የኢትዮጲያ ምሁራን የፖለቲካ ፍርሃትና ሽሽት

የአማርኛ መዝገበ ቃላት “ምሁር” የሚለውን ቃል “በትምህርት፥ በዕውቀት የበሰለ አዕምሮ ያለው ሰው” እንደሆነ ይጠቅሳል። በዚህ መሰረት፣ ምሁር ሲባል፤ በትምህርት ዕውቀት የቀሰመ፣ በዚህም ሰፊ ግንዛቤ ያለው፣ ነገሮችን ከተለያየ አቅጣጫ ማየት እና በጥልቀት ማገናዘብ የሚችል ሰው ነው። ስለዚህ፣ ምሁር ለመሆን ትምህርት መማር፣ መመራመርና ማወቅ የግድ ነው።

በመሰረቱ ምሁር ለመሆን መማር ያስፈልጋል፣ በትምህርት ደግሞ ዕውቀት ይገኛል። በዚህም ብዙ የተማረ ሰው ሊኖር ይችላል፣ ብዙ ነገር የሚያውቁ ሰዎች ይኖራሉ። ከእነዚህ ውስጥ ግን በትክክል “ምሁር” ለመባል የሚበቁት በጣት የሚቆጠሩት ናቸው። ዕውቀት በተግባር ለውጥና መሻሻል ካላመጣ ትምህርት መማሩም ሆነ ማስተማር ብቻውን ትርጉም የለውም።

በትምህርት የቀሰምነው ዕውቀት ፋይዳ የሚኖረው በራሳችንና በሌሎች ሰዎች ሕይወት ላይ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችለን ከሆነ ነው። ስለዚህ፣ አንድ ሰው በትክክል “ምሁር” የሚባለው ስለተማረ ብቻ ሳይሆን ዕውቀትና ክህሎቱን ተጠቅሞ በራሱና በሌሎች ሰዎች ሕይወት ላይ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት ጥረት የሚያደርግ ከሆነ ብቻ ነው።

በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እየተወጡ ካሉ እጅግ በጣም ጥቂት ምሁራን ውስጥ በአዲስ አበባ ዪኒቨርስቲ የፍልሰፍና መምህር የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ አንዱ ናቸው፡፡

​እስካሁን ድረስ “ምሁርነት” ከትምህርትና ዕውቀት ባለፈ በተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚገኝ ክብር ነው። ስለዚህ፣ ምሁራንን ከሌላው የሕብረተሰብ ክፍል ልዩ የሚያደርጋቸውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ምንድነው? “Edward Said”የተባለው ምሁር “Representations of an Intellectual” በሚል ርዕስ በሰጠው ትንታኔ፣ አንድ ሰው “ምሁር” የሚለውን የክብር ስያሜ ለመጎናፀፍ በተግባር ከህዝቡ ጋር እየኖረ የብዙሃኑን ጥያቄ (መልዕክት)፣ አመለካከት፣ ፍልስፍና ወይም ሃሳብ መወከል፣ መያዝና መግለፅ መቻል አለበት።

በዚህ መሰረት፣ ምሁራን ሃሳብና አስተያየታቸውን በአደባባይ በመግለፅ የህዝብን ጥያቄ የሚያንፀባርቁ፣ እንዲሁም ኋላ-ቀር አመለካከትና ግትር አቋምን በይፋ የሚሞግቱ ናቸው። ይህን የሚያደርጉት ከግል ወይም ከተወሰነ ቡድን ጥቅም አኳያ ሳይሆን በመሰረታዊ የነፃነትና እኩልነት መርሆች ላይ በመንተራስ መሆን አለበት። ስለዚህ፣ ምሁራን በትምህርት ዕውቀት ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ ለማህብረሰቡ መብትና ተጠቃሚነት የቆሙ መሆን አለባቸው።
ምሁራን በየትኛውም ግዜና ቦታ ቢሆን የሰዎች መብትና ነፃነት ሲገፈፍ፣ ፍትህ ሲዛባ በይፋ በመናገርና በመፃፍ ተቋውሟቸውን በይፋ የመግለፅ ድርሻና ኃላፊነት አለባቸው። በአደባባይ አሳፋሪ ጥያቄዎችን ለማንሳት፣ ኋላቀር አመለካከትንና ግትር ቀኖናዊነትን ለመጋፈጥ፣ እንዲሁም ለመንግስት ፍላጎት በቀላሉ እጅ ላለመስጠት ድፍረትና ቁርጠኝነት የሌለው ሰው የምሁራን ድርሻና ኃላፊነት መወጣት አይችልም።

