አምባገነኖች የሚጠሉትና የሚፈሩት እውነትን ነው!

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በኒጄር፥ ኒያሜ ከተማ በአፍርካ የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት አያያዝ ዙሪያ የተለያዩ ሰብሰባዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ። በመጀመሪያዎቹ አምስት ቀናት በተካሄደው ስብሰባ ከ28 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (NGOs) ተሳታፊ ሆነዋል። እኔም በቦታው የተገኘሁት በአፍሪካ ስላለው የኢንተርኔት ነፃነት፡ “Internet Freedom in Africa” በሚል ርዕስ ያለኝን ልምድና ተሞክሮ እንዳካፍል ተጋብዤ ነበር። ዩጋንዳዊው “ፔፔ” እና ኬኒያዊቷ “ሳሎሜ” እንደ እኔ በፓናል ውይይቱ ላይ ልምድና ተሞክሯቸውን አካፍለዋል።

በመጀመሪያ በሀገሩ ስላለው የኢንተርኔት አጠቃቀምና ነፃነት ሁኔታ እንዲናገር እንደል የተሰጠው “ፔፔ” ነበር። “ፔፔ” በቀላሉ ከሰው ጋር መግባባት የሚችልና ጨዋታ አዋቂ ነው። በሀገሩ ዩጋንዳ የሰዎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። በዚህም የላቀ ዕውቅና የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክተውለታል። በውይይቱ ወቅት የኢንተርኔት ነፃነትን ከግል ሕይወቱ ጋር አቆራኝቶ ያቀረበበት ሁኔታ ደግሞ እጅግ በጣም አስገራሚ ነበር። “እኔና ጓደኞቼ” ይላል ፔፔ፡- 

“ እኔና ጓደኞቼ ከካምፓስ ከተመረቅን በኋላ በአመት አንዴ የመገናኘት ልማድ አለን። ያው እኔ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ ስለምሰራ መንግስት ከብዙ ሰዎች ጋር እንድገናኝ አይፈልግም። …አመፅና ሁከት የምቀሰቅስ ስለሚመስላቸው በተደጋጋሚ ያስሩኛል። እስካሁን ድረስ ከስድስት ግዜ በላይ አስረውኛል። አንድ ቀን ታዲያ ከካምፓስ ጓደኞቼ ጋር አንድ ላይ ተሰብስበን እየተወያየን ሳለ ፖሊሶች በሩን በኃይል በርግደው ገቡ። በዚህ ቅፅበት በቲዊተር (Twitter) ገፄ ላይ “Arrested” ብዬ ፃፍኩ። በሀገር ውስጥና በውጪ የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎችና ዲፐሎማቶች ይህን ፅሁፍ እንዳዩ እኔን ለማስፈታት በየፊናቸው መሯሯጥ ጀመሩ …

ከፖሊስ አዛዡ “በአስቸኳይ ይፈታ” የሚለውን መልዕክት ይዞ የመጣው ፖሊስ በሩን ሲያንኳኳ በታሰርኩበት ክፍል ውስጥ ሁለት ፖሊሶች እጅግ ፀያፍ ተግባር ሊፈፅሙብኝ እየተዘጋጁ ነበር። በግልፅ ልንገራችሁ፤ አንዱ ፖሊስ የውስጥ ሱሪዬን እያወለቀ ነበር፣ ሌላኛው ፖሊስ ደግሞ “he was erecting…” አዎ…በቲውተር ገፄ ላይ የፀፍኳት አንዲት ቃል በግብረ-ሰዶም ፖሊሶች ሊፈፀምብኝ ከነበረው የአስገድዶ መድፈር ታድጋኛለች። ጥቃቱ ተፈፅሞብኝ ቢሆን ኖሮ እንደዚህ ከፊታችሁ ቆሜ ለመናገር የሚያችል የራስ መተማመን አይኖረኝም። በእርግጠኝነት አሁን ያለኝን ስብዕናና የራስ መተማመን ያሳጣኝ ነበር…”

“ፔፔ” ላይ ከደረሰው በደልና ስቃይ አንፃር የእኔ በጣም ቀላል እንደሆነ ተሰማኝ። እኔን በጣም የገረመኝ፣ የትም ሀገር ቢሆን የአምባገነን መንግስታት ሥራና ተግባር አንድና ተመሣሣይ ነው። በኢንተርኔት አማካኝነት ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት የሚገልፁ ሰዎችን ያስራሉ፥ ይደበድባሉ፥ ያሰቃያሉ፥ ይገድላሉ፥…ወዘተ። እነዚህን አምባገነን መንግስታት ከፊል እና ፍፁም በማለት ለሁለት ክፍሎ ማየት ይቻላል።  

