ከዮናታን ተስፋዬ የባሰ “አሸባሪ” ከቶ ከወደየት ይገኛል?

የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ አመራር ዮናታን ተስፋዬ ረጋሳ በተከሰሰበት የሽብርተኝነት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሏል። በዮናታን የተከሰሰው “በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ዓ.ም አንቀፅ(4) ስር የተደነገገውን በመተላለፍ” ነው። በዚህም የኦነግ ዓላማን ለማሳካት አመፅና ብጥብጥ እንዲቀጥልና ሌሎችን ለማነሳሳት አስቦ በፌስቡክ ገፁ ላይ በሚወጣቸው ፅሁፎች የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈፀም ማቀድ፣ ማዘጋጀት፣ ማሴር እና ማነሳሳት ወንጀል ተከሷል። በማስረጃነት የቀረበው ከሕዳር 24/2008 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 11/2008 ዓ.ም ባሉት ቀናት በፌስቡክ ገፁ ላይ ያወጣቸው ፅሁፎች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ በ2ኛ ተራ ቁጥር ላይ የተጠቀሰው እንዲህ ይላል፡-
“በቀን 11/04/08 ዓ/ም (ዲሰምበር 21 2015 4፡32 AM) ከቀኑ 10፡32 በሚጠቀምበት ፌስቡክ ‘ኢህአዴግ ችግር ማዳፈን እንጂ መፍታት የሚያስችል አቅም የለውም’ በሚል ከፃፈው ፅሁፍ ውስጥ ‘አምና ከ40 በላይ የኦሮሞ ተማሪዎችን ገደሎ ችግር የፈታ የመሰለው ኢህአዴግ ዘንድሮም ከአምናው ሳይማር ዜጎችን በመግደል ችግሩን ለመፍታት እየጣረ ነው። በቀና መንገድ ችግር ከመፍታት አፈና ምላሽ ሆኗልና ወደ የማይቀረው አመፅ እየተንደረደርን መሆኑን የሰሞኑ ተቃውሞና የገጠመው ምላሽ ከበቂ በላይ አስረጂ ነው’ የሚል ቀስቃሽ የሆነ ፅሁፍ በመፃፍ ሌሎችን እንዲነሳሱ በማድረጉ” አቃቤ ሕግ ለፌዴራል ክፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ካቀረበው የክስ ቻርጅ ውስጥ የተወሰደ

ታዲያ ይህ ፅሁፍ እንዴት ሆኖ ዮናታን በተከሰሰበት የሽብር ወንጀል በማስረጃነት ሊቀርብ ይችላል? በእርግጥ ለዚህ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በክስ ቻርጁ የተጠቀሱ ፅሁፎችን አንድ-በአንድ ብንመለከት “ይሄ እንዴት ፅሁፍ የሽብር ወንጀል በማስረጃነት ሊቀርብ ይችላል?” እያላችሁ ትጠይቃላችሁ። ይሁን እንጂ፣ በሕግ መሠረት ለአንዱም ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ አታገኙም። በእርግጥ ጥያቄው መልስ-አልባ ሆኖ ሳይሆን የተሳሳተ ስለሆነ ነው። ለተሳሳተ ጥያቄ ትክክለኛው መልስ ጥያቄውን ማስተካከል ነው። ለምሳሌ፣ ከላይ የተጠቀሰው ፅሁፍ “እንዴት በሽብር ወንጀል ተከሳሽ ላይ ማስረጃ ተደርጎ ሊቀርብ ይችላል?’ ብሎ መጠየቅ ስህተት ነው። ከዚያ ይልቅ፣ “ከሳሽ ወይም መንግስት ለምን በዚህ ፅሁፍ ተሸበረ?” በሚል መስተካከል አለበት።

ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ የኢህአዴግ መንግስት ከሕዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠበትን አግባብ በጥሞና ሲከታተል ለነበረ ሰው “ኢህአዴግ ችግርን ማዳፈን እንጂ መፍታት የሚያስችል አቅም የለውም” የሚለው ፅሁፍ ይዘት ሙሉ-በሙሉ “እውነት” እንደሆነ መገንዘብ ቀላል ነው። በተለይ በአምቦ ከተማ በተፈጠረው ችግር ተማሪዎች መገደላቸው የማይካድ ሃቅ ነው። በሕዳር 2008 ዓ.ም የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴው እንደገና ሲቀሰቀስ የኢህአዴግ መንግስት የሕዝብን ጥያቄ ተቀብሎ ችግሩን በቀና መንገድ ከመፍታት ይልቅ በኃይል ለማፈን በመሞከሩ ሀገሪቷን ለከፍተኛ አመፅና አለመረጋጋት ዳርጏታል። በዚህ ምክንያት፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መገደላቸውን፣ ብዙ ሺህዎችን ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውንና ከመኖሪያ ቄያቸው መፈናቀላቸውን፣ እንዲሁም በቢሊዮን የሚቆጠር የሕዝብና የመንግስት ንብረት መውደሙን ማንም አያስተባብልም። ሌላው ቀርቶ ዮናታንን የከሰሰው መንግስት እንኳን ይህን ሃቅ ሊያስተባብል አይችልም።

