የዘር/ብሔር አፓርታይድ – ክፍል 3፡- ብሔርተኝነት ሳይወጣ እኩልነት አይገባም!

የዘር/ብሔር አፓርታይድ ተከታታይ ፅሁፍ የመጀመሪያ ክፍል ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የትጥቅ ትግል የሚጀመርበት መሰረታዊ ምክንያት ለማህብረሰቡ የመብትና ነፃነት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ሳይሰጥ ሲቀር ነው። ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለሚነሱ የእኩልነት፥ ነፃነትና የተጠቃሚነት ጥያቄዎችን በኃይል ለማዳፈን መሞከር፤ በመጀመሪያ ወደ አመፅና ኹከት፣ በመቀጠል ወደ ግጭትና የትጥቅ ትግል እንደሚያመራ ተመልክተናል። በዚህ ሂደት ውስጥ ፖለቲካ ልሂቃን የማህብረሰቡን ብሶትና ተቃውሞ በብሔርተኝነት ስሜት በማቀጣጠልና በራስ-የመወሰን መብትን ተሰፋ በመስጠት አመፅና ተቃውሞን ወደ ትጥቅ ትግል ያሸጋግሩታል።

በዚህ መሰረት፣ የትጥቅ ትግል ለማስጀመር በማህብረሰቡ ውስጥ እንዲሰርፅ የተደረገው የብሔርተኝነት ስሜት በትግል ወቅት ከሚፈጠረው የጠላትነት ስሜት በመጣመር አክራሪ የፖለቲካ አመለካከት ይፈጠራል። በእርግጥ ያለ ብሔርተኝነት ስሜት ሕዝባዊ ወገንተኝነትን ማስረፅ አይቻልም። በተመሣሣይ፣ በጨቋኙ ስርዓት ላይ የጠላትነት ስሜት መፍጠር ካልተቻለ የትጥቅ ትግል ማካሄድ አይቻልም። ነገር ግን፣ ልክ የትጥቅ ትግሉ እንደተጠናቀቀ አዲስ የፖለቲካ ማህብረሰብን መፍጠር ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ በትጥቅ ትግሉ ወቅት የሰረፀውን በብሔርተኝነትና የጠላትነት ስሜት ላይ የተመሰረተ አክራሪ የፖለቲካ አመለካከት በአዲስ መቀየር ያስፈልጋል።

አዲስ የፖለቲካ ማህብረሰብ ለመፍጠር አስፈላጊ የሆኑ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እሴቶችን ለመለየትና ለማዳበር ለትጥቅ ትግሉ መነሻ የሆነውን ምክንያት ተመልሶ ማየት ያስፈልጋል። በእርግጥ የትግሉ ዓላማ የማህብረሰቡን በራስ-የመወሰን መብት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ ነው። በራስ-የመወሰን መብት ያስፈለገበት ምክንያት የማህብረሰቡን እኩልነት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማስከበር ነው። የአብዛኛውን የሕብረተሰብ ክፍል መብትና ነፃነት ማስከበር የሚቻለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ሲቻል ነው።

የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ደግሞ በእኩልነት፥ ነፃነት፥ የህግ የበላይነት፥ ግልፅነት፥ ተጠያቂነት፥ …ወዘተ በመሳሰሉ እሴቶች የታነፀ የፖለቲካ ማህብረሰብ ሊኖር ይገባል። ይህ ደግሞ በትጥቅ ትግሉ ወቅት በማህብረሰቡ ውስጥ የሰረፀው አክራሪ ብሔርተኝነትና የጠላትነት መንፈስ ሙሉ-ለሙሉ መወገድ አለበት። በዚህ መሰረት፣ በጦርነት ወቅት የተፈጠረውን አሮጌ ነፍስ በአዲስ ነፍስ መተካት ያስፈልጋል።

