“መንጋ” በስሙ ሲጠሩት የሰደቡት ይመስለዋል! 

ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ዋና መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው የቴድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) አዲሱ ዘፈን እና እነ ቴድሮስ ፀጋዬ በሙዚቃው ላይ የሰጡት ሂስ ነው። የቴዲ አፍሮን “ኢትዮጲያ” የሚለውን ዘፈን በተደጋጋሚ አዳምጬዋለሁ። የ”ርዕዮት ኪን” አዘጋጆችም በዘፈኑ ላይ የሰላ ትችት ከሰጡ በኋላ “በድምፀታችን፥ በአቀራረብ ጉድለት እና በቃላት ምርጫችን ያዘናችሁ ታዳሚዎቻችንን በይፋ ይቅርታ እንጠይቃለን” ብለዋል

ከይቅርታው በኋላ ደግሞ አንዱ ወዳጄ በፌስቡክ ገፁ ላይ እንዲህ ብሎ ለጥፏል፡- “የናቁን ያከብሩናል “መንጋ” ያሉንም ይቅርታ ይጠይቁናል። ምንም እንኳን ይቅርታው ዙሪያ ጥምጥም ቢሆንም እኛ የቴዲ አፍሮ አድናቂዎች ግን እንዲህ ነን እወቁት!” በፕሮግራሙ አዘጋጆች ላይ የቀረበው ቅሬታ በዋናነት የዘፈኑ ወይም/እና የዘፋኙ አድናቂዎችን “መንጋ” ብለው “ተሳድበዋል” የሚል ነው።

Tewodros Tsegaye

​“መንጋ” የሚለው ቃል ፍቺ “በአንድነት የተሰበሰበ ከብት፣ ብዙ፥ አያሌ” የሚል ነው። እነ ቴድሮስ ፀጋዬ “ኢትዮጲያ” የሚለው ዘፍን አድናቂዎችን “መንጋ” ሲሉ “የከብት መንጋ” ለማለት እንዳልሆነ ግልፅ ነው። ከዚያ ይልቅ፣ “የመንጋ አስተሳሰብ” (Herd Mentality) የሚለውን ፅንሰ-ሃሳብ ለመግለፅ የፈለጉ ይመስለኛል። የመንጋ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ሁለት መሰረታዊ ባህሪያ አላቸው።
አንደኛ፡- የመንጋ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች በመርህ ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ወይም ወጥ የሆነ አቋም የላቸውም። አስተሳሰባቸው ከውስጣዊ ይልቅ በውጫዊ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ በአብዛኛው የሚመርጡትና የሚያደርጉት ነገር በራሳቸው የሚፈልጉትን ሳይሆን በሌሎች ሰዎች ዘንድ ተፈላጊ የሆነውን ነው። ስለዚህ፣ በውስጣቸው ከሚያስቡትና ከሚያውቁት እውነት ይልቅ ለሌሎች ሰዎች ሃሳብና አመለካከት ቅድሚያ ይሰጣሉ።

ሁለተኛ፡- የመንጋ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች የአንድን ሃሳብ ወይም አመለካከት ትክክለኝነት የሚመዝኑት በምክንያት ሳይሆን በብዛት ነው። የሃሳባቸውን ትክክለኝነት በምክንያታዊ አምክህንዮ አይመረምሩም። አመለካከታቸውም በተጨባጭ እውነት ላይ የተመሰረተ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ በብዙሃን ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሃሳብ ወይም ብዙዎች የሚያራምዱት አመለካከት “ትክክል” እንደሆነ ያስባሉ።

ከላይ በተጠቀሱት ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች የመንጋ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች የተለየ ሃሳብና አመለካከትን ለማስተናገድ ፍፁም ፍቃደኛ አይደሉም። ምክንያቱም፣ የራሳቸው የሆነ በመርህ ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ስለሌላቸው ከእነሱ የተለየ ሃሳብን ትክክለኝነት ለመመርመር የሚያስችል አቅም የላቸውም።

እውነትነቱን ሳይመረምሩ ተቀብለው በጭፍን የሚያራምዱት አመለካከት የሃሳብ ልዩነትን በጭራሽ አያስተናግድም። የተለየ ሃሳብ ሲመጣ በዕውቀት ላይ ያልተመሰረተ አመለካከት ይፈርሳል። በጭፍን ተቃውሞና ድጋፍ የሚመሩ ሰዎች በሃሳብ የበላይነት አያምኑም። ስለዚህ፣ ከእነሱ የተለየ ሃሳብ በተነሳ ቁጥር ያላቸው ብቸኛ አማራጭ ስድብና ጥላቻ ነው። በዚህም፣ የሃሳቡን ትክክለኝነት ወይም ስህተትነት በምክንያት ከማረጋገጥ ይልቅ የተናጋሪውን ክብርና ስብዕና በሚነካ መልኩ ይሳደባሉ፥ ያንጓጥጣሉ። በእርግጥ ስድብና ዘለፋ የዕውቀት እጥረት ውጤት፣ የመንጋ አስተሳሰብ መገለጫ ናቸው።

በመጨረሻም፣ የርዕዮት ኪን አዘጋጅ የሆነው ቴዎድሮስ ፀጋዬ “መንጋ” የሚለውን ቃል የተጠቀመበት አግባብ ከላይ በተገለፀው አውድ (context) መሰረት ነው? ይህን ለመመለስ ታዳሚዎቹን ይቅርታ ለመጠየቅ ካቀረበው ፅሁፍ ውስጥ የሚከተለውን እንመልከት፡-

“ኹሌም ቢኾን በርዕዮት አዘጋጆች ላይ የተሰነዘሩትን ዓይነት ክብረ ነክ፣ መጠንና መስመር የተላለፉ ዘለፋዎች ገንቢ ሚና እንደማይኖራቸው፤ ለተዋስዖ፣ ለነጻ ሐሳብ መንሸራሸር እና ለመሻል እንደማይረዱ አጥብቀን እናምናለን፡፡ በውይይት አደባባዮቻችን ላይ አንድ ወጥ ሰልፍ ብቻ ይኑር መባሉና መጨፍለቁ አግባብ እንዳይደለ፣ ይኽ አዝማሚያም ለአገርም ኾነ ለወገን ጠንቅ መኾኑን እንገነዘባለን፡፡ የዴሞክራሲን እና የነፃነትን እሴቶች እንደምንነታችን እና ማንነታችን መገለጫ አድርገን ከፍ ያለ ዋጋ እንሰጣቸዋለን። …ማንም የሚያምንበትን በምክንያት ተደግፎ እና በሰከነ መንገድ ለማቅረብ ጨርሶ ሊሸማቀቅ እንደማይገባው፤ ይኽም ሰው በመኾኑ የሚያገኘው ተፈጥሯዊ ሽልማት እንደኾነም እናምናለን፡፡”

የፕሮግራሙ አዘጋጆች የዘፈኑ ወይም የዘፋኙ አድናቂዎችን “መንጋ” ማለታቸው እንደ ስድብ ሊቆጠር ይችላልን? በመሰረቱ፣ አዘጋጆቹ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብታቸውንና የሙያ ክህሎታቸውን መሰረት በማድረግ ይህን የኪነ-ጥበብ ሥራ መተቸታቸው ለከፍተኛ ስድብና ዘለፋ ዳርጏቸዋል። ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ ክብረ ነክ የሆኑ፥ መጠንና መስመር ያለፉ ስድቦችና ዘለፋዎች የመንጋ አስተሳሰብ መገለጫዎች ናቸው። እነ ቴዎድሮስ ፀጋዬ “መንጋ” የሚለውን ቃል የተጠቀሙት “አካፋን ‘አካፋ’ ማለት ያስፈልጋል” በሚለው አግባብ ነው። በመሆኑም፣ “’መንጋ’ ተብዬ ተሰድቤያለሁ” የሚል ካለ “’መንጋ’ በስሙ ሲጠሩት የሰደቡት ይመስለዋል” ብሎ ከማለፍ ሌላ አማራጭ ያለ አይመስለኝም።

One thought on ““መንጋ” በስሙ ሲጠሩት የሰደቡት ይመስለዋል! 

