የቢሾፍቱ የአህያ ቄራና የወደፊት መዘዙ (በአዲስ መኮንን)

እንዲህ ሆነ፡፡ በአንድ ወቅት እዚሁ ሃገራችን ውስጥ መንግስት ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቆፍሮ ውሃ ያወጣል። እንደ አሁን የህብረተሰብ ትብብር ምናምን የሚባለው ነገር አልታከለበትም ነበር። ሰራተኞች ጉዳጓዱን ሲቆፍሩ የአካባቢው ሰው አፉን በሸማዉ ሸፈን አድርጎ ያልፍ ነበር። ነዋሪዎች አፋቸዉን በሸማዉ ሸፈን አድርገዉ ሲሄዱ “ለምን?” ብሎ የጠየቀ ግን አልነበረም።

ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ የአከባቢው ነዋሪዎች ከጉድጏዱ ውሃ ይቀዳሉ ተብሎ ሲጠበቅ እነሱ ግን እንደ ቀድሞው ሩቅ ሄደው መቅዳታቸውን ቀጠሉ። ነዎሪዎቹ የጉድጏዱን ውሃ ለራሳቸው ይቅርና ለከብቶቻቸው እንኳን ለመስጠት ፋቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ። “ጅብ ከሄደ. ..” እንዲሉ የነዋሪው እንዲህ መሆን ግራ የገባቸው የመጠጥ ውሃ አስቆፋሪው አካላት ስብሰባ ተጠርተው “ስንት ወጪ ተደርጎበት ተቆፍሮ የተገነባው ለእናንተ ነው። ለምንድነው የማትጠቀሙበት” አሏቸው። ሁለት ቃል “እርማችንን አንጠጣም” ብለው መለሱ። ለካ ይሄ የውሃ ቧንቧ የተገነባበት ቦታ ምንጩ ቀድሞ የመቃብር ቦታ የነበረ እና በርካቶች አባቶቻቸው እና ዘመዶቻቸው ከተቀበሩበት አካባቢ የሚነሳ ነበር፡፡ ነዋሪዎቹ “እርማችንን አንጠጣም” ያሉት ለዚህ ነው። በዚህ ምክንያት ብዙ ብር ያላግባብ ባከነ።

Addis Mekonnen is a news caster at Ethiopian Broadcast Corporation National Radio service. He was born in Debre Berhan and studied Ethiopian language(s) and literature at Debre Markos University. Addis also blogs at: http://kemekemkemekem.blogspot.com You can reach him via his email address: addismekonen@yahoo.com

የትኛውም ቦታ ላይ ምንም ነገር ሲካሄድ የማህበረሰቡ፣ እምነት፣ ባህል፣ ወግና አስተሳሰብ ተጠንቶ መሆን አለበት። ያገኘንውን ነገር ሁሉ ወስደን አንድ ማህበረሰብ ላይ ብንጭንበት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። ከላይ እንደተጠቀሰው ለአከባቢው ማህብረሰብ አሳታፊ ያልሆኑ ሥራዎች ከገንዘብ ኪሳራ በተጨማሪ የህይወት ኪሳራም ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም፣ እንደዚህ ያሉ ጉዳዮች በጥንቃቄ ሊጠኑ ይገባል።

የቢሾፍቱው የአህያ ቄራ ጉዳይም ከዚህ ጋር ተመሣሣይነት አለው፡፡ ቄራው ሲከፈት የማህበረሰቡ እምነትና ባህል ተጠንቷል ወይ? ማህበረሰቡስ ፈቅዷል ወይ? ሳናስፈቅድ ስራ መጀመራችንስ የማህበረሰቡ ሞራል ላይ ምን ዓይነት ችግር ሊያስከትል ይችላል? እና ለመሳሰሉት ጥያቄዎች በቅድሚያ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

ሁሉም ሰው በግለሰብ ደረጃ፦ በባህሪ በአስተሳሰብ፣ በመልክ እና በአስተዳደግ፤ በሃገር ደረጃ በባህል፣ በእምነት፣ በጎሳ.. ፤ በአለም ደረጃ በዜግነት፣ በቆዳ ቀለም እና በመሳሰሉት ይለያያል። በዚህ ውስጥ ደግሞ የትየለሌ የሆኑ ልዩነቶች አሉ። ይሄ ሁሉ የሚለያይ ህዝብ ባለባት ዓለም “እነሱ ስላደረጉ” ተብሎ የሚደረግ ነገር ሊኖር አይገባም።

