ተስፋና ፍርሃት በእስር ቤት

በጦላይ ልክ ከቀኑ 12፡00 ሰዓት ሲሆን ሁሉም እስረኛ/ሰልጣኝ ተጠናቆ በመኝታ ክፍሉ ይገኛል። ከዚያ በኋላ እስከ ንጋቱ 12፡00 ሰዓት ድረስ መተኛት ይቻላል። እኔ ደግሞ በባህሪዬ ከ8 ሰዓት በላይ መተኛት አልወድም። ብዙ ሰዓት ከተኛሁ በዚያው የምሞት ይመስለኛል። ስለዚህ ሁልግዜ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ከእንቅልፌ ነቅቼ በሃሳብ መባዘን ልማዴ ሆኗል። ታዲያ 13X18 ሜትር በሆነው ክፍል ውስጥ ከተኙት 100 ሰዎች ከእየአቅጣጫው የሚሰማውን የማንኮራፋትና ፈስ ድምፅ ለመሸሽ ስል ጆሮዬን ወደ ውጪ እሰደዋለሁ። ይኄኔ ሁለት የብስራት ድምፆች ወደ ጆሮዬ ይመጣሉ። እነዚህ በተስፋ የተሞሉ ድምፆች የቀዩ አውራ ዶሮ እና የምልምል ፖሊሶች ዝማሬ ናቸው። 

ቀዩ አውራ ዶሮ በየእለቱ፣ ትላንት “ነገ” ስንለው የነበረው አዲስ ቀን ዛሬ ሊሆን መቃረቡን ይነግረኛል። ፀጥ-ረጭ ባለው ሌሊት “ኩኩሉሉሉ…” እያለ አዲስ ቀን መምጣቱን ያበስረኛል። ለአንዳንዶቻችሁ በአውራ ዶሮው ድምፅ ውስጥ ያለው ተስፋ ላይታያችሁ ይችላል። ነገር ግን፣ ትላንት እንደዋዛ ታስሮ፣ ዛሬን በእስር ላይ ያለና ነገን በተስፋ ለሚጠብቅ እስረኛ የዶሮው ድምፅ ልዩ ስሜት ይፈጥራል። 

ሌላው ድምፅ ደግሞ በጦላይ የፖሊስ ማሰልጠኛ የሚገኙ ምልምል ፖሊሶች በሌሊት የሚሰጠውን ስልጠና አጠናቀው ወደ መኝታ ክፍላቸው ሲመለሱ የሚያሰሙት፤ “መሰናበቻ መሰናበቻ፣ አሁን የቀረኝ ምርቃት ብቻ!” የሚለው ዜማቸው ነው። በእርግጥ መጀመሪያ ላይ ዜማውን ስሰማ ሰልጣኞቹ በጥቂት ቀናት ውስጥ ተመርቀው ከማሰልጠኛው የሚወጡ መስሎኝ ነበር። ነገር ግን፣ ለቀጣዮቹ 50 ቀናት ስልጠናው አለመጠናቀቁ፣ ሰልጣኞቹም ዘወትር ጠዋት-ጠዋት ያለማቋረጥ፤ “መሰናበቻ መሰናበቻ፣ …አሁን የቀረኝ ምርቃት ብቻ!” እያሉ መቀጠላቸው ግርምት ፈጠረብኝ። 

እየቆየሁ ሳስበው የሰልጣኞቹ ዜማ ወሳኝ የሆነ ስነ-ልቦናዊ ፋይዳ እንዳለው ተረዳሁ። እነዚህ ምልምል ፖሊሶች፣ ምንም እንኳን ለምርቃት ብዙ ቀናት እንደቀራቸው ውስጣቸው ቢያውቅም ጥቂት ቀናት ብቻ እንደቀሯቸው አድርገው ማሰብ የመረጡበት ምክንያት በማሰልጠኛ ተቋሙ ያለው ፈታኝና አስቸጋሪ ሕይወትን በነገ የአዲስ ሕይወት ተስፋ ተቋቁሞ ለማለፍ ነው። በእርግጥ እንደ ጦላይ ባለ በረሃማ ቦታ ከወዳጅ-ዘመድ ሳይገናኙ፣ አንድ ዓይነት ምግብ (ዳቦ በሽሮ-ወጥ) እየተመገቡ፣ ከ6-8 ወራት ሌሊትና ቀን የሚሰጥውን ከባድ የሆነ ወታደራዊ ስልጠና መውሰድ በጣም አሰልቺ ከመሆንም አልፎ ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ፣ እንዲህ ባለ ቦታ የዛሬን ውሎ በነገ ተስፋ እያካካሱ መሄድ የግድ ነው። 

እየቆየሁ ስሄድ ግን የጦላዩ አውራ ዶሮ እና ምልምል ፖሊሶች ከተስፋ በተጨማሪ የፍርሃት ስሜት ፈጠሩብኝ። አውራ ዶሮ እንዴት የፍርሃት ስሜት ሊፈጥር እንደሚችል ለአብዛኞቻችሁ ግልፅ ላይሆን ይችላል። እንዲህ እንድል ያደረገኝ አንድ ቀን የታዘብኩት ክስተት ነው። ቀጥሎ የምነግራችሁ ክስተት በእውን የታዘብኩት ነገር ነው። ይህን ነገር ታዲያ ሌላ ሰው ቢነግረኝ ኖሮ በሙሉ ልብ አምኜ ለመቀበል ይከብደኝ ነበር። ስለዚህ እናንተም ተመሣሣይ ስሜት ቢሰማችሁ አይገርመኝም። ነገሩ የፈጠራ ሳይሆን በእውን የታዘብኩት ሃቅ ነው። 