  1. ስለ አንድ መዘዘኛ ብዙኃን የሚከፍሉት ዋጋ።
    ጽሑፍ ለመጻፍ ማንኛውም ሰው የተሰማውንና የሚሰማውን ማስነበብ ይችላል። ዋናው ቁም ነገሩ የጽሑፉ መሠረተ ሐሳብ ምንነት እንጂ፡ ታዲያ ለዛሬው የእኔ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ ከላይ የአንድ በማር የተለወሰ መርዛማ እባብ ግለሰብን ሀገራዊ በደል ለመሸፈንና ከአንገት በላይ የሆነውን የይቅርታ ጥያቄውን የማስመሰል ይቅርታነት ሊያሳየኝ የዳዳውን ጽሑፍ በማንበቤ ነው። በመግቢያዬ እንዳልኩት በመጽሐፍ መብት ላይ አንዳችም ቅሬታ የለኝም። ይሁን እንጂ በጽሑፉ መሠረተ መልእክትና ሀሳብ ዙሪያ ግን ብዙ ማለት ብችል በወደድኩኝ ሆኖም ባጭሩ ሀሳብን በሀሳብ ለመሟገት ጥቂት እላለሁ። ቅጥረኛ ፍርፋሪ ጠባቂ ሆኖ መናገርና በነጻነት ለነጻነት አልሞ መናገር በእጅጉ ሊቀራረቡ የማይችሉ የሁለት ዓለም አካላት የጉንጭ አልፋ ውይይት ሜዳ ነው የሚሆነው። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ተሳዳቢው ማነው ??? በሚል አርእስት ሥር ልትገነዘቡልኝ የሚገባ ሃሳቤን አቀርባለሁ። በመሠረቱ ይህ ሰው {ቴዎድሮስ ጸጋዬ} ማለት መዘዘኛ ነው። መዘዘኛ ማለት ተናግሮ አናጋሪ ተሳድቦ አሳዳቢ መርዘኛ ሰዎችን ዱላ የሚያማዝዝ ክፉ የሰይጣን መልእክተኛ ማለት ነው።{አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ መ ቃ 582ኛው ገጽ እንደ ተረጎመው። የርእዮት አቅራቢ የመዘዘኛነት ጠባይ በቴዎድሮስ ካሳሁን ላይ የሚጀምር ሳይሆን በእድሜም፥ በእውቀትም፥ በአስተሳሰብም ሆነ በኢትዮጵያዊነት የስነምግባር መለኪያ ፍጽሞ የሰማይ ያክል ከሚርቁት ከፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ወቅት ከተሸፈነበት ጭምብል ተጋልጦ በመውጣቱ ነው። ትንሽ ለማስታወስ ያክል ፈጽሞ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን የማይፈልግና፡ ያ፥ ለዘመናት የኖረውንም የመከባበርና በእድሜ ጋፕ፥ በእውቀት ስፋት የሚለካውን የትሕትና ሰብእና ከትውልዱ አይምሮ ጠራርጎ ለመጣል ባለመ የቃላት ውርጅብኝ ሽማግሌውን በአደባባይ በመሳደብ መሠረቱን የጣለ መዘዘኝነት ነው። ዛሬ አድጎ ጭራሽ በኢትዮጵያዊነታችን ላይ ዳቦ የቀደደው አፉን በመክፈት ብዙሃኑን ያስቆጣ ተግባር ለመፈጸም ቻለ። ይህ ሆኖ እያለ በምን አይነት መለኪያ ቢታይ ነው መዘዘኛው ግለሰብ አይነካብን የአስተሳሰብ ጥልቀት የግንዛቤ አድማስ ስፋት ወዘተ እየተባለ በአንድ ባለጌ ጥፋት ብዙሃኑን ለመስደብ መነሳሳት??? በእጅጉ የሚያሳፍረው ደሞ ለመከራከሪያ የቀረበው ኃይለ ቃል ነው። መንጋ፥ የሚለው ማለቴ ነው ጸሐፊው ቃሉን ለመተርጎምና ለመሟገቻነት የሞከረበት የገደል ማሚቱ ድምጸት ከማሳፈሪያነቱ ባሻገር ምንያክል የተመሳሳይ ደናቁርት ሕብረት እንዳላቸው የሚያሳይ ግሩም መስታዎት ነው። ደሞ እኮ በእውነቱ ከሆነ ሁሉም