ሰሞኑን ኢትዮጵያ ቢሾፍቱ ከሚገኘው የአህያ ቄራ ስጋን ወደ ቬትናም ቆዳውን ደግሞ ወደ ቻይና እያስወጣች የውጭ ምንዛሬ ልታገኝ መሆኑ ሲወራ ብዙዎች ደንግጠዋል። ችግሩ አህያ ለምን ገንዘብ አስገኘ ሳይሆን የማህበረሰባችን ባህል እና እምነት ይህንን እንደ ነውር ስለሚቆጥረው ነው። እኛ ሃገር የትኛውም እምነት ይህንን የረከሰ ድርጊት እንድናደረግ አይፈቅድም። አንዳንዶች በሬ፣ በግ እና ፍየል በየግዜው እያረደ በሚበላ ማህበረሰብ ውስጥ የአህያ መታረዱ ክፋቱ ምኑ ነው? የሚል መከራከሪያ ሲያቀርቡ ይስተዋላል፡፡ ይሁን እንጂ በተለይ በክርስትና እምነት ሾኽናቸው ድፍን የሆኑ እንስሳት እንዲበሉ አይፈቅድም።

ከዚህ በተጨማሪ፣ “ቻይናዎች ለምን ለመድሃኒትነት፣ ሼትናሞች ደግሞ ለምግብነት አዋሉት?” ማለት አንችልም። ለምሳሌ፣ ህንዶች የበሬ ስጋ አይበሉም። እምነታቸው ባህላቸው ነው። “ለምን የበሬ ስጋ አይበሉም?” ብለን ማስገደድ አንችልም። ትልቁ ነገር እምነትና ባህላችን አይፈቅድም ነው። እምነትና ባህልን መተቸት ይቻል ይሆናል። ባህሌን ወድጄው እስከያዝኩት እምነቴን ተቀብየው እስከኖርኩ ድረስ ማንም እንዲያንቋሽሽብኝ አልፈልግም። ማንም እንዲበርዝብኝም አልፈልግም። “ይሄ ስህተት ነው” በሚል ጫና እንዲደረግብኝም አልፈቅድም። ለምሳሌ የጅብ ስጋ አንበላም። ማንም ቢሆን “የጅብ ስጋ ብትበሉ ምንም ችግር የለውም” እንዲለኝ አልፈልግም። በቃ…እርኩስ ነዋ!

ለማንኛውም ጉዳዩን ከተለያየ አቅጣጫ እንየው። ከእምነት አንፃር ሃገራችን ውስጥ የተለያዩ እምነቶች ይራመዳሉ፣ ይሰበካሉ። አንዳቸውም ግን የአህያ ስጋ እንደሚበላ ሲሰብኩ አይስተዋልም። በክርስትና ሃይሞኖት ዘንድ ሸሆና ክፍት የሆኑ እንስሳቶች አይበሉም። አህያ ደግሞ በዚህ ውስጥ ይካተታል። ሌሎችም እምነቶችም በተለያዩ ምክንያቶች የአህያ ስጋ እንዲበላ አይፈቅዱም። እንዲበላ
ያልተፈቀደን እንስሳ ደግሞ ባህሉ እንዳይታረድ ያደርገዋል። ከእርድ የራቀን ማረድ ደግሞ በማህበረሰቡ ዘንድ ያስወግዛል። የማህበረሰቡን ባህል እና እምነት መጠበቅ የመንግስትም ግዴታ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።

