በመንግስት ትዕዛዝ እንጂ በፌስቡክ መረጃ የሞተ ሰው የለም!

አንድ መሪ በየትኛውም መድረክ ቢሆን የሚናገረው ነገር ሀገርና ሕዝብን ወክሎ እንደመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል። ከዚህ ቀደም፣ ጠ/ሚ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ በሀገሪቱ የተከሰተውን ግጭትና አለመረጋጋት አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ አዝዣለሁ” የሚለውን ዓ.ነገር በመናገር ብቻ እንዴት በህዝብ ላይ ጦርነት እንደ አወጁ ተመልክተናል። አሁንም ጠ/ሚኒስትሩ በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር ሌላ ታሪካዊ ስህተት ፈፅመዋል። በዚህ ፅሁፍ ይህን ንግግር መሰረት በማድረግ በውስጡ የሚንፀባረቀውን የተዛባ አመለካከት እና በዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ዘንድ የሚሰጠውን ትርጉምና ፋይዳ በዝርዝር እንመለከታለን።

“Social media offered a platform to enhance popular participation, but misinformation could go viral and mislead, especially the youth. It had empowered extremists to exploit genuine concerns and spread messages of hate.” H.E. Mr Hailemariam Dessalegn, General assembly of the United Nations, General Debate of the 71st Session.

በእርግጥ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ እኔ በምኖርበትና ሌሎች አመፅና ተቃውሞ በተቀሰቀሰባቸው አከባቢዎች ማህበራዊ ሚዲያዎች በመንግስት ተዘግተዋል። ከጠ/ሚኒስትሩ ንግግር መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አሁን መንግስት በውጪ የሚኖሩና በማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት በፖለቲካው ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ኢትዮጲያኖችን ለመቆጣጠር ፍላጎት እያሳየ ነው።

በቅድሚያ በጠ/ሚኒስትሩ ንግግር ውስጥ ከማህበራዊ ሚዲያዎች ጋር በተያያዘ ያለውን የተዛባ አመለካከት በግልፅ የሚጠቁሙ ሁለት ቃላቶች አሉ። እነሱም፡- “misinformation” እና “mislead” የሚሉት ናቸው። በዚህ መሰረት፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚለቀቁት “የተሳሳቱ መረጃዎች” እና “ወጣቶችን ለስህተት የሚዳርጉ” ናቸው።

ስለዚህ፣ እንደ ጠ/ሚ ኃ/ማሪያም አነጋገር መንግስት፤ አንደኛ፡- “በማህበራዊ ሚዲያዎች በሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች ላይ ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል”፤ ሁለተኛ፡- “በማህበራዊ ሚዲያዎች የተሳሳተ መረጃ በሚለቁ ሰዎች ላይ ክትትል ሊያደርግ ይገባል”። ይህ አቋም “የፍፁማዊነት/አለመሳሳት” (infallibility) አመለካከት ውጤት ነው።

የአምባገነንነት ስረ-መሰረቱ ራስን ፍፁም ትክክል (infallible) አድርጎ ማየት ነው። “በሁሉም ነገር ላይ ‘እኛ እናቅላችኋለን’ ማለታቸውና ስለ ሕዝቡ ግን ምንም አለማወቃቸው” የአምባገነኖች መለያ ባህሪ ነው። በተመሣሣይ፣ ጠ/ሚ ኃ/ማሪያም በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ያደረጉት ንግግር የራሳቸውንና የመንግስታቸውን አምባገነንነት ከማንፀባረቅ የዘለለ ትርጉምና ፋይዳ የለውም።የኢህአዴግ መንግስት በማህበራዊ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ መረጃዎችን “ትክክለኝነት” እና “አግባብነት” ለመከታተልና ለመቆጣጠር ያለውን ፍላጎት በግልፅ አንፀባርቀዋል።

በመቀጠል የጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ንግግር ከመረጃና ሃሳብን በነፃነት ከመግለፅ መብት አንፃር ያለበትን መሰረታዊ ችግር የ“John Stuart Mill” – “On Liberty” መፅሃፍን ዋቢ በማድረግ በዝርዝር እንመለከታለን። ይህ እንግሊዛዊ ፈላስፋ ከሰው ልጅ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ጋር በተያያዘ የሚከተሉትን መሰረታዊ መርሆች ያስቀምጣል፤ አንደኛ፡-“የተሳሳተ መረጃን መከልከል በራሱ ስህተት ነው”፣ ሁለተኛ፡- “ሰው በተሳሳተ መረጃ አይመራም።” የጠ/ሚኒስትሩን ንግግር መርሆች አንፃር እንመልከት፡-

