የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ዮናታን ተስፋዬ ከወንጀል ነፃ ስለመሆኑ ያረጋገጠ ነው!

ባለፈው የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አቶ ዮናታን ተስፋዬ በፌስቡክ ገፁ ላይ ባወጣቸው ፅኁፎች ምክንያት ተከስሶ “ጥፋተኛ” መባሉ አግባብ እንዳልሆነ ገልጩ ነበር። በዛሬው ዕለት ደግሞ ፍርድ ቤቱ በስድስት አመት ከስድስት ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑ ተዘግቧል። የፍርድ ቤቱን የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ አስመልክቶ በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው፣ እንዲሁም በክስ ቻርጁ ላይ አንደኛ ተራ ቁጥር ላይ የተጠቀሰው የክስ ማስረጃ የሚከተለው ነው፡-  
image

ከላይ በፅኁፉ ውስጥ የተንፀባረቀውን ሃሳብ የአቶ ዮናታን ተስፋዬ የግል አመለካከት ወይም የግል አስተያየት (Opinion) መሆኑ እርግጥ ነው። ፅሁፉን ተከሳሽ አቶ ዮናታን ተስፋዬ እንደፃፈው እርግጥ ነው። አቃቤ ሕግም ይህንን እንደ በክስ ማስረጃነት ማቅረቡ ችግር የለውም። ችግሩ ፍርድ ቤቱ ይህንና ሌሎች ተመሣሣይ ይዘት ያላቸው ፅሁፎችን ተቀብሎ በዮናታን ላይ የጥፋተኝነትና ቅጣት ውሳኔ ማሳለፉ ላይ ነው።

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በሁለት እሳቤዎች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ አንደኛ፦ በፅሁፉ ውስጥ የተገለፀው ሃሳብና አመለካከት እውነትነት የሌለውና ስህተት ነው፡፡ ሁለተኛ፦ ይህ የተሳሳተ ሃሳብና አመለካከት ሌሎች ሰዎች ለመጥፎ ወይም ጎጂ ለሆነ ተግባር ያነሳሳል። ነገር ግን፣ የክሱ አንቀፅና ማስረጃዎች በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 29 ላይ ከተደነገገው የሃሳብና አመለካከት ነፃነት አንፃር ሲታይ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት እሳቤች ሙሉ-በሙሉ ውድቅ ያደርጋቸዋል፡፡

ተከሳሽ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 29 መሰረት የራሱን አመለካከት የመያዝና ሃሳቡን በነፃነት የመግለጽ መብቱን ተጠቅሞ ከላይ በማሳያነት የተጠቀሰው ፅሁፍ በፌስቡክ ገፁ ላይ ለጥፏል። ፍርድ ቤቱ ግን የፅኁፍ ይዘት እውነትነት የሌለውና ስህተት ነው በሚል የጥፋተኝነትና ቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ በመሰረቱ እውነትነት የሌለውና የተሳሳተ ሃሳብና አመለካከት ከራሱ ከባለቤቱ በስተቀር በማንም ላይ ጉዳት ሊያስከትል አይችልም። ምክንያቱም፣ እውነትነት የሌለው ሃሳብን ወይም የተሳሳተ አመለካከትን ሌሎች ሰዎች አይቀበሉትም።

ለክሱ በማስረጃነት ከቀረበው ፅሁፍ ውስጥ የሚከተለውን ዓ.ነገር እንደ ማሣያ ወስደን እንመልከት፦ “መንገድ መዝጋት፣ የመንግስት ስራን ማስተጓጎል፣ ለጭቆና መሳሪያነት የሚያገለግሉ ማናቸውም ቁሳቁስ ወይም ቦታ በማቃጠልና በማውደም የመሳሰሉት ተግባራት የሰላማዊ ትግል ዘዴዎች ናቸው”። በእርግጥ የተጠቀሱት ተግባራት የአመፅና የረብሻ እንጂ ፀኃፊው እንዳለው የሰላማዊ ትግል ዘዴዎች አይደሉም። በማስረጃነት የቀረበው ፅሁፍ መረዳት እንደሚቻለው አቶ ዮናታን በሰላማዊ የትግል ዜዴዎች ዙሪያ የተሳሳተ አመለካከት እንዳላቸው ያረጋግጣል፡፡

