የእኔን መብትና ነፃነት ከማያከብር ሕዝብና መንግስት ጋር ውል የለኝም!

ሰሞኑን የአህያ ነገር በጣም አነጋጋሪ ሆኗል። በተለይ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተለያየ ሃሳብና አስተያየት እየተሰጠ ይገኛል። እኔም “የበሬን ስጋ እየበላህ የአህያን ስጋ መከልከል እትችልም” በሚል ርዕስ ባወጣሁት ፅሁፍ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ደርሰዉኛል። የአብዛኞቹ አስተያየቶች “የኢትዮጲያ ሕዝብ” ወይም “የኢትዮጲያ መንግስት” በሚሉት ላይ ያጠነጠኑ ናቸው። አንዳንዶቹ “የኢትዮጲያ ሕዝብ እንዲህ ነው” ሲሉ ሌሎች ደግሞ “የኢትዮጲያ መንግስት እንዲያ ነው” ይላሉ። በመንግስትም በበኩል በሚሰጣቸው መግለጫዎች ላይ “የኢትዮጲያ ሕዝብ እና መንግስት…” ከማለት አይቦዝንም።

ነገር ግን፣ አብዛኞቹ “የኢትዮጲያ ሕዝብ እና መንግስት” የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ የእኔ መብትና ነፃነት በማክበርና ማስከበር ላይ የተመሰረተ ስለመሆኑ ግንዛቤ ያላቸው አይመስለኝም። የእኔ መብትና ነፃነት ባልተከበረበት ሁኔታ “የኢትዮጲያ ሕዝብ እና መንግስት” ማለት ባዶ ጩኸት ነው። ፅንሰ-ሃሳቡን በግልፅ ለመረዳት እንዲያስችለን ቃላቱን በተናጠል ማየት ይኖርብናል። በመጀመሪያ ደረጃ “የኢትዮጲያ ሕዝብ” የሚለውን ለመረዳት በቅድሚያ “ኢትዮጲያ ራሷ ምንድን ናት?” ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። ይህን ጥያቄ “ኢትዮጲያ ማለት ሀገር ናት” በማለት በቀጥታ መመለስ ይቻላል። ከዚህ በመቀጠል ደግሞ “ሀገር ማለት ምንድነው?” የሚለውን በዝርዝር እንመለከታለን።

የኣማርኛ መዝገበ ቃላት “ሀገር” የሚለው ቃል “በውስጡ ህዝቦች የሚኖሩበት፣ የተወሰነ ጂኦግራፊያዊ ክልል ያለውና በአንድ መንግስት አስተዳደር ስር የሚገኝ ግዛት” የሚል ፍቺ ይሰጠዋል። “ሕዝብ” የሚለውን ቃል ደግሞ “በተወሰነ መልከኣምድራዊ ክልል ውስጥ የሚገኙና በአንድ መንግስት ስር የሚተዳደሩ ጠቅላላ ሰዎች፤ የአንድ ብሔር ወይም ብሄረሰብ፥ ጎሳ፥…ወተዘ አባል የሆኑ ሰዎችን” መሆናቸውን ይጠቅሳል። ስለዚህ፣ “ሀገር” እና “ሕዝብ” የሚሉት ቃላት ፍቺ በአንድ ዓይነት ፅንሰ-ሃሳብ ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል።

“ኢትዮጲያ” የምትባል ሀገር እንድትኖር በተወሰነ መልከኣምድራዊ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች እና እነሱን የሚያስተዳድር መንግስት ሊኖር ይገባል። በተመሣሣይ፣ “የኢትዮጲያ ሕዝብ” የሚለው “በአንድ መንግስት ስር የሚተዳደሩ ጠቅላላ ሰዎችን የሚያመለክት ነው። በዚህ መሰረት፣ “ኢትዮጲያ” የሚለው ቃል እንደ ሕዝብ ሆነ እንደ ሀገር “መንግስት” ከሚለው ተነጥሎ ሊታይ አይችልም። “የኢትዮጲያን ሕዝብ” ከሚያስተዳድረው የሀገሪቱ “መንግስት” ነጥሎ ማየት አይቻልም። በመሆኑም፣ “የኢትዮጲያን ሕዝብ እና መንግስት” የሚሉትን ፅንሰ-ሃሳቦች በግልፅ ለመረዳት በሕዝብና መንግስት መካከል ያለውን ጥምረት በዝርዝር ማየት ያስፈልጋል።

