በቆሼ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የድጋፍ አሰጣጥ ማዕቀፍ

በቆሼ በደረሰው የቆሻሻ መደርመስ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውና ሀብትና ንብረታቸውን ላጡ ወገኖች የመኖሪያ ቤት ተበረከተላቸው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ነዋሪዎች በንፋስ ስልክ ላፍቶና ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች ውሰጥ በ24 ሚሊዮን ብር ወጪ የተሰሩ 110 የመኖሪያ ቤቶች ለተጎጂዎች አስርክቧል።

የከተማዋ ከንቲባ ዲሪባ ኩማ የቤቱን ቁልፍ ለተጎጂዎች ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት “የከተማ አሰተዳደሩ በተቻለ አቅም ተጎጂዎቹን የመርዳትና የማቋቋም ስራው ይቀጥላል” ብለዋል።

ቤቶቹ የተገነቡት ለኑሮ ተስማሚ በሆኑ አካባቢዎች በመሆኑ ተጎጂዎች ከህዝቡ ድጋፍ በተጎዳኝ ጠንክሮ በመስራት ኑሯቸውን ማሻሻል አለባቸው ነው ያሉት።

በቆሼ በደረሳው አደጋ ኮልፌ ቃራኒዮ ክፍለ ከተማ አስኮ አዲስ ሰፈር አካባቢ በ16 ሚሊየን ብር የተገነቡ ቤቶች ለተጎጂ ቤተሰቦች ተብርክተዋል።

በሌላ በኩልም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍል ከተማ በ8 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነቡ ቤቶች ለተጎጂዎቹ የተሰጠ ሲሆን ቤቶቹ የውሃ፣የኤሌክትሪክ፣የመጸዳጃና የምግብ ማብሰያ መሰረተ ልማት የተሟላላቸው መሆኑ በርክክብ ወቅት ተገልጿል።

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ነዋሪዎችም ህዝብና መንግስት ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አርቅበዋል።

በተያያዘ መጋቢት 2 2009 በደረሰው አደጋ ተጎጂ የሆኑ ሰዎችን በቋሚነት ለማቋቋም የሚያስችለው የድጋፍ ማዕቀፍ ዛሬ ይፋ ሆኗል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ እና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ አቶ ኤፍሬም ግዛው በጋራ በሰጡት መግለጫ፥ የድጋፍ ማዕቀፉ ድጋፍ የሚደረግላቸውን ሰዎች በስድስት ከፍሎ የያዘ ሲሆን አደጋ ያልደረሰባቸው ነገር ግን የአደጋ ስጋት ውስጥ ያሉ ሰዎችንም እንዳካተተ ተናግረዋል።

አንደኛው ማዕቀፍ፦ ህጋዊ  ይዞታ የነበራቸው አባወራ እና እማወራ የሚስተናገዱበት 

 • 16 ናቸው

 • ከቤተሰብ ውስጥ ላጡት አንድ ሰው 40 ሺህ ብር በነፍስ ወከፍ ይከፈላል። 

 • ቀደም ሲል ከነበራቸው ይዞታ አንጻር መሰረተ ልማት በተሟላበት አካባቢ ቦታ ይሰጣል። 

 • ቦታው ላይ ቤት መስሪያ በነፍስ ወከፍ 1 ሚሊየን ብር ይሰጣል (አንድ ግለሰብ የቀድሞ ቤታቸው ከነበረበት አሰራር አንጻር ተጨማሪ 300 ሺህ ብር እንዲሰጣቸው ተወስኖላቸዋል) 

 • ቤታቸውን ሰርተው እስኪገቡ የአንድ አመት የቤት ኪራይ እንዲከፈላቸው ወቅታዊ የቤት ኪራይ ሂሳቡ እየተጠና ነው። 

 • የቁሳቁስ መተኪያ ለእያንዳንዱ 140 ሺህ ብር በአጠቃላይ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ይሰጣል። 

 • በከብት እርባታ ላይ ተሰማርተው ለነበሩ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር 

 • ለመሰረታዊ የቤት ውስጥ ፍጆታ ለሶሰት ወር በወር 4500 ብር በአጠቃላይ 13 ሺህ 500 በነፍስ ወከፍ 

ሁለተኛ ማዕቀፍ ፦ ህጋዊ የዞታ ባለቤቶች ልጆች ሆነው እና ትዳር መስርተው ይኖሩ የነበሩ

 • 13 ናቸው 

 • በቤተሰብ ላጡት ሰው ለአንዱ 40 ሺህ ብር 

 • አንድ ቦታ ላይ አስተዳደሩ ገንብቶ በግል ይዞታነት ለእያንዳንዳቸው ይሰጣቸዋል። ለግንበታው 5 ነጥብ 2 ሚሊየን ይፈጃል ተብሎ ተገምቷል። 