ነገር እኮ አይተችም። ቢያንስ ለመተቸትም ቢሆን ቦታ፥ ሁኔታ፥ ጊዜና የብዙሃንን ልብ ሊገዛ የሚችል አጋጣሚን መጠበቅ ያስፈልጋል። ሕይወት ቡራቡሬ ናት ውበቷም ያነው። በእርግጥ በሕውሃት የጫካ ውስጥ አስተሳሰብ ተጸንሶ ፥ተውልዶና ተምሮ ያደገ የጠፋ ትውልድ ከራሱ በስተቀር ብዙኃን ለሱ ጥቂቶች ብቻ ሳይሆኑ ምንም ናቸው። ይህ ድፍረት በጋዜጠኝነት ሞያ አንቱ የተባሉ፥ በፖለቲካውም ሆነ በሰብአዊ መብቶች ዙሪ እድሚያቸውን ሙሉ የደከሙትን፥ በሃይማኖትና በማህበራዊ ተቋማት የዘመናት አሻራቸውን ያስቀመጡትን በሙሉ ማካተቱ በእጅጉ አስቆጥቶኛል። ምክንያቱም በቃሕ እረፍ፥ እደግ ተመንደግ ያልንህን ያክል ያጥፋህ እንዳንልህ በኢትዮጵያዊነታችን ላይ አፍህን አትክፈት ያሉትን በሙሉ መንጋ ብሎ መሳደቡ ሳያንስ ለመንጋ ኃይለ ቃል ሊሰጥ በታሰበ ቁንጣሪ ትርጉም ሀገሪቱን ሰው አልባ የምንሞች መሰብሰቢያ አድርጎ ለማሳየት መሞከር ከድፍረትም በላይ ድፍረት ነው። የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ እኔ እጅግ ብዙ መምህራን፥የሕግ ባለሙያዎች፥ እና የተለያዩ ሞያ ባለቤት የሆኑም ጓደኞችም አሉኝ እነሱ ግን የበረንዳው አምፖል የተቃጠለባቸው እንጂ እንደ ቴዎድሮስ ጸጋዬ ከዋናው የጠፋባቸው አይደሉም። ብርሃን ከዋናው ከጠፋ መጠገኛ የለውም። የአንፕል መቃጠል ግን በሌላ አምፖል ይተካል። አንድ ሰው የተለያዩ የአካል ክፍሎቹ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ሁኔታ ቢጎዱም የሁሉም ሞተር የሆነው ልባቸው ጤናማ እስከሆነ ድረስ መተኪያ አላቸው። ይልቁንስ ይህንን ግለሰብ ለመደገፍ ተመሳሳይ ጩኽት ከማስተጋባት ይልቅ ተባብረን ልንረዳውና ወደ ልቡ ልንመልሰው በተገባ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ከልብ የተረፈውን አፍ ይናገርል ይላል። ልባችን የበጎም የክፋትም መነሻ ምንጭ ነው። ልቡ የቆሸሸበት ሰው ደሞ እንኳንስ በቴዎድሮስ ካሣሁን ዘፈን ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ ዓይኑን ቢያበራለት በስህተት ነው ብሎ አቃቂር ከማውጣት የማይቆጠብ ፈሪሳዊ አስተሳሰብ የተሞላ ምስኪን ነው። ስለዚህ ለመንጋ ትርጉም በመፈለግ ሊደረስለት የሚገባውን የልብ ሕመምተኛ በሽታውን ማባባስ ጤነኝትንት ነው ለማለት ስለማያስደፍር ይታሰብበት እላለሁ። ዓለማችን ከብዙኃን ድምጽ አልፎ የግለሰብ ድምጽ እንዲከበር በሚደክምበት ምድር ላይ ሆኖ ዘጥና ሚሊዮን ሕዝብን መንጋ እያሉ መፈላሰፍ ምን ይሉታል ጎበዝ??? መታደላችን እንጂ ኢትዮጵያዊ ጨዋ ባይሆን እኮ እንዲህ አይነቱን መረን የወጣ የድፍረት ጽርፈት ስድብ ጤነኛም ሰው አይናገረውም ነበር። ግን የእኛ ሕዝብ ሃይማኖተኛ ይቅር ባይና ይህም ያልፋል ብሎ ወድፊት የሚጓዝ መሆኑ ነው የረዳው። ማስተዋሉን ይስጠን።

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