ያልተዘጋ እሰር ቤት ውስጥ ነፃነት ያስፈራል!

ከእስር ቤት የወጣሁ ሰሞን ወደ አንድ ባለሱቅ ደበኛዬ ጋር ስሄድ “እንኳን ለቤትህ አበቃህ….” እያለ አገላብጦ ከሳመኝ በኋላ “እኛ እኮ ‘እንትን’ ትመስለን ነበር” አለኝ። “‘እንትን’ ማለት ምን?” አልኩት። ፈራ-ተባ እያለ “እኛ እኮ የመንግስት ጆሮ-ጠቢ፥ ሰላይ ትመስለን ነበር” ሲለኝ ክት ብዬ ሳቅኩ። እንዲህ ማሰቡ በራሱ በጣም ገረመኝና “ያምሃል እንዴ? እስኪ አሁን እኔ ምኔ ነው ሰላይ የሚመስለው?” አልኩትና መልሱን ሳልጠብቅ ሄድኩ።

ከሳምንት በኋላ ደግሞ ለሁለት ዓመትና ከዚያ በላይ ከእኔ ጋር የአብሮነት ቆይታ ካላቸው ጓደኞቼ ጋር እየተጨዋወትን ሳለ ከመሃላቸው አንዱ “አይ ስዬ…እኔ እኮ ከእነሱ ጋር ትመስለኝ ነበር?” አለኝ። የረጅም ግዜ ጓደኛህ እንዲህ በጥርጣሬ ዓይን እያየህ መቆየቱን ስታውቅ የሆነ በቃ ያበሳጫል። “እንዴ… አንተ እንዴት ነው እንዲህ የምታስበው?” አልኩትና ወደ ሌሎቹ ዞሬ “ቆይ አንዴ ሁላችሁም…” ስል የሁሉም ትኩረት እኔ ላይ ሆነ። ከዚያ “ቆይ ከእናንተ ውስጥ ‘ስዬ ሰላይ ነው’ ብሎ የሚያስብ ነበረ?” እላቸዋለሁ ሁሉም በአንድ ድምፅ “አዎ!” አሉኝ።

ምላሻቸው ከማስገረም አልፎ አስደነገጠኝ። በለሆሳስ “ቆይ እኔ ምኔ ነው ሰላይ የሚመስለው?” ብዬ በውስጤ ማሰላሰል ስጀምር ከጎኔ የነበረው ጓደኛዬ “ቆይ ስዬ…አንተ ራስህ፣ ይህን ያህል ዓመት በነፃነት የፈለከውን እየተናገርክና እየፃፍክ ስትኖር ‘አለመፍራትህ በራሱ ሌላን ሰው አያስፈራም?’ እንደዛ በነፃነት ስትናገርና ስትፅፍ ሁላችንም ‘በቃ… ከኋላው የሆነ ነገር ቢኖር ነው’ ብለን አሰብን። ይሄ’ኮ አንተ የተለየ ነገር ስላደረክ ወይም ከሌሎቻችን በተለየ አንተን አለማመን አይደለም። እንደዛ አስፈሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ከሁላችንም በተለየ አንተ ብቻ “ነፃ” ስትሆን አያስጠረጥርም ልትለኝ ነው?”

ይህ ከሆነ አምስት ወራት አለፉ። ነገር ግን፣ “ያኔ’ኮ ‘እንትን’ ትመስለኝ ነበር” የምትለዋ ጥያቄ ቀጥላለች። ዛሬ ምሳ ሰዓት ላይ ወደ ቤት እየሄድኩ ሳለ አንድ መስፍን የሚባል ጓደኛዬ አገኘኝና “ስዬ…ድሮ እኮ እንፈራህ ነበር” አለኝ። “ለምን?” እለዋለሁ “ያኔ’ኮ ‘እንትን’ ትመስ…” አላስጨረስኩትም! ወደ ቤት እንደገባሁ ይህን ፅሁፍ መፃፍ ጀመርኩ።

በመጀመሪያ ደረጃ ያለኝ ፖለቲካ አቋምና አመለካከት ትክክለኝነቱ የሚረጋገጠው በየእለቱ በማንፀባርቀው ሃሳብና በምሰራው ሥራ ሳይሆን በመታሰሬ መሆኑ በራሱ ያበሳጫል። ነገር ግን፣ ለራሱ እስከ ሕይወቱ መጨረሻ “ባልተዘጋ እስር ቤት” ውስጥ እየኖረ እንደ እኔ “ታስሮ ለተፈታ” ሰው ከንፈሩን ሲመጥ ማየት በጣም ይገርማል። ኧረ እንደውም ከማስገረም አልፎ አንዳንዴ እንደ እብድ ለብቻ ያስቃል።

“‘እንትን’ ትመስለን ነበር” ሲሉ “ሰላይ ወይም የመንግስት ጆሮ-ጠቢ” ለማለት እንደሆነ ግልፅ ነው። ጥያቄው በጓደኞቼ ውስጥ የነበረውን ስጋትና ፍርሃት ያስከተለው ጥርጣሬን ያሳያል። እኔን የጠረጠሩበት ምክንያት ከሌሎች በተለየ መልኩ ሃሳብና አመለካከቴን በነፃነት በመግለፄ ነው። በእርግጥ ሁላችንም የራሳችንን ሃሳብና አመለካከት በነፃነት መግለፅ እንሻለን። እንዲህ ያለ ነፃነት ለእስርና እንግልት እንደሚዳርግ ደግሞ እናውቃለን። ስለዚህ፣ ሃሳብና አመለካከቱን በነፃነት የሚገልጽ ሰው እንደሚታሰር ይጠብቃሉ። ካልታሰረ ደግሞ “‘እንትን’ ቢሆን ነው” ብለው ይጠረጥራሉ።

