የሰቆቃ ልጆች ክፍል-4፡ የመንግስት ደጋፊ ምሁራን “የጭቆና ፈረሶች” ናቸው! 

4.1 ምሁርና ብሔር

እንደ አይሁዶች ወይም የደቡብ አፍሪካ ነጮች የራሱን ሀገርና መንግስት ለመመስረት፣ እንደ አልጄሪያ ከቅኝ-አገዛዝ ነፃ ለመወጣት፣ ወይም ደግሞ እንደ ኢትዮጲያ ወታደራዊ መንግስትን ከስልጣን ለማስወገድ በተደረገው ትግል ውስጥ የምሁራን ድርሻና ኃላፊነት ምን መሆን አለበት? በእርግጥ የምሁራን ስራና ተግባር በብሔር፣ ዘር ወይም ሀገር ሊገደብ አይገባም። ነገር ግን፣ የመጡበት ማህብረሰብ በጨቋኝ ስርዓት ግፍና በደል ሲፈፀምበት ግን በዝምታ ማለፍ አይቻላቸውም።

እያንዳንዱ ምሁር ከተወለደበትና ካደገበት ማህብረሰብ ጋር ያለው ቁርኝት ከየትኛውም ሙያዊ ግዴታና ስነ-ምግባር የበለጠ ጠንካራ ነው። ስለዚህ፣ አንድ ምሁር በተወለደበት ማህብረሰብ ላይ የሚፈፀም በደልና ጭቆናን ወደ ጎን ትቶ ማለፍ አይቻልም። በአንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ምሁራን በሙያተኝነት (professionalism) ስም ገለልተኛ መሆንና በደልና ጭቆናን በዝምታ ማለፍ ፍፁም ተቀባይነት የለውም። ከዚያ ይልቅ፣ ማህብረቡን ከጭቆና ነፃ ለማውጣት በሚደረገው ትግል ባላቸው አቅምና ባገኙት አጋጣሚ አስተዋፅዖ ማበርከት አለባቸው።

ነገር ግን፣ ጨቋኙ ስርዓት ሲወገድና የሚደግፉት የፖለቲካ ቡድን ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ግን የምሁራኑ ድርሻና ኃላፊነት ፍፁም መቀየር አለበት። ጨቋኝ ስርዓትን በኃይል አስወግዶ ወደ ስልጣን የመጣ የፖለቲካ ኃይል ስለ ቀድሞ ታሪኩ፣ አሁን ላይ ስላለው ሥራና አሰራር፣ ወይም ስለ ወደፊት አቅጣጫና ዕቅዱ ለመግለፅ አስፈላጊ የሆነ መንግስታዊ መዋቅርና ተቋማት አሉት። ለዚህ ተግባር የተመደበ የሰው ኃይልና ካፒታል ይኖረዋል። ስለዚህ፣ ምሁራን በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ሥራና ተግባር እያጎሉ መናገርና መመስከር የምሁራኑ ድርሻና ኃላፊነት አይደለም።

4.2 የምሁራን ድርሻና ኃላፊነት

የምሁራን ድርሻና ኃላፊነት በማህብረሰቡ ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን አጉልቶ በማውጣት የግንዛቤና አመለካከት ለውጥ እንዲመጣ መስራት ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ በመንግስት ሥራና አሰራር ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ነቅሶ በማውጣት እንዲስተካከሉ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። ከሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች አንፃር ሲታይ ምሁራን በሙያቸው ችግሮችን ቀድሞ የመለየትና መፍትሄያቸውን የመረዳት ብቃት አላቸው። እንዲሁም በጉዳዩ ላይ የሚሰጡት ሙያዊ ትንታኔ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ነው።

እንኳን በጦርነት በሕዝብ ምርጫ ራሱ ወደ ስልጣን የመጡ የመንግስት ኃላፊዎችና የሕዝብ ተወካዮች ለሥራው የሚያስፈልገው በቂ ዕውቀትና ክህሎት የላቸውም። አብዛኛውን ግዜ የፖለቲካ ስልጣን የሚጨብጡ ሰዎች ሕዝብን የማደራጀትና የመቀስቀስ አቅም እንጂ ሙያዊ ዕውቀትና ክህሎት ስላላቸው አይደለም። “John Stuart Mill” ስለ ዴሞክራሲያዊ መንግስት አመሰራረትና አሰራር በሚተነትነው መፅሃፉ “Of the Proper Functions of Representative Bodies” በሚለው ክፍል ፅንሰ-ሃሳቡን እንዲህ ገልፆታል፡-

“….the very fact which most unfits such bodies for a Council of Legislation qualifies them the more for their other office- namely, that they are not a selection of the greatest political minds in the country, from whose opinions little could with certainty be inferred concerning those of the nation, but are, when properly constituted, a fair sample of every grade of intellect among the people which is at all entitled to a voice in public affairs. Their part is to indicate wants, to be an organ for popular demands, and a place of adverse discussion for all opinions relating to public matters, both great and small; and, along with this, to check by criticism, and eventually by withdrawing their support, those high public officers who really conduct the public business.”  Representative Government, Ch.5: Page  59

