ከተሳናቸው፤ አንደኛ፡- ከላይ በተጠቀሰው መልኩ የደርግ ዘመን ጅምላ ጭፍጨፋና በደል ሊደርስ ይችላል፣ ሁለተኛ፡- ሕዝቡ ኢህአዴግን በኃይል ገፍቶ ቢጥለው እንኳን ክፍተቱን የሚሸፍን የተደራጀ የፖለቲካ ኃይል የለም። ስለዚህ፣ እነዚህ ችግሮች በዘላቂነት እንዲወገዱ በመንግስትና ተቃዋሚዎች ዘንድ ተሃድሶ ማድረግ አስፈላጊ ነው። 

አመፅ የማን ልጅ ነው፡ የልማት ወይስ አምባገነንነትን” በሚለው ፅሁፍ ላይ በዝርዝር ለማስረዳት እንደሞከርኩት፣ አሁን በሀገሪቱ የተከሰተው ግጭትና አለመረጋጋት ስረ መሰረቱ መንግስታዊ ሥርዓቱ ነው። ኢህአዴግ እንደ ገዢ ፓርቲ የሚመራው በልማታዊ መንግስት መርህ ነው። በመሆኑም፣ ጠዋት-ማት ስለ ልማትና የብሔሮች እኩልነት ሲያወራ ባልተጠበቀ መንገድ ሕዝቡ የዴሞክራሲ ጥያቄ ይዞ አደባባይ ወጣ። 

የኢህአዴግ መንግስት ራሱን “ልማታዊ-ዴሞክራሲያዊ” እያለ ይጠራል። በእርግጥ ራሱን “ልማታዊ” ብሎ ሊጠራ ይችል ይሆናል። ነገር ግን፣ 100% ምርጫ አሸነፍኩ ብሎ ብቻውን አብኩቶ መጋገር ከጀመረ ወዲህ “ዴሞክራሲያዊ” የሚለውን እንኳን በተግባር በስም አያውቀውም። ቱባ-ቱባ ባለስልጣናቱ “ሰላማዊ ሰልፍ አልፈቀድንም” እያሉ በይፋ ሲናገሩ ሕገ-መንግስቱን እየጣሱ እንደነበረ ትዝ አላላቸውም። ሕዝብ ላቀረባቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፣ “የሕግ የበላይነትን ለማስከበር” በሚል ሰበብ ሕዝቡን በኃይል ማፈን ሲጀምሩ “ከሕግ ይልቅ የጉልበት የበላይነት” ነገሰ። ይህ ሲሆን ኢህአዴግ ኢህአዴግ ከልማታዊ መንግስትነት ወደ የለየለት “አምባገነንነት” ተቀየረ። 

ኢህአዴግ በተሃድሶ አሁን ካለበት አምባገነንነት ወደ ቀድሞ “ልማታዊ መንግስትነቱ” መመለስ ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ ሕዝቡ እያደረገ ካለው ትግል በተጨማሪ ተቃዋሚዎች ወሳኝ ሚና አላቸው። የተቃዋሚዎች ተሃድሶ የራሳቸውንና የሕዝብን የፖለቲካ ጥቅም ከማረጋገጥ አልፎ ለኢህአዴግ ተሃድሶ በጣም አስፈላጊ ነው። 

በ2008 አመት በተለይ የአማራና ኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ መብቱንና ነፃነቱን ለማስከበር ያደረገው ተጋድሎ የሚደነቅ ነው። ይህ ግን ሕዝቡ በራሱ ያደረገው የለውጥ እንቅስቃሴ እንጂ በፖለቲካ ልሂቃን የተመራ አልነበረም። እንዲህ ያለ ያልተደራጀ እንቅስቃሴ፤ አንደኛ፡- የሚፈለገውን ለውጥ የማምጣት እድሉ ጠባብ ነው፣ ሁለተኛ፡- ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ከመንግስት ጋር ወደ አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ በማስገባት በሕይወትና ንብረት ረገድ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል። ይህን ለማስወገድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች በኢህአዴግ ቁመና ልክ የሚሆን የፖለቲካ አደረጃጀት ሊኖራቸው ይገባል። 

