የጭካኔ ተግባርን ለፈፀመና ለተፈፀመበት እኩል አዝናለሁ፣ አስፈፃሚው ግን አጠላለሁ (ለሀብታሙ አያሌው)

ትላንት ሀብታሙ አያሌው በእስር ላይ ሳለ የደረሰበትን የስቃይ ምርመራ አስመልክቶ ከአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ጋር ያደረገውን ቃለ-ምልልስ ሰማሁት። በቃለ-ምልልሱ የገለፃቸው የጭካኔ ተግባራት እጅግ በጣም የሚዘገንኑና ለመስማት እንኳን የሚሰቀጥጡ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ፣ ከኢትዮጲያዊያን የሞራል ስነ-ምግባርና ባህል ውጪ ናቸው በሚል ያልገለፃቸው በምርመራ ስም የተፈፀሙ ሌሎች የጭካኔ ተግባራት መኖራቸውንም አያይዞ ገልጿል። በዚህ መሰረት፣ በሰው ልጅ ላይ በተግባር ለመፈፀም ይቅርና በቃላት እንኳን ለመግለፅ የሚከብዱ አሰቃቂ ተግባራት በሀገራችን እየተፈፀሙ ይገኛል።

በእርግጥ በቃለ-ምልልሱ ከተጠቀሱት በላይ ምን ዓይነት የጭካኔ ተግባራት ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት ቀርቶ ማሰብ በራሱ ይከብዳል። አብዛኞቻችን በሀብታሙ ላይ የደረሰውን ስቃይና መከራ በሰማን ግዜ ይህን ተግባር በፈፀሙት ሰዎች ላይ ቂምና ጥላቻ ይኖረናል። እንደ ማዕከላዊ ባለ እስር ቤት ስለሚፈፀሙት የጭካኔ ተግባራት ስንሰማ የሰዎቹ ጥፋትና ክፋት ቀድሞ ይታየናል። አዎ…አለማወቅ ለፍርድ ያመቻል። ነገር ግን፣ እንዲህ ያሉ የጭካኔ ተግባራት ለምን እንደሚፈፀሙ ጠንቅቀን ስናውቅ ለበዳዮችና ለተበዳዮች እኩል እናዝናለን። እኔ በበኩሌ ሰው በሰው ላይ ለምን እንዲህ ጨካኝ እንደሚሆን ስለማውቅ ከሀብታሙ እኩል እሱን ለበደሉት ሰዎችም አዝናለሁ። ይሄ እዚህ በፅሁፍ ላይ የተወሰነ ሳይሆን ለሀብታሙ ራሱ በግልፅ የነገርኩት ሃቅ ነው። 

በተንዛዛ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ወደ ውጪ ሀገር ሄዶ ሕክምና የማግኘት ሰብዓዊ መብቱን ተነፍጎ በከፍተኛ ስቃይና እንግልት በነበረበት ወቅት ሀብታሙን በአካል ሄጄ አግኝቼዋለሁ። በእርግጥ ሀብታሙ የነበረበት ሁኔታ በጣም አሳዝኖኛል። ነገር ግን ለሀብታሙ ብቻ ሳይሆን እሱን ለበሽታና ስቃይ ለዳረጉት ሰዎች ጭምር ሀዘኔ እኩል ነበር። ልጠይቀው በሄድኩ ግዜ ለከፍተኛ ስቃይ የዳረገውን የኪንታሮት በሽታ የሚያሳይ ምስል በሞባይል ስልኩ እያሳየኝ “ተመልከት ስዩሜ… ይሄን ተሸክሜ ነው የምሄደው!” አለኝ፡፡ እኔ ግን “አይዞህ! አንድ ቀን እነሱም የእጃቸውን ያገኛሉ!…” ብዬ ላፅናናው አልሞከርኩም። ከዚያ ይልቅ፣ ቃል-በቃል ባይሆንም እንዲህ ነበር ያልኩት፤

“ሃብትሽ እዘንላቸው! …እነዚህ ሰዎች ቢያውቁ እንዲህ ያደርጋሉ? አያደርጉም! አየህ… አለማወቅ ህሊናቸውን አውሮታል፣ ሰብዓዊ ርህራሄ አሳጥቷቸው። በእነሱ ጥፋትና ቅጣት ለበሽታ ተዳርገህ፣ በእነሱ ክፋትና ጭካኔ ዘወትር ተበሳጭተህ እንዴት ትችለዋለህ? ሃብትሽ…ባለማወቅ ታውረው የሰብዓዊነት ክብር ለተገፈፉ ለእነዚህ ምስኪን ሰዎች እዘንላቸው። ያኔ ቢያንስ የእነሱን ጭካኔ ረስተህ የራስህን በሽታ ታስታምማለህ…”