ታዲያ የዮናታን ፅሁፍ ሙሉ በሙሉ የማይካድ ሃቅ ሆኖ ሳለ ፀኃፊው በሽብር ወንጀል የተከሰሰው ለምንድነው? ፀኃፊው “በሌላ ዓይነት የሽብር ድርጊት ተሰማርቶ ነበር” ቢባል እንኳን ይህን ፅሁፍ በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችልበት አግባብ የለም፡፡ ስለዚህ፣ ተከሳሽ፥ ዮናታን ተስፋዬ የፈፀመው የወንጀል ተግባር በተጠቀሰው ፅሁፍ እውነትን በትክክል መግለፁ ነው። በከሳሽ፥ የኢህአዴግ መንግስት ላይ የደረሰው ጉዳት ደግሞ እውነት እንዲያውቅ መደረጉ ነው።

በመሰረቱ፣ እውነታን ከሌሎች መደበቅ በሚሹ ዘንድ ስላለፈው፣ ስለአሁኑ ወይም ስለወደፊቱ ግዜና ሁኔታ በትክክል መናገርና መፃፍ ከአሸባሪነት ተለይቶ ሊታይ አይችልም። በተለይ አምባገነን መንግስታት ደግሞ ሀገሪቱ ስላለችበት ሁኔታ፣ ሕዝቡ ስለሚያነሳቸው ጥያቄዎች፣ ሌላው ቀርቶ ስለራሳቸው ሥራና አሰራር ማንም እንዲያውቅባቸው አይፈልጉም። ምክንያቱም፣ ሁሉም አምባገነን መንግስታት በስልጣን ላይ መቆየት የሚችሉት፤ አንደኛ፡- ብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ስለ ፖለቲካዊ መብቱና ነፃነቱ በቂ ግንዛቤ ከሌለው፣ ሁለተኛ፡- የሲቭል ማህበራትና ድርጅቶች በፖለቲካው ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ካላደረጉ እና ሦስተኛ፡- የዓለም-አቀፉ ማህብረሰብ ስለ ሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ በቂ ግንዛቤ ከሌለው ነው።

ነገር ግን፣ የኢንተርኔት ፋይዳና አጠቃቀም ከላይ ከተጠቀሰው ሁኔታ ፍፁም ተቃራኒ ነው። ለምሳሌ፣ አንድ በጉዳዩ ላይ የተሰራ ጥናት የሚከተለውን ድምዳሜ አስቀምጧል፡-
“Four separate areas of Internet use threaten authoritarian regimes: mass public use, civil society organizations (citizens’ pressure groups), economic groups and the international community.”

እንደ ፌስቡክ ያሉ ማህበራዊ ድህረ-ገፆች በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ እንደ የውይይት መድረክ ሆነው እያገለገሉ ይገኛል። ዜጎች ሃሳብና መረጃን በቀላሉ እንዲለዋወጡ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። የሙያና ሲቭል ማህበራት ከሕብረተሰቡ ጋር አሳታፊ የሆነ ግንኙነት እንዲኖራቸው እና በፖለቲካው ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲጫወቱ ያግዛሉ። የዓለም-አቀፉ ማህብረሰብ ስለ ሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ያስችላሉ። በዚህ ምክንያት፣ እንደ ኢህአዴግ ባለ አምባገነናዊ መንግስት ላይ ከፍተኛ የሆነ የሕልውና አደጋ ይጋርጣሉ።

በአጠቃላይ፣ ዮናታን ተስፋዬ በፌስቡክ ገፁ ባወጣቸው ፅሁፎች ምክንያት በሽብርተኝነት ወንጀል መከሰሱና በዚህም ጥፋተኛ ሆኖ የመገኘቱ ሚስጥርን ለመረዳት ከዚህ ጋር አያይዞ መመልከት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ በክስ ቻርጁ ላይ በማስረጃነት የቀረቡትን ጽሁፎች በዝርዝር መመልከት ብቻ ይበቃል። ዩናታን ከሕዳር – ታህሳስ 2008 ዓ.ም ባሉት ቀናት በሀገሪቱ ስለተከሰተው አመፅና አለመረጋጋት በእውነታ ላይ የተመሰረተ ትክክለኛ መረጃ የያዙ ፅሁፎችን በፌስቡክ ገፁ ላይ አውጥቷል። በእነዚህ ፅሁፎች አማካኝነት ብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል፣ የተለያዩ የሲቨል ማህበራትና ድርጅቶች፣ እንዲሁም የዓለም-አቀፉ ማህብረሰብ በወቅቱ ስለነበረው የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ ትክክለኛ መረጃ እንዲደርሳቸው አድርጓል። በዚህም በኢህአዴግ መንግስት ላይ የሕልውና አደጋ እንዲጋረጥ የበኩሉን አስተዋፅዖ አበርክቷል። በወቅቱ በሀገሪቱ ስለነበረው የፀጥታና አለመረጋጋት ችግር፣ ሕዝቡ ስለሚያነሳቸው የመብትና ነፃነት ጥያቄዎች፣ እንዲሁም የመንግስትን ሥራና አሰራር በመተቸትና በመፃፍ የኢህአዴግ መንግስትን አሸብሯል። በዚህ ምክንያት፣ መንግስት የፀረ-በሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ጠቅሶ ከሰሰና ጥፋተኛ ነህ አለው። በእውነት ላይ የተመሰረተ ትክክለኛ መረጃ ክፉኛ ለሚያሸብረው መንግስት ከዮናታን ተስፋዬ የባሰ አሸባሪ ከቶ ከወደየት ይገኛል?