ሁሉም ሰው ለራሱ ነፃ-አውጪ፣ በራሱ ነፃ-ወጪ ነው!

ነፃነት ምንድነው?
“ፍቃድ” (Will) ማለት በሃሳብ ላይ ብቻ በመመስረት አንድን ነገር ለመፍጠር ወይም ለማድረግ መሞከር ነው። አንድ ሰው፣ የተወሰነ ሃሳባዊ ወይም አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ወይም ባለማድረግ ፍቃዱን በተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲገልፅ መፍቀድ ወይም መምረጥ (willing or volition) ይባላል። “ፍቃደኛ” (voluntary) የሚለው ደግሞ በራስ ሃሳብ ላይ ተመስርቶና ያለ ምንም ውጫዊ ኃይል አስገዳጅነት መንቀሳቀስ ወይም ከእንቅስቃሴ መቆጠብ እንደማለት ነው። ከዚህ ውጪ የሆነ ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ ያለውዴታ ወይም “በግዴታ” (involuntary) እንደተደረገ ይቆጠራል።

ማንኛውም ግለሰብ አንድን ነገር በራሱ ፍቃድ ለመፍጠር ወይም ለማድረግ ፍቃደኛ ከመሆኑ በፊት ግን በቅድሚያ ስለ እንቅስቃሴው ማወቅ አለበት። ይህ ካልሆነ፣ እንቅስቃሴው በራስ ተነሳሽነት ሳይሆን በሁኔታዎች አስገዳጅነት ወይም በደመ-ነፍስ እንዳደረገ ይቆጠራል። ስለዚህ፣ በፍቃደኝነት የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ በራስ ሃሳብ፣ ዕውቀትና ግንዛቤ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት።

በአጠቃላይ፣ ሰው በማሰብ ስለ አንድ ነገር ያውቃል ወይም ነባራዊ እውነታን ይረዳል። አንድን ተግባር በራሱ ፍቃዱና ምርጫ ለማከናወን ግን በቅድሚያ በራሱ ማሰብና ማወቅ አለበት። በራሱ ለማሰብና ለማወቅ ደግሞ በራሱ መፍቀድና መምረጥ አለበት። ስለዚህ፣ አንድን ተግባር በራሱ ፍቃድና ምርጫ ለማከናወን በቅድሚያ ማሰብና ማወቅ፣ ስለ ተግባሩ ለማሰብና ለማወቅ ደግሞ በቅድሚያ በራሱ መፍቀድና መምረጥ አለበት።

በዚህ መሰረት፣ የአንድን ሰው ፍቃድና ምርጫ በራሱ ከማሰብና ማወቅ ተነጥሎ ሊታይ አይቻልም። እነዚህን ተፈጥሯዊ ባህሪያት መነጠል እስካልተቻለ ላይ አጣምሮ ማየት ያስፈልጋል ነው። “John Locke” የተባለው ፈላስፋ “An Essay Concerning Human Understanding” በሚለው መፅሃፉ፣ ፍቃድ/ምርጫ (will) እና ማሰብ/ማወቅ (understanding) የሰው ልጅ ልዩ ተፈጥሯዊ ባህሪያት መሆኑንና የሁለቱ ጥምር ውጤት ደግሞ “ነፃነት” (liberty) እንደሆነ ይገልፃል። በተመሣሣይ፣ “John Stuart Mill” የተባለው ፈላስፋ ደግሞ የሰው ልጅ ነፃነት “human liberty” ከአመለካከትና የሃሳብ ነፃነት ጋር ያለውን ቁርኝት አንደሚከተለው ይገልፀዋል፡-

“The only freedom which deserves the name, is that of pursuing our own good in our own way, so long as we do not attempt to deprive others of theirs, or impede their efforts to obtain it. …It comprises the inward domain of consciousness; demanding liberty of conscience in the most comprehensive sense; liberty of thought and feeling; absolute freedom of opinion and sentiment on all subjects, practical or speculative, scientific, moral, or theological. The liberty of expressing and publishing opinions may seem to fall under a different principle, since it belongs to that part of the conduct of an individual which concerns other people; but, being almost of as much importance as the liberty of thought itself, and resting in great part on the same reasons, is practically inseparable from it.” On Liberty – John Stuart Mill, Ch.1, Page 11

ነፃ-አውጪ” እና “ነፃ-ወጪ”
ከላይ በተገለፀው የነፃነት ፅንሰ-ሃሳብ መሰረት፣ አንድ ሰው በራሱ ነፃ-አውጪ ሆኖ ሌሎችን ነፃ-ሊያወጣ ይችላል? በመሰረታዊ የመብት መርህ መሰረት፣ የአንድ ሰው መብት የሌሎችን ነፃነት በማይገድብ መልኩ በራሱ ፍላጎትና እና ምርጫ መሰረት መንቀሳቀስ መቻል ነው። አንድ ሰው “ነፃ” የሚሆነው ደግሞ በራሱ ግንዛቤና ዕውቀት መሰረት መንቀሳቀስ ሲችልና፣ ይህንንም በራሱ መርጦና ፈቅዶ ሲያደርገው ነው። “ነፃ-ያልሆነ” ሰው ደግሞ በራሱ የማያውቀውን እና/ወይም የማይፈቅደውን ሃሳብና ተግባር በሁኔታዎች አስገዳጅነት የሚፈፅም ነው።

