ኢህአዴግና ፋና፡ በራስ መዶሻ ራስን ማስቀጥቀጥ 

የተሃድሶ ስልጠናውን ሲመሩ የነበሩት የመንግስት ኃላፊ “አንዳንድ ግለሰቦች በማህበራዊ ሚዲያዎች፣ በተለይ ደግሞ በፌስቡክ የተሳሳቱ መረጃዎች በመልቀቅ ሕዝብና መንግስትን እያቃረኑ…” በማለት ተናገሩ። ቀጠሉና “እኛ እኮ ወደ ተለያዩ ቦታዎች ሄደን ሕዝቡን እናወያያለን። ለምሳሌ በቀደም ዕለት በአንድ የገጠር ቀበሌ እያወያየሁ ሳለ አንድ አርሶ አደር እንዲህ አለኝ ‘ይሄ “ፌ-ስቡክ” ነው “ፈ-ስቡክ” የምትሉት ነገር… ማንም የውሸት መረጃ እየለቀቀ ሕዝብና መንግስትን ከሚያጋጭ ለምን አትዘጉትም?’ ብሎ እንደተጠየቁ እና ‘ዴሞክራሲ ባለበት ሀገር ይህን ማድረግ አይቻልም’ አልኩት….” እኔ ሳዳምጥ የነበረው የኃላፊውን ቃላት ሳይሆን በውስጡ ያለውን ፍርሃት ነበር።

በእርግጥ በተሃድሶ ስልጠናው አንድ ያረጋገጥኩት ነገር ቢኖር ማህበራዊ ሚዲያዎች ለኢህአዴግ መንግስት የሕልውና አደጋ እየሆኑ መምጣታቸውን ነው። ምክንያቱም፣ እንደ ማንኛውም አምባገነናዊ ሥርዓት የኢህአዴግ መንግስትም ሕልውናው የተመሰረተው የመረጃ አቅርቦትና ይዘትን በብቸኝነት በመቆጣጠር ላይ ነው። ነገር ግን፣ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ይህ መሰረት ባልተጠበቀ ሁኔታ እየተናደ ይገኛል።

ባለፉት አመታት ከኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) መስፋፋት ጋር ተያይዞ ከመረጃ አቅርቦት፣ ተደራሽነትና ይዘት አንፃር ከፍተኛ ለውጥ እንዳለ መገንዘብ ይቻላል። ምንም እንኳን በዘርፉ ልማት ኢትዮጲያ ከአለም የመጨረሻ ደረጃ ላይ የምትገኝ ቢሆንም፣ ማህበራዊ ሚዲያዎች ግን ባልተጠበቀ መልኩ እያደጉና የአከባቢያዊና ዓለማቀፋዊ ጉዳዮች የመረጃ ምንጭ እና የውይይት መድረክ እየሆኑ መጥተዋል። ከእነዚህ ማህበራዊ ሚዲያዎች ውስጥ ደግሞ ፌስቡክ (Facebook) ትልቁን ድርሻ ይወስዳል።

አንዳንድ የጥናት ውጤቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ኢትዮጲያ ውስጥ ያለው የፌስቡክ ተጠቃሚ ብዛት ከአጠቃላይ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ብዛት ይበልጣል። ከተጠቃሚዎች ብዛት በተጨማሪ የፌስቡክ አጠቃቀማችንም ከሌሎች የዓለም ሀገራት የተለየ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ። እንደ ምሁራኑ አገላለፅ፣ ኢትዮጲያኖች ከሌሎች ሀገራት በተለየ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ የሚያወጧቸው መረጃዎች በድንገት ወይም በዘፈቀደ የመጣላቸውን ብቻ ሳይሆን የተለየ ዓላማና ግብ ያለው ነው። ከዚያ ይልቅ የተጠቃሚዎችን ግንዛቤ ለማዳበር አላማ ያላቸውና ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና በልማታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው። በዚህ መሰረት፣ በኢትዮጲያ የማህበራዊ ድረገፆች አጠቃቀምና ፋይዳ ከሌላው ዓለም የተለየ፣ በማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፍ ሚናቸው የላቀ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።

