የሦስት ምርጫዎች ወግ: 100% ያደነቁራል!

(ይህ ፅሁፍ በ2007 ዓ.ም የተካሄደውን ሀገራዊ ምርጫ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ 100% አሸንፌያለሁ ማለቱን አስመልክቶ በፌስቡክ ገፄ ላይ ያወጣሁት ነው፡፡ ፅሁፉን ደግሜ ሳነበው የሀገራች ፖለቲካ አሁን ከገባበት “አዙሪት” ውስጥ እንዳይገባ ቅድመ ማስጠንቀቂያ የሰጠሁበት መስሎ ተሰማኝ፡፡ እስኪ እናንተም አንብቡና ሃሳባችሁን ስጡበት፡፡)


አብዛኞቻችን (አንዳንድ የኢህአዴግ ደጋፊዎችን ጨምሮ) ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፓርላማ እንዲገቡ የምንፈልገው ለምንድነው? “በተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛ ድምፅ ኖሯቸው አዲስ ህግ እንዲያረቁ ነው?”…አይደለም! መንግስት ከፈለገ ማታ ህግ አርቅቆ ጠዋት በፓርላማ ሊያፀድቅ እንደሚችል በስዬ አብረሃ ህግ አሳይቶናል (በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ ግለሰቦችን የዋስትና መብት እንዳይኖራቸው የሚያትተው የህግ አንቀፅ በፓርላማ የፀደቀበት…)

…”መንግስት በሚያቀርባቸው የዉሳኔ ሃሳቦች ላይ ድጋፍ በመንፈግ ውድቅ እንዲያደርጉ ነው?” አይደለም! ልክ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ “ለረቂቅ ሰነዱ ድጋፍ…” ሲሉ ከእንቅልፋቸው የሚነቁና በደመ-ነፍስ እጃቸውን የሚያወጡ የምክር ቤት አባላት ባሉበት በተቃዋሚዎች ጩኸት የሚለወጥ የውሳኔ ሃሳብ ሊኖር አይችልም።

“የህግ አስፈፃሚውና ተርጓሚውን ተግባር እንዲቆጣጠሩልን ነው?”…አይደለም! የትኛው ሚኒስትር፣ የትኛው ዳኛ፣ የትኛው ፖሊስ…ኧረ የቱ የመንግስት መስሪያ ቤት ነው የህዝብ ተወካዮችን ከቁብ ቆጥሮ ሥራና አሰራሩን ያሻሽለው? እስኪ አፈ-ጉባኤ አባ-ዱላ ገመዳ “በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ቅጥ-ያጣ ሙስና በአስቸኳይ እንዲወገድ” ጥብቅ ማሳሰቢያ ሲሰጡ ትንሽ ደንገጥ ያለ የዩንቨርሲቲ ፕሬዘዳንት አጋጥሟችሁ ያውቃል? የፍርድ ቤት ዳኛ ሆነ ፖሊስ የሚታዘዙት፣ የሚፈሩት… በህገ-መንግስቱ የበላይ አካል የሆኑትን የህዝብ ተወካዮች ነው ወይስ ለአንድ የኢህአዴግ ካድሬ?

“የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ፓርላማ እንዲገቡ አጥብቀን የምንሻው በሕገ-መንግስቱ የተጣለባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ ይወጣሉ በማለት ነው?” አይደለም! ከዚያ ይልቅ፣ የመንግስትን ስህተትና ትክክለኝነት የሚያሳዩ “መስታዎት” ሆነው ስለሚያገለግሉ ነው።

እንደ ሀገር የህዝቡን ሃሳብ፣ ብሶትና ጥያቄ የሚስተናገዱበት ነፃ የሆነ ሚድያ የለንም፣ በቅጡ የተደራጁ የሙያና ሲቪል ማህበራት የሉንም ወይም ደግሞ ገዢው ፓርቲ በራሱ የሃሳብ ልዩነቶችን የማስተናግድ ባህል የለውም፡፡….ለዚህ ተግባር በህግ የተቋቋሙት እንደ የህዝብ እምባ-ጠባቂ፣ የኢትዮጲያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን፣… ወዘተ ያሉትም ቢሆኑ የተደራጀ አቅም የላቸውም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ከመንግስት አካላት ተፅዕኖ ነፃ ሆነው አገልግሎታቸውን ለህዝብ አይሰጡም።

በእንዲህ ያለ ሁኔታ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ትክክለኛውን የህዝብ ስሜት ለመንግስት አካላት የሚያደርሱ ብቸኛ አካላት ናቸው። በተለይ ደግሞ ልክ እንደ አንድ ግለሰብ በስሜት ለሚነዳው የእኛ ሀገር መንግስት ብዙ ሺህ ዶላር ከሚከፈላቸው አማካሪዎች፣ ከምንትስ ዩኒቨርሲቲ በዶላር ማስተርስና ዶክትሬት ድግሪ ከሸመቱ አማካሪዎች በተሻለ ስህተትን የሚጠቁሙ ስለሆኑ ነው። ጋዜጠኞችን ለእስርና ስደት ከዳረገ በኋላ ተቃዋሚዋች በህዝብና መንግስት መካከል ያሉ ብቸኛ ድልድይ ናቸው።

በአጠቃላይ፣ የፌደራል ፖሊስና ደህንነት ፀረ-ሽብር ግብረ-ሃይል፣ የፍርድ ቤት ቀጠሮ እየጠየቀ ወንጀል ከሚፈበርክ አቃቤ-ህግ፣ በሙስና ከሚውጠው በላይ የጎረሰ የፍርድ ቤት ዳኛ፣ …በነፃነት የመኖር፣ የማሰብ እና የመናገር መብትህ በእነሱ ፍቃድ የተገኘ የሚመስላቸው የሰፈር ካድሬዎች፣….በእነዚህ የጨቋኝ ስረዓት ጡንቻዎች ሳይደቆሱ የህዝብን ጥያቄ ለመንግስት የሚያደርሱ ብቸኛ ወኪሎች የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ብቻ ናቸው።

አሁን “ምርጫውን 100% አሸነፍኩ…“ እያለ የሚለፍፈው ኢህአዴግ “ያያት ወንድ ሁሉ በአድናቆት ፈገግታ ታጅቦ ‘ቆንጆ…ውብ ፅጌረዳ’ እያለ ሲያቆለጳጵሳት ከቤቷ ያለውን ብቸኛ የፊት መስታዎት እንደሰበረች ቀበጥባጣ ኮረዳ አይነት ነው። ከተወሰነ ግዜ በኋላ በጠወለገ ውበቷ የለበጣ ሳቅ ሲስቅቧት እሷ ግን በደስታ የምትስቅ፣ ባገጠጠው ፈገግታዋ ሲሳለቁ፣ መልሳ የምታገጥ፣ …. በመጨረሻም ሁሉም ሲሰለቿትና ሲያገሏት አስቀያሚነቷን እንደምትረዳ አይነት ኮረዳ…….

አሁን በ100% የሚያስጨፍረው የምርጫ ውጤት ኢህአዴግ’ ስህተቱን ከውድቀቱ እንዲማር ከማድረግ ሌላ ፋይዳ የለውም።