1ኛ፡- የተሳሳተ መረጃን መከልከል በራሱ ስህተት ነው
አንድ ሰው በራሱ “ትክክል ነው” ብሎ ያመነበትን ሃሳብ በነፃነት እንዳይገልፅ መከልከል ፍፁም ስህተት ነው። ከሁሉም ሰዎች በተቃራኒ አንድ ሰው ብቻውን የተለየ ወይም የተሳሳተ አቋም የሚያራምድ ከሆነና ሃሳቡን እንዳይገልፅ የሚከለከል ከሆነ፣ ከግለሰቡ በላይ ተጎጂው አመለካከቱን እንዳገልፅ የከለከለው አካል ነው። ነገር ግን፣ “John Stuart Mill”፣ አንድ ግለሰብ ሃሳቡን የመግለፅ ነፃነቱን ሲገፈፍ በከለከሉት ሰዎች ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ እንደሚከተለው ይገልፀዋል፡-

“If all mankind minus one were of one opinion, and only one person were of the contrary opinion, mankind would be no more justified in silencing that one person, than he, if he had the power, would be justified in silencing mankind. …the peculiar evil of silencing the expression of an opinion is, that it is robbing the human race; those who dissent from the opinion, still more than those who hold it. If the opinion is right, they are deprived of the opportunity of exchanging error for truth: if wrong, they lose, what is almost as great a benefit, the clearer perception and livelier impression of truth, produced by its collision with error.” John Stuart Mill, On Liberty, Page 13.

ለምሳሌ ከዚህ ቀድም ለጠ/ሚ ኃ/ማሪያም “ሁሉንም የፀጥታ ኃይሎች የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ አዝዣለሁ” በማለት በሰጡት መግለጫ ላይ ተመስርቼ “በሕዝብ ላይ ጦርነት አውጀዋል” ብዬ ግልፅ ደብዳቤ ፅፌያለሁ። ፅሁፉ በማህበራዊ ድረገፆች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል። እኔ ያስቀመትኩት የመከራከሪያ ሃሳብ “ስህተት” ከሆነ ጠ/ሚኒስትሩ “የሕግ የበላይነትን ለማስከበር” የወሰዱትን እርምጃ “ትክክለኝነት” ያረጋግጣል። የእኔ ሃሳብ “ትክክል” ከሆነ ጠ/ሚኒስትሩ “ለሁሉንም የፀጥታ ኃይሎች የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ” የሰጡት ትዕዛዝ “ተጠያቂነትና ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ተግባራዊ እንዳይደረግ” ለቅድመ ጥንቃቄ ያግዛል።

የእኔ ፅሁፍ ትክክልም ሆነ ስህተት ጠቀሜታው ለጠ/ሚኒስትሩ ነው። ነገር ግን፣ ፅሁፉ በማኅበራዊ ሚዲያዎች እንዳይወጣ ከተከለከለ ግን የውሳኔው ትክክለኝነት ወይም ስህተትነት የሚታወቀው በጠ/ሚኒስትሩ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ የፍፁማዊነት ወይም አለመሳሳት (infallibility) አመለካከት ነው።

2ኛ፡- ሰው በተሳሳተ መረጃ አይመራም
ከላይ በአንደኛ ላይ የተጠቀሰው “በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁት የተሳሳቱ መረጃዎች (misinformation) ናቸው” የሚል ነበር። በጠ/ሚ ንግግር ውስጥ ታሳቢ የተደረገው ሁለተኛው ችግር “በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ የተሳሳቱ መረጃዎች ወጣቶችን ወደ ተሳሳቱ ተግባራት (ድርጊቶች) ይመራሉ (mislead)” የሚለው ነው። ስለዚህ የመጀመሪያው ስለ መረጃዎቹ “ትክክለኝነት” (truth) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ስለ መረጃዎቹ ጠቀሜታ (utility) ነው። ነገር ግን፣ እንደ “John Stuart Mill” አገላለፅ፣ በመረጃ መመራት በራሱ አመለካከት ስለሆነ በተሳሳተ መረጃ መመራት የመረጃውን ትክክለኝነት ከማረጋገጥ ጋር ተነጥሎ ሊታይ አይችልም ይለናል፡-

“…there can be nothing wrong, it is thought, in restraining bad men, and prohibiting what only such men would wish to practice. This mode of thinking makes the justification of restraints on discussion not a question of the truth of doctrines, but of their usefulness; …[But] the usefulness of an opinion is itself matter of opinion: as disputable, as open to discussion, and requiring discussion as much as the opinion itself. …
The truth of an opinion is part of its utility. …Those who are on the side of received opinions never fail to take all possible advantage of this plea; you do not find them handling the question of utility as if it could be completely abstracted from that of truth: on the contrary, it is, above all, because their doctrine is “the truth,” that the knowledge or the belief of it is held to be so indispensable.” John Stuart Mill, On Liberty, Page 18.