ሕዝብና መንግስትን በአንድነት አጣምሮ ያሰረው ገመድ “ነፃነት” ነው። በኣማርኛ የመዝገበ ቃላት መሰረት “ነፃነት” ለሦስት ይከፈላል። 1ኛ፡- ሌላውን ሳይነኩ የፈለጉትን ነገር የመስራት፥ የመናገር፥ የመፃፍ፣ … መብት፣ 2ኛ፡- በባዕድ መንግስት ወይም በሌላ ሰው ቁጥጥር ስር አለመሆን፣ 3ኛ፡- ራስን በራስ የማስተዳደር፥ የመምራት ስልጣን፥ መብት ናቸው።

በመሰረታዊ የነፃነት መርህ መሰረት፣ የእያንዳንዱ ሰው “መብት” በነፃነት መስራት፥ መናገር፥ መፃፍ፥ ማሰብ፥…ወዘተ ሲሆን፣ በዚያው ልክ የሌሎችን ሰዎች ነፃነት እንዳይገድብ ግዴታ አለበት። ስለዚህ፣ ሁሉም ሰው እኩል መብቱን ማስከበርና ግዴታ መወጣት አለበት። ለዚህ ደግሞ የሁሉም ሰው መብትና ግዴታ በግልፅ የተደነገገበት ሕጋዊ ሥርዓት ሊኖር ይገባል። ከዚህ በተጨማሪ፣ እያንዳንዱ ሰው በነፃነት እንዲኖር በባዕድ መንግስት እና በሌሎች ሰዎች ቁጥጥር ስር መውደቅ የለበትም። ነገር ግን፣ እያንዳንዱ ከባዕድ መንግስት የሚቃጣን ወረራ በራሱ ለመከላከል ሆነ ሌሎች ሰዎች ግዴታቸውን እንዱወጡ ለማስገደድ የሚያስችል ኃይል የለውም።

ስለዚህ፣ የሁሉም ሰዎች መብትና ግዴታን የተደነገገበት ሕጋዊ ሥርዓትን የሚዘረጋ፣ እንዲሁም ከባዕድ መንግስት የሚቃጣ ጥቃት እና አንዱ ሌላውን በኃይል ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ጥረት ለመከላከል የሚችል፣ ከሁሉም ሰዎች የተወጣጣና እያንዳንዱ ሰው ሊኖረው ከሚችለው ኃይል የበለጠ ኃይል ያለው አካል አካል ያስፈልጋል። በዚህ መሰረት፣ በተወሰነ መልከኣምድራዊ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ማህበራዊ ግንኙነታቸው የሚመራበት ሕግን የሚያወጣ፣ የሚተረጉምና የሚያስፈፅም አካል በማቋቋም የሁሉንም ሰዎች መብትና ነፃነት ለማስከበር የሚፈጥሩት አካል “መንግስት” ይባላል። የመንግስት ድርሻና ኃላፊነት የሚደነገግበት ሰነድ ደግሞ ሕገ መንግስት ይባላል።

ሕገ-መንግስት እያንዳንዱ ሰው ከመንግስት ጋር ብቻ ሳይሆን ከሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ጋር የእያንዳንዱና የሁሉም ሰው መብትና ነፃነት እኩል እንዲከበር በጋራ ውል የገቡበት ሰነድ ነው። ይህን እንግሊዛዊው ፈላስፋ ቶማስ ሆብስ እንደሚከተለው ገልፆታል፡-

“This is more than consent, or concord; it is a real unity of them all in one and the same person, made by covenant of every man with every man, in such manner as if every man should say to every man: ‘I authorize and give up my right of governing myself to this assembly of men, on this condition; that [you] give up, [your] right to [them], and authorize all [their] actions in like manner. This done, the multitude so united in one person is called a COMMONWEALTH… And he that carries this person is called sovereign, and said to have sovereign power;….” Leviathan, Part-II, CH. XVII, Para-13

