የፍርሃት ቆፈን በውይይት ይፍታታል

“ተስፋና ፍርሃት በእስር ቤት” በሚለው ፅሁፍ ላይ በዝርዝር ለመግለፅ እንደሞከርኩት፣ እስር ቤት ነገን ተስፋ በማድረግ ዛሬን በፍርሃት የሚኖርበት ቦታ ነው። ነገር ግን፣ ከጦላይ ከወጣሁ በኋላ በመጀመሪያ የታዘብኩት ነገር ከእስር ቤት ውጪ ያለው ሕይወት በተመሣሣይ የፍርሃት ድባብ ውስጥ መሆኑን ነው። በዚህ ፅሁፍ ተስፋና ፍርሃት የሕይወት አካል መሆናቸውን በመዳሰስ፣ በተለይ በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ የሰፈነው የፍርሃት ድባብ ለማስወገድ ከየት መጀመር እንዳለብን ለመጠቆም እሞክራለሁ።

በመሰረቱ ሰው ያለ ተስፋ መኖር አይችልም። እያንዳንዱ እንቅስቃሴ የተሻለ ሕይወት የመኖር ተስፋን ለማለምለም ያለመ ነው። በተመሣሣይ የሰው-ልጅ ከፍርሃት ነፃ ሆኖ መንቀሳቀስ አይቻለውም። ምክንያቱም ተስፋ እስካለ ድረስ እሱን የማጣት ስጋት ሁሌም አብሮት አለና። ሕይወት የተሻለ ሕይወት የመኖር ተስፋችንን ለማለምለም በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የተሞላች ናት።

የእኛን ተስፋ ለማለምለም የምናደርገው ማንኛውም እንቅስቃሴ የሌሎችን ተስፋ ማቀጨጭ የለበትም። የእኛ ተስፋ በሌሎች ላይ ፍርሃት መፍጠር የለበትም፤ እኛም በፍርሃት የሌሎችን ተስፋ ማጨለም የለብንም። ይህ “የሌሎችን መብት በማይነካ መልኩ በራስ ምርጫና ፍላጎት መሠረት መንቀሳቀስ መቻል” በሚለው መሰረታዊ የነፃነት መርህ ላይ የተመሰረተ ነው። ይሁን እንጂ፣ በራሳችንም ሆነ በሌሎች ሕይወት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሌለው ተግባራዊ እንቅስቃሴን ለማድረግ መፍራት የለብንም።

አሁን በሀገራችን ባለው ነባራዊ እውነታ ዜጎች የሌሎችን መብትና ነፃነት በማይነካ መልኩ ለመንቀሳቀስ እንኳን ይፈራሉ። ዜጎች ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት መግለፅ አይችሉም። በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ያላቸውን የተለየ ሃሳብና አስተያየት በግልፅ ከማንፀባረቅ በሚያግድ የፍርሃት ቆፈን ውስጥ ናቸው። ይህ ደግሞ በግልና የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ነፃ ውይይት እንዳያደርጉ፣ በዚህም የጋራ የሆነ ግንዛቤ እንዳይኖራቸው አንቅፋት ሆኗል። በዚህ ምክንያት በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል የአለመተማመን መንፈስ ሰፍኗል።

የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ የአብዛኞቻችንን ተስፋ የሚያጨልምና ሁላችንንም በፍርሃት ቆፈን ውስጥ የሚከት ነው። በግልና በጋራ የምናደርገው እንቀስቃሴ በሙሉ በፍርሃት የተሞላ ነው። ምክንያቱም በመካከላችን መተማመን የለም። አለመተማመን በሰፈነበት ፍርሃት ይነግሳል። በመንግስትና በሕዝብ መካከል ያለው የመተማመን መንፈስ ተሟጥጦ አልቋል። ሕዝብ መንግስትን፣ መንግስት ደግሞ ሕዝብን አያምንም።

ዜጎች ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት የሚገልፁበት ዕድል ባለመኖሩ ተስፋና ፍርሃታቸውን አይጋሩም። በዚህ ምክንያት ዜጎች እርስ-በእርስ አይተዋወቁም፤ ስለማይተዋወቁ አይተማመኑም፤ ስለማይተማመኑ አይነጋገሩም፤ ስለማይነጋገሩ አይተዋወቁም። የነፃነት እጦት ፍርሃት ውስጥ ከትቶናል፤ ፍርሃት በተራው ነፃነት አሳጥቶናል።

