የተሳሳተ ሃሳብን መገደብ በራሱ ስህተትና ጎጂ ነው (ለአብርሃ ደስታ)

ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ የዓረና ትግራይ ፓርቲ አባል የሆኑት አቶ ዘነበ ሲሳይ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ ያወጧት ፅሁፍ እና ይህን ተከትሎ ከፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ የተሰጠው ምላሽ ነው። አቶ አብርሃ ደስታ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ በሰጡት ምላሽ የግለሰቡ ተግባር ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለውና ፓርቲውንም እንደሚጎዳ ገልፀው፣ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት አስቸኳይ ስብሰባ መጥራታቸውን አስታውቀዋል።

ጉዳዩን አስመልክቶ በፌስቡክ ገፄ ላይ ባወጣሁት ፅሁፍ የዓረና ፓርቲ ተግባሩን ከማውገዝ አልፎ በአቶ ዘነበ ላይ እርምጃ ለመውሰድ የአስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱ የግለሰቡን “ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት” የሚገድብና ለዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት እታገላለሁ ከሚል ድርጅት የማይጠበቅ እንደሆነ ገልጬያለሁ። ሆኖም ግን፣ አቶ አብርሃ ደስታ ለአስተያየቴ የሰጡት ምላሽ በተጨባጭ እውነታና በነፃነት መርህ ላይ የተመሰረተ አይደለም። ስለዚህ፣ በዚህ ፅሁፍ እንግሊዛዊው ፈላስፋ “John Stuart Mill” ስለ ሃሳብና የአመለካከት ነፃነት ጥልቅ የሆነ ትንታኔ የሰጠበት “On Liberty” የተሰኘውን መፅሃፍ ዋቢ በማድረግ በጉዳዩ ዙሪያ በዝርዝር ለማሳየት እሞክራለሁ።

ይህ ፅሁፍ አቶ ዘነበ ሲሳይ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ ስላወጡት ፅሁፍ “ትክክለኝነት” ወይም “ስህተትነት” ትንታኔ ለመስጠት ወይም ለማስተባበል የቀረበ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ “አቶ ዘነበ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ የፃፉት ሃሳብ ፍፁም ስህተት ነው” በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። ይሁን እንጂ፣ በዚህ ምክንያት በፓርቲው አመራሮችና ደጋፊዎች እየደረሰባቸው ያለው ጫና እና በቀጣይ ሊወሰድባቸው የሚችለው አስተዳደራዊ እርምጃ ስህተት ከመሆኑ በተጨማሪ ለፓርቲውና ለማህብረሰቡ ጎጂ መሆኑን ለማሳየት የቀረበ ነው። ለዚህ ደግሞ የሚከተሉትን ሦስት የመከራከሪያ ሃሳቦች ቀርበዋል፡-

1ኛ፡- የዓረና ፓርቲ የተሳሳተ ሃሳብን የመከልከል ስልጣን የለውም

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የዓረና ፓርቲ ሊቀመንበር በሰጡት ምላሽ፤ “የሃሳብ ነፃነት የዴሞክራሲ መርህ ከሆነ፣ ዴሞክራሲ ደግሞ የሕዝብ የበላይነትን ማክበርና ማረጋገጥ ከሆነ፣ ሕዝብን ለማዋረድና ለመሳደብ የሚሰጥ ነፃነት የለም። …ዓረና ለሕዝብ የሚታገል ድርጅት ነው። ፀረ-ሕዝብ ከሆንክ ታዲያ ፀረ-ዓረና ነህ። ፀረ-ዓረና ከሆንክ ደግሞ የዓረና አካል አይደለህም” ብለዋል። የዓረና ፓርቲና የሚወክለው ሕዝብ አንድ መሆናቸውን እና በአቶ ዘነበ ላይ የሚወስደው እርምጃ በዋናነት የሕዝብን የበላይነት ለማስከበርና ለማረጋገጥ እንደሆነ ከአስተያየቱ መረዳት ይቻላል። ነገር ግን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ “John Stuart Mill” እንዲህ ብሏል፡-
“Let us suppose, therefore, that the government is entirely at one with the people, and never thinks of exerting any power of coercion unless in agreement with what it conceives to be their voice. But, the power itself is illegitimate. The best government has no more title to it than the worst… They have no authority to decide the question for all mankind, and exclude every other person from the means of judging.” On Liberty – John Stuart Mill, Ch.2: Of the Liberty of Thought and Discussion, Page 13

