የኢህአዴግ “የደርግ ናፋቂዎች” እና የእናቴ “ጭራቅ” አንድ ናቸው!

ውድ ተማሪዎች “በ2009 ዓ.ም መጀመሪያ አከባቢ በአንዳንድ የሀገራችን አከባቢዎች ለተከሰተው የፀጥታ ችግር እንደ ዋንኛ መንስዔ ሊሆን የሚችለው የቱ ነው?” ለሚለው የጥያቄ “የደርግ ሥርዓት ናፋቂዎች የፈጠሩት ችግር” ተብሏል። “የደርግ ስርዓት ናፋቂዎች” ማለት ምን ማለት ነው? የደርግን ስርዓት የሚናፍቁትስ እነማን ናቸው።

image

በእርግጥ እናንተ የደርግ ስርዓትን በተግባር አታውቁትም። የደርግ ስርዓት ሲወድቅ እኔም ገና የ3ኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ። በእርግጥ ቤተሰቦቻችሁ የደርግ ስርዓትን ሊያውቁት ይችላሉ። በተለይ እድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የደርግ ስርዓትን በተግባር ኖረው አይተውታል። እኔና እናንተ ግን የደርግ ስርዓትን ባንኖርበትም መፅሃፍ በማንበብ፣ በወቅቱ የነበሩ ሰዎችን በመጠየቅ ማወቅ እንችላለን።

በተለይ ደግሞ በቀይ-ሽብር ዘመን የደረሰውን በደልና ጭፍጨፋ በሰው-ልጅ ታሪክ እጅግ አሰቃቂ የሚባሉ ድርጊቶች በኢትዮጲያኖች ላይ እንደተፈፀመ እንገነዘባለን። ለምሳሌ፣ እኔ ሰሞኑን ሳነብ ያገኘሁትን አንድ መረጃ ላካፍላችሁ። የቀይ-ሽበር ዘመቻ በተጀመረ የመጀመሪያ ሳምንት ውስጥ ብቻ እንደ እናንተ ያሉ 5000 ተማሪዎች እንደ አውሬ ታድነው ተገድለዋል፣ 30000 ደግሞ ታስረዋል። በጠቅላላ በቀይ-ሽብር ዘመን የተገደሉት ኢትዮጲያኖች ብዛት 500000 (ግማሽ ሚሊዮን) ይደርሳል።

ከቀይ-ሽብር በኋላ ደግሞ ለምሳሌ በትግራይ ሃውዜን ባፈፀመው የአየር ድብደባ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ 1800 ንፁሃን ዜጎችን ገድሏል። ከዚህ በተጨማሪ፣ የደርግን አስከፊነት በግልፅ ለመረዳት እንዲያግዛችሁ፣ በሸገር ሬድዮ ጣቢያ “የጨዋታ እንግዳ” ፕሮግራም ላይ ጋዜጠኛ ማዕዛ ብሩና ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነብይ መኮንን ጋር ያደረገችውን ጭውውት ከጣቢያው ድህረ-ገፁ ላይ አውርዳችሁ ብታዳምጡት ብዙ ጠቃሚ መረጃዎች ታገኙበታላችሁ።

አያችሁ ተማሪዎች፣…”የደርግ ስርዓት ናፋቂዎች” ማለት ይሄን ሁሉ መከራና ስቃይ የሚናፍቁ ሰዎች ማለት ነው። በእርግጥ በሰው ልጅ ታሪክ እንዲህ ያለ የመከራና ስቃይ ዘመን የሚናፍቁ ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው። በእርግጥ እንዲህ ያሉ ሰዎች እርኩስ መንፈስ የተጠናወታቸው ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ያንን አሰቃቂ ዘመን እያስታወሱ እኔና አናንተን በነፃነት እንዳንናገር፥ እንዳናስብ በፍርሃት ቆፈን መለጎም የሚሹ ሰዎች ናቸው።

ውድ ተማሪዎች፣ የእናንተ ወላጆች ያደርጉ እንደሆነ እኔ አላውቅም። እኔ ልጅ ሳለሁ ግን “ዋ…ጭራቅ ይበላሃል” እያለች ታስፈራራኝ ነበር። ለምሳሌ፣ “ወንዝ ውስጥ ብቻህን ከተቀመጥክ “ጭራቅ” ይበላሃል” ትለኛለች። ማታ ማታ እያለቀስኩ ሳስቸግር “ጆሮ የሚቆርጠው ሰውዬን ልጥራው” ትለኛለች። እኔም ካደኩ በኋላ፣ ታናሾቼን “ጆሮ ቆራጩ መጣ!” እያልኩ አስፈራርቼያለሁ። …ሌላ እናንተ የተባላችሁት ነገር ካለ ጨምሩበት። ነገር ግን፣ ጭራቁም ሆነ ጆሮ-ቆራጩ ማስፈራሪያ እንጂ በእውን የሉም። በአጠቃላይ፣ ልጆች ሲያስቸግሩ ታላላቆቻችን ለማስፈራሪያነት የፈጠሯቸው አስፈሪ ምናባዊ ምስሎች ናቸው።
    
በተመሳሳይ፣ አሁን በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት “የደርግ ስርዓት ናፋቂዎች” የሚለው እንደ እናንተ ያሉ ወጣቶችን ለማስፈራራት የፈጠረው አሰቃቂ ምናባዊ ምስል ነው። ከኢህአዴግ መንግስት በስተቀር የደርግን ስርዓት የሚናፍቅ አንድም ኢትዮጲያዊ የለም። ውድ ተማሪዎች፣ አሁንም ደግሜ የምላችሁ፣ ሀገርን መሃን ያደረገ፣ አንድ ትውልድን ያጨናገፈን የደርግ ስርዓት የሚናፍቅ ኢትዮጲያዊ በጭራሽ የለም።

ልክ በሕፃንነት እድሜዬ እናቴን ሳስቸግር “ጭራቅ ይበላሃል፣ ጮሮ ቆራጩን ልጥራው፣…” እያለች እንደምታስፈራራኝ ሁሉ የኢህአዴግ መንግስትም እኔና እናንተን ለማስፈራራት የፈጠረው ምናባዊ ድርሰት ነው። ከ2008 ዓ.ም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ለታየው የፀጥታ ችግር ዋና መንስዔው የኢህአዴግ መንግስት ራሱ በአደባባይ እንዳመነው “የመልካም አስተዳደር ችግር” ነው። የተለያዩ ሕብረተሰብ ክፍሎች ለሚያነሱት የመብትና ነፃነት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በወታደርና በጥይት ለማፈን ጥረት በማድረጉ የተከሰተ ችግር ነው።

በአጠቃላይ፣ አሁን በፈተናችሁ ላይ የተጠቀሰው “የደርግ ስርዓት ናፋቂዎች የፈጠሩት ችግር” የሚለው ልክ እንደ እናቴ “ጭራቅና ጆሮ-ቆራጩ ሰውዬ” የፈጠራ ድርሰት ነው። ልዩነቱ እናቴ ስላስቸገርኳት ትቆጣኛለች፣ ታስፈራራኛለች፣ ትገርፈኛለች። የኢህአዴግ መንግስት ግን መብትና ነጻነቴን ስለጠየቅኩት ያስረኛል፣ ይደበድበኛል፣ ይገድለኛል! እናቴ እኔን በስነ-ምግባር አንፃ ልታሳድገኝ ነው፣ ኢህአዴግ ግን የዜግነት መብቴን ነፍጎ የራሱን እድሜ ለማራዘም ነው።