የኦህዴድ ተሃድሶ፡ ከማሳደድ ወደ ማውረድ

የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ሁለት ከፍተኛ አመራሮቹን፤ የፓርቲው ሊቀመንበርና የክልሉ ፕረዘዳንት የነበሩትን አቶ ሙክታር ከዲር እና ምክትል ሊቀመንበር የነበረችውን ወ/ሮ አስቴር ማሞ ከኃላፊነት ማውረዱ ተገልጿል። በምትኩ አቶ ለማ መገርሳን ሊቀመንበር እና ዶ/ር ገበየሁ ወርቅነህን በም/ሊቀመንበርነት መርጧል። ኦህዴድ/ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮቹን ከኃላፊነት ማውረዱ በድርጅቱ ውስጥ “ተሃድሶ” እየተካሄደ ስለመሆኑ ይጠቁማል? 

ሁለቱ ከፍተኛ አመራሮች ከኃላፊነት ለመውረድ ለማዕከላዊ ኮሚቴ ፍቃደኝነታቸውን እንደገለፁ አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ከድርጅቱ ታሪክ አንፃር ሲታይ ይህ በራሱ አንድ ነገር ነው። ከዚህ ቀደም ክልሉን በፕረዜዳንትነት ያገለገሉት አቶ ሀሰን ዓሊ እና አቶ ጁነዲን ሳዶ ከሀገር ተሰድደዋል። የቀድሞዋ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የነበረችው ወ/ሮ አልማዝ መኮ’ን ጨምሮ እንደ ዮናታን ዲቢሣና ድርባ ሀርቆ ያሉ የቀድሞ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ሀገር ጥለው ኮብልለዋል። ይህ፣ ከሌሎቹ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በተለየ፣ ኦህዴድ ከፍተኛ አመራሮቹን ለስደት ሲዳርግ የነበረ ድርጅት ስለመሆኑ ያሳያል። 

ለስደት ከመዳረግ በተጨማሪ፣ ኦህዴድ የቀድሞ አመራሮቹን ለሞት ሲዳርግ የነበረ ድርጅት ነው። የቀድሞ የክልሉ ፕረዘዳንት አቶ አለማየሁ አቶምሳ አሟሟት፣ ከዚያ በፊት አቶ መኮንን ፊጤ፣ ባዩ ጉሩሙ እና አልማየሁ ደሳለኝ የተባሉ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች አሟሟት የሚጠቀስ ነው። ከዚህ አንፃር፣ አቶ ሙክታር ከዲር እና ወ/ሮ አስቴር ማሞ፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ ለሞት፥ ለስደትና ለእስራት ሳይዳረጉ፣ ፍቃደኝነታቸውን ተጠይቀው ከኃላፊነት መውረዳቸው በራሱ ትልቅ ነገር ነው። 

ከላይ እንደተጠቀሰው፣ የድርጅቱን አመራሮች ከማሳደድ ወደ ማውረድ መምጣቱ በራሱ እንደ ለውጥ ሊጠቀስ ይችላል። ነገር ግን፣ ኢህዴድ/ኢህአዴግ የሚያስፈልገው “ተሃድሶ” ከዚህ ፍፁም የተለየ ነው። አቶ ሰለሞን ስዩም የተባሉ ኦህዴድ/ኢህአዴግን በቅርብ የሚከታተሉ የፖለቲካ ተንታኝ ስለ ድርጅቱ ለ“Addis Standard” መፅሔት ከሰጡት አስተያየት ውስጥ የሚከተለው የድርጅቱ ተሃድሶ ከየት መጀመር እንዳለበት በግልፅ ይጠቁማል፡- 

“OPDO has no Intellectual, Historical and Moral background to compete neck and neck with [the rest of the parties within the ruling EPRDF] The current Oromo protest have, more than any time in the past, wide opened the doors for sincere reflections on the legitimacy and relevance of the party. …OPDO has to struggle to assert its legitimacy and relevance back from square one.”

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት ኦህዴድ/ኢህአዴግ የኦሮሞን ሕዝብ መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቂ የዕውቀት፣ የታሪክና የሞራል መሰረት የለውም። በእርግጥ የሕዝቡን መብትና ነፃነት የሚነፍጉ አመራሮች ላይ የተገቢነትና አግባብነት ጥያቄ መነሳቱ አያጠራጥርም። ስለዚህ፣ ድርጅቱ የሚያስፈልገው በውስጡ ያሉትን አመራሮች መቀያየር አይደለም። 

በፌደራል እና በክልል ደረጃ የኦሮሞን ሕዝብ ጥያቄ፣ ታሪክና እሴት ተገንዝበው መብቱንና ፍትሃዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የሚያስችል ብቃት ባላቸው፣ በመንግስታዊ ሥርዓቱ ውስጥ የሚገባውን ስልጣንና የአመራርነት ሚና መወጣት በሚችሉ የሕዝብ ልጆች መተካት ያስፈልጋል። ይህንን ኦህዴድ/ኢህአዴግ በሩብ ምዕተ አመታት ግዜ ውስጥ እንኳን ማሳካት አልቻለም። ከዚያ ይልቅ፣ የኦሮሞ ሕዝብ መብትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ሲሟገቱ የነበሩትን ወጣቶችና የተቃዋሚአመራሮች ለእስርና ስደት ሲዳርግ ነበር። 

ኦህዴድ ለኦሮሞ ሕዝብ ሊያደርግ የሚችለው ትልቅ ውለታ እነዚህ በእስር ቤት ያሉ የሕዝብ ልጆች እንዲለቀቁ፣ በስደት ያሉትም ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ ነው። የድርጅቱ ያሉበትን ችግሮች አውቆ ዛሬ እየወሰደ ያለውን የማስተካከያ እርምጃ እንዲጀምር የማንቂያ ደውል ያሰሙትን ባለውለታዎቹን “ሽብር፥ ሁከትና ብጥብጥ አስነስታችኋል” በሚል ሲወነጅል ከርሟል። አሁን ላይ ችግሮቹን እንዲረዳ ለማድረግ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ለሞትና ጉዳት፣ ሺህዎች ደግሞ ለእስራት ተዳርገዋል። ስለዚህ፣ የፓርቲው “ተሃድሶ” መጀመር ያለበት እነዚህን ወጣቶችና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ከእስርና ከስደት ነፃ እንዲወጡ በማድረግ መሆን አለበት።

በአጠቃላይ፣ የኦህዴድ/ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮቹን እንደ ከዚህ ቀደም ለሞትና ስደት ከመዳረግ ይልቅ በፍቃደኝነት ከኃላፊነት ማንሳቱ መልካም ነው። ድርጅቱ የሚያስፈልገው ተሃድሶ ግን በውስጡ ያሉትን አመራሮች መቀያየር አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ የኦሮሞ ሕዝብ በራሱ ምርጫና ፍላጎት – በነፃነት እንዲቀሳቀስ መፍቀድና ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ነው። ወደፊት በሕይወትና ንብረት ላይ ጥፋት ሳይደርስ ፓርቲው ያሉበትን ችግሮች ቀድሞ እንዲያውቅ፣ ህዝቡ ብሶትና ቅሬታውን በነፃነት እንዲገልፅ መፍቀድ አለበት። በተመሳሳይ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በክልሉ ውስጥ በነፃነት እንዲቀሳቀሱ መፍቀድና አስፋላጊውን ድጋፍ ማድረግ አለበት። የተሃድሶ ስም “ዴሞክራሲ” ይባላል። ያኔ የኦሮሞ ሕዝብ መብቱንና ነፃነቱን ተጠቅሞ የሚያደርገውን አብረን እናያለን።