አምባገነን መንግስት ከጦርነት በላይ ጦማሪን ይፈራል!

በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ መንግስት የሕዝቡን የለውጥ ፍላጎት በጉልበት ከማፈን ይልቅ ሥራና አሰራሩን እየቀየረና እያሻሻለ ይሄዳል። በተቃራኒው፣ አምባገነናዊ የመንግስት ሥራና አሰራሩን የሚቀይረው በሕዝብ ፍላጎት ሳይሆን በመሪዎቹ ትዕዛዝ ነው። ስለዚህ፣ ሁሉም ነገር በመሪዎቹ ሃሳብና ፍቃድ መሰረት ይሆናል። ይህ ደግሞ የሀገርና የሕዝብን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በሙሉ መቆጣጠር ይጠይቃል።

አምባገነኖች ከሕዝቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ጥያቄ እንዳይነሳ የሕዝብን አፍና ጆሮ ለመቆጣጠር ይሻሉ። ይሁን እን፣ ምንም ያህል ብዙ የፀጥታና የደህንነት ሰራተኞች ቀጥረው ቢያሰማሩ፣ ሚሊዮኖች የሚናገሩትንና የሚሰሙትን መቆጣጠር አይችሉም። በሁሉም ቦታና ግዜ ተገኝተው የሕዝቡን አፍና ጆሮ በቀጥታ መቆጣጠር ስለማይችሉ ሌላ ዘዴ ይጠቀማሉ። ይህ የሕዝብን አፍና ጆሮ ለመቆጣጠር የሚጠቀሙበት ዘዴ ፍርሃት ነው። ስለዚህ፣ “ፍርሃት” የአምባገነን መንግስታት መርህና መመሪያ ነው።

ከላይ እንደተገለፀው የአምባገነን መንግስታት ፍርሃት መሰረቱ ሁሉንም ነገር የመቆጣጠር ፍላጎት ነው። ነገር ግን፣ ነፃነት ደግሞ ከአምባገነኖች መርህና መመሪያ ጋር ፍፁም ተቃራኒ ነው። ነፃነት ማለት በራስ ፍላጎትና ምርጫ መሰረት መንቀሳቀስ መቻል ነው። አንድ ሰው በራሱ ፍላጎትና ምርጫ መሰረት የሚንቀሳቀስ ከሆነ ሌሎች ሰዎች የእንቅስቃሴውን አቅጣጫ በቀላሉ መገመትና መድረሻውን ማወቅ ይሳናቸዋል። በተለይ የእያንዳንዱን ሰው እንቅስቃሴ መቆጣጠር ለሚሹት አምባገነኖች ከቁጥጥራቸው ውጪ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ለፍርሃትና ስጋት ይዳርጋቸዋል።

ከምንም በላይ በተለያዩ መድረኮች የሕዝቡን ጥያቄ የሚያንፀባርቁ ሰዎች ደግሞ ለአምባገነን መንግስት ሁሌም ስጋት ናቸው። ምክንያቱም፣ የእነዚህ ግለሰቦች ተግባር አብዛኛውን የሕብረተሰብ ክፍል መብቱና ግዴታውን እንዲያውቅና እንዲጠይቅ ያደርገዋል። አንዳንድ የማህብረሰቡ አባላት የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥየቄ እንዲያነሱ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል። መንግስት ከሚሸሸው የሕዝብ ጥያቄ ጋር ያጋፍጠዋል። በዚህ ረገድ ከአምባገነናዊ መንግስት ጋር ዘወትር አይና-ናጫ የሆኑትን ጦማሪያንና ጋዜጠኞች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።

የኢህአዴግ መንግስት በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ሃሳብና አስተያየታቸውን በነፃነት የሚገልፁ ጦማሪያንንና ጋዜጠኞችን በአይነ-ቁራኛ ነው የሚመለከታቸው። አብዛኞቹን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የኒዮ-ሊብራሊስቶች ዕርዮተ-አለም አራማጆች፣ የፀረ-ሰላም ኃይሎች አጀንዳ አስፈፃሚዎች፣ የአሸባሪ ድርጅቶች ተላላኪዎች፣ …ወዘተ እያለ በጅምላ ይፈርጃቸዋል፣ ህዝብን ለአመፅና ረብሻ አነሳስታችኋል በሚል ይወነጅላቸዋል።

