የስቃይ ምርመራ በቴዲ አፍሮ “ሰምበሬ” ሲዜም!

ለእኔ ቴዲ አፍሮ (ቴድሮስ ካሳሁን) ዘፋኝ አይደለም፣ ሙዚቀኛም አይደለም። ቴዲ ከዘፋኝነቱ ይልቅ ገጣሚነቱ ያመዝንብኛል፤ ከሙዚቃው ጣዕም ይልቅ የግጥሙ ቅኔ ይመስጠኛል። ስለዚህ፣ የቴዲን ዘፈኖች የማዳምጠው በውስጣቸው የታጨቀውን ቅኔ ለመዝረፍ ነው። ከቴዲ አዲሱ አልበም ውስጥ ገና ከመጠሪያው ትኩረቴን የሳበው “ሰምበሬ” የሚለውን ዘፈን ነው።

ሰሞኑን በስራ መደራረብ ምክንያት ዘፈኑን በጥሞና ለማዳመጥ ግዜ አላገኘሁም ነበር። ዛሬ ግን ሰምበሬን እየደጋገምኩ አዳመጥኩት። ቴዲ በግጥሙ ውስጥ የተቀኘውን ቅኔ ለመዝረፍ ሞከርኩ። ነገር ግን፣ እኔ ጦማሪ እንጂ ባለቅኔ አይደለሁም፣ ፀኃፊ እንጂ ገጣሚ አይደለሁም። በወቅታዊ ፖለቲካ ላይ ትንታኔ መፃፍ እችል ይሆናል፣ የሰንበሬን ግጥምና ቅኔ ለመተንተን ግን ሙያዊ ብቃትና ክህሎት የለኝም። እኔ ማድረግ የምችለው ነገር ግራ እግሬ ላይ ያለውን ሰንበር እያየሁ ሰምበሬን ማዜም ነው። ስለዚህ፣ ይህ ፅሁፍ የገጣሚውን ምልከታና የግጥሙን ጭብጥ ለመዳሰስ ያለመ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ እጅግ አስከፊ የሆነውን የራሴን የሕይወት ገጠመኝ በሰምበሬ እያዋዛሁ ለማቅረብ የምሞክርበት ነው።

ከድፍረት ወደ ፍርሃት
እንደ አጋጣሚ ሆኖ መጀመሪያ ወደ ዩኒቨርሲቲ ስገባ የተቀበለኝ ፍርሃት ነው። ተመርቄም ስወጣ የሸኘኝ ፍርሃት ነው። እኔ ወደ ዩኒቨርሲቲ የገባሁት በ1994 ዓ.ም ሲሆን የተመደብኩት ሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ (በቀድሞ መጠሪያው አለማያ ዩኒቨርሲቲ) ነበር። ነገር ግን፣ በ1993 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (አ.አ.ዩ) ተነስቶ በነበረው የተማሪዎች አመፅ ምክንያት አብዛኞቹ ተማሪዎች ለአንድ አመት ተቀጥተው ነበር። ከጥቂት (የሕግ?) ተማሪዎች በስተቀር የአ.አ.ዩ ግቢ ባዶ ነበር። ስለዚህ፣ ሃሮማያ፣ ሃዋሳ፣ ባህር ዳር፣…ዩኒቨርሲቲዎች የተመደብን የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች አንደኛውን ሴሜስተርን በአ.አ.ዩ እንድንማር ተደረገ። የመጀመሪያው ሴሜስተር እንደተጠናቀቀ ወደ ተመደብንባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ሄድን።

ከላይ እንደተገለፀው፣ እኔ ወደ ዩኒቨርሲቲ ስገባ አብዛኞቹ የአ.አ.ዩ ተማሪዎች በአመፅና ተቃውሞ ምክንያት ከትምህርታቸው ለአንድ አመት ያህል ታግደው ነበር። በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ በነበረኝ ቆይታም ተደጋጋሚ የተማሪዎች አመፅና ተቃውሞ እንደነበር አስታውሳለሁ። በተለይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ ከተማ ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ መቀየሩን ተከትሎ፣ የ4ኛ አመት ተመራቂ በነበርኩበት 1997 ዓ.ም በወቅቱ ከተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የተማሪዎች አመፅና ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር። በአጠቃላይ፣ የዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በተማሪዎች አመፅና ተቃውሞ የታጀበ ነው።