በክፍል-2 ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ “የትጥቅ ትግሉ የመጨረሻ ግብ ደግሞ አዳዲስ ነፍሶችን መፍጠር ነው” (the invention of new souls) የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ ይህን ያመለክታል። የትግል መሪዎች/ልሂቃን አዲስ ነፍስ የሚፈጥሩት በትግል ወቅት የተፈጠረውን የብሔርተኝነትና ጠላትነት ስሜት ከትግል በኋላ በእኩልነትና ነፃነት በመተካት ነው። ነገር ግን፣ እንደ “Frantz Fanon” አገላለፅ፣ አዳዲስ ነፍሶችን መፍጠር የሚቻለው ከትግል በኋላ አይድለም። ከዚያ ይልቅ፣ ጦርነቱ በተፋፋመበትና የታጋዮች የብሔርተኝነት/ብሔራዊ ስሜት በተጋጋለበት ወቅት ራስንና ሌሎችን፤ “በእኛ ላይ እየደረሰ ያለውን በደልና ጭፍጨፋ በሌሎች ላይ እያደረስን ይሆን?” የሚለውን ጥያቄ መጠየቅና መመለስ ሲቻል ነው።

የትግሉ መሪዎችና ልሂቃን “በእኛ ላይ እየደረሰ ያለውን በደልና ጭፍጨፋ በሌሎች ላይ እያደረስን ይሆን?” የሚለውን ጥያቄ ራሳቸውንና የትግል አጋሮቻቸውን ያለገደብ፥ በግልፅ የሚጠይቁና የሚወያዩ፣ በዚህም ጥያቄውን በነባራዊ እውነታ ላይ ተመስርተው ጥያቄውን የሚመልሱ ከሆነ የትግሉን የመጨረሻ ግብ ማሳካት ይቻላሉ። ስለዚህ፣ በትግል ወቅት ይህን ማድረግ የቻሉ መሪዎችና ልሂቃን፣ የጨቋኙ ስርዓት ከተወገደ በኋላ በትግል ወቅት የተፈጠረውን አክራሪ ብሔርተኝነትና የጠላትነት ስነ-ልቦናን በማስወገድ በምትኩ በዴሞክራሲያዊ እሴቶች የታነጸ የፖለቲካ ማህብረሰብ መፍጠር ይችላሉ። ነገር ግን፣ በቀድሞ ጨቋኝ ስርዓት የተፈፀመውን በደልና ጭፍጨፋ እያሰቡ የጠላትነት ስሜትን ማስወገድ አይቻልም። በተመሣሣይ፣ በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ የሚንፀባረቀውን አክራሪነት ብሔርተኝነት ሳያስወግዱ የዴሞክራሲ እሴቶችን ማስረፅ አይቻልም።

ከዚህ በተጨማሪ፣ በትግል ወቅት መጠየቅ የነበረበት ጥያቄ ከትግል በኋላ መልስ አያገኝም። “በእኛ ላይ እየደረሰ ያለውን በደልና ጭፍጨፋ በሌሎች ላይ እያደረስን ይሆን?” ለሚለው ጥያቄ በነባራዊ እውነታ ላይ የተመሰረተ ትክክለኛ መልስ መስጠት የሚቻለው በጦርነት ወቅት የተጠየቀ እንደሆነ ብቻ ነው። ምክያቱም፡- አንደኛ፡- በትግል ወቅት የተፈጠረው የብሔርተኝነትና የጠላትነት ስሜት ከትግል በኋላ ወደ ተበዳይነትና ፍርሃት ስለሚቀየሩ፣ ሁለተኛ፡- የጥያቄውን አውድ በግልፅ መገንዘብና በእውነታ ላይ የተመሰረተ ምላሽ መስጠት የሚቻለው ራሳችንን በድርጊት ፈፃሚዎቹ ቦታና ግዜ ላይ በማስቀመጥ፣ ተግባሩን የፈፀመበትን ትክክለኛ አውድና ምክንያት መረዳት ስንችል ነው። ከዚህ ቀጥሎ የመጀመሪያውን ምክንያት በአጭሩ የምንመለከት ሲሆን ሁለተኛውን ምክንያት ደግሞ በቀጣዩ ክፍል አራት በዝርዝር ለመዳሰስ እንሞክራለን።