 • ቤቱ እስከሚሰጥ የአንድ አመት የቤት ኪራይ ይሰጣል፤ ወቅታዊ የቤት ኪራይ ሂሳብ እየጠና ነው። 

 • ለወደመባቸው ንብረት በነፍስ ወከፍ 70 ሺህ ብር 

 • ለመሰረታዊ የቤት ውስጥ ፍጆታ ለሶሰት ወር በወር 4500 ብር በአጠቃላይ 13 ሺህ 500 በነፍስ ወከፍ

ሶስተኛ ማዕቀፍ፦ ተከርይተው ይኖሩ የነበሩ 

 • 54 ናቸው 

 • አራቱ የጋራ መኖሪያ ቤት የደረሳቸው በመሆኑ የጋራ መኖሪያ ቤቱ ሙሉ ክፍያ ይከፈልላቸዋል 

 • 50ዎቹ ደግሞ የ10/90 ቤቶች ከአስተዳደሩ በልዩ ፈቃድ ተገዝቶ እንዲሰጣቸው ተወስኗል፤  ወጪው 4 ሚሊየን ብር ተገምቷል። 

 • ባል ወይንም ሚስት ለሞተበት 40 ሺህ ብር ይሰጣል። 

 • በዘላቂነት ለማቋቋም 100 ሺህ ብር ይሰጣል፤ በአጠቃላይ 5 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ይከፈላል። 

 • ለእለት ፍጆታ ለሶስት ወራት 4500 ብር ይሰጣል፤ አጠቃላይ 729 ሺህ ይወጣል ተብሏል። 

አራተኛ ማዕቀፍ፦ በህገወጥ መንገድ የጭቃ እና የላስቲክ ቤት ሰርተው ይኖሩ የነበሩ 

 • 102 አባወራ ናቸው 

 • 96ቱ ምንም የቤተሰብ አካል በአደጋው ያልሞተባቸው ሲሆን ለእነዚህ አስተዳደሩ የገነባቸው ቤቶች በኪራይ ይሰጠቸዋል። ዛሬ መጋቢት 23 2009 ቁልፍ ርክክብ ተደርጎላቸዋል (በኮልፌ ቀራንዮ እና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ) 

 • ስድስቱ የቤተሰብ አባል የሞተባቸው የ10/90 ቤት በስማቸው ይሰጣቸዋል። ለዚህ 480 ሺህ ብር ተገምቷል። 

 • በሞት ላጡት ሰውም በአንድ ሰው 40 ሺህ ብር ይሰጣል። 

 • በአደጋው ላጡት ቁሳቁስ ለእያንድንዱ 15 ሺህ 410 ብር ይሰጣል። አጠቃላይ 1 ሚሊየን 571 ወጪ ይደረጋል። 

 • ለቤት ውስጥ ፍጆታ ለሶሰት ወር በየወሩ 4 ሺህ 500 ብር ይሰጣል ተብሏል። 

አምስተኛ ማዕቀፍ፦ አደጋ ያልደረሰባቸው ነገር ግን ለአደጋ የተጋለጡ 

 • እንዲነሱ እየተደረገ ሲሆን የቤት ኪራይ እንዲሰጣቸው ታስቧል። 

 • ወረዳው እና ክፍለ ከተማው የተወያየበት ሲሆን፤ ቶሎ እንዲነሱ ለከንቲባው እና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቷል። 

 • ለእነዚህ ተነሺዎች የሚደረገው ድጋፍ እና የሚወጣው ወጪ ሙሉ በሙሉ ከአስተዳደሩ ካዝና በሚወጣ ገንዘብ ብቻ ይሸፈናል። 

ስድስተኛ ማዕቀፍ፦ በነፍስ አድን ስራው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ የአከባቢው ወጣቶች 

 • በማህበር ተደራጅተው መስራት ለሚፈልጉት ስራ በማህበር 25 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል ይሰጣቸዋል። 

 • በነፍስ አድን ስራ ላደረጉት አስተዋጽኦ ለእያንዳንዳቸው 5 ሺህ የኪስ ገንዘብ እና በነፍስ አድን ስራ ወቅት ለደረሰባቸው አደጋ የምርመራ እና ህክምና በአስተዳደሩ የጤና ተቋማት በነጻ ያደርጋሉ። 

በማዕቀፉ መሰረት እንዲሰጡ የተወሰኑት ድጋፎች የቀበሌ ቤቶችን በኪራይ እንዲወስዱ ለተወሰነላችው አካባቢው ላይ በህገወጥ መንገድ የጭቃ እና የሸራ ቤት ሰርተው ይኖሩ ለነበሩ ዜጎች የቁልፍ ርክክብ በማድረግ ዛሬ ተጀምሯል።

ከሰኞ ጀምሮ ደግሞ ለህጋዊ ይዞታ ባለቤቶች የመሬት ርክክብ ይደረጋል ነው የተባለው።

መጋቢት 2 በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ በደረሰው የቆሻሻ መደርመስ አደጋ ተጎጂዎችን ለመደገፍ ቃል ከተገባው 84 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ውስጥ 60 ሚሊየን 992 ሺህ 428 ብር አስተዳደሩ በከፈተው የድጋፍ ማሰባሰቢያ የባንክ ሂሳብ ገብቷል።

6 ሚሊየን 697 ሺህ 279 ብር የሚገመት የቁሳቁስ እና የምግብ እርዳታም ተደርጓል ተብሏል።


አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ)