የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት እና የማዕድን ቦታ ውዝግብ  

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ተግባራዊ ማድረግ የጀመረውን “የኢኮኖሚ አብዮት” አስመልክቶ ባወጣናቸው ፅሁፎች ከዕቅዱ መነሻ ሃሳብ እስከ አተገባበር ሂደቱ መሰረታዊ ችግር እንዳለበት ለመግለፅ ሞክረናል። በመጀመሪያው ፅሁፍ ክልላዊ መስተዳደሩ ከሕዝቡ የተነሱትን ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ችግሮች ከኢኮኖሚ አንፃር ብቻ በማየት መፍትሄ ለመስጠት የሚያደርገው ጥረት ስህተትን በሌላ ስህተት ለማረም መሞከር እንደሆነ ገልፀናል። በቀጣይ ፅሁፍ ደግሞ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ተግባራዊ መደረግ የጀመረው የኢኮኖሚ ዕቅድ ከሀገሪቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አንፃር ተገቢነት እንደሌለው፣ እንዲሁም በተለይ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በውጪ ንግዱ ረገድ እየታየ ያለውን ማሽቆልቆል ለመግታት እንደማያስችል በዝርዝር ተገልጿል።

ሆኖም ግን፣ የሁለቱም ክልል መስተዳደሮች ችግሩን በድጋሜ ለማጤንና አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ዕቅዱን ተግባራዊ ማድረግ ቀጥለዋል። የኦሮሚያ ኢኮኖሚ አብዮት አተገባበር ሂደት በተለይ የሲሚንቶ ጥሬ ዕቃ አቅርቦት ዘርፍ ከተሰማሩ ድርጅቶችና ባለሃብቶች ጋር ወደ አላስፈላጊ ውዝግብ ውስጥ አስገብቶታል። ሰሞኑን የክልሉ መንግስት በዘርፉ ግንባር ቀደም ከሆኑት ደርባ ሲሚንቶ እና ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጋር የገጠመው አተካራ የዚሁ አካል ነው።

“የማዕድን ቦታ እንዲያስረክቡ የታዘዙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር በመደራደር ይዞታቸውን አስከበሩ” በሚል ርዕስ በቀረበው ዘገባ ለፋብሪካዎቹ የኢንቨስትመንት ቦታ አሰጣጥ ሂደቱ በጉዳዩ ዙሪያ የተቀመጠውን ህግና የአሰራር ደንብ የተከተለ አለመሆኑን በግልፅ ይጠቁማል። ምክንያቱም፣ የክልሉ መንግስት የተጠቀሱት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በይዞታቸው ስር ያልነበረን የማዕድን ቦታ እስካሁን ድረስ እንዲጠቀሙ ፈቅዷል ወይም ደግሞ በኢንቨስትመንት የተሰጣቸውን ይዞታ ያለ አግባብ እንዲያስረክቡ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

የክልሉ መንግስት የማዕድን ቦታው ለፋብሪካዎቹ አስረክቦ ከነበረ ዛሬ ላይ ድንገት ተነስቶ “አስረክቡ” ማለት አይችልም፡፡ ፋብሪካዎቹ እስካሁን ድረስ ከክልሉ መንግስት ሳይረከቡ ማዕድኑን ሲጠቀሙ ከነበረ ያለ አግባብ ለተጠቀሙበት ተገቢውን ካሣ ማስከፈል እንጂ ሲጀመር ያልተሰጣቸውን ቦታ “እንዲያስረክቡ” መጠየቅ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚታየው ውዝግብ የክልሉ መንግስት የማዕድን ቦታውን እንዲያስረክቡ ትዕዛዝ ከማስተላለፉ በፊት “እንደ መንግስት” ከፋብሪካዎቹና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር አስፈላጊውን ውይይትና ምክክር አለማድረጉን ያሳያል። በአጠቃላይ፣ የችግሩ ዋና መንስዔ ግልፅነትና ተጠያቂነት የጎደለው የፌደራልና የክልሉ መንግስት ሥራና አሰራር ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።

የሪፖርተር ጋዜጣ የደርባ ሲሚንቶ ዋና ስራ አስኪያጅን ጠቅሶ ያቀረበው ዘገባ እና የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በፌስቡክ ገፃቸው የሰጡትን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበናል።