በተለይ በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ የተለየ አመለካከት ያላቸውና ሃሳባቸውን በነፃነት ከሚገልፁ ጦማሪያንና ጋዜጠኞች ውስጥ አብዛኞቹ ለተደጋጋሚ እስር ተዳርገዋል፣ የስቃይ ምርመራ ተፈፅሞባቸዋል። በዚህ ምክንያት ገሚሶቹ ከሀገር ተሰደው ከዚያ ሆነው ያቀነቅናሉ። ሀገር ውስጥ የቀሩት ደግሞ ዘወትር እየታሰሩና እየተሰቃዩ ሃሳባቸውን በነፃነት ይገልፃሉ። የኢህአዴግ መንግስት እነዚህን ሰዎች በተደጋጋሚ የሚያስራቸውና የሚያሰቃያቸው ለምድነው? እነሱስ አንዴ ከታሰሩና ከተሰቃዩ በኋላ “አርፈው የማይቀመጡት” ለምንድነው?

በቅድሚያ “የአምባገነን መንግስት በደልና ጭቆና ሳይበግራቸው ሃሳብና አስተያየታቸውን በነፃነት የሚገልፁ ጦማሪያንና ጋዜጠኞች የሚከተሉት የህይወት መርህና መመሪያ ምንድነው?” የሚለውን እንመልከት። ለዚህ ደግሞ ከአንድ ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ ከአራት ጦማሪያን ጋር በነበረኝ ቆይታ የታዘብኩትን ላካፍላችሁ።

ከሦስቱ ጦማሪያን ጋር በአካል ስንገናጅ ለመጀመሪያ ግዜ ነው። ነገር ግን፣ ከተቀጣጠርንበት ካፌ ስንገናኝ “ሃይ…ሰላም ነው!” ከሚል ሰላምታ በኋላ ወዲያው በሳቅ የተሞላ ጨዋታ ጀመርን። አንድ ከጎናችን ብቻውን ተቀምጦ ሞባይሉን ሲጎረጉር የነበረ ሰውዬ ትላንት ማታ አብረው ስንጫወት አምሽተን ልክ ለዛሬ ያሳደርነውን ጨዋታ የጀመርን ሳይመስለው አይቀርም ሞባይሉን መጎርጎር ትቶ ትክ ብሎ ይመለከተን ጀመር። ከሁለት ሰዓት በኋላ ስንለያይም ደግሞ ልክ ነገ እንደሚገናኙ ሰዎች “በቃ መሄዴ ነው!” እየተባባልን ወደየፊናችን ሄድን።

በአካል መገናኘታችን ሆነ መለያየታችን ምንም የተለየ ስሜት አልፈጠረብንም። ምክንያቱም፣ ትላንትም ሆነ ወደፊት በመካከላችን ጠንካራ የአብሮነት ስሜት አለ። ይህ የአብሮነት ስሜት ደግሞ በዝምድና፣ ትውውቅ ወይም ጥቅም ላይ የተመሰረተ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ በሁላችንም ውስጥ ካለ የነፃነት መንፈስ የመነጨ ነው። በውስጣችን ስላለው የነፃነት መንፈስ ለመግለፅ በጨዋታ መሃል አንዱ ጓደኛችን ለሰነዘረው ሃሳብ የሰጠንውን ምላሽ እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል።

ጓደኛችን “እንደ እኔ የተደራጀ የፖለቲካ ኃይል እስከሌለ ድረስ ይሄ አምባገነናዊ ሥርዓት በፅሁፍና በመናገር መቼም አይወድቅም” ነበር ያለው። እኔም ከአፉ ቀበል አድርጌ “ወዳጄ…ይሄ ስርዓት መቀየር ምናምን የምትሉትን እዛው! እኔ የምፅፈውም ሆነ የምታገለው በመጀመሪያ ራሴን ነፃ ለማውጣት ነው” አልኩት። ሌላኛው ደግሞ “ለእኔም ነገሩ ፐርሰናል (የግል) ነው። እኔ የምፅፈው የራሴን ነፃነት ለማረጋገጥ ነው” አለው። ስለዚህ፣ አብዛኞቻችን በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ሃሳብና አስተያየት የምንገልጣ በቅድሚያ የራሳችንን ነፃነት ተግባራዊ ለማድረግ እንጂ የብዙሃኑን መብትና ነፃነት ለማረጋገጥ በሚል አይደለም።

በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 29 ላይ የተጠቀሰውን የአመለካከትና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ወስደን እንመልከት። በዚህ አንቀፅ አንደኛ ቁጥር ላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ “ማንኛውም ሰው ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት የመያዝና ሃሳቡን በነፃነት የመግለጽ መብት አለው”። ስለዚህ፣ ማንኛውም ሰው የራሱን አመለካከት የመያዝና ሃሳብ በነፃነት የመግለጽ መብት አለው። ነገር ግን፣ የእኔ አመለካከትና ሃሳብ ስለ እኔ ብቻ ሊሆን አይችልም። በአከባቢ፣ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ኩነቶች ላይ የራሴ የሆነ አመለካከት የሚኖረኝ ሲሆን ሃሳቤንም ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የመግለፅ መብት አለኝ።

ለምሳሌ፣ “እኔ በምኖርበት አከባቢ የሚኖሩ ሰዎች መብትና ነፃነት አልተከበረም” የሚል አመለካከት ሊኖረኝ ይችላል። ምንም እንኳን በእኔ ላይ የደረሰ በደልና አድልዎ ባይኖርም፣ በሌሎች ላይ እየደረሰ ስላለው በደልና አድልዎ የራሴን አመለካከት መያዝና ሃሳቤን በነፃነት የመግለጽ መብት አለኝ። “የእነዚህ ሰዎች መብትና ነፃነት አልተከበረም” በሚል በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ሃሳብና አስተያየት እሰጣለሁ። ነገር ግን፣ ስለ ሌሎች ሰዎች መብትና ነፃነት የመሰለኝን አመለካከት እንዳልይዝ፣ ሃሳቤንም በነፃነት እንዳልገልፅ ከተደረግኩ፣ ከማንም በፊት የተነካው የእኔ መብት ነው።

በሌሎች ሰዎች ለይ የደረሰው የመብት ጥሰት እንዳለ ሆኖ፣ ከእነሱ በፊት የእኔ የመሰለኝን አመለካከት የመያዝና ሃሳቤን የመግለፅ መብት ተገፍፏል። ስለዚህ፣ ከማንም በፊት የራሴን ዴሞክራሲያዊ መብት ለማስከበር እንቀሳቀሳለሁ። በዚህ መሰረት፣ ስለ ሰዎች መብትና ነፃነት መከበር በነፃነት መናገርና መፃፍ ለሌሎች ውለታ፣ ለራስ ግን ግዴታ ነው። ሃሳብን በነፃነት በመግለፅ በቅድሚያ የሚያረጋግጡት በአንቀፅ 29 ላይ የተደነገገውን ዴሞክራሲያዊ መብት ነው። ለዚህ ነው፣ “ከማንም በፊት ቅድሚያ የምሰጠው የራሴን ነፃነት ነው” ያልኩት። በአጠቃላይ፣ ሁሉም ሰው የመሰለውን አመለካከት መያዝና ሃሳቡን በነፃነት መግለፅ እስካልቻለ ድረስ የእኔም መብትና ነፃነት ሊረጋገጥ አይችልም።

ከላይ አንደተገለፀው፣ እኛ ሳንገናኝ ያወዳጀን፣ ሳንነጋገር ያግባባን በሁላችንም ውስጥ ያለው የነፃነት መንፈስ ነው። በተቃራኒው፣ አምባገነን መንግስታት ከምንም በላይ የሚጠሉት ነገር እንዲህ ያለውን የነፃነት መንፈስ ነው። እንደ ኢህአዴግ ያሉ መንግስታት ሳያውቁን የሚጠሉን፣ ሳናጠፋ የሚፈርዱብን እኛ የምንመራበት የነፃነት መርህ ከእነሱ የፍርሃት መርህ ፍፁም ተቃራኒ ስለሆነ ነው። በነፃነት የሚንቀሳቀሱ፣ የሚያስቡና የሚናገሩ ሰዎች ቀስ-በቀስ ሕዝብና ሀገርን ከፍርሃት ቆፍን ያላቅቃሉ። በመሆኑም፣ እያንዳንዷ የሚፅፏትና የሚናገሯት ቃል ለአምባገነኖች ከፍተኛ አመፅና ብጥብጥ የሚያስነሳ ይመስላቸዋል። ስለዚህ፣ አምባገነን መንግስት ከጦርነት በላይ ጦማሪን ይፈራል!