ባለፉት አስር አመታት በሀገራችን የተማሪዎች ብዛት ከ10 ሚሊዮን በእጥፍ ጨምሮ 20 ሚሊዮን ደርሷል። የሀገሪቱ የተማረ ሰው ኃይል በዚያው ልክ እንደጨመረ መገንዘብ ይቻላል። ነገር ግን፣ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ዙሪያ ሃሳብና አስተያየታቸውን በይፋ የሚገልፁ ሰዎች ቁጥር እጅግ በጣም አነስተኛ ነው። የትምህርት ደረጃው ከመሰረተ-ትምህርት እስከ ፕሮፌሰርነት ሊደርስ ይችላል። ነገር ግን፣ ከላይ የተጠቀሰውን የምሁራን ድርሻና ኃላፊነት በድፍረትና ቁርጠኝነት መወጣት እስካልቻለ ድረስ “ምሁር” የሚለው የክብር ስያሜ አይገባውም። ከዚህ አንፃር፣ አሁን ባለው ሁኔታ “ኢትዮጲያ ውስጥ ምሁር አለ” ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር የሚከብድ ይመስለኛል።

በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ “ፖለቲካ እሳት ነው!” የሚለው አባባል የተለመደ ነው። ይህ ከፍርሃት በተጨማሪ ከፖለቲካ መሸሽን ያመለክታል። በተለይ በተማረው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ከፍርሃት በተጨማሪ የፖለቲካ ሽሽት በግልፅ ይስተዋላል። ይህ ሽሽት በዋናነት በሙያተኝነት ወይም ፕሮፌሽናሊዝም ስም የሚደረግ ነው።

ሙያተኝነት ወይም ፕሮፌሽናሊዝም (professionalism) በአብዛኞቹ የሀገራችን ምሁራን ዘንድ በግልፅ የሚስተዋል ችግር ነው። በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ እያንዳንዱ ምሁር በሰለጠነበት የሙያ መስክ ላይ ብቻ እንዲያተኩር ይፈለጋል። ብዙውን ግዜ ምሁራን ከመደበኛ ሥራቸው በተጓዳኝ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ በተለይ ደግሞ ከፖለቲካ ጋር የሚነካካ ከሆነ በፍፁም አይበረታታም።

በእርግጥ ሙያተኝነት በራሱ እንደ ችግር ሊወሰድ አይገባም። እያንዳንዱ ባለሙያ በሰለጠነበት መስክ የሚጠበቅበትን አገልግሎት የመስጠት ሃላፊነትና ግዴታ አለበት። ነገር ግን፣ እንደ አንድ የተማረ ሰው ሙያተኝነት የተጣለብንን ማህበራዊ ኃላፊነት ከመወጣት ሊያግደን አይገባም ነው። በአጠቃላይ፣ ሙያና ሙያተኝነት እንደ መደበቂያ፣ ከኃላፊነት መሸሸጊያ ተደርጎ መወሰድ የለበትም።

አንድ የተማረ ሰው በሰለጠነበት ሙያ (profession) ስም ከሚፈፅማቸው ስህተቶች በጣም የከፋው፣ ከማንኛውም ዓይነት ውዝግብና ከፖለቲካ ነፃ ለመሆን በሚያደርገው ጥረት፣ መደበኛ ሥራውን በተለመደው መንገድ እየሰራ፣ በከረመ አስተሳሰብ አንድ ዓይነት ሃሳብ እያመነዠከ፣ በማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የሚጠበቅበትን ድርሻ ሳይወጣ ሲቀር ነው። በዚህ መልኩ፣ “እኔ ከውዝግብና ፖለቲካ ነፃ ነኝ” እያሉ የሚመፃደቁ ምሁራን የተጣለባቸውን ማህበራዊ ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት እንደተሳናቸው በራሳቸው ላይ እየመሰክሩ ያሉ ናቸው።