ከላይ እንደተጠቀሰው፣ ወጣቶች የመረጃውን ትክክለኝነት ሳያረጋግጡ የተሰጣቸውን የተሳሳተ መረጃ ዝም ብለው ተቀብለው ተግባራዊ አያደርጉም። በማህበራዊ ሚዲያ በተለቀቀ መረጃ መመራት የመረጃውን ትክክለኝነት ከማረጋገጥ የተቆራኘ ነው። ለምሳሌ፣ የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች፣ የሀገሪቱ ጠ/ሚኒስትር እና የክልሉ ፕረዘዳንት በኢብኮ ያስተላለፉትን መረጃ በመተው፣ ከአሜሪካ አቶ ጀዋር መሃመድ በፌስቡክ ያስተላለፈውን መረጃ ተግባራዊ የሚያደርጉት፣ ካለው ነባራዊ እውነታ አንፃር የአቶ ጀዋር መረጃ ከጠ/ሚኒስትሩ ሆነ ከፕረዘዳንቱ በተሻለ ትክክለኛ እና ጠቃሚ ስለሆነ ነው። በአጠቃላይ፣ ወጣቶች ከኢብኮ (EBC) ይልቅ “OMN” እና “ESAT”ን፣ ከ“FANA” ይልቅ “VOA”ን፣ ከመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ይልቅ የጀዋር መሃመድ የፌስቡክ ገፅን እንደ ዋና የመረጃ ምንጭ የመጠቀማቸው ሚስጥር የመረጃው ትክክለኝነት ነው።

ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ በንግግራቸው፤ “አክራሪ ኃይሎች በማህበራዊ ሚዲያዎች የተሳሳተ መረጃ በማቅረብ ተገቢ ጥያቄ ያነሱ ወጣቶችን ለራሳቸው አጀንዳ ማስፈፀሚያ ይጠቀሙባቸዋል” በማለት ስጋታቸውን ገልፀዋል። ነገር ግን፣ ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጨውን መረጃ ተቀብለው ተግባራዊ የሚያደርጉት የአክራሪ ኃይሎች መጠቀሚያ ሆነው ሳይሆን መረጃው ትክክል እና መልዕክቱም አግባብ ስለሆነ ነው። አሁንም፣ የጠ/ሚኒስትሩ ንግግር፣ “መንግስት ለወጣቶች ትክክል የሆነውን መረጃ እና ተግባር ከራሳቸው ከወጣቶቹ በላይ ያውቃል” በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። ይኼ ሁለተኛው የፍፁማዊነት ወይም አለመሳሳት (infallibility) አመለካከት ማሳያ ነው።

3ኛ፡- የመንግስት ትዕዛዝ እንጂ የፌስቡክ መረጃ ሰው አይገድልም
በ“John Stuart Mill” ትንታኔ መሰረት ከላይ 1ኛ እና 2ኛ ላይ በዝርዝር ለማሳየት እንደተሞከረው፣ ወጣቶች በፌስቡክ የቀረበላቸውን የሰለማዊ ሰልፍ ጥሪ ተቀብለው ወደ አደባባይ የሚወጡት ከመረጃው ትክክለኝነት በተጨማሪ በመረጃው አግባብነትና ጠቃሚነት ላይ ሙሉ እምነት ስላላቸው ነው። ምክንያቱም፣ እንያንዳንዱ ወጣት ተግባራዊ የሚያደርገውን መረጃ ትክክለኝነት የሚመዝንበት የራሱ ምክንያታዊ አስተሳሰብ (rational thinking)፣ ተግባሩን የሚመራበት የሞራል እሴት (Moral value) አለው።

ጠ/ሚኒስትሩ “በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት በሚቀርቡ የተሳሳቱ መረጃዎች ወጣቶች የአክራሪ ኃይሎች መጠቀሚያ ይሆናሉ” የሚለው ስጋት እውን ሊሆን የሚችለው ወጣቶቹ ምክንያታዊ አስተሳሰባቸውን እና የሞራል ስብዕናቸውን ሲያጡ ብቻ ነው። ሰው የቀረበለትን መረጃ ትክክለኝነት እና ስህተትነት ሳያጣራ፣ ከሞራል እሳቤ ውጪ የሆኑ ተግባራትን የሚፈፅመው በመንግስት ትዕዛዝ እንጂ በማህበራዊ ሚዲያዎች በሚለቀቁ መረጃዎች አይደለም።