አቶ ዮናታን ተስፋዬ በፌስቡክ ገፁ ላይ ያወጣው ፅሁፍ ይዘት ከእውነት የራቀና የተሳሳተ ነው። ስለዚህ፣ አንድ ሰው አቶ ዮናታን በፌስቡክ ገፁ ላይ በለጠፈው ፅሁፍ የተንፀባረቀውን ሃሳብ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ በቅድሚያ የሃሳቡን ትክክለኝነት ማረጋገጥ አለበት። በፌስቡክ ገፅ ላይ የተለጠፈውን ፅሁፍ ይዘት አመኖ ለመቀበል በራሱ ማወቅ፣ ሃሳቡን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ በራሱ መፍቀድ አለበት። ለዚህ ደግሞ ፅሁፉ በእውነት ላይ የተመሰረተና ትክክል ስለመሆኑ በራሱ ማወቅና ማመን አለበት።

በአጠቃላይ፣ ማንኛውም ጤናማ አዕምሮ ያለው ሰው ደግሞ እንዲህ ያለ በተሳሳተ እሳቤና ግንዛቤ ላይ የተመሰረተ ሃሳብና አመለካከትን ተቀብሎ ተግባራዊ አያደርግም። ስለዚህ፣ በሌሎች ሰዎች ዘንድ ተቀባይነትና ተፈፃሚነት የሌለው ሃሳብን በፌስቡክ ገፅ ላይ መለጠፍ “ሽብርተኝነትን በማበረታታት” ሊያስጠይቅ አይችልም። ፍርድ ቤቱ ግን በዮናታን ላይ “ሽብርተኝነትን በማበረታታት ወንጀል ጥፋተኛ ነው በሚል እስራት ፈርዶበታል፡፡ ይህ የተከሳሹ ሃሳብና አመለካከት ትክክልና በሌሎች ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው እንደሚችል ያረጋግጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ውሳኔው የተከሳሹን ሃሳብና አመለካከት ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ “ጠቃሚነት” እንዳለው አረጋግጧል፡፡

በእውነታ ላይ ያልተመሰረተ ሃሳብን ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ ስህተት ነው። ምክንያቱም የተሳሳተ ሃሳብን መቀበልም ሆነ መፈፀም ጠቀሜታ የለውም። ነገር ግን፣ ሌሎች ሰዎች አቶ ዮናታን በፌስቡክ ገፁ ላይ የጠቀሳቸውን የአመፅና ረብሻ ተግባራትን ተቀብለው ለማቀድና ለመፈፀም በቅድሚያ ትክክለኝነታቸውን በራሳቸው ማወቅና መቀበል አለባቸው። ነገር ግን፣ የእሱን ሃሳብና አመለካከት ትክክለኝነት ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ከጠቃሚነቱ (utility ) ተነጥሎ ሊታይ አይችልም፡፡ እንደ “John Stuart Mills” አገላለፅ፦

“The truth of an opinion is part of its utility. If we would know whether or not it is desirable that a proposition should be believed, is it possible to exclude the consideration of whether or not it is true? ..Those who are on the side of received opinions never fail to take all possible advantage of this plea; you do not find them handling the question of utility as if it could be completely abstracted from that of truth.”
On liberty

በአጠቃላይ፣ ዮናታን ተስፋዬ በፌስቡክ ገፁ ላይ ባወጣው ፅሁፍ ላይ ያንፀባረቀው ሃሳብና አመለካከት ከእውነት የራቀና ስህተት ቢሆን ኖሮ በሌሎች ሰዎች ዘንድ ተዓማኒነትና ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡ እውነትነት የሌለው ሃሳብና አመለካከት ስህተት እንደመሆኑ ተግባራዊ ቢደረግ ጉዳት እንጂ ጠቃሜታ አይኖረውም፡፡ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ግን ዮናታን ተስፋዬ በፌስቡክ ገፁ ላይ ባወጣው ፅሁፍ የገለፀው ሃሳብና አመለካከት ትክክል፣ ተዓማኒነትና ተቀባይነት ያለው፣ እንዲሁም ተግባራዊ ቢደረግ ጠቀሜታ እንዳለው ያረጋገጠ ነው፡፡ አንድ ሰው ትክክልና ጠቃሚ የሆነ ሃሳብና አመለካከት በማንፀባረቁ ጥፋተኛ ተብሎ በፅኑ እስራት የሚቀጣ ከሆነ ውሳኔው ተከሳሹ ከወንጀል ነፃ መሆኑን ከማረጋገጥ የዘለለ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም፡፡