ቴዲ አፍሮ እና ዶ/ር ቴድሮስ ሲያሸንፉ ኢትዮጲያ ተሸንፋለች!

ሁለት ቴዲዎች ባለፉት ሳምንታት ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ዋና መነጋገሪያ አጀንዳ ሆነው ሰንብተዋል። በእርግጥ ሁለቱም በየፊናቸው ስኬታማ ለመሆን በቅተዋል። ከዚያ በስተጀርባ ግን በሁለቱ ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች መካከል የነበረው ውዝግብ ስለ ሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ ብዙ ነገር ይጠቁማል።

በመጀመሪያ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሁለቱም ቴዲዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች እንዳላቸው መገንዘብ ይቻላል። ሁለቱም ወገኖች ለድጋፍና ተቃውሟቸው የራሳቸውን ምክንያቶች ዘርዝረዋል። ነገር ግን፣ ከሁለቱ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ሲነሱ የነበሩት ሃሳቦች በዋናነት “ኢትዮጲያ” በሚለው ጭብጥ ላይ ያጠነጠኑ ነበሩ።

እንደ ማንኛውም እውቅ ሙዚቀኛ በተለይ “ኢትዮጲያ” በሚለው ነጠላ ዜማ እንደወጣ ሌላው ቴድሮስ (ፀጋዬ) የሰነዘረው ሂስና ትችት ከዘፈኑና ዘፋኙ አልፎ የቴዲ አፍሮ አድናቂዎችን አሳዝኗል፥ አስቆጥቷል። ከዚያ በተረፈ፣ ዘፋኙ የለቀቀው አልበም ተደማጭነት እንዳያገኝ ወይም ለአድማጭ ተደራሽ እንዳይሆን “በገበያ ላይ መቅረብ የለበትም” የሚል ተቃውሞ አልገጠመውም። ከዚያ ይልቅ፣ የቴዲ አፍሮ ተቃዋሚዎች ትኩረታቸው “አርቲስቱ ከብዙሃንነት ይልቅ የአህዳዊ አንድነት አቀንቃኝ ነው” የሚል ነበር። በዚህ ምክንያት ከአርቲስቱ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ በኢትዮጲያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት – ኢብኮ (EBC) እንዳይቀርብ ታገደ። ስለ “ኢትዮጲያ” በመዝፈኑ አርቲስቱን “የአንድነት አቀንቃኝ ነው” በሚል ቃለ-ምልልሱ የሕዝብ ንብረት በሆነው ብሔራዊ ቴሌቪዥን እንዳይቀርብ ሲከለከል የፖለቲካችን ሕመም አገረሸ። በውሳኔው የቴዲ አፍሮ ደጋፊዎች ክፉኛ ሲቆጡ፣ ተቃዋሚዎቹ ደግሞ በጣም ተደሰቱ። 

የቴዲ አፍሮ ቃለ-ምልልስ በኢብኮ እንዳይተላለፍ በታገደበት ሳምንት ሌላኛው ቴድሮስ (ዶ/ር) “ኢትዮጲያን” ወክሎ የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ዳይሬክተር ጄኔራል ሆኖ ለመመረጥ የመጨረሻውን ጥረት እያደረገ ነበር። በአንድ በኩል የቴዲ አፍሮ ተቃዋሚዎች ከነበሩት ውስጥ አብዛኞቹ ዶ/ር ቴድሮስን በመደገፍ የዓለም-አቀፉ ድርጅት መሪ ሆኖ እንዲመረጥ ድጋፍና ቅስቀሳቸውን አጠናከረው ቀጠሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ከቴዲ አፍሮ አድናቂዎች ውስጥ አብዛኞቹ በዶ/ር ቴድሮስ ላይ ተቃዉሟቸውን አጠናክረው ቀጠሉ። ከሁለቱም ወገኖች ምርጫው በሚካሄድበት ቦታ በአካል ተገኝተው ያሳዩት ድጋፍና ተቃውሞን እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል።