ታዲያ ሰሞኑን ወሬው ሁሉ ሆኖ “ቢሾፍቱ አህያ መታረድ ሊጀምር ነው” የሚለው ወሬ ወግ አጥባቂ በሆነው ማህበረሰባችን ውስጥ የፈጠረው ስሜት አስቀያሚ ነው። “እንኳን ቢሾፍቱ አዲስ አበባም ስጋ ሆቴል ላልበላ ነው” ያሉት በርካቶች ናቸው። “የአህያ ስጋ ለቄራ ለገበያ ሊያቀርቡ ሲሉ ተያዙ የሚሉ የተድፈነፈኑ ወሬዎች በተሰሙባት ሃገራችን ህጋዊ ማረጃ ሲገኝ በግብረግብነት የላሸቁ እና በገንዘብ ፍቅር የሰከሩ ግለሰቦች ይህን ሽፋን አድርገው እድሉን ተጠቅመው ለሆቴሎችና ለስጋ ቤቶች ላለማቅረባቸው ምን ዋስትና አለን? የእኛ ሀገር ሥጋ ነጋዴዎች ይህን ግዜ’ኮ በሬ በ12ሺህ ብር ገዝተው ሥጋ ከሚሸጡ አንዱን አህያ በ3ሺህ ብር ገዝተው፣ 4 አህያ በ12 ሺህ ብር ሂሳብ በሰፊው ማትረፍ እንደሚችሉ ቀድመው አስልተዋታል።

ነጋዴዎቹ አህያ ሲያርዱ ቢገኙ “ለቄራው ለማቅረብ ነው” ብለው ለማመካኘት እድል ተፈጥሮላቸዋል! ይኼኔ ትልቁ ክስረት አብሮ ይመጣል። የቢሾፍቱ ከተማን መፍራት ይጀመራል። ለእንግድነት የመጣ እና አየሩ ከለመደው አካባቢ ተቀይሮበት ወይ ምግብ አልስማማ ቢለው አዕምሮው ውስጥ የሚመጣበት “የተለየ ስጋ አብልተውኝ ነው” የሚለው ይሆናል። የተለየው ስጋ ደግሞ የአህያ ሥጋ ነው” መባል ይጀምራል፡፡ በዚህ ምክንያት የከተማዋ የሆቴል ዘርፍ ክፉኛ ይጎዳል። ይህንን ግልፅ የሚያደርግ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተለጥፋ የነበረች አጭር ግን ግልፅ ቃለ-ምልልስ እንመልከት፦
ልጅ፦ “እማዬ ቢሾፍቱ “ፊልድ” ልሄድ ነው”
እናት፦ “ለስንት ቀን”
ልጅ፦ “ለ3 ቀናት”
እናት፦ “ምናለ ቀድመህ ብትነግረኝ ስንቅ የማዘጋጅልህን። እሺ አሁን እንዴት ልትሆን ነው?”
ልጅ፦ “እማየ ምን ሆነሻል። ከመቼ ወዲህ ነው ፊልድ ስወጣ ስንቅ አዘጋጅተሽልኝ የምታውቂው?”
እናት፦ “የት ትበላለህ ብዬ እኮ ነው”
ልጅ፦ “ትልልቅ ሆቴሎች እና ሪዞርቶች ያሉባት ከተማ እኮ ናት”
እናት፦ “እሱን መቼ አጣሁት። አህያ ማረድ ጀምረዋል ሲባል ብሰማ እኮ ነው። ይህንን እየሰማሁ ሆቴል እንዴት ይበላልሃል ብየ ነዋ። ደግሞስ ምን ይታመናል ቱ…ቱ.. ወይ እንደተማሪነትህ የበሶ ዱቄት ይዘህ ትሄድ?” ይላል።

በከተማዋ ላይ ይህንን አይነት አስተሳሰብ ያመጣል። ከስነ ህይወት አንፃር የምድር ስነ ፍጥረታት ሁሉ ሲፈጠሩ በመደጋገፍ እና በመበላላት ነው። ይሄ የተፈጥሮ ህግ ነው። ይሄ ባይሆን ህይወት አትቀጥልም ነበር፡፡ እባብ አይጥ ይበላል። እባብ ሲሞት ደግሞ አይጥ ይበለዋል። የእኛ ሃገር ሰው የእህያ፣ የፈረስ እና የውሻ ስጋ አይበላም። ሌላው ቀርቶ የበግ ግልገል ስጋ፣ የጥጃ ስጋ እንዲሁም ደግሞ ከእርድ ውጭ የሞተ በሬ፣ ላም፣ በግ፣ ፍየል አይበላም። ጥንብ ነዋ!

