አመፅና ተቃውሞ በራሱ ልማትና ዴሞክራሲ ነው

ባሳለፍነው የ2008 ዓ፣ም የታየው ህዝባዊ ተቃውሞና አመፅ በአመቱ የመጨረሻ ወር የመጀመሪያ ሳምንት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር ይታወሳል። በአዲሱ አመትም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ግጭትና አለመረጋጋት እንደቀጠለ ነው። ነገር ግን፣ በ2008 ሐምሌና ነሃሴ ላይ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የነበረው አይነት እንቅስቃሴ አሁንም አለ ለማለት አያስደፍርም። 

ይህን በማስመልከት አንዳንድ የገዢው ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ሀገሪቷን ሊበታትናት ተቃርቦ የነበረው የፖለቲካ ሲናሚ በፌደራሊዝም ሥርዓቱ አማካኝነት መክሸፉን እየተናገሩ ይገኛሉ። እንዲህ ያለ አስተያያት የቁንፅል ግንዛቤ ውጤት ነው። በእርግጥ አብዛኞቹ የገዢው ፓርቲ አባል/ደጋፊ የሆኑ ልሂቃን ያለባቸው መሰረታዊ ችግር ይሄ ነው። አሁን ያሉትን ፖለቲካዊ ኩነቶች በጥልቀት አይመረምሩም፣ ወደፊት ያላቸውን ተፅዕኖ አርቀው አያስተውሉም። 

በ2006 ዓ.ም የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ በአምቦ ከተማ የተነሳው የሕዝብ አመፅና ተቃውሞ፣ እንደገና በ2008 ዓ.ም በአማራና በኦሮሚያ የተነሳው የህዝብ ተቃውሞ፣ በጎጃም ከተቀሰቀሰው የህዝብ አመፅ በጅግጅጋ እስከተደረገው የድጋፍ ሰልፍ፣… በአጠቃላይ የአሁን ሀገሪቷ ላጋጠማት የፖለቲካ አለመረጋጋት መነሻውና መድረሻው አንድ፡- እኩልነት (Equality) ጥያቄ ነው። ትላንት፣ ዛሬም ሆነ ነገ ለዚህ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ መስጠት የተሳናት ኢትዮጲያ መቼና ከየት እንደሚነሳ በማይታወቅ ታላቅ የፖለቲካ ሱናሚ ትመታለች። 

የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር እንዲህ ብለው ነበር፤ “ዓለም በፍትህ አትመራም፣ ‘ዓለም በፍትህ ትመራለች’ የሚሉ ብፁዓን ናቸው፡፡” በእርግጥ አባባሉ በከፊል ትክክል ነው። በሁሉም ዘርፍ ሚዛናዊ ዳኝነት (impartiality) የተረጋገጠበት ስርዓት የለም። በሌላ በኩል፣ በሁሉም ዘርፍ አድሏዊነት (partiality) የሰፈነበት ስርዓት ደግሞ ሊኖር አይችልም። 

ለዚህ ደግሞ ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። አንደኛ፡- “እኩልነት” የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ አንደመሆኑ ይህን የሚፃረር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስተጋብር በዘላቂነት ሊኖር አይችልም። ሁለተኛ፡- የዜጎችን እኩልነት ማረጋገጥ የተሳነው መንግስታዊ ሥርኣት ያለ ምንም ጥርጥር ይወድቃል። እነዚህን ሁለት መሰረታዊ ፅንሰ-ሃሳቦች “Jean-Jacques Rousseau” እንደሚከተለው እንዲህ ይገልፃቸዋል፡-  

“’Man is born good,’ that is, man’s nature really makes him desire only to be treated as one among others, to share equally. This natural love of equality includes love of others as well as love of self, and egoism, loving one’s self at the expense of others, is an unnatural and perverted condition. …The Sovereign must, therefore, treat all its members alike; but, so long as it does this, it remains omnipotent. If it leaves the general for the particular, and treats one man better than another, it ceases to be Sovereign” The Social Contract and Discourses [1761]

ፍትሃዊ ሥርኣት ሁሉም ዜጎች እኩል የሚዳኙበት፥ የዜጎች እኩልነት የተረጋገጠበት ስርዓት ነው። ነገር ግን፣ የቀድሞ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ “ዓለም በፍትህ አትመራም” ሲሉ የዜጎች እኩልነት ሙሉ በሙሉ የተረጋገጠበት መንግስታዊ ሥርዓት ሊኖር እንደማይቻል ይጠቁማል። ከዚህ በተቃራኒ፣ “Jean-Jacques Rousseau” ደግሞ በዜጎች መካከል እኩልነትን ማረጋገጥ የተሳነው መንግስት ህለውናው እንደሚያከትም ይገልፃል። 

እዚህ ጋር ሌላኛውን የፈረንሳይ ፈላስፋ “Montesquieu” መትቀስ ያስፈልጋል። እንደ እሱ አገላለፅ፤ “in a republic the principle of action is virtue, which, psychologically equates with love of equality” በዚህ መሠረት፣ ዴሞክራሲ ማለት የዜጎች እኩልነት የተረጋገጠበት ስርዓት ነው።

በተመሣሣይ፣ ልማት ማለት በማያቋርጥ እድገትና መሻሻል አማካኝነት የዜጎችን ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው። ስለዚህ፣ ልማት በራሱ የዜጎችን እኩልነት ማረጋገጥ ነው። ነገር ግን፣ ሙሉ በሙሉ የበለፀገ ወይም ምንም ልማት የሌለበት ሀገርና ህዝብ ሊኖር አይችልም። ከዚያ ይልቅ፣ የልማትም ልክ እንደ ዴሞክራሲ ሁሉ አንፃራዊ እና በማያቋርጥ ለውጥና መሻሻል የሚረጋገጥ ነው። 