ነገሩ እንዲህ ነው። ከእለታት አንድ ቀን ሰልጣኞች/እስረኞች ምሳ ለመብላት ከምግብ ቤቱ ፊት ለፊት ተሰልፈናል። እኔም ያ ብቸኛ አውራ ዶሮው ከእጅ መታጠቢያው ስር ውሃ ሲጠጣ ተመስጬ እያሁት ነበር። ድንገት አንገቱን ቀና አድርጎ የሆነ ነገር አየና እየሮጠ ሄደ። ወደሚሮጥበት አቅጣጫ በአይኔ ተከተልኩት። ከእሱ አነስ ያለ ሌላ ወንድ ዶሮ ተገዝቶ ኖሯል ለካ። ትልቁ አውራ ዶሮ ሮጦ እንደሄደ ያደረገውን ነገር አስገራሚ ነው። ክንፉን ከቀኝ እግሩ ላይ አስታኮ እያሻሸ አዲሱን ዶሮ ለመስረር ማሽኮርመም ጀመረ። ይኄኔ አዲሱ ዶሮ ልክ እንደ ሴት ዶሮ ማስካካት አይጀምርም? የተመለከትኩትን ነገር ማመን አቅቶኝ በዙሪያዬ የነበሩትን ሰዎች እየጎተጎትኩ አሳየኋቸው። ከእነዚህ ውስጥ አንድ በእድሜ ጠና ያሉ ሽማግሌ፤ “እንዳይነክሰው ፈርቶ ነው! ከዚህ በፊት አይተህ አታውቅም እንዴ?” አሉኝ። 

እኔ ትንሽ ዶሮ በትልቅ ዶሮ እንዳይነከስ ሸሽቶ ሲያመልጥ እንጂ ተፈጥሯዊ ባህሪውን ቀይሮ እንደ ሴት ዶሮ ሲያስካካና ሲሽኮረመም በጭራሽ አይቼ አላውቅም። ነገሩ ለብዙ ቀናት ከአዕምሮዬ አልጠፋ አለ። በመጨረሻም እንደ ጦላይ ባለ ቦታ እንኳን የእንስሳ ሰውም በፍርሃት እንደሚመራ ተረዳሁ። በእርግጥ በጦላይ ከዛፎቹ በስተቀር ሁሉም ነገር በፍርሃት ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ ሌላው ቀርቶ እኛ የምንፈራቸው ፖሊሶች ራሳቸው ይፈራሉ። 

ከእለታት አንድ ቀን አንድ የትግራይ አከባቢ ተወላጅ የሆነ የፌደራል ፖሊስ አባል ምሳ ለመብላት በተሰለፍንበት በጦላይ በብዛት ስለሚገኙት ትላልቅ ዛፎች ገለፃ መስጠት ጀመረ፡፡ በግቢው ውስጥ ዛፍ መቁረጥ ፍፁም የተከለከለ እንደሆነና ይህ ከረጅም አመታት ጀምሮ ተግባራዊ መደረጉን እየገለፀ ሳለ ከመካከላችን አንዱ፤ “ግን ይህ ተቋም መቼ ነው የተገነባው?” ብሎ ያልጠበቀው ጥያቄ ጠየቀው? ፖሊስ መልሱን እንደማያውቀው በሚያሳብቅበት መልኩ፤ “ኧኧኧ……ድሮ፥ በጣም ድሮ …” ብሎ መለሰ፡፡ ነገር ግን ከፊት-ለፊት ተሰልፈው የነበሩ አንድ ሽማግሌ “ኧረ ምን ድሮ ነው! በ1972 ዓ.ም ደርግ እኮ ነው የገነባው!” በማለት አረሙት፡፡ 

ፖሊሱ መልሱን ከመሣሣቱ በተጨማሪ በጣም እያደነቀ በኩራት ሲናገርለት የነበረው ተቋም ጭራቅ አድርጎ በሚስለው “ደርግ” መገንባቱ ስቅጥጥ ያለው ይመስላል። “ደርግን አሞግሰሃል” ተብሎ እንዳይከሰስ የፈራ ይመስል፤ “ደርግ ገነባው… ሌላ ገነባው እኛ ምን አገባን! እኛ ተቋሙን መጠቀም ብቻ ነው!” ብሎ ተኮሳተረ፡፡ ነገረ-ስራው ሁሉ የደርግ መንግስት ስለ ሰራው ጥሩ ነገር መናገር ይቅርና ማሰብ በራሱ እንደሚያስፈራው ያስታውቅበታል።   

በነፃነት ማሰብና መናገር እንዲህ የሚያስፈራው ፖሊስ ትላንት ላይ “መሰናበቻ መሰናበቻ፣ አሁን የቀረኝ ምርቃት ብቻ!” ብሎ እየዘመረ ከጓደኞቹ ጋር የአዲስ ሕይወት ተስፋን ሲጋራ የነበረ ነው። እኔ ግን ዘወትር ከእጁ የማይለየውን ክላሽ መሣሪያ እና ቆመጥ ዱላ እያየሁ እፈራዋለሁ። በተመሣሣይ፣ ዛሬ ተስፋ የሚያበስሩኝ ምልምል ፖሊሶች ነገ ላይ ሳገኛቸው እፈራቸዋለሁ። በእርግጥ እስር ቤት ማለት በጦር መሣሪያ የሚጠበቅ ቦታ ነው። መደብደብ፣ መቁሰልና መገደል ባይኖር ኖሮ ለአንድ ቀን እንኳን እዚያ መቆየት የሚፈልግ ሰው ያለ አይመስለኝም። በአጠቃላይ አስገዳጅ የሆነ ቅጣት ባይኖር ኖሮ ጦላይ ሰው አልባ ቦታ ይሆን ነበር።

One thought on “ተስፋና ፍርሃት በእስር ቤት

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