የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት፡ የዜጎች ፍርሃት ለአምባገነኖች ሕይወት ነው!

1: ሻዕቢያን ፈርቶ ኢትዮጲያን….
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በኒጄር፥ ኒያሜ ከተማ በአፍርካ ሀገሮች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ የተለያዩ ሰብሰባዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ። በተወሰኑ ሰብሰባዎች ላይ የመታደም እድሉ ገጥሞኝ ነበር። ከእነዚህ ውስጥ የተባበሩት መንግስታት የኤርትራ ልዩ ራፖርተር (UN Special Rapporter on Eritrea) የሆኑት ¨Sheila Keetharuth” ስለሀገሪቱ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሪፖርት ያቀረቡበት ስብሰባ አንዱ ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ የተለያዩ የአፍርካ ሀገራት የተወጣጡ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች፣ እንዲሁም አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት መንግስታዊ ድርጅቶች፣ በተለይ የኢጣሊያን መንግስት ጦር ኃይል ተወካዮች በተገኙበት በኤርትራ ስላለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የሀገሪቱ ዜጎች የሜዲትራኒያንን ባህር አቋርጠው ወደ አውሮፓ ከመሰደዳቸው ጋር ያለው ግንኙነት ተዳሷል።

ከላይ በተጠቀሱት ስብሰባዎች ላይ የኤርትራ መንግስት በዜጎቹ ላይ ስለሚፈፅመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በዝርዝር ተገልጿል። በየወሩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሀገሪቱ ዜጎች ወደ ኢትዮጲያና ሱዳን፣ እንዲሁም በሊቢያ በኩል ባህር አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመሰደዳቸው በዋናነት የተጠቀሰው የብሔራዊ አገልግሎት (National Service) ግዴታ ነው። በእርግጥ ጉዳዩን ከኤርትራ መንግስት እይታ አንፃር ስንመለከተው፣ የኢሳያስ አፍወርቂ አስተዳደር በተለይ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ የሕልውና አደጋ እንደተጋረጠበት መገንዘብ ይቻላል። በመሆኑም፣ በብሔራዊ አገልግሎት አማካኝነት ከፍተኛ ቁጥር ያለው መደበኛና ተጠባባቂ የጦር ኃይል በብዛት አሰልጥኖ ካላዘጋጀ በስተቀር በስልጣን ላይ የመቆየት ዕድሉ የመነመነ ሊባል ይችላል።

ነገር ግን፣ መቀመጫውን ኬኒያ ናይሮቢ ያደረገ የኤርትራ ሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት መስራችና ኃላፊ የሆነቸው ሩት ክፍሌ በስብሰባው ላይ እንደገለፀችው፣ የኢሳያስ አፈወርቂ መንግስት የሀገሪቱን ወጣቶች እስከ አመስት አመት ድረስ ያለ ምንም ክፍያ ወታደራዊ ሰልጠና እና አገልግሎት እንዲሰጡ በማስገደድ፣ ከባድ የጉልበት ሥራ በማሰራት፣ ፆታዊ ብዝበዛን ጨምሮ የተለያዩ በደሎችና ጭቆናዎች እንደሚፈፅም በመድረኩ ገልፃለች። እንደ እሷ አገላለፅ፣ የብሔራዊ አገልግሎት (National Service) ዓላማ ወጣቶችን ማሸማቀቅና ለመንግስታዊ ስርዓቱ ተገዢ እንዲሆኑ ማድረግ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ፣ በተባበሩት መንግስታት የኤርትራ ልዩ ራፖርተር (UN Special Rapporter on Eritrea) ወ/ሮ ¨Sheila Keetharuth” ስለሀገሪቱ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ እንደገለፁት በኢትዮጲያና ኤርትራ መካከል ያለው ሰላም እና ጦርነት ያለየበት የ“No peace” – “No war” ሁኔታ በኤርትራ የብሔራዊ አገልግሎት (National Service) ግዴታ ተግባራዊነት፣ በዚህም አማካኝነት በሀገሪቱ ዜጎች ላይ ለሚፈፀመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ይህን ተከትሎ ለሚከሰተው ስደት በዋና ምክንያትነት ጠቅሰዋል። (የራፖርተሯን ሪፖርት በከፊል በፌስቡክ ገፄ ላይ ከለጠፍኩት የቪዲዮ ምስል መመልከት ይቻላል)።