ተቃዋሚዎች የተቀናጀ የፖለቲካ አደረጃጀት በመዘርጋት የሕዝቡን እንቅስቃሴ ማገዝ አለባቸው። ከዚህ አንፃር የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርኣት ባላቸው የምዕራብ ሀገራት ያለው አይነት ተጠባባቂ መንግስት (Shadow Government) መመስረት አንዱ ነው። በዚህ መሰረት፤ የተቃውሞ እንቅስቃሴውን ወጥና የተደራጀ ማድረግ፣ ሕዝቡ አማራጭ ፖለቲካ ኃይል እንዲኖረው ማስቻል እና እንቅስቃሴውን በማቀናጀት በአጭር ግዜ ውስጥ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት ይቻላል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ የእያንዳንዱን የመንግስት መስሪያ ቤት ተግባርና እንቅስቀሴ የሚከታተል ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ስለሚኖር፣ በዕየለቱ የሚታዩ ክፍተቶች ለሕዝብ በማጋለጥ፣ ሥራና አሰራራቸውን እንዲያሻሽሉ በማድረግ፣ የኢህአዴግ መንግስት ተሃድሶ እንዲያደርግ ያግዘዋል። በዚህ ረገድ የኦሮሞን ሕዝብ ጥያቄዎች ተቀብሎ በማስተጋባትና የመንግስትን ክፍተት በማጋለጥ ረገድ አቶ ጀዋር መሃመድ አይነተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ለእያንዳንዱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት እንደ ጀዋር አይነት ትንታግ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ቢኖር በኢህአዴግ ለፈጥር የሚችለው ጫና በጣም ትልቅ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። 

እያንዳንዱ የፖለቲካ ኃይል መሰረታዊ ዓላማው የሕዝብን ኑሮና አኗኗር ለመቀየር የሚያስችለውን የፖለቲካ ስልጣን መያዝ ነው። ኢህአዴግ በስልጣን ላይ መቆየት ይፈለልጋል፣ ተቃዋሚዎችም መንግስት መሆን ይፈልጋሉ። በዚህ ፅሁፍ የቀረበው የመፍትሄ ሃሳብ ደግሞ “ሁሉም ተቃዋሚዎች የኢህአዴግን ተሃድሶ ማገዝ አለባቸው” የሚል አድምታ አለው። ይህ ደግሞ በቅድሚያ ተቃዋሚዎች የራሳቸውን ተሃድሶ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። እውነታው ይኼ ነው – ተቃዋሚዎች ተሃድሶ ካላደረጉ ኢህአዴግ አይወድቅም፣ ሕዝብ ከፍቶ ቢጥለው እንኳን ክፍተቱን የሚሸፍን የተደራጀ የፖለቲካ ኃይል የለም።

በተለይ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ኢህአዴግ “ዴሞክራሲን” ወደ ጎን ጥሎ “ልማታዊ መንግስት” በሚለው መርህ ብቻ እየተመራ እንዳለ ግልፅ ነው። በዚህ መሰረት ገዢው ፓርቲ ምንም ያህል ተሃድሶ ቢያደርግ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት የሚያስቸል አቅምና አመለካከት የለውም። በዋናነት በቡድን መብት እና እኩልነት መርሆች የሚመራው የኢህአዴግ መንግስት፣ ሕዝቡ የግለሰብ መብት እና እኩልነትን መሰረት አድርጎ እያነሳበት ያለውን የዴሞክራሲ ጥያቄ መመለስ አይችልም። በመሰረቱ በግለሰብ መብቶች፡- ነፃነት፣ እኩልነትና ፍትህ ላይ የተመሰረተው የሕዝብ ጥያቄ፣ ኢህአዴግ በቡድን መብቶች፡- የብሔር፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት፣ ሕገ-መንግስታዊ ሥርኣትና በልማት መመለስ ይሳነዋል። 

የኢህአዴግ ተሃድሶ መንግስት አሁን ካለበት ፍፁም አምባገነናዊነት ወደ ቀድሞ “ልማታዊ መንግስትነት” እንዲመለስ ማስቻል ነው። ነገር ግን፣ እያንዳንዷ የልማት እንቅስቃሴ ተጨማሪ የዴሞክራሲ ጥያቄ ታስከትላለች። በዚህም፣ ኢህአዴግ ምንም ያህል ለውጥና ተሃድሶ ቢያደርግ ለዴሞክራሲ ጥያቄ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት አይችልም። ነገር ግን፣ አሁን እያደረገ እንዳለው የሕዝቡን ጥያቄ በኃይል ማፈን ሊያቆም ይችላል። ይህ ሲሆን ከወታደር ጥይትና ከፖሊስ ዱላና እስር ጋር እየተጋፋ መብቱን እየጠየቀ ያለው ሕዝብ በአጭር ግዜ ውስጥ ከስልጣን ያወርደዋል። በመሆኑም፣ የኢህአዴግ ተሃድሶ ራሱ ኢህአዴግን ነው የሚጥለው። ከሌሎች አማራጮች በተሻለ ይህ በትንሽ ዋጋና ኪሳራ ኢህአዴግን ከስልጣን ማስወገድ እና አስተማማኝ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትም መገንባት የሚቻልበት መንገድ ነው። በአጠቃላይ፣ ኢህአዴግ ካልታደሰ አይወድቅም፤ ቢወድቅም የሚፈለገው ለውጥ አይመጣም።