የሰቆቃ ልጆች ክፍል-2፡ “ጭቆና ሲበዛ አሸባሪነት ይወለዳል!”

እ.አ.አ. ከ1989 – 1902 ዓ.ም እንግሊዝ እና በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ነጭ ሰፋሪዎች መካከል የተካሄደው ጦርነት “Anglo-Boers War II” በመባል ይታወቃል። በዚህ ጦርነት ሂትለር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በአይሁዶች ላይ የፈፀመውን ዓይነት ጭፍጨፋ እንግሊዞች በደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች ላይ ፈፅመውታል። በደቡብ አፍሪካ የነጮች አፓርታይድ ሊመሰረት የቻለው እንግሊዞች በደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች ላይ በፈፀሙት ጭፍጨፋ ነው።

በክፍል አንድ በዝርዝር እንደተመለከትነው፣ ናዚዎች በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት በአይሁዶች ላይ የፈፀሙት የዘር-ማጥፋት እ.አ.አ. በ1948 ዓ.ም በእስራኤል የአይሁዶች አፓርታይድ እንዲመሰረት ምክንያት መሆኑን ተመልክተናል። በተመሣሣይ፣ በደቡብ አፍሪካ የነጮች አፓርታይድ ስርዓት ወደ ስልጣን የመጣው እ.አ.አ. በ1948 ዓ.ም ነው። ለአንዳንዶች በእስራኤል ከተመሰረተው የአይሁዶች አፓርታይድ ጋር በተመሣሣይ አመት ስልጣን መያዙ ሊያስገርም ይችላል። ነገር ግን፣ በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ስርዓት ወደ ስልጣን የመጣበትን አግባብ ስንመለከት ከእስራኤል ጋራ ፍፁም ተመሳሳይ መሆኑን እንገነዘባለን።

ለምሳሌ “Concentration Camp” ሲባል ቀድሞ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው ናዚዎች በፖላንድ የገነቡት የማጎሪያ ካምፕ ነው። በእርግጥ፣ ከናዚዎች በፊት እንግሊዞች በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ነጭ ሰፋሪዎችን በ“Concentration Camp” ውስጥ አጉረዋቸው ነበር። በዚህ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ወደ 28000 የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች በወረርሽኝ በሽታና በርሃብ ለሞት ተዳርገዋል። ይህም ከአጠቃላይ የነጭ ሰፋሪዎች ብዛት ውስጥ 10% የሚሆነው ሕዝብ ለሞት ተዳርጓል። ከምንም በላይ ነገሩን አሰቃቂ የሚደርገው ደግሞ ከሟቾቹ ውስጥ 81% (22074) ሕፃናት መሆናቸው ነው።

እንግሊዞች በበደቡብ አፍሪካ ነጮች ላይ እንዲህ ያለ ግፍና ጭፍጨፋ የፈፀሙበት ምክንያት በተለይ የ“Anglo-Boers War II” በተጀመረ የመጀመሪያ ሁለት አመታት ውስጥ እጅግ አስከፊ ሽንፈትና ውርደት ስለደረሰባቸው ነዉ። ከ27000 የማይበልጥ ወታደር የነበራቸው የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች ግማሽ ሚሊዮን ወታደሮች ያሰለፈውን የእንግሊዝ ጦር ገጥመው ከፍተኛ ጉዳት አድርሰውበታል። በድምሩ 22000 የእንግሊዝ ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን ወደ 200 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ አስወጥቷል። በአጠቃላይ፣ ከ1815 – 1915 ዓ.ም (እ.አ.አ.) ባለው አንድ ክፍለ ዘመን ታይቶ ባልታወቀ መልኩ እንግሊዝ በደቡብ አፍሪካ ነጮች አሳፋሪ ሽንፈት አጋጥሟት እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። ይሄ ደግሞ ጀርመኖች በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ካጋጠማቸው አሳፋሪ ሽንፈት ጋር ፍፁም ተመሳሳይ ነው።

በአይሁዶች በፍልስጤሞች ላይ የፈፀሙትን አይነት በደል እና ጭቆና የደቡብ አፍሪካ ነጮች በጥቁሮች ላይ ፈፅመውታል። ለምሳሌ፣ ከ1963 – 1987 ዓ.ም (እ.አ.አ.) ባሉት ዓመታት ለጮች ብቻ በተከለሉ አከባቢዎች ይኖሩ የነበሩ 3.5 ሚሊዮን ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያንን ከአያት-ቅደመ አያቶቻቸው ከወረሱት መሬት እንዲፈናቀሉ አድርገዋል። በአጠቃላይ፣ ከ80% በላይ የሚሆኑትን ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊ ከ15% በታች በሆነ መሬት ላይ እንዲሰፍሩ አድርገዋቸዋል። ይህም የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮችን ለከፋ ድህነትና ርሃብ ዳርጓቸዋል።

በሕዝባቸው ላይ ሲፈፀም የነበረን በደልና ጭቆና ለማስወገድ ታግለው ወደ ስልጣን የመጡ መንግስታት በሌሎች ሕዝቦች ላይ ተመሳሳይ በደልና ጭቆና ይፈፅማሉ። ናዚዎች በአይሁዶች ላይ የፈፀሙትን ግፍና ጭፍጨፋ ዛሬ የእስራኤል መንግስት በፍልስጤሞች ላይ እየፈፀመ ይገኛል። በፍልስጤሞች ላይ የተፈጸመው ግፍና በደል በመቃወም ለአረቦች ነፃነት ለመታገል የተቋቋሙ እንደ ሃማስ፣ ሂዝቦላህ፣ አልቃይዳ፣ “ÏSIS”፣ …ወዘተ ያሉ ድርጅቶች በራሳቸውንና በሌሎች ሀገራት ዜጎች ላይ የሽብር ጥቃት ይፈፅማሉ። እንዲሁም፣ እንግሊዞች በደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች ላይ የፈጸሙትን በደልና ግፍ የአፓርታይድ አገዛዝ በጥቁሮች ላይ ፈፅሞታል።

በናዚ የተፈፀመውን የዘር-ማጥፋት ተከትሎ የተፈጠረው የአይሁዶች አፓርታይድ ከሞላ-ጎደል ላለፉት 70 ዓመታት በፍልስጤም ዜጎችና ሌሎች የአረብ ሀገራት ላይ ተመሣሣይ በደልና ጭቆና እየፈፀመ ይገኛል። የእስራኤል መንግስት በፍልስጤሞች ላይ የሚፈጽመው ግፍና በደል ከቀጠለ እንደ ሂዝቦላህና ሃማስ ያሉ ቡድኖች በአዲስ እየተተኩ ወይም እንደ አዲስ እየተጠናከሩ ይሄዳሉ እንጂ በጭራሽ አይጠፉም። እነዚህ ቡድኖች እድልና አጋጣሚ የሰመረላቸው ዕለት በእጃቸው የገባ ማንኛውም ዓይነት የጥፋት መሳሪያ እስራኤልን የመጀመሪያ መሞከሪያ መሆኗ የማይቀር ነው። ለዚህ ደግሞ የኢራን ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች አቅም የሚለካው እስራኤልን ከማውደም አንፃር መሆኑ አንዱ ማሳያ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ፣ በሁሉም ፍልስጤማዊያን ፊት ላይ በግልፅ የሚስተዋለው ሽንፈትና ውርደት በፍልስጤም ግዛት ሌላ “አዶልፍ ሂትለር” እንዲፈጠር ማድረጉ አይቀርም። እስራኤል በፍልስጤሞች ላይ የምትፈፅመው በደልና ጭቆና በዚሁ ከቀጠለ አይሁዶች ከኋላ የሚሸሹት የዘር-ማጥፋት ሰቆቃ ከፊት-ለፊታቸው ቆሞ ይጠብቃቸዋል። በእርግጥ እስራኤል ጠንካራ ወታደራዊ አቅምና የደህንነት ተቋም እንዳላት ይታወቃል። ይህ ግን አንድ ፍልስጤማዊ ለራሱ ካለው ክብር አይበልጥም፤ የእስራኤል ወታደሮች እያደረሱበት ካለው ውርደት (humiliation) በላይ አያስፈራውም። ዋሌ ሶይንካ፣ በጣም አስተዋይ እንደሆኑ የሚመሰክርላቸው የቀድሞ የእስራኤል ፕሬዘዳንት “Shimon Peres” እንኳን ይህንን በሚፈለገው ደረጃ እንዳልተገነዘቡት እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል፡- 

“Most depressing of all, I read it in the eyes of the young where humiliation had hardened into a resolve not to abandon that ineffable possession, dignity, the loss of which would finally affirm the nullification of their human status. Most frightening of all, I saw it congealed into a hard, cold, unremitting hatred. …Nevertheless, it was clear to me that, on his part, this astute Israeli leader, perhaps the most thoughtful of past Israeli leaders, did not truly grasp, or else deeply underestimated the factor of humiliation, and the human attachment to that contentious possession – dignity.”

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የሰው ልጅ ጭቆና ሲበዛበት፣ የሚደርስበት ግፍና በድል ከሚሸከመው በላይ ሲሆንበት ባህሪው ፍፁም ይቀየራል። ከመጠን ያለፈ በደልና ጭቆና ሰብዓዊ ክብሩን (dignity) አሳጥቶ በምትኩ ውርደትን ያከናንበዋል። በዚህ ምክንያት በሕይወት የመኖር ጉጉት እና ሰብዓዊ ርህራሄ ከውስጡ ተሟጥጦ ያልቃል። ይህ ሲሆን በራሱና በሌሎች ላይ ጨካኝ ይሆናል። ለምሳሌ፣ እስራኤል በምድርና በአየር የምትፈፅመው ጥቃት ለእነ ሃማስ፣ ሂዝቦላህና አልቃይዳ ጥሩ “የቅጥር ማስታወቂያ” ሆኖ ያገለግላል። በዚህ መሰረት፣ የእስራኤል መንግስት የሚፈፅመው በደልና ጭቆና በፍልስጤሞች ልብ ውስጥ ቂምና ጥላቻ ይዘራል፣ የእስራኤል ሕዝብ ሞትና ሰቀቀን ያጭዳል።

ሌላው ለአረብ አብዮት መነሻ የሆነውን ቱኒዚያዊ እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል። እንደ ፍልስጤሞች በሌላ ሳይሆን በራስህ መንግስትና ወታደሮች የሚፈፅሙብህ ግፍና በደል በራስህ ላይ ጨካኝ ያደርግሃል። በደልና ጭቆና ሲበዛብህ በራስህ ላይ ጋዝ አርከፍክፈህ እሳት ትለኩሳለህ። በእርግጥ እንዲህ ያለ ተግባር አብዮት ለመቀስቀስ ተብሎ የሚደረግ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ በራስህና በሌሎች ላይ ጨካኝ የምትሆነው መብትና ነፃነትህ ተገፍፎ ሰብዓዊ ክብርህን ስታጣ፣ በዚህም ሽንፈትና ውርደት ነፍስህ ደርስ ጠልቆ ሲሰማህ የምትወስደው የመጨረሻ እርምጃ ነው።   

One thought on “የሰቆቃ ልጆች ክፍል-2፡ “ጭቆና ሲበዛ አሸባሪነት ይወለዳል!”

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