በዚህ መሰረት፣ አንደኛ፡- እኩልነት (Equality) ሙሉ በሙሉ የተረጋገጠበት ወይም ያልተረጋገጠበት ሥርዓት ሊኖር እንደማይችል፣ ሁለተኛ፡- ልማትና ዴሞክራሲ አንፃራዊ እንደመሆናቸው፣ በአንድ ግዜ ወይም በድንገተኛ አብዮታዊ ለውጥ ሳይሆን በማያቋርጥ ለውጥና መሻሻል እንደሚመጡ መገንዘብ ይቻላል። ስለዚህ፣ ልማትና ዴሞክራሲ ማለት በእውን ያለውን ሥርዓት፣ ደንብና ልማድ መለወጥና ማሻሻል ነው። ይህን እንግሊዛዊው “John Stuart Mill” እንዲህ ሲል ይገልፀዋል፡-

“The despotism of custom is everywhere the standing hindrance to human advancement, being in unceasing antagonism to that disposition to aim at something better than customary, which is called, according to circumstances, the spirit of liberty, or that of progress or improvement.” John Stuart Mill, On Liberty, Page-57

ልማትና ዴሞክራሲ ማለት የዜጎችን እኩልነት ለማረጋገጥ የሚደረግ የማያቋርጥ ለውጥና መሻሻል ነው። ነገር ግን፣ ሁለቱም በአንድ ግዜ ወይም በአብዮታዊ ለውጥ እውን ሊሆኑ አይችሉም። ከዚህ አንፃር፣ ደርግና ኢህአዴግ ሁለቱም የአብዮታዊ የለውጥ ኃይሎች ናቸው። ደርግ በ1966ቱ አብዮት ዘውዳዊ አገዛዝን ከስልጣን በማስወገድ የመሬት ለአራሹ አዋጅ አውጥቷል። በዚህም፣ ከመሬት ባለቤትነት ጋር በተያያዘ የዜጎችን እኩልነት አረጋግጧል። በመቀጠል ሁሉም ዜጎች እኩል የሚዳኙበት ፍትሃዊ ሥርኣትን ግን መዘርጋት ተስኖታል። 

ደርግ የሕግ-የበላይነትን በማስፈን የዜጎች እኩልነት ማረጋገጥ ስለ ተሳነው በኢህአዴግ በኃይል ከስልጣን ወረደ። ወደ ስልጣን የመጣው የኢህአዴግ መንግስት የመጀመሪያ ተግባሩ የደርግ መንግስት የተሳነውን የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበት ስርዓት መዘርጋት ነበር። በዚህም፣ የኢፊዴሪ ሕገ-መንግስትና የፌደራላዊ መንግስታዊ ሥርዓትን ዘረጋ።  

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ ልማትና ዴሞክራሲ ማለት በማያቋርጥ የለውጥና መሻሻል ሂደት ውስጥ የዜጎችን ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፡- እኩልነትን ማረጋገጥ ነው። ደርግ ወደ ስልጣን እንደመጣ በመሬት ለአራሹ አዋጅ ከመሬት ባለቤትነት አንፃር የዜጎችን እኩልነት ያረጋገጠ ሲሆን የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ግን ተስኖት ነበር። የሕግ የበላይነት ከማረጋገጥ ይልቅ የሶሻሊስት ዕዝ-ኢኮኖሚን ተግባራዊ በማድረግ በመሬት ለአራሹ ያመጣውን ለውጥ መልሶ መናድ ጀመረ። 

በተመሣሣይ፣ የኢህአዴግ መንግስት በሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱ አማካኝነት የሕግ የበላይነትን በማስፈን ረገድ ያመጣውን ለውጥና መሻሻል እየቆየ ሲሄድ በራሱ መልሶ መሸርሸር ጀመረ። በሕገ-መንግስቱ የተከበሩ መብቶችና ነፃነቶችን የሚፃረሩ እንደ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ፣ የሚዲያና የመረጃ ነፃነት አዋጅ፣ የበጎ አድራጎት ማህበራት ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የኮምፒውተር ነክ ወንጀሎች አዋጅ፣ …ወዘተ በማውጣት ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን በራሱ መልሶ መናድ ጀመረ። 

ለሕዝብ አመፅና ተቃውሞ መሰረታዊ መንስዔው የለውጥና መሻሻል መቋረጥ ነው። አሁን በሀገራችን እየታየ ያለው ግጭትና አለመረጋጋት በሌላ ምክንያት ሳይሆን በኢህአዴግ መንግስት በነበረበት መቆም ምክንያት የተከሰተ ነው። በእርግጥ ለውጥ ተፈጥሯዊ ሂደት ነው። ይህን ተፈጥሯዊ ሂደት ለመግታት መሞከር ራስን ለውድቀት ከመጋበዝ የዘለለ ፋይዳ የለውም። የኢህአዴግ መንግስት ልክ እንደ ደርግ መንግስት በራሱ ላይ ውድቀትን መጋበዝ ከጀመረ ቢያንስ አስር አመት ሆኖታል። 

በአጠቃላይ፣ የህዝብ አመፅና ተቃውሞ በራሱ የለውጥና መሻሻል፣ የልማትና ዴሞክራሲ ጥያቄ ነው፡፡ ስለዚህ፣ አመፅና ተቃውሞ በራሱ ልማትና ዴሞክራሲ ነው፡፡ እንደ ደርግና ኢህአዴግ ከአንድ ግዜ ለውጥና መሻሻል በኋላ ለቀጣይ ለውጥና መሻሻል እንቅፋት የሚሆኑ መንግስታት በባህሪያቸው ፀረ-ልማት እና ፀረ-ዴሞክራሲ ናቸው፡፡