የማህበራዊ ሚዲያዎች አጠቃቀምና ፋይዳን በቅርበት የሚከታተሉ ምሁራን እንደሚገለፁት፣ በተለይ የፌስቡክ ድረገፅ የህትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ተደራሽነትን ከማሳደጉ በተጨማሪ፣ ዋና የመረጃ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። በሀገሪቱ ውስጥ የተለያየ አቋምና አመለካከት፣ እንዲሁም ለብዙሃኑ የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ የሆኑ የህትመት ዉጤቶች በሌሉበት፣ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎቹ ግልፅና አሳታፊ ባለመሆናቸው ምክንያት እንደ ፌስቡክ ያሉ ድረገፆች ለሕዝቡ ዋንኛ የመረጃ ምንጭ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ፌስቡክ መንግስት የመረጃ አቅርቦትና ይዘትን በበላይነት ለመቆጣጠር የሚጠቀምባቸውን የሚዲያ ተቋማት በሕብረተሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተዓማኒነት በማሳጣቱ ረገድ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል። የኢህአዴግ መንግስት የመረጃ አቅርቦትና ይዘትን በበላይነት ለመቆጣጠር ከሚጠቀምባቸው ተቋማት ውስጥ የኢትዮጲያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ የኢትዮጲያ ፕሬስ ድርጅት እና ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። እነዚህ በከፍተኛ በጀትና የሰው ሃይል የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች የሚያቀርቧቸውን የተሳሳቱ፣ ግልፅነት የጎደላቸው፣ በጣም የተጋነኑ ወይም የተደጋገሙ ዘገባዎችን ከስር-ከስር እየተከታተሉ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ የሚያጋልጡ ግለሰቦች ከግዜ ወደ ግዜ እየተበራከተ መጥቷል።

በዚህ ረገድ በፌስቡክ ገፁ ላይ ዓይነተኛ ሚና እየተጫወተ ያለው ‘”እሸቱ ሆማ ኬኖ” (Eshetu Homa Keno) በኣረዓያነት የሚጠቀስ ነው። ወደ 30ሺህ የሚጠጉ የፌስቡክ ተከታዮች ያሉት እሸቱ ነዋሪነቱ በአሜሪካን ሀገር ሲሆን በተለያዩ የሀገር ውስጥ ሚዲያ ተቀቋማት የሚቀርቡ የተሳሳቱ ዘገባዎችና መረጃዎችን በማጋለጥ በታዳሚዎች ዘንድ የነበራቸው ተዓማኒነት እያሳጣቸው ይገኛል። እሸቱ ካወጣቸው የተሳሳቱ፣ የተዛቡና የተደጋገሙ ዘገባዎች ውስጥ የተወሰኑትን ቀጥሎ በማሳያነት የምናቀርብ ሲሆን የተቀሩትን የፌስቡክ ገፁን ላይክ በማድረግ መከታተል ትችላላችሁ። ለምሳሌ፣ የሀገራችን የማምረቻ ዘርፍ ያለው እድገትና ከሀገሪቱ ዓመታዊ የምርት መጠን አንፃር ያለው ድርሻን አስመልክቶ የቀረቡት የሚከተሉትን ዘገባዎች እንመልከት።

ከላይ የተጠቀሱት ዓይነት ዘገባዎች በዋናነት የሚቀርቡት ለፖለቲካ ፍጆታ ነው። ነገር ግን፣ በተጨባጭ መረጃ ያልተደገፈ አስተያየት እና እርስ-በእርሳቸው የሚቃረኑ ዘገባዎች በመንግስትና በሚዲያዎቹ ተዓማኒነት ላይ ኣሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸው እርግጥ ነው። ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡት ዘገባዎች ደግሞ መንግስት ከፕሮጀክት እቅድ፣ ዲዛይንና አፈፃፀም አንፃር ያሉበትን ዘርፈ-ብዙ ችግሮች በግልፅ የሚጠቁም ነው። ችግሩ ለብዙ ዓመታት በተሳሳቱና በተጋነኑ ዘገባዎችና ሪፖርቶች እየተድበሰበሰ ስለቆየ መንግስትን ወደ 13 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ እንዳስወጣው በቅርቡ መገለፁ ይታወሳል።

