የዘር/ብሔር አፓርታይድ – ክፍል 4፡ ደርግ ጨፈጭፊ ከነበረ “አማፂያኑ” አስጨፍጫፊ ነበሩ!

ባለፉት ክፍሎች የትግል መሪዎችና ልሂቃን “በእኛ ላይ እየደረሰ ያለውን በደልና ጭፍጨፋ በሌሎች ላይ እያደረስን ይሆን?” የሚለውን ጥያቄ በትግል ወቅት መጠየቅና በነባራዊ እውነታ ላይ የተመሰረተ መልስ መስጠት እንዳለባቸው ተመልክተናል። በክፍል ሦስት በዝርዝር እንደተገለፀው፣ የመጀመሪያው ምክንያት በትግል ወቅት የተፈጠረው የብሔርተኝነትና የጠላትነት ስሜት ከትግል በኋላ ወደ ተበዳይነትና ፍርሃት ስለሚቀየሩ ከትግል በኋላ አዲስ ለውጥ ማምጣት አስቸጋሪ እንደሚሆን ተመልክተናል። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የጥያቄውን በትክክል መመለስ የሚቻለው በጦርነት ወቅት እንደሆነ ተጠቅሷል። ነገር ግን፣ “በጦርነት ወቅት በንፁሃን ዜጎች ላይ በደልና ጭፍጨፋ የሚፈፀመው ለምንና እዴት እንደሆነና ተጠያቂ አካል ማን እንደሆነ ለማወቅ በቅድሚያ የሽምቅ ውጊያን መሰረታዊ ባህሪ መገንዘብ ያስፈልጋል። በዚህ ፅሁፍ ስለ ሽምቅ ውጊያ ስልትና በንፁሃን ዜጎች ላይ ስለሚያስከትለው ጉዳት የኢትዮጲያና ደቡብ አፍሪካን ታሪክ በማጣቀስ እንመለከታለን።

በኢትዮጲያ ጨቋኙን የደርግ አምባገነናዊ መንግስት ከስልጣን ለማስወገድ፣ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የአንግሊዝን የኢምፔሪያሊዝም ወረራን ለመመከት የተደረገው ትግል በዋናነት በሽምቅ ውጊያ (guerrilla warfare) ላይ የተመሰረተ ነበር። የቀድሞ የሕወሓት መስራችና አመራር አረጋዊ በርሄ ስለ ሽምቅ ውጊያን ዓላማ፣ ስልትና ውጤት ከሰጡት ትንታኔ ውስጥ የሚከተለውን ቀንጭበን ወስደናል፡-

“The essence of the revolutionary struggle is therefore to completely isolate the state from the populace and push it to its grave. This is why guerrilla warfare is dependent on a high level of popular involvement to provide the demographic ‘sea’ for the insurgent ‘fish’… The counter-offensive of government forces to nip the TPLF in the bud – a series of punitive campaigns that by-and-large came upon the peasant masses who were accused as hosts of the guerrilla fighters – definitely helped to bring closer the Front and the people as never before.” A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991): Revolt, Ideology and Mobilisation in Ethiopia, Amsterdam 2008, Page 42 – 151

የደርግ አምባገነናዊ መንግስት እና የእንግሊዝ የኢምፔሪያሊዝም ወራሪ ተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው የሚመራበት መርህ “በአማፂያኑና በደጋፊዎቻቸው ላይ ከቀድሞው የበለጠ የኃይል እርምጃ መውሰድ የሽምቅ ተዋጊዎቹ የሚፈፅሙት ጥቃትና ከማህብረሰቡ የሚያገኙት ድጋፍ ይቀንሳል” የሚል ነው። በዚህ መሰረት፣ የአማፂያኑን ጥቃትና ድጋፍ ለመቀነስ ከዚህ ቀደም ከተወሰደው የበለጠ የኃይል እርምጃ ይወስዳል።

የሽምቅ ተዋጊዎች ሕዝቡን እንደ “ባህር” ተጠቅመው በውስጡ እንደ “ዓሣ” የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው ተጠቅሷል። ዓሣ ደግሞ ከባህሩ አይወጣም። ባህሩ ውስጥ ገብቶው ውሃውን ሳይነኩ ዓሣውን መያዝ ሆነ መግደል አይቻልም። ስለዚህ፣ በአማፂያኑ ላይ የሚወሰድ የኃይል እርምጃ በንፁሃን ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ያደርሳል። ከላይ እንደተጠቀሰው፣ የሽምቅ ተዋጊዎቹን ደብቃችኋል፥ ተባብራችኋል፥ ድጋፍ አድርጋችኋል፥…ወዘተ በሚል በማህብረሰቡ ላይ የሚፈጸመው በደልና ጭቆና የአማፂያኑን የሰው ኃይል አቅምና ድጋፍ ይበልጥ ያሳድገዋል። በዚያው ልክ የመንግስትን ድጋፍና ተቀባይነት ከቀድሞ በባሰ እንዲቀንስ ያደርገዋል።

ስለዚህ፣ አምባገነንና ጨቋኝ የሆኑ መንግስታት የአማፂያኑን ጥቃት ለመከላከል እና ከማህብረሰቡ የሚገኙትን ድጋፍ ለመቀነስ በሚል ከከዚህ በፊቱ የበለጠ የኃይል እርምጃ መወሰድ አለበት በሚል መርህ ይመራሉ። ከበፊቱ የበለጠ የኃይል እርምጃ በወሰዱ ቁጥር አማፂያኑ በሚንቀሳቀሱበት ማህብረሰብ ላይ ከበፊቱ የበለጠ በደልና ጭቆና ይፈፅማሉ። ከበፊቱ የበለጠ በደልና ጭቆና በፈጸሙ ቁጥር በማህብረሰቡ ዘንድ የመንግስት ድጋፍነ ተቀባይነት እየቀነሰ፣ የአመፂያኑ ድጋፍና ተቀባይነት እየጨመረ ይሄዳል።

የቀድሞ የሕዋሓት መስራችና አመራር በጉዳዩ ዙሪያ የተለያዩ የጥናት ውጤቶች በማጣቀስ የሽምቅ ተዋጊዎች ውድቀትና ስኬት የሚወሰነው በዚህ ስሌት መሰረት እንደሆነ ያስረዳል። አያይዞም ሕወሓት የደርግ ስርዓትን ከስልጣን ማስወገድ የቻለው በዚህ ስሌት መሰረት እንደሆነ ገልጿል፡-          

“Neither sheer poverty nor peasant discontent, not merely modernization or class oppression, and certainly not the simple appearance of guerrillas or foreign aid to them, can explain the relative successes and failures of guerrilla revolutionary movements …, apart from domestic governmental conditions. There is a wealth of evidence and principle that repressive policies defeat their purpose, in the long run if not necessarily in the short run.…exclusive reliance on force eventually rises up the forces that destroy it, and often a self-defeating fallacy is the perception of well established states, that dissidents will give up their resistance by the threat or application of great force.
This analysis helps us understand to what extent a repressive regime (the militaristic Dergue of Ethiopia a case in point) by employing sheer force and terror creates favourable conditions for revolutionary guerrilla movements (like the TPLF) to grow and be crowned as upholding a just and legitimate cause on behalf of the oppressed people.” A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991): Revolt, Ideology and Mobilisation in Ethiopia, Amsterdam 2008, Page 43

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ አምባገነን መንግስታትና ሽምቅ ተዋጊዎች ጨፍጫፊ እና አስጨፍጫፊ ናቸው። ለምሳሌ፣ በደቡብ አፍሪካ የነጭ ሰፋሪ ሸምቅ ተዋጊዎች እ.አ.አ. ከ1899 – 1901 ዓ.ም ባሉት ሦስት አመታት ውስጥ ወደ 22000 በላይ የእንግሊዝ ወታደሮችን ገድለዋል። የሕወሓት መስራችና የቀድሞ አመራር የነበረው አረጋዊ በርሄ “A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991)” በተሰኘው መፅሃፋቸው፣ በ1979 ዓ.ም የኤርትራ አማፂያን ሁለተኛውን አብዮታዊ ጦርን ሲያሸንፉ ወደ 10000 የደርግ ወታደሮችን፣ እንዲሁም የሕወሓት ታጋዮች በ1981 ዓ.ም ከደርግ ጋር ባደረጉት የእንዳ-ስላሴ ውጊያ ወደ 12000 የደርግ ወታደሮችን መግደላቸውን ገልጿዋል። በደቡብ አፍሪካና በኢትዮጲያ የሚገኙ አማፂያን በሦስት አመታት ውስጥ ብቻ እያንዳንዳቸው 22000 ወታደሮችን ገድለዋል።

የእንግሊዝ ጦር የሽምቅ ተዋጊዎቹን ጥቃትና ድጋፍ ለማስወገድ “መሬቱን በእሳት መለብለብ” (Scorched-earth) በሚል ተዋጊዎቹ በሚንቀሳቀሱበት አከባቢ ያሉ መኖሪያ ቤቶች ሙሉ-ለሙሉ በእሳት አወደማቸው። ከጠቅላላው የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎችን ሕዝብ ብዛት በአማካይ ግማሹን በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ በማስገባት ከጠቅላላው የሕዝብ ብዛት 10% (280000) የሚሆነው ሕዝብ በርሃብና በበሽታ ሞቱ። በዚህ ምክንያት፣ የሽምቅ ተዋጊዎቹ የተኩስ አቁም ስምምነት በመፈረምና እስከ 1948 ዓ.ም ድረስ በእንግሊዝ ቅኝ-አገዛዝ ስር ወደቁ።

ልክ እንደ እንግሊዞች ደርግም የሕውሃት የሽምቅ ተዋጊዎችን ጥቃትና ድጋፍ ለማስወገድ “ዓሳውን ለማጥፋት ባህሩን ማድረቅ” በሚል እንደ በአውሮፕላን የአየር ድብደባ ፈፀመ። በዚህም በአንድ ቀን ውስጥ 1800 ንፁሃን ዜጎች ተገደሉ። ከዚያ በኋላ ግን የደርግ ሰራዊት በሽንፈት ላይ ሽንፈት አስተናገደ። አረጋዊ በርሄ የሕውሃት የወታደራዊ ደህንነት መረጃን ዋቢ አድርጎ አደገለፀው፣ የሃውዜን የአየር ድብደባ በተፈፀመበት 1980 ዓ.ም የሕውሃት ሰራዊት በከፍተኛ ቁጥር ጨምሮ ከ20ሺህ በላይ ሆነ። በተቃራኒው፣ የደርግ ሰራዊት ከአስር አመት በፊት ከነበረው 300000 ወታደር እየቀነሰ ሄዶ በ1980 ዓ.ም 139,500 ወታደሮች ብቻ ነበሩት። ከሁለት ዓመት በኋላ ግንቦት 20/1983 ዓ.ም የደርግ መንግስት ተገረሰሰ። በዚህ መሰረት፣ በንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈፀመ በደልና ጭፍጨፋ እንደ ሕወሓት ላሉ የሽምቅ ተዋጊ ቡድኖች ዋና የስኬት ምንጭ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። በቀጣይ ክፍል አምስት ከላይ ለተጠቀሰው በደልና ጭፍጨፋ ከሞራልና ሕግ አንፃር ተጠያቂው አካል ማን እንደሆነ እንመለከታለን።