በእርግጥ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት እንደ ፀበል በጥቂቱ፥ ለጥቂቶች በሚታደልበት ዘመን ከት/ት ገበታ ላይ መባረር ማለት የተሻለ ሕይወት የመኖር ተስፋን እንደማጨለም ነው። ስለዚህ፣ ዩኒቨርሲቲ ሳለሁ ተማሪዎች መብትና ነፃነትን ከመጠየቅ ይልቅ በደልና ጭቆናን ተቀብለው እንዲኖሩ ይገደዳሉ። ተማሪነት አልፎ በመምህርነት መስራት ከጀመርኩ አስር አመታት (ከ1998 – 2008) አለፉ። በተማሪነት ዘመን ከዕውቀት ገበታ ያፈናቅል የነበረው የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴ በመምህርነት ዘመን ደግሞ ከሥራ ገበታ ያፈናቅል ጀመር።

በአጠቃላይ ባለፉት አስራ አምስት አመታት የዜጎች ፍርሃት በየአመቱ እየጨመረ፣ ከመብትና ነፃነትን ይልቅ አድርባይነትና ተገዢነት እየነገሰ ሄዷል። ከሞላ ጎደል በሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ የፍርሃት ቆፈን እየሰፈነ መጥቷል። ሆኖም ግን፣    ከዚህ ቀደም በተማሪነት ሆነ በሰራተኝነት ዘመናቸው በአመፅና ሁከት ቀስቃሽነት ተጠርጥረው ታስረው የነበሩ ሰዎች ፍርሃት ግን ፍፁም የተለየ ነው።

ከአካሌ ሳይጠፋ ሰምበሬ

ከዚህ ቀደም የፖሊስን ቆመጥና የወታደርን ጥይት ሳይፈሩ በደልና ጭቆናን በአደባባይ ሲቃወሙ የነበሩ ሰዎች አንዴ ወደ ማዕከላዊ፥ አዋሽ አርባ፥ ጦላይ፣…ወዘተ የመሳሰሉ እስር ቤቶች ተወስደው ከታሰሩ በኋላ ባህሪያቸው ሙሉ በሙሉ ይቀየራል። በእርግጥ በእነዚህ እስር ቤቶች ውስጥ የስቃይ ምርመራ የተፈፀመባቸው ግለሰቦች በስደት ሀገር ጥለው ካልወጡ በስተቀር እንኳን ባህሪያቸው የመንገድ አካሄዳቸው ሳይቀር ይለወጣል። ከመታሰራቸው በፊት ግልፅና ደፋር የነበሩት ሰዎች በአንድ ግዜ ጭምትና ፈሪ ይሆናሉ። ከመስሪያ ቤት – መኖሪያ ቤት የሚሄዱት በውስጥ ለውስጥ መንገድ ነው። በዋናው መንገድ ላይ ሲሄዱ እንኳን ጠርዝ-ጠርዝ ተከትለው ነው።

ለምሳሌ፣ በተማሪነት ዘመናቸው በአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴ ንቁ ተሳትፎ የነበራቸው ሦስት የሥራ ባልደረቦች አሉኝ። ሁለቱ በ1993 ዓ.ም፣ አንዱ ደግሞ በ1996 ዓ.ም ሲማሩበት በነበረው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተነስቶ በነበረው የተማሪዎች አመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ የነበሩና ወደ ተለያዩ እስር ቤቶች ተወስደው የስቃይ ምርመራ ተካሂዶባቸዋል። ሦስቱም ባልደረቦቼ ስለ ፖለቲካ ሲያወሩ እንደ ሃሜት በሹክሹክታ ነው። በወቅታዊ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳብና አስተያየት ለመስጠት እጅግ በጣም ይፈራሉ። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት የሚሄዱት በውስጥ ለውስጥ መንገድ ነው። በአስፋልት ላይ ሲሄዱ እንኳን ጠርዝ-ጠርዙን ተከትለውና አንገታቸውን አቀርቅረው ነው።

“ከዚህ ቀደም በድፍረት ስለ ራሳቸውና ስለ ሌሎች መብትና ነፃነት ሲከራከሩ የነበሩ ሰዎችን እንዲህ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ የከተታቸው እስር ቤት ውስጥ ምን ቢያደርጓቸው ነው?” የሚለው ጥያቄ ዘወትር በውስጤ ይመላለስ ነበር። ለዚህ ፅሁፍ መነሻ በሆነው “ሰምበሬ” ጉዳዩ እንዲህ በረቀቀ መልኩ ተገልጿል፡- 

“ከአካሌ ሳይጠፋ ሰምበሬ
ከአካሌ ሳይጠፋ ሰምበሬ
አምና ፍቅር ጎድቶኝ ከአካል ከልቤ ላይ ሳይጠፋ ሰምበሬ
ደግሞ ሌላ አገኘኝ አዲስ ገላ ለብሶ እዩትና /ይኸውና/ ዛሬ
ሰው መውደድ ዕርሜ ነው
እያልኩኝ ፎክሬ
ያንን ጉራ ሁላ
ገላ ናድው ዛሬ”

የፖሊስ ዱላና የወታደር ጥይት ሳያስፈራቸው፣ መብትና ነፃነታቸውን ለማስከበር፣ ለብዙሃን እኩልነትና ተጠቃሚነት ለመከራከር በአመፅና ተቃውሞ አደባባይ የወጡ ወጣቶች እንደ ማዕከላዊ ባለ እስር ቤት ውስጥ በስቃይ ምርመራ ያላግባብ ሲሰቃዩ፤ በጭካኔ ሲገረፍ፣ በአሰቃቂ ቅጣት አካላቸው ሲዝለፈለፍ፣ የሕመም ሰቆቃው ከአቅማቸው በላይ ሲሆን፣… አዎ…ያኔ አዕምሯቸው የሚያሰላው የነፍስ ጥያቄን ሳይሆን የቁስላቸውን ጥዝጣዜ ነው። ሰው ያለ-ቅጥ መከራና ስቃይ ሲበዛበት ከቃሉ ይልቅ ለአካሉ ቅድሚያ ይሰጣል። ምክንያቱም ቃል የእምነት ዕዳ ነው፣ አካል ግን ከስሜት የተሰራ ቆዳ ነው። መከራና ስቃይ በደረሰ ግዜ ጆሮና ሕሊና አንድ ይሆናሉ። ቃልና እምነትን ትተው የሕመም ስሜትን ያዳምጣሉ። ይህ ሲሆን፣ ትላንት በድፍረት ሲናገሩ የነበሩ ወኔያቸው ከድቷቸው በፍርሃት መሸማቀቅ ይጀምራሉ፡- 

“አልደክምም ቃሌ ነው
እያልኩኝ ፎክሬ
ያንን ጉራ ሁላ
ቀን አራደው ዛሬ
ያን ጉራ ሁላ ጉራ ሁላ
ያን ጉራ ሁላ ትታ ነፍሴ
ወኔዬ ከዳኝ ወንድነቴ
ወድቆ ጨነቀኝ ኩራቴ”