የሥራ ዕድል በብር አይገዛም” በሚለው ፅሁፍ፣ በኦሮሚያ ክልል ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት መሰረታዊ የአመለካከትና አሰራር ችግር እንዳለበት በዝርዝር ለመግለፅ ሞክሬያሁ። ይህ ችግር ባልተቀረፈበት ሁኔታ ምንም ያህል በጀት ቢመደብና እንዴትም ተደርጎ ቢዘገብ ለክልሉ ወጣቶች ተጨባጭ የሆነ ለውጥና መሻሻል አያመጣም። ከታች በቀረቡት ዘገባዎች ላይ በግልጽ የሚስተዋለው ይኼው ነው።

​ስለ አዲስ አበባ የከተማ ሴፍቲኔት በሚያትተው ፅሁፌ ደግሞ ፕሮግራሙ በራሱ በተሳሳተ እሳቤ ላይ የተመሰረተ መሆኑን በዝርዝር ለመግለፅ ሞክሬያለሁ። በተሳሳተ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ፕሮግራም በየዓመቱ “ተግባራዊ ሊደረግ ነው” እየተባለ ለፖለቲካ ፍጆታ ከመዋል የዘለለ ፋይዳ የለውም። ምክንያቱም፣ መርሃ-ግብሩ ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር መስራት ለማይችሉ ነዋሪዎች የኪስ ገንዘብ መክፈል እስከሆነ ድረስ መጨረሻው ከኪራይ ሰብሳቢነትን ከማስፋፋት አያልፍም።

​ከላይ የቀረቡት የተሳሳቱ ዘገባዎችና መረጃዎች ከይዘታቸው በተጨማሪ የሚዲያ ተቋማቱ ከሙያ ሥነ-ምግባር አንፃር ምን ያህል ደካማ ሥራና አሰራር አንዳላቸው በግልጽ ያሳያል። በእርግጥ የሀገራችን የሚዲያ ዘርፍ ከመንግስት ባልተናነሰ ሁኔታ በኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት እና ሙስና ውስጥ የተዘፈቀ ነው። ለምሳሌ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተሰራ ጥናት 83.3% የሚሆኑት የሀገራችን ጋዜጠኞች ለሚሰሩት ዘገባ ገንዘብ ወይም ሌላ ጥቅማ-ጥቅም እንዲሰጣቸው እንደሚፈልጉ እና የግሉ ዘርፍ ተቋማት ለጋዜጠኞች የሚሆን የጉቦና ጥቅማ-ጥቅም “በጀት” እስከ መመደብ መድረሳቸውን አረጋግጧል።

ከቅርብ ግዜ ወዲህ መንግስት እንደ ፌስቡክ ባሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል እያደረገ ይገኛል። ነገር ግን፣ የኢህአዴግ መንግስት ማህበራዊ ሚዲያዎችን ጨምሮ በኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ላይ ምንም ያህል ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ቢያደርግ ተፅዕኖውን ጭርሶ መግታት ሆነ ማስቀረት አይችልም። ይህን ለማድረግ የሀገሪቱን ኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት አቅርቦት ሙሉ-በሙሉ ማቋረጥ አለበት። የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎትን ሙሉ-ለሙሉ ማቋረጥ ራስን-በራስ እንደማጥፋት ይቆጠራል።