በአጠቃላይ፣ የኤርትራ መንግስት በዜጎቹ ላይ ለሚፈፅመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና አስከፊ ስደት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ኢትዮጲያን ተጠያቂ የሚያደርግ አቋም በመድረኩ መሪዎችና ተሳታፊዎች በግልፅ ተንፀባርቋል። ነገር ግን፣ የኤርትራ መንግስት በኤርትራዊያን ላይ ለሚፈፀም የሰብዓዊ መብት ጥስት ኢትዮጲያን ተጠያቂ ለማድረግ መሞከር በራሱ የመድረኩ መሪዎችና ተሳታፊዎች ስለ ሁለቱ ሀገራት ታሪክ እና መንግስታት ያላቸው ግንዛቤ ውስን መሆኑን ያሳያል። ከዚህ በተጨማሪ፣ በተጠቀሱት መድረኮች ላይ ኢትዮጲያን እንደ ሀገር፤ የሀገሪቱን ሕዝብና መንግስት ወክሎ ሃሳብና አስተያየት የሚሰጥ አንድም ሰው አለመኖሩ ያበሳጫል።

በእርግጥ በቦታው ብዙ ኢትዮጲያዊን የነበሩ ቢሆኑም በስብሰባው ላይ የተገኙት መንግስታዊ ያልሆኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ወክለው ስለሆነ በጉዳዩ ላይ የራሳቸውን ሃሳብና አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል። በተመሣሣይ፣ እኔም በቦታው የተገኘሁት በአንድ የውጪ ድርጅት ተጋብዤ ነው። ነገር ግን፣ ለኤርትራ መንግስት ጥፋት ኢትዮጲያ እንደ ሀገር ተጠያቂ ስትደረግ፣ ሌላው ቢቀር የሀገሪቷ መልካም ገፅታ በይፋ ጥላሸት ሲቀባ እየተመለከትኩ በዝምታ ማለፍ አልችልም።

በመሰረቱ፣ በአምባገነኖች ዘንድ ካልሆነ በስተቀር ሀገር እና መንግስት የተለያዩ ናቸው። የኤርትራ መንግስት በራሱ በዘጎቹ ላይ የሚፈፅመውን አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እቃወማለሁ። ሆኖም ግን፣ ለችግሩ ብቸኛው ተጠያቂ አካል ራሱ የኤርትራ መንግስት ነው። ለተጠቀሰው የኤርትራ ችግር እንኳን ኢትዮጲያ እንደ ሀገር ተጠያቂ ልትሆን ይቅርና አምባገነኑ የኢህአዴግ መንግስት እንኳን ተጠያቂ ሊደረግ አይገባም። በአጠቃላይ፣ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ፣ ለኤርትራ ችግር ኢትዮጲያን ተጠያቂ ለማድረግ የታየው ዝንባሌ “አህያውን ፈርቶ ዳውላውን…” የሚሉት ነው። 

2፡ የዜጎች ፍርሃት ለአምባገነኖች ሕይወት ነው!

ከላይ በተጠቀሰው መልኩ፣ የኤርትራ መንግስት በዜጎቹ ላይ ለሚፈፅመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ኢትዮጲያን ተጠያቂ ለማድረግ የተሞከረበት አግባብ የሁለቱን ሀገራት መንግስታት መሰረታዊ ባህሪ ጠንቅቆ ካለማወቅ የመጣ ነው። በእርግጥ የሻዕቢያ እና የኢህአዴግ መንግስት “ፀረ-ሰላም፥ ፀረ-ሕዝብ፥ ፀረ-ልማት፣ አሸባሪ፥ አምባገነን፥ አተራማሽ፣…” እየተባባሉ እርስ-በእርሳቸው በጠላትነት ይፈራረጃሉ። ይሁን እንጂ፣ ከምንም በላይ ሁለቱን መንግስታት አንድ የሚያደርጋቸው ፍፁም አምባገነን መሆናቸው ነው።