ከፊል አምባገነን የሆኑ መንግስታት የኢንተርኔት አገልግሎት አቅርቦትንና ተጠቃሚዎቹን መቆጣጠር የሚሹት ከብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል የሚደብቁት ነገር ስላለ ነው። የተዝረከረከ የመንግስት የአሰራር ግድፈቶችን፣ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ማጭበርበሮችን፣ እንደ ሙስና ያሉ አስተዳደራዊ ችግሮችን ወይም ሌሎች ፖለቲካዊ ችግሮችን ከማህብረሰቡ መደብቅ ይሻሉ። ስለዚህ፣ በኢንተርኔት አማካኝነት እነዚህን ችግሮች የሚያጋልጡ ሰዎችን ብዙ ግዜ ያስፈራራሉ፣ አንዳንዴ ደግሞ ያስራሉ።

ከላይ በተተቀሰው የውይይት መድረክ ተሳታፊ የነበረችው ኬኒያዊቷ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ “ሳሎሜ” በኬኒያ ስላለው የኢንተርኔት ነፃነት የሰጠችው አስተያየት እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል። “ሳሎሜ” ቅድሚያ የሰጠችው በቀጣዩ አመት በኬኒያ ስለሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ነበር። የኬኒያ መንግስት ጎረቤት ዩጋንዳን እንደ ምሳሌ በመውሰድ፣ በምርጫ ወቅት አመፅና ብጥብጥን ለመከላከል በሚል የኢነተርኔት አገልግሎትን ሊዘጋ እንደሚችል ስጋቷን ገልፃለች።

ፍፁም አምባገነን የሆኑ መንግስታት ግን የኢንተርኔት አገልግሎትን ከማቋረጥና መከታተል አልፎ-ተርፎ ተጠቃሚዎቹን ከማስፈራራት፥ ማሰርና መደብደብ እስከ መግደል ሊደርሱ ይችላሉ። የኢንተርኔት ግንኙነት መረቡን በከፊል ሳይሆን ሙሉ-ለሙሉ መቆጣጠር ይሻሉ። የተወሰኑ ሰዎችን ሳይሆን ሁሉም የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ለመከታተል ይሞክራሉ። ምክንያቱም፣ ፍፁም አምባገነን የሆኑ መንግስታት እንዳይታወቅ የሚሹት የፈፀሙትን ስህተት ወይም ለሕዝብ የተናገሩትን ውሸት ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ በእውን የሚያውቀውን እውነት ለመደበቅ ይጥራሉ።

ለምሳሌ፣ እኔ በማህበራዊ ድህረ-ገፆች ላይ “ሕዝብን ለአመፅ በማነሳሳት ወንጀል” ተከስሼ ለ82 ቀን ታስሬያለሁ። ሰብዓዊ ክብሬንና ስብዕናዬን በሚነካ መልኩ ተደብድቤያለሁ፥ ተሰድቤያለሁ። ነገር ግን፣ ስለተፈፀመብኝ በደልና ጭቆና እንኳን በነፃነት ለመናገርና ለመፃፍ እንኳን ያስፈራኛል። ምክንያቱም፣ በእኔ ላይ በእውን የፈፀሙብኝን ነገር ሌሎች በምናብ እንኳን እንዳያውቁት ይፈልጋሉ። አንተ በእውን ስለሆንከው ወይም በገሃደድ ስለምታውቀው ነገር በግልጽ መናገርና መፃፍ በራሱ “ሕዝብን ለአመፅ በማነሳሳት ወንጀል” በሚል ዳግም ሊያስከስስ ይችላል።

በአጠቃላይ፣ አምባገነኖች ከምንም በላይ የሚጠሉትና የሚፈሩት እውነትን ነው። በኢንተርኔት አማካኝነት የእነሱን ውሸት አጋለጥክ ወይም በእውን የምታውቀውን ፃፍክ፣ ዞሮ-ዞሮ ያው እነሱ የሚጠሉትን ተግባር ፈፅመሃልና በሄድክበት መውጫና መግቢያ ያሳጡሃል። ስለዚህ፣ ወይ እነሱን ፍርተህ ትኖራለህ፣ አሊያም ያመንክበትን አድርገህ የሚመጣውን ትቀበላለህ።