“የዓረና ፓርቲ የሚወክለውን ሕዝብ የበላይነት ለማስከበር ነው” በሚል አቶ ዘነበ የተሳሳተ ሃሳቡን እንዳይገልፅ ለመገደብና ይህን ተከትሎ አስተዳደራዊ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ስልጣን የለውም። አቶ አብርሃ ደስታ ግለሰቡ ፀረ-ሕዝብ የሆነ አቋም በይፋ አንፀባርቋልና በአባልነት መቀጠል የለበትም ማለታቸው ፍፁም ስህተት ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ ይህ ተግባራቸው ያለ በቂ ማስረጃና ጥፋት በተደጋጋሚ ለእስርና እንግልት ከዳረጋቸው ገዢው ፓርቲ ጋር አንድና ተመሳሳይ ያደርጋቸዋል። በአጠቃላይ፣ ኢህአዴግ/ሕወሃት ሆነ ዓረና ትግራይ በአቶ ዘነበ ሲሳይ አዕምሮ ውስጥ ሊነሳ የሚችለውን ጥያቄ ዓይነትና አግባብነት የመወሰን ስልጣን የላቸውም።

2ኛ፡- የተሳሳተ ሃሳብን መከልከል በራሱ ስህተት ነው!

እንደ አቶ አብርሃ ደስታ አገላለጽ፣ ስለ ሃሳብ ነፃነትና የሕዝብ የበላይነት የተሳሳተ ያላቸው ግለሰቦች የዓረና ፓርቲ አባል ሆነው መቀጠል የለባቸውም። በዚህ መሰረት፣ እንደ አቶ ዘነበ ያሉ የሕዝብን ክብር በሚነካ መልኩ የተሳሳተ ሃሳብ የሚያንፀባርቁ ግለሰቦች ከዚህ ተግባራቸው ሊታገዱ እንደሚገባ ጠቁመዋል። ነገር ግን፣ እንደ “John Stuart Mill” አገላለፅ፣ ይህ አመለካከት “ሁሉንም ነገር አውቃለሁ” ከሚል ፍፁማዊነት (infallibility) የመጣ እንደሆነ እንደሚከተለው ይገልፃል፡-
“There is no greater assumption of infallibility in forbidding the propagation of error, than in any other thing which is done by public authority on its own judgment and responsibility. Judgment is given to men that they may use it. Because it may be used erroneously, are men to be told that they ought not to use it at all? An objection which applies to all conduct can be no valid objection to any conduct in particular…”
On Liberty – John Stuart Mill, Ch.2: Of the Liberty of Thought and Discussion, Page 15

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ እንዳንድ ሰዎች ገና-ለገና የተሳሳተ ሃሳብ ሊያስቡ ይችላሉ፣ ወይም ደግሞ ከሕግና የሞራል ስነ-ምግባር ውጪ የሆነ ተግባር ሊፈፅሙ ይችላሉ በሚል በራሳቸው ሕሊና እንዳያስቡና የግል አመለካከታቸውን በነፃነት እንዳይገልጹ ሊከለከሉ አይገባም። እያንዳንዱ ሰው በራሱ ሕሊና ማሰብ እንዲችል ሆኖ የተፈጠረ እንደመሆኑ፣ ሁለትና ሦስት ግዜ የተሳሳተ ሃሳብ ስላንፀባረቀ የሃሳብ ነፃነቱን እስከ መጨረሻው ሊያጣ ይገባል ማለት አይደለም።