ይህንን ማህበረሰቡ የማይበላውን ስጋ ደግሞ ቀን ውሾች ሌሊት ደግሞ ጅቦች ይበሉታል። ተፈጥሮ ያመቻቸው አይመስልም? ለምሳሌ ይሄን የተፈጥሮ ህግ እንስበረውና ሰው የማይመገበውን ሁሉ ወደ ሰዎች ምግብነት ብቻ እናምጣው። ውሾች ሰው የሚመገበውን እንጀራ ስለሚበሉ ችግር ላይገጥማቸው ቢችልም ጆቦች ግን አደጋ ውስጥ ይወድቃሉ። ሲርባቸው ሰውን ወደ ማጥቃት ይሸጋገራሉ። በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ “ከጉሬዛ ማሪያም እስከ አዲስ አበባ የህይወት ጉዞ እና ትዝታዬ” በሚለው መፀሃፋቸው የ1967ቱ ድርቅ ያስከተለዉን የስነ-ህይወት መዛባት እንዲህ አስፍረውታል።

“…እኔም በ1967 ዓ.ም. በፎኪሳ አካባቢ (ወሎ) አንድ ወጣት እናት ቤት ውስጥ የነበረ ተባይ እና የአይጥ መንጋ እንቅልፍ ሲነሳት፣ ሁለት ህፃናት ልጆቿን (የሁለት እና የአምስት አመት እድሜ) ይዛ፣ ከቤት ውጭ ለማደር ተገደደች። ሌሊት እግሯን ጅብ ሲነክሳት ነቃች፤ የአምስት አመት ልጇን ከአጠገቧ አጣችው፤ ጅብ ይዞባት እንደኼደ ተረዳች። ሲነጋ በአካባቢው የተገኘ የተበጣጠሰ የአምስት ዓመት ህፃን አስከሬን ነበር። ይሄ በሆነ በሁለተኛው ቀን ሌላ ሰፈር ከቤት ውስጥ ጅብ ገብቶ የስድስት አመት ልጅ በላ ተብሎ ተነገረኝ። እኔ በዚያ በነበርኩበት ወቅት ከሰዓት በኋላ፣ እኔ በነበርኩበት አካባቢ በጠራራ ፀሓይ ጅብ አንድ ፍየል በላ። ያ ለፈሪነት
ምሳሌ የምንጠቀምበት የጅብ አውሬ፣ ሰውን በቀን፣ በጠራራ ፀሓይ ማጥቃት ጀመረ።…” ከጉሬዛ ማሪያም እስከ አዲስ አበባ: የህይወት ጉዞ እና ትዝታዬ” በሚለው መፀሃፋቸው ገጽ 294

ይሄ የሚያሳየው ስነ ምህዳሩን እንዴት ሊያፋልሰው እንደሚችል ነው። ለጅብ የሚገባውን ሰው ካቀላጠፈው ሰው በጅብ የመበላቱ እድል እየሰፋ ይሄዳል። ከህገ መንግስቱ ላይ አንቀጽ 27 የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነጻነት በሚመለከተው ቁጥር 1 ላይ “ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የሕሊና እና የሃይማኖት ነጻነት አለው፡፡

ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል፣ ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን ያካትታል” ከዚህ ቀጥሎ ቁጥር 5 ላይ “ሃይማኖትና እምነትን የመግለጽ መብት ሊገደብ የሚችለው የሕዝብን ደህንነት፣ ሰላምን፣ ጤናን፣ ትምህርትን፣ የሕዝብን የሞራል ሁኔታ፣ የሌሎች ዜችን መሰረታዊ መብቶች፣ ነጻነቶች እና መንግስት ከሃይማኖት ነጻ መሆኑን ለማረጋረገጥ በሚወጡ ሕጐች ይሆናል” ይላል።