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ በጦርነት ወቅት የሰረፀው የብሔርተኝነት ስሜት ከትግል በኋላ ወደ ጭፍን ወገንተኝነትና የተበዳይነት ስሜት ይቀየራል። በተመሣሣይ፣ በጦርነት ወቅት የተፈጠረው የጠላትነት ስሜት ከጦርነቱ በኋላ ወደ ፍርሃትና ጥርጣሬ ይቀየራል። በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ በትግል ወቅት ስለተፈፀመ አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ ከስሜታዊነት በፀዳ መልኩ መወያየትና መግባባት በጣም አስቸጋሪ ይሆናል።

በቀድሞ ጨቋኝ ስርዓት የእሱ ማህብረሰብ ብቻ ተለይቶ እንደተበደለ ከሚስብና “የቀድሞ ስርዓት ተመልሶ ሊመጣ ይችላል” በሚል ስጋትና ፍርሃት ውስጥ ካለ ሰው ጋር በመተማመን ላይ የተመሰረተ ውይይት ማድረግ አይቻልም። “Edward Said” እንዲህ ያለውን ውጥረት ለማስወገድ የአልጄሪያዊው የነፃነት ታጋይና ልሂቅ “Frantz Fanon” እንደ ምሳሌ በመጥቀስ የትግል መሪዎችና ልሂቃን ድርሻና ኃላፊነትን እንደሚከተለው ገልፆታል፡-

“It is inadequate only to affirm that a people was dispossessed, was oppressed or slaughtered, was denied its rights and its political existence without at the same time doing what [Frantz] Fanon did during the Algerian war: affiliating those horrors with the similar afflictions of other people. This does not at all mean a loss in historical specificity, but rather it guards against the possibility that a lesson learned about oppression in one place will be forgotten or violated in another place or time. …For the intellectual, the task is explicitly to universalise the crisis, to give greater human scope to what a particular race or nation suffered, to associate that experience with the sufferings of others.” REITH LECTURES 1993: Representations of an Intellectual, Lecture 2: Holding Nations and Traditions at Bay, 1993.

ከላይ እንደተጠቀሰው፣ የትግል መሪዎችና ልሂቃን በእነሱ ብሔርና ዘር ላይ የተፈጸመን በደልና ጭቆና በማስፋትና በሌሎች ብሔሮችና ሕዝቦች ላይ ከተፈጸመው በደልና ጭቆና ጋር አያይዘው ማቅረብ አለባቸው። ናጄሪያዊው ሎሬት “Wole Soyinka” የቀድሞውን የደርግ ወታደራዊ መንግስት በተለያዩ የዓለም ሀገራት ከነበሩ አምባገነናዊ እና ጨቋኝ መንግስታት ተመሳሳይ እንደሆነ ይገልፃል። ሌላው ቀርቶ የደርግ መንግስት የፈፀመው በደልና ጭቆና፣ የኢራን ኢስላማዊ መሪዎች፣ በአፍጋንስታኑ ታሊባኖች፣ እንዲሁም በሩሲያ የሶቬት ሕብረት አምባገነናዊ ስርዓት ከፈፀሙት በደልና ጭቆና ጋር ፍፁም ተመሳሳይ እንደሆነ ይገልፃል።

“The saturation of society by near-invisible secret agents, the cooption of friends and family members – as has been notoriously documented in Ethiopia of The Dergue, former East Germany, Idi Amin’s Uganda or Iran of the Shah Palahvi and the Ayatollahs prior to the Reformist movement – all compelled to report on the tiniest nuances of discontent with, or indifference towards the state – they all constitute part of the overt, mostly structured forces of subjugation. To fully apprehend the neutrality of the suzerainty of fear in recent times, indifferent to either religious or ideological base, one need only compare the testimonies of Ethiopian victims under the atheistic order of Mariam Mengistu, and the theocratic bastion of Iran under the purification orgy of her religious leaders, or indeed the Taliban of Afghanistan and the aetheistic order of a Stalinist Soviet Union.” REITH LECTURES 2004: Climate of Fear, Lecture 2: Power and Freedom, 2004.

