መሪዎቻችን ስልጣን ላይ ሙጭጭ የሚሉባቸው ሦስት ምክንያቶች

የእኛ ሀገር ባለስልጣናት ከስልጣን መውረድ በጣም ያስፈራቸዋል። ይህ ከሚኒስትር እስከ ቀበሌ ሊቀመንበር ባሉት የስልጣን እርከኖች የሚስተዋል ችግር ነው። በራስ ፍቃድ ስልጣን መልቀቅ ቀርቶ፣ “በስራው ላይ ከፍተኛ የአቅም ማነስ ችግር አለበት” የተባለ ባለስልጣን እንኳን ከስልጣኑ ወርዶ-አይወርድም። 

አንዳንድ ምሳሌዎችን ለመጥቀስ ያህል፤ ከሚኒስትርነት ወረደ የተባለ ባለስልጣን በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ይሆናል፣ ከክልል ወይም ከዩኒቨርሲቲ ፕረዘዳንትነት የወረደ ቀጣይ ሥራው በአንዱ ሀገር የኢትዮጲያ አምባሳደር መሆን ነው፣ የክልል ሴክተር መስሪያ ቤትን መምራት የተሳነው ካቢኔ ወደ ሌላ ሴክተር መስሪያ ቤት ይዛወራል፣ በአንዱ ዞን፥ ወረዳ፥ ከተማ ወይም ቀበሌ በሙስና የተጠረጠረ ወይም የመልካም አስተዳደር ችግር የፈጠረ ካድሬ ወደ ሌላ ዞን፥ ወረዳ፥ ከተማ ወይም ቀበሌ ይዛወራል። ከገዢው ፓርቲ ጋር ፀብ ያላቸው ከሆኑ ግን ያው መጨረሻቸው ወይ እስር ቤት ወይም ስደት መሆኑ እርግጥ ነው። 

በተለይ ደግሞ የኢህአዴግ ባለስልጣናነት እንኳን በራሳቸው ፍቃድ በግድ ተገፍተውም ከስልጣን አይወርዱም። “ከስልጣን መውረድ እንዲህ የሚያስፈራቸው ለምንድነው?” የሚለው ጥያቄ ዘወትር በውስጤ ይመላለስ ነበር። በመጨረሻም ስልጣን ላይ እንዲህ ሙጭጭ የሚሉባቸውን ሦስት መሰረታዊ ምክንያቶችን መለየት ቻልኩ። እነሱም፡- ተፈላጊነት፣ ተጠቃሚነት እና የአመራር ወጥመድ ናቸው። እስኪ እያንዳንዳቸውን በዝርዝር እንመልከት፡- 

1ኛ፡- ተፈላጊነት

የተፈላጊነት ችግር በዋናነት ባለስልጣናቱ ለራሳቸው ከሚሰጡት ግምት ጋር የተያያዘ ነው። አንድ ሰው በየትኛውም የኃላፊነት ደረጃ፤ በዝቅተኛ የኃላፊነት እርከን፣ ያለ ምንም ስልጣን (በተራ ሰራተኝነት) ወይም ስራውን ለቅቆ በራሱ የተሻለ ነገር መስራት እንደሚችል የሚያስብ ከሆነ ከስልጣን መውረዱ የተለየ ስሜት አይፈጥርበትም። በመሆኑም፣ በሌሎች ሰዎች፤ በቤተሰቦቹ፣ በባልደረቦቹና ተገልጋዮቹ ዘንድ ያለው ክብርና ተፈላጊነት የሚቀንስ መስሎ አይሰማውም። ስለዚህ፣ ከስልጣን መውረድን የተሻለ ነገር ለመስራት እንደ ምቹ አጋጣሚ ይወስደዋል። እንዲህ ያለ ስብዕና ያለው ግለሰብ እንኳን ከስልጣን ውረድ ተብሎ ይቅርና፣ ያቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በአለቆቹ ተቀባይነት ስላላገኘ ብቻ ከስልጣን ሊወርድ ይችላል። 

ነገር ግን፣ አብዛኞቹ የሀገራችን ባለስልጣናት ከስልጣን ቢወርዱ በቤተሰቦቻቸው፣ ባልደረቦቻቸው እና በአጠቃላይ በማህብረሰቡ ዘንድ ያላቸው ክብርና ተፈላጊነት የሚቀንስ መስሎ ይሰማቸዋል። በመሆኑም፣ ከስልጣን መውረድን ልክ እንደ ሞት ይፈሩታል። በተለይ የፖለቲካ ተሿሚዎች ስልጣንን ለሕዝብ ጥቅምና አገልግሎት ከማዋል ይልቅ እንደ ክብርና ዝና ስለሚቆጥሩት፣ ከስልጣን ውረዱ ሲባሉ ክብርና ሞገሳቸው ተገፎ “እርቃናችሁን ቁሙ” የተባሉ ይመስል ይሰቀጥጣቸዋል። ስለዚህ አንዴ ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ እዚያ ሙጭጭ….     