ይህ ማለት ‘ቻይኖች አህያ ማረድ እምነታቸው ነው’ ብለን ብንወስድ፣ ቬትናሞች ደግሞ የአህያን ስጋ መብላት ባህላቸው ቢሆንም፣ ወደ እኛ ሃገር ስናመጣው ግን በቁጥር 5 የተገለፀውን የህዝቡን ሞራል ስነ-ልቦና ስለሚጎዳ ኢትዮጲያ ውስጥ ተግባራዊ መደረግ የለበትም። በእርግጥ ጉዳዩ በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ አንቀጽ 845 ላይ የህዝብን ሞራል የሚቃረኑ ድርጊቶች ተብሎ ተቀምጧል። በዚህ መሰረት በኢትዮጵያ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህልና ወግ ብሎም በሁሉም የሀገሪቱ ሃይማኖቶች ውስጥ የአህያ ስጋን መብላት ኢ-ሞራላዊ ድርጊት እና በህበረተሰቡ ተቀባይነት ስለሌለው ሊቆም ይገባል። በመሆኑም አዋጁ ሊተገበር እና ቅጣቱ ሊጣል ግድ ይላል።

ከአርሶ አደሩ አንፃር በሃገራችን እንደ አህያ ያገለገለ የለም ማለት ይቻላል፡፡ በርካታ ኪሎሜትሮችን ጭነትን ለማመላለስ ሲያገለግሉ ኖረዋል። ባደጉት ሃገራት ከመኪና መንገድ መሟላት እና መኪና እንደ ልብ መኖር ጋር ተያይዞ እንስሳትን ለመጓጓዣነት መጠቀም እየቀረ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። መኪና ብርቅ በሆነባት የእኛ ሃገር ግን አህዮች ባለውለታዎቻችን ናቸው። ሌላው ቀርቶ እስከ 30 ኪሎሜትር ተጉዘው አዲስ አበባ የአርሶ አደሩን ምርት የሚያመላልሱት አህዮች ናቸው። ሰብሉን ከማሳ ወደ አውድማ የሚያመላልሰው፣ አውድማ የተወቃውን እህል ወደ ጎተራ የሚያስገባው፣ የከብቶች መኖ የሚያመላልሰው፣ ውሃ የሚቀዳው፣ ያመረተውን ወደ ገበያ የሚያደርሰው በአህያ ነው። ስለዚህ፣ አህዮች ለአርሶ አደሩ የደም ስር ናቸው።

ይህ የአህያ ቄራ ገበያውን ተቆጣጥሮ እህዮችን ማረድ ሲጀምር (300 አህዮች ለሙከራ ታረደዋል) አንደኛ አርሶ አደሩ ተወዳድሮ የደም ስሩ የሆኑትን አህዮች በውድ ዋጋ መግዛት አይችልም። በዚህም ቀውስ ውስጥ ይገባል። ሻንዶንግ ዶንግ የተሰኘዉ የቻይና ኩባንያ ቢሾፍቱ ከተማ ላይ ከትሞ በቀን 200 አህያዎችን አርዶ ለቻይናና ለቬትናም ለዉጭ ገበያ ለማቅረብ እየተዘጋጀ ነው ተብሏል። በአመት 72 ሺ አህዮች ጥቅም ላይ ይውላሉ ማለት ነው። አርሶ አድሩ በአመት ይህንን ያክል ኪሳራ ይደርስበታል። በዚያ ላይ አህዮች በአመት አንድ ግዜ ነው የሚወልዱት። ኢትዮጵያ ካሏት ጠቅላላ አህዮች ውስጥ ሴቶቹ ምን ያክል ይሆናሉ የሚለውም ሌላ ጥያቄ ነው።

በዚህ ሁኔታ የአርሶ አደሩ የደም ስር የሆነው አህያ ከጥቂት አመታት በኋላ “ነበር” ለማለት “ሙዚየም ካልተቀመጠ” ሊባል ይችላል። ይሄ እጅግ አሳሳቢ ነው። አርሶ አደሩን ከመግደል አይተናነስም። ኒጀር እና ቡርኪና ፋሶ ይሄ ችግር ገጥሟቸዋል። በኒጀር በ 2016 ብቻ 80 ሺ አህዮች ወደ ቻይና ተሸጠዋል። በቡርኪና ፋሶ ደግሞ በዚሁ አመት 18 ሺ አህዮች ወደ ቻይና ተሸጠዋል። በቡርኪና ፋሶ የአንድ አህያ ዋጋ ከ 34 ዶላር ወደ 147 ዶላር ተመንድጏል። ሃገራቱ የአህያ ቁጥራቸው መመናመን ሲያሰጋቸው አሁን ወደ እገዳ ገብተዋል። ቢሆንም ግን እነሱ አህዮቹን በቁማቸው ነው የሸጡት።