አቶ ዘነበ ሲሳይ እንደ ማንኛውም ሰው በራሱ ህሊና የሚያስብ ነው። የራሱን ሕይወት ከመምራት አልፎ-ተርፎ ሀገርና ሕዝብን ወደ ተሻለ ደረጃ ለመምራትበሚያስችለው መልኩ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኖ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ነገር ግን፣ ከዕለታት አንድ ቀን በውስጡ ሲመላለስ የነበረን ሃሳብ በፌስቡክ ገፁ ላይ በመፃፍ ሃሳቡን ገለፀ። ነገር ግን፣ በዓረና አመራሮችና ደጋፊዎች ዘንድ የፅሁፉ ይዘት “እወክለዋለሁ” የሚለውን ሕዝብ ክብር የሚያጎድፍና የፓርቲውን የሥነ-ምግባር ደንብ የሚጥስ ሆኖ ተገኘ። በዚህ ምክንያት፣ ግለሰቡ የፓርቲው አባል ሆኖ ሊቀጥል እንደማይችል ሊቀመንበሩ ጠቁሟል።

እዚህ ጋር አብርሃ ደስታ ራሱ ፍርድ ቤት ቀርቦ በነበረበት ወቅት ያጋጠመውን መጥቀስ ይቻላል። በወቅቱ አብርሃ ደስታ ያለ በቂ ማስረጃና ወንጀል ተከስሶ ለእስርና እንግልት በተዳረገበት ወቅት ጉዳዩን የሚመለከቱት ዳኞች ከራሳቸው ሕሊና ይልቅ ለባለስልጣናት ተገዢ መሆናቸው አበሳጭቶት ችሎት ፊት በማጨብጨብ ተቃውሞውን መግለፁ የሚታወስ ነው። በእርግጥ ዳኞቹ ለሕሊናቸው ተገዢ አለመሆናቸው እንዳለ ሆኖ፣ አብርሃ ደስታ በማጨብጨቡ ግን ደንብ ጥሷል። ችሎት ፊት በአጨበጨበ ቁጥር ችሎት ተዳፍረሃል ተብሎ ቅጣት ተበይኖበታል። ዳኞቹ ባለስልጣናቱን ፈርተው ለእውነትና ለሕሊናቸው ተገዢ መሆን እንደተሳናቸው ሁሉ፣ አቶ ዘነበም እነ አብርሃን ፈርቶ ሃሳቡን ከመግለፅ መቆጠብ ነበረበት?

በእርግጥ አብርሃ ደስታ በችሎት ፊት በማጨብጨብ ተቃውሞውን የገለጸው ለምንና እንዴት ነበር? በችሎት ላይ የተሰየሙት ዳኞች ከአቃቤ ሕግና ፖሊስ የቀረበላቸውን የተሳሳተ ማስረጃ ትክክለኝነት ሳያጣሩ የጥፋተኝነት ብይን ስለሰጡ ነው። አብርሃ ደግሞ የቀረበበትን ማስረጃ ሃሰት እንደሆነ ለማስረዳት ሲሞክር የእሱን እውነት ለመስማት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው፣ በዚህም በዳኞቹና በፍርድ ቤቱ እምነት በማጣቱ ምክንያት አልነበረም?

አዎ…አብርሃ ደስታ በችሎቱ ፊት በማጨብጨብ ተቃውሞውን የገለጸበት ምክንያት በውስጡ ያለውን እውነት ተናግሮ የቀረበበትን የሃሰት ማስረጃ ውድቅ ለማድረግ ተናግሮ ለማስረዳት እድል ስለተነፈገው ነው። ዳኞቹም የእሱን እውነት ለመስማትና የቀረበበትን የሃሰት ማስረጃ ውድቅ ለማድረግ የሚያስቸል የራስ-መተማመን ስላልነበራቸው ነው። ታዲያ እውነትን ተናግሮ በፍርድ ቤት የቀረበበትን የሃሰት ማስረጃ ውድቅ ለማድረግ ሲታገል የነበረው አብርሃ ድስታ ዘነበ ሲሳይ በፌስቡክ ገፁ ላይ የፃፈውን የተሳሳተ ሃሳብ የራሱን እውነት ተናግሮ ግለሰቡን ማሳመንና ሃሳቡን ውድቅ ማድረግ እንዴት ይሳነዋል? ትክክለኛ ሃሳብና አመለካከት ያለው የፓርቲ ሊቀመንበር አንድ አባል የተሳሳተ ሃሳብና አመለካከቱን በውይይት ከማዳበርና ከማሻሻል ይልቅ አስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት አስተዳደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ለምን ይጣደፋል?