በሀብታሙ ላይ በቃላት እንኳን ለመግለፅ የሚከብዱ የጭካኔ ተግባራትን የተፈፀመበት “ባለማወቅ ነው” ማለት በራሱ እንደ “አላዋቂነት” ሊወሰድ ይችላል። ለአንዳንዶቻችሁ እሱን ለከፍተኛ ስቃይና መከራ የዳረጉትን ሰዎች መልሶ “እዘንላቸው” ማለት ከመጀመሪያው የባሰ ጭካኔ ይመስላል። ከድምዳሜ ላይ ከመድረሳችሁ በፊት ግን እስኪ ስለ ስልጣን መዋቅርና አሰራር የምነግራችሁን በጥሞና አድምጡኝ።

የስልጣን መዋቅር የሚንቀሳቀሰው የዕዝ ሰንሰለትን ተከትሎ ነው። የዕዝ ሰንሰለቱን ተከትለን በስልጣን መዋቅሩ ወደላይ ስንወጣ፤ በተግባራዊ እንቅስቃሴው ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸው ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ፣ በእንቅስቃሴው ላይ ያላቸው የማዘዝ ስልጣን ግን እየጨመረ ይሄዳል። በስልጣን መዋቅር ወደታች ስንወርድ ደግሞ በተግባራዊ እንቅስቃሴው ያላቸው ቀጥተኛ ተሳትፎ እየጨመረ፣ በሥራና ተግባራቸው ላይ ያላቸው የማዘዝ ስልጣን እየቀነሰ ይሄዳል። ስለዚህ፣ በስልጣን መዋቅሩ ላይ ወደላይና ወደታች በሄድን ቁጥር የሰዎቹ ቀጥተኛ ተሳትፎ እና የማዘዝ ስልጣን እንደ ሁኔታው እየጨመረና እየቀነሰ ይሄዳል። ለምሳሌ፣ በዕዝ ሰንሰለቱ የላይኛው ጫፍ ላይ ያለ አካል (ለምሳሌ የሀገሪቱ ጠ/ሚኒስትር) የመንግስት መዋቅርን ተከትሎ በሚሰሩ ስራዎች ላይ ሙሉ የማዘዝ ስልጣን ቢኖረውም በተግባራዊ እንቅስቃሴው ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ የለውም። በዕዝ ሰንሰለቱ የታችኛው ጫፍ ላይ ያለ አካል (ለምሳሌ፣ የማዕከላዊ እስር ቤት መርማሪ ፖሊስ) በተግባራዊ እንቅስቃሴው ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ቢኖረውም በሥራና ተግባሩ ላይ የማዘዝ ስልጣን የለውም።

በተግባራዊ አንቅስቃሴው ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆኑት መርማሪ ፖሊሶች ስለ ሥራቸው “አግባብነት” የማሰብና የመወሰን ስልጣን የላቸውም። በምርመራ ሥራው ቀጥተኛ ተሳታፊ ያልሆነው የበላይ አዛዥ ግን ስለ ፖሊሶቹ ሥራ አግባብነትና አስፈላጊነት የማሰብና የመወሰን ስልጣን አለው። ስለ ስቃይ ምርመራው ምክንያታዊነት የማሰብ እና አግባብነቱን የመወሰን ስልጣን ያላቸው አዛዦች በምርመራ ሂደቱ ላይ በቀጥታ ተሳታፊ አይደሉም። በምርመራው ሂደቱ በእስረኞች ላይ የጭካኔ ተግባር የሚፈፅሙት መርማሪ ፖሊሶችና የደህንነት ሰራተኞች ደግሞ ስለሚያከናውኑት የምርመራ ተግባር ምክንያታዊነትና አግባብነት የማሰብና የመወሰን ስልጣን የላቸውም።

ከላይ በተጠቀሰው አሰራር መሰረት፣ በስቃይ ምርመራ ተግባር በቀጥታ ተሳታፊ የሆኑ ሰዎች ከምክንያታዊ ግንዛቤ ይልቅ በስሜታዊ ግንዛቤ የሚመሩ ናቸው። ከበላይ አለቆቻቸው የተሰጣቸውን ትዕዛዝና መመሪያ ከማናቸውም ዓይነት የሞራል ግዴታና ሰብዓዊ ርህራሄ ነፃ ያደርጋቸዋል። በዚህ ግዜ በደመ-ነፍስ አንደሚመሩ ፍጡራን እጅግ አስፈሪና ዘግናኝ የሆኑ ድርጊቶችን ሊፈፅሙ ይችላሉ።