የቅብጥ ሃሳብ
እንሆ የ2008ቱ አመፅና አለመረጋጋት ተነሳ። በተለያዩ አከባቢዎች ወጣቶች ለአመፅና ተቃውሞ በታላቅ ወኔ ወደ አደባባይ ወጡ። አብዛኞቹ “የሕዝብ ነፃነት፣ እኩልነትና ፍትህ ይከበር!” እያሉ ከወታደር ጥይትና ፖሊስ ቆመጥ ጋር በድፍረት ተጋፈጡ። አንዳንዶቻችን “የሕዝብ ነፃነት፣ እኩልነትና ፍትህ ይከበር!” የሚለውን ጥያቄ በማህበራዊ ሚዲያዎች ማስተጋባት ጀመርን። ከዚህ ቀደም፣ እንደ እኛ በድፍረት “መብታችንና ነፃነታችን ይከበር” እያሉ፣ በዚህም ለእስር፥ ስደትና የአካል ጉዳት የተዳረጉና ዛሬን በፍርሃት የሚኖሩትን አጎብዳጆች፥ የባርነት ጠበቃዎች፥…ወዘተ እያልን አንጓጠጥናቸው።

በመስከረም 2009 ዓ.ም መጨረሻ ላይ አብዛኞቻችን ታሰርንና ወደ አዋሽ አርባ፣ ብር ሸለቆ፣ ጦላይ፣…ወዘተ የመሳሰሉ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ተላክን። ከእነዚህ ውስጥ 5600 የምንሆነው ወደ በጦላይ ማዕከል ታስረን። ለአስር ወራት ያህል “የዜጎች መብትና ነፃነት ይከበር!”፣ “የብዙሃኑ እኩልነትና ተጠቃሚነት ይረጋገጥ!” እያልን በአካልና በሚዲያ በድፍረት ስናቀነቅን እንዳልነበርን፣ በጦላይ እግራችን ተገልብጦ ሲገረፍ፣ በማኮብኮብ አካላችን ሲዝል፣ ‘አሁን ከአሁን ስሜ ተጠራ’ የሚለው ሰቆቃ፣ መቀመጫችን፥ ታፋችን እና ውስጥ እግራችን ላይ ያረፈው ሰምበር፣ የእጃችንና እግራችን ጥፍር ጥዝጣዜ…ወዘተ፣ በአጠቃላይ፣ በጦላይ የደረሰብን መከራና ስቃይ “ሕዝብ፥ ነፃነት፥ እኩልነትና ፍትህ” የሚሉት የቅብጥ ቃላት ሆኑብን። ከህሊናችን ጥያቄ ይልቅ የቁስላችን ጥዝጣዜ ዘልቆ ይሰማን ጀመር። የትላንት ድፍረታችን ከድቶን አፋችን በፍርሃት ተለጎመ። ቴዲ አፍሮ በሰምበሬ እንዲህ እያለ እስከ ዶቃ ማሰሪያችን ነገረን፡-

“የቅብጥ /ቀበጥ/ ሐሳብ ጤዛ ነው ሲነጋ ረጋፊ
ወትሮም በአፍ ቃል ይፈጥናል ቀድሞ ተሸናፊ
ላያድን ቃል ብቻ
ምን ያደርጋል ዛቻ
ጉራ ብቻ
….
ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ስልቻ………….ጉራ ብቻ
ቦታ ቢለዋወጥ ወጥ ላያጥም ጉልቻ…………ጉራ ብቻ
ልቤ ዛሬም ወደህ ልትሆን መተረቻ……………..ጉራ ብቻ
ታዲያ ምን አመጣው ያንን ሁሉ ዛቻ …………ጉራ ነው ከአካሌ
ከአካሌ ሳይጠፋ ስምበሬ
ከአካሌ ሳይጠፋ ስምበሬ
…..
ታላቅና ታናሽ ምላስ እና ሰምበር ………….ጉራ ብቻ
ያስገምታል ስጋ ሞቶ ለሚቀበር …………. ጉራ ብቻ
ወርቅ የዘጋ ሳጥን ቁልፍ የሌለው መፍቻ ………….ጉራ ብቻ
ምን ያደርጋል ወድቀው አለሁ ማለት ብቻ ………….ጉራ ነው ከአካሌ
ከአካሌ ሳይጠፋ ስምበሬ
ከአካሌ ሳይጠፋ ስምበሬ