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የዜጎች መብትና ነፃነት የተከበረበት የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሊኖር የሚቻለው በፖለቲከኞች/የፖለቲካ ቡድኖች እና በምሁራን መካከል ያለው ልዩነት እንደተጠበቀ መቀጠል ሲችል ነው። በመሰረቱ፣ የፖለቲከኞች መደበኛ ስራ ፖለቲካዊ አመራርና አስተዳደር ነው። የምሁራን ድርሻ ደግሞ የዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እና የመንግስት ፖለቲካዊ አመራርና አስተዳደር በዕውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማስቻል ነው።

ከዚህ አንፃር፣ ምሁራን ድርሻና ኃላፊነታቸውን መወጣት የሚችሉት በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በሚያደርጓቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እና በመንግስት ሥራና አሰራር ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን መለየትና የሚስተካከሉበትን አማራጭ የመፍትሄ ሃሳቦችን ማቅረብ ነው። የፖለቲካ ስልጣን ያላቸው የመንግስት ባለስልጣናት ደግሞ ከምሁራን የተሰጣቸውን ሃሳብና አስተያየት ተቀብለው በሀገሪቱና በሕዝቡ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚስተዋሉ ከፍተቶችን ለማስወገድ የፖለቲካ አመራር መስጠትና አስተዳደራዊ ስርዓቱን ማሻሻል ነው።

በዚህ መሰረት፣ ምሁራን የሚጠበቅባቸውን ሚና በአግባቡ ከተወጡ በመንግስት ሥራዎችና አስራሮች ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ወዲያው ይስተካከላሉ። መንግስት ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ይሰጣል። የመንግስት ስራና አሰራር ግልፅነት እና ተጠያቂነት ይኖረዋል። የአስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጡ የብዙሃኑን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ይሆናል። ስለዚህ፣ ምሁራን ድርሻና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሲወጡ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያችን ላይ ቀጣይነት ያለው ለውጥና መሻሻል ይኖራል።

ቀጣይነት ያለው ለውጥና መሻሻል ለዘላቂ ልማት፣ ለአስተማማኝ ሰላም እና ለዳበረ ዴሞክራሲ መሰረት ይሆናል። ያለ ምሁራን ተሳትፎ ቀጣይነት ያለው ለውጥና መሻሻል ማምጣት አይቻልም። ስለዚህ፣ እንደ “John Stuart Mill” አገላለፅ፣ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ለውጥና መሻሻል እንዲመጣ ምሁራን ሕግ አውጪዎች የሚያፀድቋቸውን አዋጆች፣ የሕግ አስባሪዎች አሰራርና የፍትህ ስርዓቱ ገለልተኝነትን፣ የሕግ አስፈፃሚዎች የሚያሳልፏቸውን የአፈፃፀም መመሪያዎችና ደንቦች፣ በአጠቃላይ የመንግስት አካላት ሥራና አሰራርን አዎንታዊና አሉታዊ ጎኖች ከሙያው አንፃር መተንተን፣ የተለያዩ የማሻሻያ ሃሳቦችን እያነሱ መወያየትና በኃላፊዎችና በሕብረተሰቡ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን መጠቆም አለባቸው።

4.3 “የጭቆና ፈረሶች”

በእርግጥ ምሁራን እንደ ማንኛውም ዜጋ የመንግስት ባለስልጣን ሆነው መስራት ይችላሉ። ይህ ሲሆን እንደ ማንኛውም ባለስልጣን የመንግስትን ሥራና ተግባር ደግፈው ሃሳብና አስተያየት ሊሰጡ ይችላሉ። የመንግስት ተሿሚ ወይም ባለስልጣን ካልሆኑ ግን የሕዝብን ድምፅ ተቀብለው ማስተጋባት አለባቸው። በዚህ መሰረት፣ የመንግስት ሰራተኛ ሆነ የግል ድርጅት ተቀጣሪ፣ እያንዳንዱ ምሁር ያለውን ሙያዊ ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅሞ በተለይ የመንግስትን ስራና አሰራር የመተቸት ማህበራዊ ግዴታ አለበት።

ከዚህ በተቃራኒ፣ መሰረታዊ ችግር ያለባቸው አዋጆች፥ እቅዶችና ውሳኔዎች በተለያዩ የመንግስት አካላት ተግባራዊ ሲደረጉ እያዩ በዝምታ የሚያልፉ ሰዎች እንደ ምሁር ያለባቸውን ማህበራዊ ግዴታ እየተወጡ አይደለም። በተለይ የሕዝብ ቅሬታዎችና አቤቱታዎችን እያጣጣሉ፣ የመንግስትን ስራና ተግባር እያጋነኑ የሚያቀርቡ፣ ከመንግስት ኃላፊዎች በላይ የመንግስት ጠበቃና ደጋፊ ለመሆን የሚቃጣቸው ሰዎች “ምሁር” ለሚለው የክብር ስያሜ አይመጥኑም።  