በደርግ መንግስት የተፈፀመው በደልና ጭቆና በሌሎች ዓለም ሀገራት ከሚፈጸሙ በድልና ጭቆናዎች ጋር ፍፁም ተመሳሳይ እንደሆነ ከላይ በአጭሩ ተመልክተናል። እንዲሁም የደርግ መንግስት በሀገሪቱ ዜጎች ላይ ሲፈፅም የነበረው በደልና ጭፍጨፋ ፍፁም ተመሳሳይ ነው። ለምሳሌ፣ በቀይ-ሽብር ዘመቻ የደርግ መንግስት ከሦስት አመት ባነሰ ግዜ ውስጥ እስከ 500ሺህ የሚደርሱ የሀገሪቱን ዜጎች ገድሏል።

በክፍል-2 የቀድሞውን የሕወሓት መስራችና አመራር አረጋዊ በርሄን ዋቢ በማድረግ እንደተጠቀሰው በሰኔ 1980 ዓ.ም በሃውዜን በተፈፀመው የአውሮፕላን ድብደባ በአንድ ቀን 1800 ንፁሃን ዜጎች መገደላቸውና ይህም የትጥቅ ትግሉ ከተጀመረበት ግዜ አንስቶ ብዙ ሰዎች በአንድ ቀን የተገደለበት እንደሆነ ተጠቅሷል። ነገር ግን፣ በ1970 ዓ.ም የቀይ-ሽብር ዘመቻ በተጀመረ የመጀመሪያው ሳምንት ውስጥ ብቻ 5ሺህ ተማሪዎችን ገድሏል፣ 30ሺህ አስሯል። ታዲያ የደርግ መንግስት በትግራይ ሕዝብ ላይ የፈፀመው በደልና ጭፍጨፋ በአጠቃላይ የኢትዮጲያ ሕዝብ ከፈጸመው በምን ይለያል?

በአጠቃላይ፣ የደርግ መንግስት በትግራይ ሕዝብ ወይም በሌላ ብሔር ላይ ብቻ በደልና ጭፍጨፋ እንዳደረገ ወይም ለአንደኛው ብሔር ይበልጥ “ጥሩ” ሌላው ደግሞ “መጥፎ” እንደነበረ አድርጎ መግለፅ፥ መዘርዘርና መዘከር በትግል ወቅት የሰረፀው የብሔርተኝነትና ተበዳይነት ስሜት፣ እንዲሁም በጦርነት ወቅት የተፈጠረው የጠላትነት ስሜትና እሱን ተከትሎ የተፈጠረው የፍርሃትና ጥርጣሬ ምልክት ነው። ለዚህ ደግሞ አንዱ ምክንያት የሕወሃት መሪዎችና ልሂቃን የብሔርተኝነትና የጠላትነት ስሜትን በማስወገድ የእኩልነትና ነፃነት መርህን ማስረፅ አለመቻላቸው ነው። ሁለተኛውና ዋናው ምክንያት የሕወሓት መሪዎችና ልሂቃን ከደርግ ጋር ጦርነት ውስጥ በነበሩበት ወቅት “በእኛ ላይ እየደረሰ ያለውን በደልና ጭፍጨፋ በሌሎች ላይ እያደረስን ይሆን?” የሚለውን ጥያቄ ለመጠየቅና ተገቢ የሆነ መልስ አለመስጠታቸው ነው። ሁለተኛውን ምክንያት እና በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ስርዓት ላይ ያሳረፈውን ተፅዕኖ በቀጣዩ ክፍል-4 በዝርዝር እንመለከታለን።