“የኦሮሚያ ክልል በጀመረው ‹‹የኢኮኖሚ አብዮት›› ምክንያት ለጥሬ ዕቃ ማውጫ የሚገለገሉባቸውን የማዕድን ሥፍራዎች እንዲያስረክቡ የታዘዙት ግዙፍ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች፣ ከክልሉ መንግሥት ጋር ባካሄዱት ረዥም ጊዜ የወሰደ ድርድር ተጨማሪ ገንዘብ በመክፈል ይዞታቸውን አስከበሩ፡፡

በአዲስ አበባ ዙሪያ 90 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ የሚገኙትንና የአገሪቱን የሲሚንቶ ገበያ በውድድር ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ማድረግ የቻሉት ደርባ፣ ዳንጎቴና ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ባካሄዱት ድርድር የጥሬ ዕቃ ማውጫ የማዕድን ሥፍራቸውን ማስጠበቅ ችለዋል፡፡

ኩባንያዎቹ በተናጠል ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋር ባካሄዱት ድርድር በአንድ ሜትር ኪዩብ ፑሚስ 20 ብር ለመክፈል በመስማማት፣ ከቁጥጥራቸው ውጪ ሊሆኑ የነበሩትን የማዕድን ሥፍራዎች ዳግም በይዞታቸው ሥር እንዲሆኑ ማድረጋቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ምንጮች ጨምረው እንደገለጹት የእነዚህ ግዙፍ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የጥሬ ዕቃ አቅርቦት መዛነፍ ስለሌለበትና ጥራቱም የተጠበ ሆኖ እንዲቀጥል፣ ዋጋውም ከዋዠቀ ውድድሩን አስቸጋሪ ስለሚያደርገው ከይዞታቸው መውጣት እንደሌለባቸው ፋብሪካዎቹ ከክልሉ ጋር ምክክር በማድረግ ስምምነት ላይ መድረስ መቻላቸው ታውቋል፡፡

የደርባ ሚድሮክ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሌ አሰግዴ፣ ‹‹እኛ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በተነደፈው የሥራ ዕድል ፈጠራ የመፍትሔው አካል መሆን እንፈልጋለን፡፡ ስለዚህ በአንድ ሜትር ኪዩብ ተጨማሪ ክፍያ ለመፈጸም ተስማምተናል፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ግዙፍ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የገነቡት ደርባና ዳንጎቴ፣ እንዲሁም ከነባሩ በተጨማሪ ሰፊ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች የገነባው ሙገር ሲሚንቶ የአገሪቱን የሲሚንቶ ገበያ ድርሻ በበላይነት ይመራሉ፡፡

ነገር ግን ለመክፈል በተስማሙት አዲስ የጥሬ ዕቃ ክፍያ የማምረቻ ወጪያቸው ላይ ችግር ስለሚኖረው፣ የዋጋ ጭማሪ ሊያስከትል እንደሚችል ባለሙያዎች ይገምታሉ፡፡

አቶ ኃይሌ እንዳሉት ግን፣ በአሁኑ ወቅት ምንም የታሰበ የሲሚንቶ ዋጋ ጭማሪ አይኖርም፡፡ የማምረቻ ዋጋ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለማወቅ የተወሰነ ጊዜ ይወስዳል ብለዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኘው የሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር ያስገነባው ፋብሪካ፣ ሚያዝያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ተመርቆ ወደ ገበያ እንደሚገባ ቀን ተቆርጧል፡፡

ለኢትዮጵያ የአክሲዮን ገበያ ፈር የቀደደውና ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ የቻለው ሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር፣ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያዎች ከሆኑት ፒፒሲና አይአይዲ ጋር እኩል 50 በመቶ ድርሻ በመያዝ የሲሚንቶ ፋብሪካውን ግንባታ አጠናቋል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለዚህ ፕሮጀክት 945 ሚሊዮን ብር ብድር አቅርቧል፡፡ ሐበሻ ሲሚንቶ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር በዓመት 1.4 ሚሊዮን ቶን የማመረት አቅም ሲኖረው፣ ማምረት የሚጀምረው የአቅሙን 83 በመቶ ያህል ነው ተብሏል፡፡

ይህ ፋብሪካ ወደ ምርት የሚገባው የኦሮሚያ ክልል የ‹‹ኢኮኖሚ አብዮት›› ከጀመረ በኋላ እንደመሆኑ፣ ክልላዊ መንግሥቱ ባስቀመጠው መንገድ መሄድን መርጧል፡፡

የሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን አቢ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት ፑሚስ የጥሬ ዕቃ ማምረቻ ቦታ ለማግኘት ተንቀሳቅሶ ነበር፡፡ ነገር ግን ለተነሽዎች ካሳ ባለመክፈሉ ቦታውን መረከብ ባለመቻሉ፣ የኦሮሚያ ክልል አዲስ አሠራር ማምጣቱን አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡

‹‹ሐበሻ ሲሚንቶ ለወጣቶች ከተሰጠው ማምረቻ ጥሬ ዕቃ በመረከብ ወደ ምርት ይገባል፤›› ሲሉ አቶ መስፍን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በተገኙበት የሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ እንደሚመረቅ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡


ምንጭ፦ ሪፖርተር (14 Apr, 2017 By ውድነህ ዘነበ)

#Oromiyaa
“የማዕድኑ ጉዳይ”
—————
“የማዕድን ቦታ እንዲያስረክቡ የታዘዙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከኦሮሚያ ጋር በመደራደር ይዞታቸውን አስከበሩ” በሚል ሪፖርተር ጋዜጣ ሚያዚያ 6/2009 ይዞት የወጣዉ ዘገባ የተሳሳተ መሆኑን በመግለጽ፣ ጉዳዩን የበለጠ ግልጽ ለማድረግ ያህል ተጨማሪ ማብራሪያ እናቀርባለን፡፡
—-
ለሲሚንቶ ግብዓት ሚዉሉ የማዕድን ቦታዎችን በተመለከተ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሁለት መሰረታዊ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ አንደኛዉ እርምጃ የሲሚንቶ ማምረቻ ፋብሪካ ሳይኖራቸዉ የማዕድን ቦታዎችን በተለያየ መንገድ ይዘዉ ምንም እሴት ሳይጨምሩ አሸዋ እና ፑሚስ እያፈሱ ሲሸጡ የነበሩ “ባለሀብቶች” ላይ የተወሰደ እርምጃ ነዉ፡፡ እነዚህ “ባለሀብቶች” ከዚህ ዘርፍ እንዲወጡ ተደርጓል፡፡
—-
ሁለተኛዉ እርምጃ በክልላችን የሚገኙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በሲሚንቶ ምርት የዕሴት ሰንሰለት ለሲሚንቶ ግብዓት የሚዉለዉን የማዕድን ጥሬ ዕቃ ከማዉጣት ጀምሮ ያለዉን ሁሉንም ስራ ራሳቸዉ ኩባንያዎች ጠቅልለዉ ይሰሩ ስለነበረ፣ ከዕሴት ሰንሰለቱ ዉስጥ ማዕድን የማዉጣቱን ስራ ለተደራጁ ወጣቶች እንዲለቁ የማድረግ ነዉ፡፡ በዚህም መሰረት ከሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ ባለሀብቶችና የማኔጅመንት አካላት ጋር በተደረገ ዉይይት የሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ ከዕሴት ሰንሰለቱ ዉስጥ ጥሬ ዕቃን የማቅረብ ጉዳይ ለወጣቶቹ በመልቀቅ የስራ ዕድል እንዲፈጠርላቸዉ በመስማማት፣ ወጣቶቹ የሚያመርቱተን ጥሬ ዕቃም ገዝተዉ ለመጠቀም ተስማምተዉ በይፋ ዉል ተፈራርመዉ ወደ ተግባር ገብተዋል፡፡ በዉላቸዉ መሰረትም መገበያየት ጀምረዋል፡፡
—-
ከሲሚንቶ ጥሬ ዕቃ ግብዓት አቅርቦት አንጻር የተወሰዱት ዕርምጃዎች ሶስት መሰረታዊ ዓላማዎች አላቸዉ፡፡ አንደኛዉ ለሲሚንቶ አምራች ኩባንያዎች አስተማማኝ እና ዘላቂነት ያለዉ ግብዓት እንዲያገኙ በማስቻል ምርታማነታቸዉ እንዲያድግ ማገዝ ነዉ፡፡ ሁለተኛዉ መሰረታዊ ዓላማ በሲሚንቶ የዕሴት ሰንሰለት በግብዓት አቅርቦት የወጣቶቻችንን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነዉ፡፡ ሶስተኛዉ ትልቅ ካፒታል እና ዕዉቀት ያላቸዉ “ባለሀብቶች” ምንም ዕሴት ሳይጨምሩ አሸዋ እና ፑሚስ አፍሰዉ እየሸጡ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ዉስጥ ከአቅም በታች ከመተወን ይልቅ ከዚህ ዘርፍ ወጥተዉ ዕሴት ወደሚጨምሩ እና ከአቅማቸዉ ጋር ተመጣጣኝ ወደ ሆኑ ዘርፎች እንዲሄዱ ታስቦ ነዉ፡፡
—-
በዚህም መሰረት የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ዉሳኔን ተከትሎ ከባለድሻ አካላት ጋር ስምምነት ተደርሶ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡ በዘርፉ የተደራጁ ወጣቶች ለሲሚንቶ ግብዓት የሚሆኑ ማዕድናትን አምርተዉ ለፋብሪካዎቹ በመሸጥ ላይ ይገኛሉ፡፡የሲሚንቶ ፋብሪካዎቹም ከወጣቶቹ ጋር በገቡት ስምምነት መሰረት የሲሚንቶ ማምረቻ የማዕድን ግብዓቶችን ከወጣቶች ገዝተዉ እየተጠቀሙ ነዉ፡፡

ከዚህ ዉጭ ሪፖርተር ጋዜጣ ያወጣዉ ዘገባ መሰረተ ቢስ ነዉ፡፡ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከላይ ከተጠቀሰዉ ዉሳኔ እና ስምምነት በኋላ ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጋር ምንም አይነት ድርድር አላደረገም፡፡ ከአሁን በኋላም ወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራን ወደኋላ ሊመልስ የሚችል ድርድርም አያደርግም፡፡
—-
ይህ ጉዳይ ተግባራዊ በመደረጉ ጥቅማቸዉ የሚነካባቸዉ አካላት እንደሚኖሩ በጣም ግልጽ ነዉ፡፡ ጥቅማቸዉ ተነካባቸዉ ግለሰቦች የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ እና ከዛም ያለፈ ነገር ለማድረግ መሞከራቸዉ አይቀርም፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የወጣዉ ዘገባም የዚህ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አካል እንደሆነ ይሰማናል፡፡ ዘገባዉ እዉነት እና ሚዛናዊ ከሆነ የኦሮሚያ ክልል መንግስትን ወክሎ ማን መቼ በዚህ ጉዳይ እንደተደራደረ ሊገልጽልን ይገባል፡፡ መንግስትን ወክሎ ተደራድሯል የተባለ የመንግስት የስራ ኃላፊ አስተያየትም መካተት አለበት፡፡ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በኩል ተደረገ ስለተባለዉ ድርድር አስተያየት የሠጠ የስራ ኃላፊ ከሌለ ግን ዘገባዊ ግምታዊ እና የጸሐፊዉ ምኞት ብቻ ነዉ ማለት ነዉ፡፡ ስለሆነም ሪፖርተር ጋዜጣ ዘገባዉን በማስተባበል የክልሉን መንግስት በይፋ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርበታል ብለን እናምናለን፡፡ ይህን የማያደርግ ከሆነ ግን ትክከለኛ ያልሆነን መረጃ ለህዝብ በማሰራጨቱ በህግ ተጠያቂ ይሆናል ማለት ነዉ፡፡
—-
በማዕድን ዘርፍ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በበኩል እተደረገ ያለዉን እንቅስቃሴ ተግባራዊነት እና እየመጡ ያሉ ለዉጦችን በተመለከተ ተጨባጭ መሬት ላይ ያለዉን ሀቅ ተጠቃሚ ከሆኑ ወጣቶች አንደበት ህዝባችን እንዲሰማ እና እዉነታዉን እንዲገነዘብ ከነገ ጀምሮ በኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በዜና እና በፕሮግራም የምናቀርብ ይሆናል፡፡

ቸር እንሰንብት!”

ምንጭ፦ ፌስቡክ (17 Apr, 2017 By Addisu Arega Kitessa)