ከላይ በጥቅሱ አንደተገለፀው፣ የሕዝብና መንግስት ጥምረት የተመሰረተው፣ እያንዳንዱ ዜጋ፤ አንደኛ፡- የሌላውን መብት ሳይነካ የፈለገውን እየሰራ፣ እየተናገረና እየፃፈ በሰላም እንዲኖር፣ ሁለተኛ፡- በባዕድ ሀገር መንግስት ወይም በሌላ ሰው ተገዢ እንዳይሆን ጥበቃና ከለላ እንዲያደርግለት “ራሱን በራሱ የማስተዳደር፥ የመምራት ስልጣኑን ወይም መብቱን ለመንግስት አሳልፎ በመስጠት ነው። በዚህ መሰረት፣ የመንግስት ስልጣን የዜጎችን ነፃነት እንዲያስከብር ከእያንዳንዱ ግለሰብ ላይ ተቀንሶ የተሰጠ ነፃነት ነው። በአጠቃላይ፣ የአንድ ሀገር ሕዝብና መንግስት የተመሰረቱት የግለሰብን መብትና ነፃነት በማክበርና ማስከበር ላይ ነው።

የግለሰብ መብትና ነፃነት ሲገፈፍ፤ አንደኛ፡- ግለሰቡን ከመንግስትና ከሕዝቡ ጋር ያስተሳሰረው ገመድ ይበጠሳል፣ ሁለተኛ፡- ሕዝቡ ከግለሰቡና ከመንግስት ጋር የገባውን ውል ይፈርሳል፣ ሦስተኛ፡- መንግስት ከሕዝቡና ከግለሰቡ ጋር የገባውን ውል ማክበር ይሳነዋል። ስለዚህ፣ የግለሰብ መብትና ነፃነት ሲገፈፍ በሕዝብና መንግስት መካከል ያለው ጥምረት ይፈርሳል። የዜጎች ነፃነት ሲገደብ ሀገር ትርጉም-አልባ፣ መንግስት ፋይዳ-ቢስ ይሆናሉ።

እኔና እናንተን ከኢትዮጲያ ሕዝብና መንግስት ጋር ያስተሳሰረን የእያንዳንዳችንና የሁላችንም ነፃነት መከበር ነው። የእኔ በነፃነት የመስራት፣ የማሰብ፣ የመናገርና የመፃፍ መብትን ማክበር የእናንተ ግዴታ ነው። የኢትዮጲያ ሕዝብ የእኔን መብት የማክበር፣ መንግስት ደግሞ የእኔን መብት የማስከበር ግዴታ አለባቸው። ነገር ግን፣ እንደ ማንኛውም ሰው በነፃነት ማሰብ፥ የመናገርና የመፃፍ ነፃነቴ ከተገደበ፣ በሀገሪቱ ውስጥ ተንቀሳቅሼ የመስራት እና ሃብት የማፍራት መብቴ ካልተከበረ ከኢትዮጲያ ሕዝብ እና መንግስት ጋር የነበረኝ ውል ይፈርሳል።

ከምንም በላይ ደግሞ፣ የእኔን መብትና ነፃነት አክብሮ እንዲያስከብርልኝ ራሴን በራሴ የማስተዳደር መብቴን አሳልፌ የሰጠሁት መንግስት መልሶ የእኔን በነፃነት የማሰብ፥ የመናገርና የመፃፍ መብት የሚገድብ ከሆነ እንደ ግለሰብ ከኢትዮጲያ ሕዝብ ጋር፣ እንደ ዜጋ ከኢትዮጲያ መንግስት ጋር የነበረኝ ውል ሙሉ በሙሉ ይቋረጣል። በአጠቃላይ፣ የእኔ መብትና ነፃነት ካልተከበረ ከኢትዮጲያ ሕዝብና መንግስት ጋር ውል የለኝም።