ምሁራን በዜጎች ማህበራዊ፥ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለውጥ ማምጣት፣ እንዲሁም የመንግስት ስራና አሰራር ማሻሻል የሚችሉት፣ በአጠቃላይ የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት፣ ዘላቂ ልማትና ሰላም እንዲረጋገጥ የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅዖ ማበርከት የሚችሉት ራሳቸውን ከመንግስት ሲነጥሉ ነው። ልክ እንደ የመንግስት ተሿሚ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አባል የመንግስትን ሥራና ተግባር በመደገፍ፣ ጥሩን እያጋነኑ፥ መጥፎውን እየሸፋፈኑ የሚያቀርቡ ከሆነ፣ በዜጎች ላይ የሚፈፀም የመብት ጥሰትን በማጣጣል የመንግስትን ጥሩ ምግባር አጉልተው ለማውጣት የሚጥሩ ከሆነ፣ ከሕዝብ ይልቅ በመንግስት ላይ የሚያደርሱት ጉዳት እጅግ የከፋ ነው። ምሁራን በደጋፊነት ስም ራሳቸውን ከመንግስት ጋር ማጣበቃቸው በፖለቲካዊ ስርዓቱ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት “John Stuart Mill” እንዲህ ገልፆታል፡-   

“Nothing but the restriction of the function of representative bodies within these rational limits will enable the benefits of popular control to be enjoyed in conjunction with the no less important requisites of skilled legislation and administration. There are no means of combining these benefits except by separating the functions which guarantee the one from those which essentially require the other; by disjoining the office of control and criticism from the actual conduct of affairs, and devolving the former on the representatives of the Many, while securing for the latter, under strict responsibility to the nation, the acquired knowledge and practised intelligence of a specially trained and experienced Few.” Representative Government, Ch.5: P.59

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የመንግስት ደጋፊ የሆኑ ምሁራን የተለያዩ የመንግስት አካላት የሚያሳልፋቸው የብዙሃኑን እኩልነትና ተጠቃሚነትን የማያረጋግጡ እቅዶችና ውሳኔዎች እንዳይሻሻሉ፣ የዜጎችን ሕገ-መንግስታዊ መብትና ነፃነት የሚገድቡ አዋጆችና ደንቦች ማሻሻያ እንዳይደረግባቸው፣ የሕዝብ ጥየቄዎችና ቅሬታዎችን እንዳይሰማ፣ እንዲሁም የመንግስት ኃላፊዎች ያለባቸውን የግንዛቤ እና የብቃት ማነስ ችግር እንዳይቀርፉ እንቅፋት ናቸው።

ምሁራን የመንግስትን እርምጃዎችን በመደገፍ ብቻ ሳይሆን ሙያተኝነት ስም ገለልተኛ መስለው ለማለፍ መሞከራቸው በራሱ በህዝብ ላይ የሚፈፀም በደልና ጭቆናን እንደመደገፍ ይቆጠራል። ስለዚህ፣ በገለልተኝነት (neutrality) ስም መንግስትን ከመተቸት የሚቆጠቡ ምሁራን “የመንግስት ደጋፊ ነን” ከሚሉት በምንም የተለዩ አይደሉም።

እንደ ምሁር ከማህብረሰቡ የተጣለባቸውን ግዴታና ኃላፊነት አልተወጡም። በማህበራዊ ሕይወታችን ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማንሳት የግንዛቤና የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። እንዲህ ያሉ ማህበራዊ ጉዳዮች የሚያስከትሉትን ጭቅጭቅና ውዝግብ በመፍራት ማህበራዊ ግዴታቸውን የማይወጡ፣ “ፖለቲካ እሳት ነው!” የሚለውን ያረጀ አባባል እየደጋገሙ ጥግጥጉን የሚሄዱ ሰዎች ትክክለኛ መጠሪያቸው “ምሁራን” ሳይሆን “ፈሪዎች” የሚለው ነው።

በአጠቃላይ፣ “ምሁር” ለመባል በቅድሚያ እንደ ምሁር የተጣለብንን ማህበራዊ ግዴታ መወጣት ያስፈልጋል። ሃሳብና አመለካከቱን በነፃነት ለመግለፅ የሚፈራ ወይም መንግስትን ለማሞገስ የሚተጋ ሰው “ምሁር” ለሚለው የከብር መጠሪያ አይመጥንም። ከዚያ ይልቅ፣ የመንግስት ደጋፊዎች ሕሊናቸው በጥቅም ሱስ ተለጉሞ፣ እንዲሁም መንግስትን ለመተቸት የሚፈሩት ደግሞ አንደበታቸው በፍርሃት ቆፈን ተለጉሞ፣ ጭቋኝ ስርዓትን በጀርባቸው ተሸክመው የሚጋልቡ “ፈረሶች” ናቸው። ወታዳራዊ ፋሽስቶች፣ አምባገነኖች፣ የአፓርታይድ ስርዓት አራማጆች፣ …ወዘተ በሕዝብ ላይ አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ የሚፈፅሙት እነዚህን “የጭቆና ፈረሶች” እያጋለቡ ነው።