ፍርሃት የፈጠረውን ችግር መልሶ በፍርሃት መፍታት አይቻልም። እርስ-በእርስ ከመፈራራት ይልቅ መተማመን አለብን። እርስ-በእርስ ለመተማመን በጋራ ጉዳዮቻችን ላይ በግልፅ መነጋገር ይኖርብናል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ሃሳብና አስተያታቸውን በነፃነት የሚገልፁበት መድረክ ሊኖር ይገባል። በዚህ መልኩ የጋራ ግንዛቤና መግባባት ይፈጠራል፤ ለጋራ ችግሮቻችን የጋራ መፍትሄ ይሰጣል። ይህ ሲሆን አሁን ላይ የቀፈደደን የፍርሃት ቆፈን በነፃነት ሙቀት ይፍታታል።

ለዚህ ደግሞ በጦላይ በነበሩት እስረኞች/ሰልጣኞች እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት መካከል የነበረው ግንኙነት እንደ ጥሩ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል። በእርግጥ መጀመሪያ ላይ ፖሊሶቹ ከእኛ ጋር መነጋገርና መግባባት ቀርቶ ፊት-ለፊት ለመተያየት እንኳን ፍላጎት አልነበራቸውም። ሆኖም ግን፣ የአብሮነት ቆይታችን እየቀጠለ በሄደ ቁጥር ቀስ-በቀስ መነጋገርና መግባባት እየተፈጠረ መሄዱ አልቀረም። በሰላምታ የጀመረ መግባባት ቀስ-በቀስ እየጎለበተ ሄዶ የወደፊት ተስፋና ፍርሃትን ወደ መጋራት ይደርሳል።

በዚህ መልኩ እስረኞች/ሰልጣኞች እና የፌደራል ፖሊሶቹ እርስ-በእርስ ሲነጋገሩ እየተዋወቁ፤ ሲተዋወቁ እየተማመኑ፤ እርስ-በእርስ ሲተማመኑ ደግሞ መተዛዘን ጀምረዋል። መጀመሪያ ቀን ወደ ጦላይ ስንገባ “መጣህልኝ!” እያሉ በስድብና በዛቻ የተቀበሉን ፖሊሶች መጨረሻ ላይ እስከ ግቢው መውጫ በር ድረስ እየተከተሉ “ደህና ግቡ” ብለው ሲሰነባበቱ፣ ከአንዳንዶቹ ጋር ደግሞ “እንደዋወል…!” እያሉ ስልክ ቁጥር ሲቀያየሩ ተመልክቼያለሁ።
እስር ቤት ውስጥ በእስረኞች/ሰልጣኞች መካከል የነበረው የፍርሃትና ያለመተማመን ስሜት በመነጋገርና በመግባባት ቀስ-በቀስ እንደተፈታ ተመልክተናል። በተመሣሣይ በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ ያጠላውን የፍርሃት ድባብ በንግግርና በውይይት በማስወገድ ሀገራዊ መግባባት መፍጠር ይቻላል። ለዚህ ደግሞ በቅድሚያ ዜጎች ሃሳብና አስተያየታቸውን በነፃነት የሚገልፁበት የጋራ መድረክ ሊኖር ይገባል።

One thought on “የፍርሃት ቆፈን በውይይት ይፍታታል

  1. የዚህ “አይደገምም” ትሸርት ነገር “ኢህአዴግ እጅግ አስተዋይና አማካሪ የሆነ የውስጥ ጠላት አለው ማለት ነው”እንድል አስገደደኝ። እንዲህ ብሎ መሆን አለበት ጠላታዊ ምክር የምሰጣቸው፣ “ያለ ጥፋት በርካታ ሰዎችን በየበረሃው አጉርና ከዚያ ስልችት ጥልት ብለው እስር ቤት ከመግባታቸው በፊት ከምጠሉህ የበለጠ እንዲያማርሩህ አድርግና መጨረሻ ላይ በመራርነቱ የማይረሳ ነገር አቅምሳቸው – የአይደገምምን ትሸርት አስገድደህ በማስለበስ!”

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