በሌላ በኩል፣ ከሆቴል መስክ ሆቴሎች የደንበኞቻቸው ትልቁ አቅርቦት ከስጋ የሚሰሩ ምግቦች ናቸው። የአቅም ጉዳይ እንጂ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አፍቃርየ ቁርጥ ነው። ባይበላ እንኳ በሉከንዳ ሰፈር ሲያልፍ ምራቁ ጢቅ እስኪል ድረስ ጎምዥቶ ማለፉ አይቀርም። ነገር ግን የአህያ እርድን ተከትሎ የሚመጣው መጥፎ አስተሳሰብ ሆቴል መብላትንም ሆነ ስጋ ቤት ቁርጥ መብላትን ይጠየፋል። 

ባህል እና እምነት እንዲህ እየተሸረሸሩ እያየ የማይጠረጥርበት ምክንያት አይኖርም። ስለዚህ ህዝቡ የራሱን አማራጭ ይወስዳል። ከስጋ ቤቶች ስጋ መግዛት ይተውና ድሮ የለመደውን ቅርጫ አማራጭ የሌለው ምርጫ ያደርጋል። ሆቴል ቤት ገብቶ መብላት ይፈራና ወንደላጤው ሳይቀር ቤቱ ዳቦ በሻይ በልቶ ማደርን ሊመርጥ ይችላል። ሆቴሎች እና ሉካንዳ ቤቶች ይከስራሉ። ለመንግስት የሚከፍሉትን ግብር መክፈል የማይችሉበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ። መንግስት የውጭ ምንዛሬ ያመጣልኛል ብሎ ተስፋ ያደረገው የአህያ ቄራ በሆቴል ዘርፍ ያለውን አገልግሎት ሰጪ ያከስረውና ሌላ የኢኮኖሚ ቀውስ ይፈጥራል። ታዲያ ከዚህ ሁሉ እኛም ክብራችንን ይዘን ብንቀመጥስ?

ከአንዳንድ ጥያቄዎች “በሬ፣ በግ እና ፍየል ያለርህራሄ ስንጨፈጭፍ ኖረን አህያ ሲባል እንዴት ከፋን?” የሚል ነው፡፡ በሌላ በኩል፣ “ገንዘብ ካገኝነበት ዶለር እስካመጣ ድረስ ችግሩ ምንድነው?” የሚሉም ወገኖች አሉ። ሁኔታው የሚገናኘው ከነፍስ ማጥፋት ጋር አያደለም። ከቅዱስነት እና ከእርኩስነት ጋር ነው፣ ከእምነትና ከባህል ጋር ነው፣ ከግብረገብነትና ከወግ ጋር ነው፡፡ ነገሩን ከነፍስ ማጥፋት ጋር ብቻ ካገናኘንው “ሰውም እንስሳ ስለሆነ በሬ የሚያርድ ሰው ሁሉ ሰው ቢያርድ ምን ችግር አለው” አይነት ቀሽም ጥያቄ ያመጣብናል። ገንዘብም (ዶላር) ጣፍጦ የሚበላው ባህል፣ እምነትና ወጋችንን ጠብቆ ሲሆን ነው።

በእርግጥ መንግስት አህያን አርዶ ስጋውን ለቬትነም ቆዳውን ደግሞ ለቻይና ወደ ውጭ ለመላክ ያቀደውን ድርጅት ፍቃዱን የሰጠው ይህንን የሚከለክለው አዋጅ ከማፅደቁ ቀድም ብሎ መሆኑ ተገልፁዋል። ከአዋጁ በፊት ግን እምነታችን እና ባህላችን ይህንን ይከለክላል። ስለዚህ እምነትና ባህላችን ይከበርልን። የማህበረሰብ እምነትና ባህል ካልተከበረ ህዝቡ በጉልበት አክብሩልኝ ይላል። ጉልበት ደግሞ አደገኛ ነው። ቸር ያሰማን!!


Addis Mekonnen is a news caster at Ethiopian Broadcast Corporation National Radio service. He was born in Debre Berhan and studied Ethiopian language(s) and literature at Debre Markos University. Addis also blogs at: http://kemekemkemekem.blogspot.com You can reach him via his email address: addismekonen@yahoo.com