ግልፅ ደብዳቤ ለጠ/ሚ ኃ/ማሪያም፡ “በሕዝብ ላይ ጦርነት አውጀዋል” በሚለው ፅሁፍ በዝርዝር እንደገለፅኩት፣ የጠ/ሚኒስትሩ ስጋት እውን ሊሆን የሚችለው የሚከተሉት ሦስት መስፈርቶች ሲሟሉ ነው፤ አንደኛ፡- በዕዝ ሰንሰለት (Chain of commands) የታሰሩ ከሆነ፣ ሁለተኛ፡- በተግባራቸው ላይ የማዘዝ ስልጣን (Commanding Power) ከሌላቸው፣ እና ሦስተኛ፡- ስለሚፈፅሙት ተግባር ተገቢነት የማሰብ ግዴታ (Justifications) ከሌለባቸው ነው። 

እነዚህን መስፈርቶች የሚያሟሉት ደግሞ የመንግስት ወታደሮች፣ ፖለሶች ወይም የደህንነት ሰራተኞች ብቻ ናቸው። የጦር ኃይሎች አዛዥ እና ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች ተግባርና እንቅስቃሴ የሚቆጣጠሩት ደግሞ ጠ/ሚ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ናቸው። በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጥፋት እየደረሰ ያለው በባለስልጣናት ትዕዛዝ እንጂ በማህበራዊ ሚዲያዎች በሚለቀቁ መረጃዎች አይደለም። በአጠቃላይ፣ የመንግስት ትዕዛዝ እንጂ የፌስቡክ መረጃ ሰው አይገድልም።

ማጠቃለያ
ከስህተቶች ሁሉ ትልቁ ስህተት፣ የዜጎችን አመለካከት “ስህተት” ነው ብሎ ማሰብ ነው። የአምባገነንነት የመጨረሻ ደረጃ ደግሞ፣ የሕዝብ አመፅና ተቃውሞ በመንግስት ስህተት ሳይሆን በፀረ-ሰላም ኃይሎች አነሳሽነት እንደተፈጠረ ማሰብ ነው። ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ፣ በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ፣ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የቀጥታ ስርጭት ላይ፣ የራሳቸውንና የሚመሩት መንግስት የተዛባ አቋምና አመለካከት በይፋ ገልፀዋል። በዚህም፣ የኢህአዴግ መንግስት የተለየ አመለካከት ያላቸውን ወገኖች ከሀገሪቱ በማጥፋቱ የራሱን አቋም ትክክለኝነት እንኳን መለየት እንደተሳነው በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ አረጋግጠዋል። በዚህ መሰረት ጠ/ሚኒስትሩ ለዓለም አቀፍ ማህብረሰብ የመንግስታቸውን “አምባገነንነት” መስክረዋል።

ሕዝብ በመንግስት ላይ አመፅና ተቃውሞ የወጣበት ዋና ምክንያት ኢህአዴግ ከእሱ የተለየ አቋምና አመለካከት ያላቸውን አካላት በሙሉ ከሀገር ውስጥ ጠራርጎ በማጥፋቱ እንደሆነ ግልፅ ነው። የኢህአዴግ መንግስት ከእሱ የተለየ አቋምና አመለካካት አላቸው ያላቸውን የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ ጋዜጠኞች፣ ዩኒቨርሲቲ መምህራን፣…ወዘተ ከሀገር ጠራርጎ በማባረሩ፣ ይኼው ዛሬ ላይ የሕዝቡን ጥያቄና የለውጥ ፍላጎት መስማትና ማየት ተስኖታል። ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ፣ በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ ፊት፣ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የቀጥታ ስርጭት ላይ ይህን የመንግስታቸውን አባዜ በግልፅ አንፀባርቀዋል። የጠ/ሚኒስትሩ ንግግር በዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ዘንድ የሚሰጠው ትርጉምና አንድምታ እንደሚከተለው ሊገለፅ ይችላል፡-

“በኢትዮጲያ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን፣ ነፃ-ፕሬስ፣ የሲቭልና ሙያ ማህበራትን፣ እንዲሁም ለሀገርና ሕዝብ የሚቆረቆሩ ታዋቂ ግለሰቦችና ምሁራንን ከሀገሪቱ ጠራርጌ አጥፍቼ ሳበቃ፣ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሕዝቡን ችግርና ጥያቄ እያጋለጡ አስቸገሩኝ። በሀገር ውስጥ እነዚህን ሚዲያዎች በመዝጋት መቆጣጠር ስችል፣ በውጪ ሀገር ያሉ ትውልደ ኢትዮጲያኖች አስቸገሩኝ። ስለዚህ፣ እባካችሁ እነዚህን ሰዎች አሳልፋችሁ ስጡኝና ማዕከላዊ እስር ቤት አስገብቼ ወፌ-ላላ ልግረፋቸው?”

One thought on “በመንግስት ትዕዛዝ እንጂ በፌስቡክ መረጃ የሞተ ሰው የለም!

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