ዜጎች ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት ለመግለፅ የሚፈሩት ሆነ የሌሎችን ነፃነት የሚጠራጠሩት መንግስትን ስለሚፈሩ ነው። ይሁን እንጂ፣ እንደ ፈረንሳዊው ፈላስፋ “Montesquieu” አገላለፅ፣ መንግስት የተፈጠረበት መሰረታዊ ዓላማ ዜጎች እርስ-በእርስ አንዳይፈራሩ ነው፡-

“The political liberty of the subject is a tranquility of mind arising from the opinion each person has of his safety. In order to have this liberty, it is requisite the government be so constituted as one man need not be afraid of another.” Baron de Montesquieu, The Spirit of Laws, trans. Thomas Nugent, 2 vols. (New York: The Colonial Press, 1899), 1:151–162.

የመንግስት ሥራና ተግባር ዜጎች እርስ-በእርስ ሳይፈራሩ ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት አንዲገልፁ ማስቻል ነው። ሆኖም ግን፣ በሀገራችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር፣ ዜጎች የራሳቸውን ሃሳብና አመለካከት በነፃነት መግለፅ ይቅርና የጥቂቶች ነፃነት ብዙሃኑን ለስጋትና ጥርጣሬ እየዳረገው ይገኛል። ይህ የሆነበት ምክንያት ሌላ ሳይሆን መንግስት የተፈጠረበትን መሰረታዊ ዓላማ ስለሳተ ነው። መንግስታዊ ሥርዓቱ የዜጎችን መብትና ነፃነት ከማስከበር ይልቅ መንግስትን ሕዝቡን የሚፈራና ሕዝቡም እርስ-በእርስ እንዲፈራራ የሚያደርግ ስለሆነ ነው። በመሰረቱ ፍርሃት ለፍፁም አምባገነናዊ መንግስት የተግባር መመሪያና መርህ ነው፡-

“In a tyranny, the moving and guiding principle of action is fear. Fear in a tyranny is not only the subjects’ fear of the tyrant, but the tyrant’s fear of his subjects as well. [It] is not merely a psychological motive, but the very criteria according to which all public life is led and judged.”  On the Nature of Totalitarianism: An Essay in Understanding

በዚህ መሰረት፣ መንግስትን በመፍራት ሆነ በመጠራጠር፣ ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት ከመግለፅ የሚቆጠቡ ሰዎች በሙሉ በፍርሃት መርህና መመሪያ መሰረት ለሚመራው ሥርዓት ተገዢዎች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ፣ ስርዓቱን በስልጣን ላይ ለማቆየት የመሚያስፈልገውን ፍርሃት እየለገሱ ስለሆነ እንደ ቀንደኛ ደጋፊ መታየት አለባቸው።

ፀኃፊዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያንና ሌሎች በተደጋጋሚ ለእስርና እንግልት የሚዳረጉት በራሳቸው ያጠፉት ጥፋት ወይም የፈፀሙት ወንጀል ስላለ አይደለም። የአምባገነናዊ መንግስት ዓላማም እነሱን በማሰቃየትና በማስፈራራት ወደፊት ለሥርዓቱ ተገዢ እንዲሆኑ ለማድረግ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ሌላው የሕብረተሰብ ክፍል ልክ እንደ እነሱ ሃሳብና አመለካከቱን በነፃነት ለመግለጽ እንዳይሞክር ለማስፈራራት ነው።

ብዙ ፀኃፊዎች፣ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን እስር ቤት ውስጥ የተዘጋባቸው ከእስር ቤት ሲወጡ ነፃነታቸውን ስለሚቀዳጁ ነው። በዚህም፣ ከእስር ቤት ውጪ ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት ስለሚገልፁና ሌላውም የሕብረተሰብ ክፍል ልክ እንደነሱ ነፃነቱን እንዲቀዳጁ ፈር-ስለሚቀዱ ለእስር ይዳረጋሉ። ምክንያቱም፣ እነዚህ ሰዎች ነፃነታቸውን የሚያጡት እስር ቤት ሲገቡ ብቻ ነው።

ከዚህ በተቃራኒ፣ ከእስር ቤት ውጪ ሀኖ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ያለን ሰው ማሰርና ማሰቃየት አስፈላጊ አይደለም። በመኖሪያ ቤቱ እና በስራ ቦታ ሃሳብና አመለካከቱን በነፃነት ለመግለጽ የሚፈራ ሰው ባልተዘጋ እስር ቤት ውስጥ ራሱን ያሰረ ስለሆነ ድጋሜ ማሰር አያስፈልግም። ከዚህ በተጨማሪ፣ ፍርሃትን ማስፈን ለሚሻ ስርዓት ፈሪዎች ወዳጆቹና ደጋፊዎቹ ናቸው። በአጠቃላይ፣ ፀኃፊዎች፣ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን በተደጋጋሚ የሚታሰሩት አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ሃሳብና አመለካከቱን ለመግለፅ፣ መብትና ነፃነቱን በይፋ ለመጠየቅ ስለሚፈራ ነው። ስለዚህ፣ እነሱ የሚታሰሩት ሌሎችን ካልተዘጋው እስር ቤት ነፃ ለማውጣት ሲሞክሩ ነው። 

One thought on “ያልተዘጋ እሰር ቤት ውስጥ ነፃነት ያስፈራል!

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