ስምበሬ
በመጀመሪያዎቹ ሃያ ቀናት በጦላይ የሚሰማው የሰቆቃ ድምፅ፣ የልመና ቃላት እና የስቃይ ጩኸት ብቻ ነበር። እስረኞች ከእያንዳንዱ ከፍል በስተጀርባ እየተወሰዱ በደረታቸው ተኝተው፣ እግራቸውን ወደላይ ተሰቅሎና ግርግዳ ተደግፈው በትላልቅ ዱላ ሰውነታቸው እስኪተለተል ተገርፈዋል። ራሳቸውን እስኪስቱ ድረስ የወታደራዊና ስፖርታዊ ቅጣት ተቀጥተዋል። ሰብዓዊ ክብርና መብታቸውን በሚገፍ መልኩ ተደብድበዋል፥ ተሰድበዋል፥ ተዋርደዋል። ከዚያ አንድ ቀን እንዲህ አልኩ፡-

“ጥፋታችን ምንድነው? ቆይ ይሄ ሁሉ መከራና ስቃይ የሚደርስብን ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ስለጠየቅን፣ ‘እኩልነት፣ ነፃነትና ፍትህ ይረጋገጥ!’ በማለታችን ነው። ይሄው ነው ጥፋታችን። ወደዚህ ቦታ ያመጡን ለምንድነው? ከኢትዮጲያ ሕዝብና ከአለም-አቀፉ ማህብረሰብ እይታ ውጪ እንዲህ በነፍስ-ስጋችን ለመጫወት እንዲያመቻቸው አይደለም? ነው! ስለዚህ፣ እዚህ ያለን ሁላችንም እያንዳንዳችን ቢያንስ የአምስት ሰው ስልክ ቁጥር እንፀፍና በልብሳችን ውስጥ እንደብቅ። ከዚህ ግቢ ስንወጣ እነዚህን የስልክ ቁጥሮች እርስ-በእርስ እንቀያየራለን። ከዚያ በኋላ በስልክና በአካል እየተገናኘን እያንዳንዳችሁ ስለደረሰባችሁ በደልና ስቃይ የቃል ምስክርነት ትሰጣላችሁ። በዚህ መሰረት፣ እዚህ ከማንኛውም እይታ ውጪ እየተፈፀመብን ያለውን በደልና መከራ የኢትዮጲያ ሕዝብና የአለም-አቀፉ ማህብረሰብ እንዲያውቁት እናደርጋለን።”

ከጥቂት ቀናት በኋላ ከላይ የተናገርኩት ከፖሊሶች ጆሮ ደረሰ። በጦላይ የተፈፀመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማጋለጥ እየተንቀሳቀስኩ እንደሆነ ተደረሰበት። ሕዳር 02/2009 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ሦስት የፌዴራል ፖሊሶች ከክፍሌ ጠሩኝና በዱላ እየቀጠቀጡኝ፣ እንደ እሳት በሚቃጥል አሸዋ ላይ እንደ እባብ በደረትህ እየተሳብክ ወደ ዋና አዛዡ ቢሮ ሄድኩ። ዋና አዛዡ ልክ ገና ከአጠገቡ እንደ ደረስኩ “እናትህ ትበ**” የሚለውን ፀያፍ ስድብ እየተሳደበ መጣና በከስክስ ጫማው አንገቴን ከመሬት አጣብቆ ረገጠኝ። ከዚያ በኋላ በዙሪያ ተሰብስበው የነበሩትን የፌደራል ፖሊስ አባላት “በሉት…” አላቸው። እስከ ቀኑ 10፡30 ድረስ ደበደቡኝ። ሰውነቴ እስኪተለተል ድረስ እየተፈራረቁ ቀጠቀጡኝ። ስቃዩን መቋቋም እየተሳነኝ ሦስት ግዜ ራሴን ሳትኩ። በመጨረሻም ከታች የሚታየውን ሰምበር ይዤ ወጣሁ። ታዲያ አሁን ቴዲ አፍሮ “ስምበሬ” እያለ ሲዘፍን እኔም “ሰምበሬ የጦላይ ሰምበሬ” እያልኩ አብሬው አዜማለሁ።