የኤርትራ መንግስት የብሔራዊ አገልግሎትን (National Service) ተግባራዊ የሚያደርገው ከኢትዮጲያ መንግስት ሊቃጣበት የሚችለውን ወረራና ጥቃት ለመከላከል እንደሆነ ይገልፃል። ነገር ግን፣ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፣ ይህ ፕሮግራም የሀገሪቱን ወጣቶች ለማሸማቀቅና ለመንግስታዊ ስርዓቱ ተገዢ እንዲሆኑ የማድረግ ዓላማ ያለው ነው። በተመሣሣይ፣ የኢህአዴግ መንግስት ኤርትራን ዋና ፀብ አጫሪና በሀገሪቱ ለሚስተዋሉ ማናቸውም የፖለቲካ አለመረጋጋቶች በተጠያቂ ያደርጋል። የኤርትራ መንግስት ከኢትዮጲያ ጋር ያለውን ግንኙነት በሀገሪቱ ዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመፈፀም እንደሚጠቀመው ሁሉ፣ የኢትዮጲያም መንግስት “ከኤርትራ ጋር ተመሳጥራችኋል” በሚል የተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎችን ይወነጅላል፥ ያስራል፥ ያሰቃያል።

ሁለቱም መንግስታት በዜጎቻቸው ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመፈፀም ከሌላኛው ወገን የተደቀነበትን የደህንነት ስጋት በምክንያትነት ይጠቅሳሉ። ነገር ግን፣ የሀገር ደህንነት በምንም አግባብ ቢሆን የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ለመገደብ ሆነ ለመጠስ ምክንያት ሊሆን አይችልም።

ነገር ግን፣ ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የኤርትራ መንግስት በዜጎቹ ላይ ለሚፈፅመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከኢትዮጲያ ጋር ያለው ግንኙነት በምክንያትነት ተጠቅሷል። በተለይ ከኢትዮጲያ መንግስት የተጋረጠበትን የደህንነት ስጋት የዜጎቹን መብትና ነፃነት ለመገደብ እንደ ምክንያት በመጠቀም ላይ ይገኛል። በተመሣሣይ፣ የኢትዮጲያ መንግስት በተለያዩ አጋጣሚዎች በሀገሪቱ ለሚከሰቱ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች የኤርትራን መንግስት ተጠያቂ ሲያደርግ ይስተዋላል። በዚህም ከኤርትራ መንግስት የተጋረጠበትን የደህንነት ስጋት መነሻ በማድረግ የራሱን ዜጎች መብት እና ነፃነት ለመገደብ ሲጠቀምበት ይስተዋላል።

የሁለቱ ሀገራት መንግስታት አንዱ በሌላው ላይ የጋረጠውን የደህንነት ስጋት የዜጎቻቸውን መብትና ነፃነት ለመገደብና ለመጣስ ለምን ይጠቀማሉ? የዚህ መሰረታዊ ምክንያት አምባገነን መንግስታት የሀገር ሰላምና ድህንነት ምክንያት በማድረግ ዜጎችን ለማስፈራራት እንደሆነ ይገልፃል። ቆፈን ውስጥ መክተት ስለሚሹ እን በማስፈን ነው። እንደ ሎሬት “Wole Soyinka” አገላለፅ፣ ይህ በአብዛኞቹ የአፍሪካ አምባገነን መንግስታት ዘንድ የሚስተዋል ስልት እንደሆነ ይገልፃል።

“…under the burgeoning trade of dictatorship and governance through a forced diet of fear, most especially on the African continent – in common parlance, the fear of ‘the midnight knock’. Arbitrary detentions. Disappearances. Torture as the rule rather than the exception. … [Its purpose] to instil fear into the populace by deliberately flouting the most elementary principles of justice.” REITH LECTURES 2004: Climate of Fear, Wole Soyinka Lecture 1: The Changing Mask of Fear, 7 April 2004

