የሥራ ዕድል መፍጠር ያለበት መንግስት አይደለም

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ይፋ ያደረገው “የኢኮኖሚ አብዮት” እያነጋገረ ሲሆን ሰሞኑን ኦዳ ትራንስፖርት ኩባንያን ለመመሥረት በግማሽ ቀን በተካሄደ የአክሲዮን ሽያጭ 617 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ አክሲዮኖች መሸጣቸው ታውቋል፡፡ የኦዳ ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር በሙሉ አቅሙ ሲመሰረት ከወጣቶች ጋር በጋራ የሚያስተዳድራቸው የነዳጅ ማደያዎችና የነዳጅ ዲፖዎች እንደሚኖሩትም ተጠቁሟል፡፡ በሌላ በኩል የክልሉ መንግስት 1.2 ሚሊዮን ለሚደርሱ የኦሮሚያ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር በሚል በባለሃብቶች ይዞታ ሥር የነበሩ የማዕድን ማውጫ ቦታዎችን እየነጠቀ ለተደራጁ ወጣቶች ማከፋፈል የጀመረ ሲሆን ባለሃብቶች በዚህ እርምጃ መከፋታቸውን ገልፀዋል፡፡

ከ15 ዓመት በላይ በክልሉ በጠጠር ማዕድን ማውጣት ስራ ላይ ተሰማርተው ሲሰሩ እንደነበር የገለጹ አንድ ባለሀብት፤ “በዘርፉ የተሰማሩ አልሚዎችን አስወጥቶ ለኪሳራና ለውድቀት በመዳረግ ምንም ላልለፉ ወጣቶች ማከፋፈል በፍፁም ተቀባይነት የለውም” ሲሉ የክልሉን መንግስት እርምጃ ተቃውመዋል፡፡ ሌሎች የማዕድን ማውጫ ቦታቸውን የተነጠቁ ባለሀብቶችም “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የግል ሀብት የማፍራት መብት አለው” የሚለውን የህገ መንግስቱን አንቀፅ 40 በመጥቀስ፣ህገ መንግስታዊ መብታቸው መጣሱን ጠቁመው አቤቱታቸውን ለመንግስት እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በጉዳዩ ዙሪያ ምሁራን አነጋግሮ አስተያየታቸውን እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡


“የሥራ ዕድል መፍጠር ያለበት መንግስት አይደለም”
ስዩም ተሾመ (ጦማሪና የዩኒቨርሲቲ መምህር)

ከባለሀብቶች የማዕድን ማውጫዎችን መንጠቅ የኮሚኒስቶች አካሄድ ነው፡፡ በስነ ምጣኔ አመክንዮ ስንመለከተው፤ መንግስት በተለያዩ ቢዝነሶች መግባቱም የሚደገፍ አይደለም፡፡ ከግለሰቦች የኢንቨስትመንት ቦታ መውረስም ሆነ መንግስት ነጋዴ መሆኑ በየትኛውም መንገድ አይደገፍም፡፡ ይሄ የኮሚኒስት ስርአት ባህሪ ነው፡፡ የክልሉ መንግስት ይሄን በማድረጉ ግለሰብ ባለሀብቶችን እየቀጣ ነው ማለት ነው፡፡

የስራ ዕድል መፍጠር ያለበት እኮ መንግስት አይደለም፡፡ የስራ ዕድል በገንዘብ አይገዛም። መፍጠር የሚችለው ማህበረሰቡ ራሱ ነው፡፡ መንግስት ኃላፊነቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ የፋይናንስ ስርአቱን፣ ቢሮክራሲውን ማስተካከል፣ የቢዝነስ ስልቶችን ማስተማር የመሳሰሉት ናቸው የመንግስት ኃላፊነቶች፡፡ ከባለሀብቶች ላይ ሀብት ቀምቶ ለስራ አጥ ወጣቶች ማከፋፈል ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ ይሄ ማለት እናለማለን ያሉትን ኢንቨስተሮች እንደ መቅጣት ነው፡፡ እነዚህ ተነጥቆ የሚሰጣቸው ወጣቶችም ቢሆኑ በሙሉ ፍላጎታቸው ሳይሆን በመንግስት ግፊትና ድጎማ ወደ ስራው ስለሚገቡ ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

በግላቸው ተሯሩጠው አዲስ የስራ መስክ የፈጠሩትን ሰዎች እየቀጡ፣ የቢዝነስ ክህሎት ለሌላቸው ስራ አጦች መሸለም በየትኛውም አካሄድ አይደገፍም፡፡ ቢዝነስ ከግለሰቦች እየቀሙ ለስራ አጥ መሸለሙ ወጣቶችን ምርታማ አያደርግም። ምክንያቱም እነሱ ስለ ቢዝነሱ በቂ እውቀት አይኖራቸውም፡፡ ለወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር የሚቻለው በዚህ መርህና አካሄድ አይደለም፡፡ ተወዳዳሪና ብቁ የቢዝነስ ሰዎችንም በዚህ አካሄድ መፍጠር አይቻልም፡፡ የአለም ተሞክሮም ይሄን አያሳይም፡፡ ሰዎች በሚሰሩት ስራ በቂ እውቀት፣ ፍላጎትና ክህሎት ሲኖራቸው ነው ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉት፡፡

በሌላ በኩል መንግስት ከባለሀብቱ ልጣመርና ቢዝነስ ላቋቁም የሚለውም የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ከዚህ በፊትም ታይቶ ውጤት ያላመጣ አካሄድ ነው። በነዚህ አካሄዶች ቀደም ሲል ህዝቡ ሲጠይቃቸው ለነበሩ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አይቻልም፡፡ ተወዳዳሪ የቢዝነስ ሰዎችን ለመፍጠር በመጀመሪያ የሚደራጁት ሰዎች ብቃትና ፍላጎት ወሳኝነት አለው፡፡ ዝም ብሎ አደራጅቶ ሀብት ውረሱ ማለት እንዴት ውጤት ያመጣል? እነዚህ ሰዎች በምንም መመዘኛ ተወዳዳሪ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ እየጨመረ ለሚሄደው የስራ ዕድል ፍላጎትም ተጨማሪ የስራ ዕድል አይፈጥርም፡፡

በሌላ በኩል በኦሮሚያ በነበረው ተቃውሞ ወደ አደባባይ የወጡት ወጣቶች ጥያቄ በእርግጥስ የስራ ማጣት ጥያቄ ብቻ ነው? የሚለውንም መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ እንደ‘ኔ የነበረው ጥያቄ የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ነው፡፡ ይሄን ደግሞ ከአንዱ ነጥቆ ለሌላው በመስጠት ማስታገስ አይቻልም፡፡ በአመፁ ወቅት በዋናነት የተነሳው ጥያቄ፤ ከፊንፊኔ ዙሪያ የሚፈናቀሉ ሰዎች መብትና ጥቅማቸው አልተከበረላቸውም የሚል ነው፡፡ ይሄን ደግሞ በዚህ መንገድ ለመፍታት መንቀሳቀስ ከስነ ምጣኔ መርህ አንፃር አያስኬድም፡፡ የመብት ጥያቄዎች ባልተመለሱበት ሁኔታ ይሄን ቁንፅል እርምጃ ለመውሰድ መሞከር ትክክል አይደለም፤ ውጤትም አያመጣም፡፡

ምንጭ፦ አዲስ አድማስ ጋዜጣ