የኢንተርኔት አገልግሎት እስካለ ድረስ እንደ ፋና ያሉ የሚዲያ ተቋማት ከላይ እንደተጠቀሱት ዓይነት የተሳሳቱና የተጋነኑ ዘገባዎችን ግልፅነትና ተጠያቂነት በጎደለው መልኩ በኢንተርኔት መልቀቃቸውን ይቀጥላሉ። በተመሣሣይ፣ እንደ እሸቱ ያሉ ግለሰቦች ደግሞ ከስር-ከስር እየተከታተሉ በዘገባዎቹ ውስጥ የታጨቀውን አይን-ያወጣ ውሸትና ቅጥ-ያጣ ግነት ማጋለጣቸውን ይቀጥላሉ። በዚህ መልኩ፣ የኢህአዴግ መንግስት በሀገሪቱ ያለውን የመረጃ አቅርቦትና ይዘት በበላይነት ለመቆጣጠር ያለው አቅም እየቀነሰ ሲሄድ ፖለቲካዊ ሥርዓቱ መፈራረስ ይጀምራል። ማህበራዊ ሚዲያዎች እንደ ኢህአዴግ ባሉ መንግስታት ላይ የሚፈጥሩትን የሕልውና አደጋ “Anthony Giddens” እንዲህ ሲል ገልፆታል፡-

“Information monopoly, upon which the political system was based, has no future in an intrinsically open framework of global communications. A deepening of democracy is required, because the old mechanisms of government don’t work in a society where citizens live in the same information environment as those in power over them”

በብዙ ሚሊዮን ብር በጀት የሚንቀሳቀስ ተቋም የተከመረ ውሸትና አስመሳይነት በጥቂት ግለሰቦች ጥረት ይናዳል። በዚህ ምክንያት፣ የተቋማቱ ተዓማኒነት እና የመንግስት ተቀባይነት ከቀን ወደ ቀን እየተሸረሸረ ይሄዳል። ስለዚህ፣ የኢህአዴግ መንግስት ሕልውናውን ለማረጋገጥ ያለው ብቸኛ አማራጭ ማህበራዊ ሚዲያዎችን ለማፈን ከመጣጣር ይልቅ ባለፉት አስር አመታት ያፈረሰውን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መዋቅር መልሶ ለመገንባት መጣር ነው። በተመሣሣይ፣ የተሳሳቱና የተዛቡ ዘገባዎችን የሚያቀርቡት የሚዲያ ተቋማት በታዳሚዎች ዘንድ ያላቸውን ተዓማኒነት ለመታደግ ያላቸው አማራጭ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራር መዘርጋትና ነፃና ገለልተኛ መረጃ ለሕዝቡ ማቅረብ ነው።

በእርግጥ ኢህአዴግና የሚዲያ ተቋማቱ ከላይ ከተጠቀሱት ውጪ ሌላ አማራጭ የላቸውም። ምክንያቱም፣ እነዚህን ብቸኛ አማራጮች ተግባራዊ ማድረግ ከተሳናቸው ግን በራሳቸው በጀትና ጉልበት የእነ እሸቱን ተልዕኮ ለማሳካት ደፋ ቀና ማለታቸውን ይቀጥላሉ። እሸቱ ሆማ ኬኖ በፌስቡክ ገፁ ላይ ያስቀመጠው መመሪያ እንዲህ ይላል፡- “Hitting them hard on the head using their own hammer” ኢህአዴግና ተቋማቱ በተጠቀሰው መልኩ ሥር-ነቀል ለውጥና መሻሻል ማምጣት እስካልቻሉ ድረስ በራሳቸው መዶሻ ራሳቸውን ያስቀጠቅጣሉ። ፈጣን፣ አሳታፊና ተደራሽ በሆነ የመረጃ ዘመን ውስጥ በሃሰት ፕሮፓጋንዳ ተቀባይነትና ተዓማኒነትን ለማግኘት መሞከር የራስን መቃብር እንደመቆፈር ይቆጠራል።

2 thoughts on “ኢህአዴግና ፋና፡ በራስ መዶሻ ራስን ማስቀጥቀጥ 

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