አምባገነኖች የሀገርና ሕዝብን ደህንነት ለማስከበር በሚል ሰበብ በዜጎች ላይ የፍርሃትና ስጋት ድባብ የሚፈጥሩት ለሌላ ሳይሆን መንግስታዊ ስርዓቱን ለማስቀጠል ነው። በዚህ ረገድ፣ “Wole Soyinka” ሀገሩ ናይጄሪያ ከእንግሊዝ ነፃ በወጣች ማግስት ወደ ስልጣን የመጡት አምባገነን መሪዎች በቅኝ-አገዛዝ ወቅት እንኳን ባልታየ መልኩ መላ ሀገሪቱን በፍርሃት በማራድ እንዴት በስልጣን መቆየት እንደቻሉ በማሳያነት ይጠቅሳል፡-

“…The entire nation was deeply traumatized. …While that regime lasted, there was no question about it – for the first time in the brief history of her independence, the Nigerian nation, near uniformly, was inducted into a palpable intimacy with fear, an experience that was never undergone even in the most brutal season of the colonial mandate.”  REITH LECTURES 2004: Climate of Fear, Wole Soyinka Lecture 1: The Changing Mask of Fear, 7 April 2004

ከላይ በዝርዝር ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የኤርትራና የኢትዮጲያ መንግስታት አንደኛው በሌላኛው የተጋረጠበትን የደህንነት ስጋት መነሻ በማድረግ የራሱን ዜጎች የሚጨቁንበት ምክንያት ሕዝቡን በማስፈራራት የስልጣን ላይ ለመቆየት ነው። ነገር ግን፣ የሀገር ሰላምና ደህንነት በምንም አግባብ ቢሆን የዜጎችን መብት እና ነፃነት ለመገደብና ለመጣስ በምክንያትነት ሊጠቀስ አይችልም። ለምሳሌ፣ የቀድሞ የእንግሊዝ የሀገር ውስጥ ደህንነት ዳይሬክተር “Eliza Manningham Buller” የሀገር ደህንነት የዜጎችን መብትና ነፃነት ለመገደብ በፍፁም ምክንያት ሊሆን እንደማይችል እንዲህ ትገልፃለች፡-    

“I do not see that liberty and freedom and security are polar opposites. …We must recognise the limits of what any government can do and be deeply cautious of anything that leads to security being seen as the opposite of liberty rather than essential to it. …governments need to practise a foreign policy that, while acknowledging the world as it is, tries to secure freedom for others – and to pursue a domestic policy that protects the liberties we value and which the [enemy] tries to destroy.”  FREEDOM, REITH LECTURER: ELIZA MANNINGHAM-BULLER, 20 September 2011.

በአጠቃላይ፣ በኤርትራዊያን ላይ ለሚፈፅመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ብቸኛው ተጠያቂ የኤርትራ መንግስት ነው። በሀገሪቱ የብሔራዊ አገልግሎት ግዴታ እንዲቀጥል ከማድረግ አንፃር ወይም የአልጄርስ ስምምነትን ባለመቀበሏ ምክንያት እንደ ሀገር ኢትዮጲያን ወይም የኢህአዴግ መንግስትን ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም። በእርግጥ የኢህአዴግ መንግስት የአልጄርስ ስምምነት ቢቀበል ወይም ውዝግብ የተነሳባትን ባድመ ለኤርትራ አሳልፎ ለመስጠት ቢስማማ እንኳን የኢሳያስ አፈወርቂ አስተዳደር በዜጎቹ ላይ በሚፈፅመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሆነ ስደት ላይ በፍፁም ለውጥ ሊመጣ አይችልም። በአጠቃላይ፣ በኢትዮጲያና ኤርትራ መካከል ያለው መሰረታዊ ችግር የድንበር ይገባኛል፣ የጦርነት ወይም ሌላ ዓይነት የደህንነት ስጋት አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ሁለት አምባገነን መንግስታት ላለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን የራሳቸው ዜጎችን በፍርሃት ቀፈን ቀፍድደው በስልጣን ላይ ለመቆየት ያላሳለሰ ጥረት ማድረጋቸው ነው።