በእርግጥ እንደ ማዕከላዊ ባሉ እስር ቤቶች ውስጥ የጭካኔ ተግባር የሚፈፅሙ መርማሪ ፖሊሶችና የደህንነት ሰራተኞች እንደ ሁላችንም ሰብዓዊ ፍጥሯን ናቸው። እንደ ማንኛውም ሰው ሥራና ተግባራቸው በምክንያታዊ አስተሳሰብና በሞራል ስነ-ምግባር የሚመራ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በራሳቸውም ሆነ በሌሎች ሰዎች ላይ እንዲደርስ በግላቸው የማይፈልጉትን የጭካኔ ተግባር ሲፈፅሙ ይስተዋላል። እነዚህ ሰዎች እንደ ግለሰብ በግላቸው የማያደርጉትን ነገር በአለቃዎቻቸው ሲታዘዙ ግን ያደርጉታል። ይህ እንደ ሰው ያላቸውን ምክንያታዊነት (rationality) እና የሞራል ስብዕና ያሳጣቸዋል። ለዚህ ደግሞ ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች አሉ። አንደኛ፡- እንደ ሰው ያላቸውን ምክንያታዊ አስተሳሰብ የሚያጡት በሥራቸው ላይ በነፃነት የማሰብም ሆነ የመወሰን ስልጣንና ኃላፊነት ስለሌላቸው ነው። ምክንያቱም፣ እንደ ሰው የማሰብ ነፃነቱን ወይም ኃላፊነቱን ለበላይ አለቆቻቸው አሳልፈው ሰጥተዋል። የበላይ አዛዦችና ባለስልጣናት ስለ ተግባራቸው አግባብነትና አስፈላጊነት የሚያቀርቧቸው ምክንያቶች (justifications) በሰው-ልጅ ላይ የጭካኔ ተግባር እንዲፈፅሙ ከሞራል ዕዳ ነፃ ያደርጋቸዋል። ይህን ሊዮ ቶልስቶይ እንዲህ ገልፆታል፡-

“When a man works alone he always has a certain set of reflections which as it seems to him directed his past activity, justify his present activity, and guide him in planning his future actions. Just the same is done by a concourse of people, allowing those who do not take a direct part in the activity to devise considerations, justifications, and surmises concerning their collective activity. …These justifications release those who produce the events from moral responsibility. These temporary aims are like the broom fixed in front of a locomotive to clear the snow from the rails in front: they clear men’s moral responsibilities from their path.” Leo Tolstoy, War and Peace, P.1156-7

የሰው-ልጅ ከሌሎች እንስሳት የሚለይበት መሰረታዊ ባህሪ በምክንያታዊ አስተሳሰብ እና በሞራል ስነ-ምግባር የሚመራ መሆኑ ነው። እንደ ማዕከላዊ ባሉ እስር ቤቶች ውስጥ በቃላት እንኳን ለመግለጽ የሚከብዱ እጅግ በጣም ዘግናኝ የሆኑ የጭካኔ ተግባራት የሚፈፅሙ መርማሪ ፖሊሶችና የደህንነት ሰራተኞች ከላይ በዝርዝር እንደተገለፀው ይህን የሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪያት የተገፈፉ ናቸው። በዚህ መልኩ ሰብዓዊ ክብራቸውን ተገፍፈው ወደ አውሬነት ከመቀየር በላይ የሚያሳዝን ነገር ከቶ ምን አለ? የሰው ልጅ ሰብዓዊ ክብሩን ተገፍፎ በደመነፍስ እየተመራ በሌሎች ሰዎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ቢፈፅም የማዝነው ለማን ነው? የጭካኔ ተግባሩን የፈፀመም ሆነ የተፈፀመበት ሁለቱም ሰብዓዊ ክብራቸውን ተገፈዋል፡፡ ሁለቱም ሰብዓዊ ክብራቸውን ተገፍፈዋልና እኔ ለሁለቱም እኩል አዝናለሁ፡፡ 

በመጨረሻም፣ ሀብታሙ አያሌው በቃላት የጠቀሳቸውና ያልጠቀሳቸውን የጭካኔ ተግባራት እንዲፈፀሙ የመፍቀድ ሆነ እንዳይፈጸሙ የማገድ ሙሉ ስልጣን ያለው በስልጣን መዋቅሩ የላይኛው እርከን ላይ ያለው አካል ነው። እንደ ማዕከላዊ ባሉ እስር ቤቶች የሚፈፀሙ የጭካኔ ተግባራት እንዲፈፀሙ ሆነ እንዳይፈፀሙ በማድረግ ረገድ ሙሉ ስልጣንና ኃላፊነት ያለው የሀገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ናቸው። ከእሳቸው በመቀጠል በየደረጃው ያሉ የመንግስት አካላት የራሳቸው የሆነ ድርሻና ኃላፊነት ያላቸው ሲሆን ሦስቱንም የመንግስት አካላት፡- ሕግ አውጪ፥ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈፃሚ አካላትን አንድ ላይ ያካትታል።

በዚህ መሰረት፣ በተለያዩ እስር ቤቶች እና ጣቢያዎች በሚካሄደው የስቃይ ምርመራ ላይ ለሚፈፀሙ የጭካኔ ተግባራት ግንባር ቀደም ተጠያቂ መሆን ያለበት መንግስታዊ ስርዓቱ ነው። በዜጎች ላይ እየተፈፀሙ ላሉት የጭካኔ ተግባራት እንዲፈፀሙ ያደረገው በሁላችንም ላይ የተጫነው አምባገነናዊ ሥርዓት ነው። እያንዳንዱ ሰው መጥላትና መጠየፍ ያለበት ይህን የፈቀደውን መንግስታዊ ሥርዓት ነው። ከዚህ ቀደም፣ አሁንና ወደፊት በምርመራ ስም የሚፈፀሙ የጭካኔ ተግባራትን ማስቀረት የሚቻለው በቂምና ጥላቻ ሳይሆን የሁላችንም መብትና ነፃነት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ሲቻል ነው።