በተለይ እንደ ኢትዮጲያ ባሉ ሀገራት የብዙሃን ሕይወት በዘርፈ-ብዙ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች የተተበተበ መሆኑ እርግጥ ነው። እነዚህን ችግሮች መቅረፍ የሚቻለው የማያቋርጥ ለውጥና መሻሻል ሲኖር ነው። ከዚህ አንፃር ምሁራን ከመደበኛ ሥራቸው በተጓዳኝ አስፈላጊውን ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

እያንዳንዱ ሰው በሙያዊ ገለልተኝነት ስም በስልጣን ላይ ላለ አካል ድጋፍ ሰጪ ሆኖ ከማገልገል ይልቅ በራሱ ሕሊና እየተመራ የተጣለበትን ማህበራዊ ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅበታል። ሆኖም ግን፣ ምሁራን በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የሚያደርጉት ማንኛውም እንቅስቃሴ ከውዝግብና ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ፣ ምሁራን ከአወዛጋቢነትና ከፖለቲካዊ ተፅዕኖ ነፃ በሆነ መልኩ ሚናቸውን መወጣት አይችሉም።

በሙያተኝነት ስም ከአወዛጋቢና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ነፃ ሆኖ ለመንቀሳቀስ መሞከር ፍፁም አገልጋይነት እንጂ ከአንድ ምሁር የሚጠበቅ ባህሪ አይደለም። በመደበኛው ሥራና አሰራር ላይ ብቻ ተወስኖ መቅረት ማህበራዊ ኃላፊነትን ካለመወጣት በተጨማሪ በስልጣን ላይ ካለው ኃይል ጋር በመተባበር በሕዝቡ ላይ በደል እንደመፈፀም ይቆጠራል። ያለ ምሁራን ተሳትፎ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት አይችልም። የተማረው የሕብረተሰብ ክፍል ከፖለቲካው መድረክ ገለልተኛ በመሆናቸው ምክንያት ተጎጂ የሚሆነው በፖለቲካ ስልጣን ላይ ያለው አካል ጭምር ነው። ምክንያቱም፣ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ማረጋገጥ የተሳነው ፖለቲካዊ ስርዓት ሕልውና ሊኖረው አይችልም።

በተለይ ከደርግ ዘመን በኋላ በስፋት እንደሚስተዋለው የተማረው የሕብረተሰብ ክፍል “ፖለቲካ እሳት ነው!” በሚል እንደ ምሁር ድርሻና ኃላፊነቱን በሚገባ ተወጥቷል ለማለት አያስደፍርም። በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ዙሪያ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ሃሳብና አስተያየት በሌለበት መንግስት እና ሕዝብ በራሳቸው ችግሮቹን በዘላቂነት መቅረፍ አይችሉም። የተማረው የሕብረተሰብ ክፍል ዕውቀትና ክህሎቱን ተጠቅሞ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከማድረግ ይልቅ ነባራዊ እውነታን የሚፈራና የሚሸሽ ከሆነ የሚፈለገው ለውጥና መሻሻል ሊመጣ አይችልም።

በአጠቃላይ፣ በየትኛውም የትምህርት ደረጃ ቢሆን አንድ ሰው “ምሁር” ሊባል የሚችለው እንደ ምሁር ድርሻና ኃላፊነቱን በተግባር የሚወጣ ከሆነ ብቻ ነው። ፖለቲካን የሚፈራና የሚሸሽ ራሱን እንደ ተማረ ሰው ከመቁጠር ባለፈ “ምሁር” የሚለው የክብር ስያሜ አይገባውም። ምንም እንኳን በሀገራችን የተማሪና አስተማሪ ቁጥር በእጥፍ ቢጨምርም ከእነዚህ ውስጥ “ምሁር” ለመባል የሚበቁት በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦች ናቸው። ሀገሪቷና ህዝቧ በዘርፈ-ብዙ ችግሮች የተተበተቡበት የተማረው የሕብረተሰብ ክፍል በአብዛኛው ፍርሃትን ፊት-ፊት ከመጋፈጥ ይልቅ በሽሽት ለማምለጥ ስለሚሞክር ነው። ነገር ግን፣ ፍርሃትን በድፍረት ይጋፈጡታል እንጂ በሽሽት አያመልጡትም።


ይህ ፅሁፍ መጋቢት 07/2009 ዓ.ም በታተመው “የሐበሻ ወግ” መፅሄት ላይ የቀረበ ነው፡፡