አብዛኞቹ የዶ/ር ቴድሮስ ደጋፊዎች ለራሳቸው የብዙሃንነት አቀንቃኝ ሆነው የቴዲ አፍሮ አድናቂዎችን “የአንድነት አቀንቃኞች” እያሉ ሲያብጠለጥሏቸው ነበር። ለዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ዳይሬክተርነት የሚደረገው ውድድር ሊጠናቀቅ ሲቃረብና በዶ/ር ቴድሮስ ላይ የሚካሄደው የተቃውሞ እንቅስቃሴ እየተጠናከረ ሲሄድ በአብዛኛው “የብዙሃንነት አቀንቃኝ” የነበሩት ደጋፊዎቹ ስለ አንድነት ማቀንቀን ጀመሩ። በዚህም “ዶ/ር ቴድሮስ እየተወዳደረ ያለው እንደ ግለሰብ ወይም መንግስት ሳይሆን ኢትዮጲያ እና አፍሪካን ወክሎ እንደመሆኑ ልዩነታችንን ወደ ጎን በመተው ሁሉም ኢትዮጲያዊ ድጋፉን ሊቸራቸው ይገባል” የሚል መከራከሪያ ይዘው ቀረቡ። ቀድሞ የአንድነት አቀንቃኝ የነበሩት አብዛኞቹ የቴዲ አፍሮ አድናቂዎች ደግሞ “ስለ አንድነት ሲባል ዶ/ር ቴድሮስ ከፍተኛ አመራር ከሆኑበት የኢህአዴግ መንግስት ጋር ያለንን ቅራኔና ልዩነት መተው አይቻለንም” በሚል ተቃውሟቸውን አጠናክረው ቀጠሉ። በዚህም የኢትዮጲያ ፖለቲካ ሕመሙ በጣም እንደፀናበት መገንዘብ ይቻላል።

አብዛኞቹ የቴዲ አፍሮ ተቃዋሚዎች ከኢትዮጲያ አንድነት ይልቅ ብዙሃንነትን በማስቀደም የሁላችንም በሆነ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ቃለ-ምልልሱ እንዳይተላለፍ አደረጉ። በተመሣሣይ፣ አብዛኞቹ የዶ/ር ቴድሮስ ተቃዋሚዎች ከአንድነት ይልቅ የፖለቲካ ልዩነትን በማስቀደም የዓለም-አቀፍ ድርጅት መሪ እንዳይሆን ተቃወሙ። ይሁን እንጂ፣ ሁለቱም ቴዲዎች በየፊናቸው ስኬታማ ሆነዋል። በሁለቱም አጋጣሚዎች ተነስታ የወደቀችው ኢትዮጲያ ናት። ኢትዮጲያ ውስጥ እየኖረ ስለ ሀገር አንድነት ሲዜም የሚቀፋቸው በአንድ ወገን፣ ስለ ኢትዮጲያ አንድነት እያዜሙ የኢትዮጲያን ተወካይ የሆነ ተወዳዳሪ የሚቃወሙ በሌላ ወገን ሆነው አንዱ ሌላውን ሲጠላና ሲያጥላላ በመሃል ግራ ተጋብታ መሄጃ የጠፋት ኢትዮጲያ ናት።

“ኢትዮጲያ” በሚለው አልበም ዙሪያ ከትችትና ተቃውሞ ባለፈ ቃለ-ምልልሱ በብሔራዊ ቴሌቪዥን እንዳይተላለፍ ቢታገድም ቴድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በሥራው ስኬታማ ከመሆን አላገደውም። ስለዚህ፣ ቴድሮስ አሸንፏል! ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ዳይሬክተር ጄኔራል ለመሆን ያደረገው ውድድር ምንም ያህል ተቃውሞ ቢገጥመው በምርጫው ስኬታማ ከመሆን አላገደውም። አሁንም ቴድሮስ አሸንፏል። በሁለቱም አጋጣሚዎች የታየው በቂምና ጥላቻ የታጨቀ ጭፍን ድጋፍና ተቃውሞ “አንድነት” የሚለውን ቃል ትርጉምና ፋይዳ አሳጥቶታል። በአጠቃላይ፣ ቴዲ አፍሮ እና ዶ/ር ቴድሮስ ሲያሸንፉ ኢትዮጲያ ተሸንፋለች!!!