3ኛ፡- የተሳሳተ ሃሳብን መገደብ ጎጂ ነው!

በአጠቃላይ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቀውስ የሚፈጠረው፤ የዜጎች መብትና ነፃነት የሚጣሰው፣ እኩልነትና ፍትህ የማይረጋገጠው የተሳሳተ ሃሳብና አመለካከት ስላለ ብቻ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ሰዎች የራሳቸውን እውነት በነፃነት እንዳይናገሩ በመከልከላቸው፣ ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት እንዳይገልጹ በመገደባቸው ምክንያት ነው። በተለይ ደግሞ ሰዎች በውስጣቸው ያለውን የተሳሳተ ሃሳብና አመለካከት በነፃነት እንዳይገልፁ ሲከለከሉ ከማንም በፊት ተጎጂ “እውነት” ናት። ምክንያቱም፣ እንደ “John Stuart Mill” አገላለፅ፣ ስህተትና ውይይት “እውነት” የሚረጋገጥበት ብቸኛ መንገድና የሰው ልጅ አሁን ለደረሰበት የዕውቀት እና ሞራል ደረጃ ምንጭ እንደሆኑ ይጠቅሳል፡-
“ …the source of everything respectable in man either as an intellectual or as a moral being, he is capable of rectifying his mistakes, by discussion and experience. Wrong opinions and practices gradually yield to fact and argument; but facts and arguments, to produce any effect on the mind, must be brought before it. The whole strength and value, then, of human judgment, depending on the one property, that it can be set right when it is wrong, reliance can be placed on it only when the means of setting it right are kept constantly at hand.” On Liberty – John Stuart Mill, Ch.2: Of the Liberty of Thought and Discussion, Page 16

በመጨረሻም፣ አቶ ዘነበ ሲሳይ በፌስቡክ ገፁ ላይ ባወጣው ፅሁፍ ምክንያት በፓርቲው ደጋፊዎችና አባላት የተለየ ጫና የሚደረግበት ከሆነ፣ እንዲሁም የዓረና ፓርቲ አመራሮች ለዚህ ተግባሩ አስተዳደራዊ እርምጃ የሚወስዱበት ከሆነ ከግለሰቡ ባላይ ተጎጂ የሚሆነው ፓርቲውና የሚወክለው ሕዝብ ነው። ምክንያቱም፣ በአቶ ዘነበ ላይ የሚደረግባቸው ጫናና የሚወሰድባቸው እርምጃ በቀጣይ ሌሎች የፓርቲው አባላትና አመራሮች በውስጣቸው ያለውን የተሳሳተ ሃሳብና አመለካካት እንዳይገልፁ ይገድባል። ይህ ደግሞ በፓርቲው የወደፊት እንቅስቃሴና በማህብረሰቡ የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል። ይህን አስመልክቶ “John Stuart Mill” ያለውን በመጥቀስ ሃሳቤን እቋጫለሁ፡-
“…the peculiar evil of silencing the expression of an opinion is, that it is robbing the human race; posterity as well as the existing generation… If the opinion is right, they are deprived of the opportunity of exchanging error for truth: if wrong, they lose, what is almost as great a benefit, the clearer perception and livelier impression of truth, produced by its collision with error.” On Liberty – John Stuart Mill, Ch.2: Of the Liberty of Thought and Discussion, Page 13