ነፃ-የወጣ ሰው የራሱን ሃሳብና ተግባር በራሱ አውቆና ፈቅዶ የሚያደርግ ነው። ሁሉም ሰው ነፃ የሚወጣው እያንዳንዱ ሰው የራሱን ሃሳብና ተግባር በራሱ አውቆና ፈቅዶ የሚያደርግ ከሆነ ነው። ነፃ ሰው ሌሎችን ነፃ ማውጣት የሚችለው በራሱ አመለካከት ትክክል ወይም አግባብ ነው ያለው ሃሳብ ወይም ተግባር ሌሎቹም ሰዎች በፍቃዳቸው እንዲያውቁትና እንዲተገብሩት ማድረግ ሲችል ነው።

ሌሎችን ነፃ-ለማውጣት የእኛን ሃሳብና አመለካከት ሌሎች እንዲያውቁት፣ እንዱቀበሉትና ተግባራዊ እንዲያደርጉት ማድረግ ይጠይቃል። ነገር ግን፣ ሌሎች ሰዎች የእኛን ሃሳብና አመለካከት በራሳቸው አውቀው ለመቀበል ከትክክለኝነቱና አግባብነቱ በተጨማሪ ፍቃደኛ መሆን አለባቸው። ስለዚህ፣ በነፃነት ስም ሰዎች ሳያውቁና ሳይፈቅዱ፤ የእነሱን ነፃ ምርጫ እና ፍቃደኝነት በሚፃረር መልኩ የእኛን ሃሳብና አመለካከት በኃይል ወይም በግድ ለመጫን መሞከር ፍፁም ስህተት ነው።

ከላይ ለመግለፅ አንደተሞከረው፣ ፍቃድ/ምርጫ (will) እና ማሰብ/ማወቅ (understanding) የሰው ልጅ ልዩ ተፈጥሯዊ ባህሪያት ሲሆኑ ነፃነት ደግሞ የእነዚህ ጥምር ውጤት ነው። እነዚህ ባህሪያት በተናጠል ነፃነት ሊሆኑ አይችሉም። በዚህ መሰረት፣ አንድን ሃሳብ ወይም ተግባር በራሳችን አውቀንና ተገንዝበን፣ በራሳችን ምርጫና ፍቃድ ተግባራዊ እስካላደረግን ድረስ ነፃነት ሊኖረን አይችልም።

እያንዳንዱ ሰው ነፃ-ሊወጣ የሚችለው በራሱ ሲያውቅና ሲፈቅድ ነው። በእርግጥ ሌሎች ሰዎች ስለ ነፃነት ትርጉምና ፋይዳ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ እንዲኖረው ሊያደርጉ ይችላሉ። ነገር ግን፣ እያንዳንዱ ሰው ነፃነትን አውቆና ፈቅዶ እስካልተቀበለ ድረስ ነፃ-ሊወጣ አይችልም። ስለዚህ፣ ሁሉም ሰው ነፃ የሚወጣው በራሱ ፍቃድና ምርጫ ስለሆነ እያንዳንዱ የራሱ “ነፃ-አውጪ” ነው!

ሌሎችን ነፃ-ለማውጣት የእኛን ትክክለኛ ሃሳብና አመለካከት ለሌሎች መግለፅና ማሳወቅ ይጠበቅብናል። ነገር ግን፣ እንደ “John Stuart Mill” አገላለፅ፣ የግል ሃሳብና አመለካከትን የመግለፅ ነፃነት (the liberty of expressing and publishing opinions) የራሳችንን ነፃ ፍቃድ/ምርጫ እና ሃሳብና ግንዛቤ የምናፀባርቅበት እንደመሆኑ ከእኛ ነፃነት ተለይቶ ሊታይ አይችልም።

ሌሎችን ስለ ነፃነት ትርጉምና ፋይዳ ለማሳወቅ የምናከናውነው ማንኛውም ተግባር በዋናነት የራሳችንን ነፃነት ለማረጋገጥ የሚደረግ ነው። ስለ ሌሎች ሰዎች ነፃነት መከበርና አለመከበር የምንናገረውና የምንፅፈው ከማንም በፊት የራሳችንን የአመለካከት የመያዝና ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታችንን ለማረጋገጥ ነው። ስለዚህ፣ እያንዳንዱ ሰው የራሱ “ነፃ-አውጪ” ነው። ነገር ግን፣ እያንዳንዱ ሰው ከራሱ በስተቀር የሌሎች “ነፃ-አውጪ” ሊሆን አይችልም። ሁሉም ሰው የራሱ ነፃ-አውጪ ነው! በራሱ ነፃ-ወጪ ነው!