2ኛ፡- ተጠቃሚነት

ይህ በዋናነት ከስልጣን ከሚገኙ ጥቅማ-ጥቅሞች ጋር የተያያዘ ነው። አንድ ባለስልጣን ከደሞወዝ በተጨማሪ የወንበር፣ የነዳጅ፣ የሞባይል፣…ወዘተ አበሎች ያገኛል። እንደው በጥቅሉ ለመናገር ያህል፣ ለአንድ ቀን ሥራ የወጣ ኃላፊ ከሦስት ቀን በታች ውሎ-አበል አይታሰብለትም፡፡ በአበል መልክ ከሚያገኘው ያልተገባ ጥቅም በተጨማሪ፣ ሙስና እና ሌሎች ያልተገቡ ጥቅማ-ጥቅሞች እንዳሉ ግልፅ ነው። 

አብዛኞቹ የሀገራችን ባለስልጣናት የእነዚህ ጥቅሞች “ሱሰኛ” ናቸው። ለምሳሌ፣ አብዛኞቹ ባለስልጣናት በዚህ መልኩ በሚያገኙት ጥቅም የልጆቻቸውን የትምህርት ቤት ክፍያ እየከፈሉ ወይም ትልቅ መኖሪያ ቤት እየገነቡ ሊሆን ይችላል። ታዲያ እነዚህን ከስልጣን ውረዱ ሲባሉ በቅድሚያ ወደ አዕምሯቸው የሚመጣው የልጆቻቸው የትምህርት ክፍያ ወይም በጡረታ እንድሜያቸው እንኳን የማይጨርሱት ቤት ነው። ስለዚህ፣ እዚያው ሙጭጭ….    

3ኛ፡- የአመራር ወጥመድ (Leadership Trap)

የዚህን ፅንሰ-ሃሳብ “ኢህአዴግን የጠለፈው የአመራር ወጥመድ” በሚለው ፅኁፍ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥቼበታለሁ። አጠቃላይ ሃሳቡን ለመዳሰስ ያህል፣ ችግሩ “ለምን ወደ አመራርነት መጣሁ?” ከሚለው እሳቤ ጋራ የተያያዘ ነው። ብዙውን ግዜ የሀገራችን ባለስልጣናት “ለምን ወደ ስልጣን እንደመጡ” ሲጠየቁ “ሕዝብን ለማገልገል” እንጂ “ባለስልጣን መሆን ስለፈለኩ” አይሉም። ነገር ግን፣ የመጀመሪያው እሳቤ ያላቸው ባለስልጣናት “በአመራር ወጥመድ” የመጠለፍ ዕድላቸው የሰፋ ነው። 

“ባለስልጣን መሆን ስለፈለኩ” የሚል እሳቤ ያላቸው ባለስልጣናት በሥራቸው ውስጣዊ እርካታ (Internal Satisfaction) ስለሚያገኙ፣ የተሳሳተ ውሳኔ ከወሰኑ ወይም ዝቅተኛ የሆነ አፈፃፀም ካስመዘገቡ በሥራቸው ደስተኛ አይሆኑም። ስለዚህ፣ የበለጠ ስራቸውን በመስራት፣ በዚህም ደንበኞችን/ሕዝብን በማገልገል እርካታ ያገኛሉ። 

“ሕዝብን ለማገልገል” ከራሳቸው ይልቅ ሌሎች ሰዎችን በማስደሰት (External Gratification) የሚያተኩሩ ናቸው። እነዚህ ባለስልጣናት ደስታቸውን በራሳቸው ሳይሆን ከሌሎች ሰዎች እርካታ የሚያገኙ ናቸው። ነገር ግን፣ ዘወትር ለትችትና ነቀፌታ ስለሚጋለጡ በሥራቸው ደስተኛ አይሆኑም። ስለዚህ፣ በቀጣይ ስህተት-አልባ ሥራ ለመስራት (perfectionism) ጥረት ያደርጋሉ። ይህ ደግሞ ጭራሽ ድክመቶቻቸውን ተለይተው እንዳይታወቁ ይጋርዳቸዋል። እንደዚህ ያሉ አመራሮች “የአመራር ወጥመድ” (Leadership Trap) ውስጥ የወደቁ ናቸው። 

በአመራር ወጥመድ ውስጥ የወደቁ ባለስልጣናት መሰረታዊ ችግር ከማህብረሰቡ የሚሰጣቸውን ትችትና አስተያየት ለመቀበል ዝግጁ አለመሆን ነው። በመሆኑም፣ እንደ አምላክ ፍፁም መሆን ይቃጣቸዋል። በዚህ ምክንያት፣ በስህተት ላይ ስህተት እየሰሩ፤ “ተሳስታችኋል” ሲባሉ አይሰሙም፣ “ተሳስተናል” ብለው አያምኑም። በየግዜው ይሳሳታሉ፣ ሲነግሯቸው ስለማይሰሙ ስህተታቸውን መልሰው ይሳሳታሉ። በቃ…”ውረዱ” ቢባሉ እንኳን መስሚያቸው ጥጥ ነው። እዚያው ሙጭጭ….