ብሔርተኝነት ጨቋኝ ሰርዓትን ለማስወገድ እንጂ ዴሞክራሲን ለመገንባት አይጠቅምም! (ክፍል-3)

ጨቋኝ ስርዓትን ለማስወገድና በምትኩ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመዘርጋት የሚደረገው ትግል ከየትና እንዴት መጀመር አለበት? ይህን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ እንዲቻል የትግሉን መነሻ እና መድረሻ በግልፅ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ጨቋኝ ስርዓትን ለማስወገድ የሚደረገው ትግል መነሻ ምክንያቱ የዜጎች ነፃነትና እኩልነት አለመከበሩ ነው። ስለዚህ፣ የትግሉ ዓላማ ከሕዝቡ ለሚነሳው የነፃነትና እኩልነት ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ነው። በመሆኑም፣ የትግሉ የመጨረሻ ውጤት የዜጎች ነፃነትና እኩልነት የተከበረበት ፖለቲካዊ ስርዓት መዘርጋት ነው። በአጠቃላይ፣ ጨቋኝ ስርዓትን ለማስወገድ የሚደረገው ትግል መነሻና መድረሻ የሕዝብ ነፃነትና እኩልነት ናቸው።

በየትኛውም ግዜና ቦታ ቢሆን ጨቋኝ ስርዓት እስካለ ድረስ ዜጎች ብሶትና ቅሬታ ይኖራቸዋል። ዜጎች በመንግስት ላይ ያላቸውን ብሶትና ቅሬታ የሚገልፁበት ምርጫና አማራጭ ሲያጡ ለአመፅና ተቃውሞ ወደ አደባባይ ይወጣሉ። ነገር ግን፣ ጨቋኝ ስርዓት አመፅና ተቃውሞ በተነሳ ቁጥር ከቀድሞ የበለጠ አስፈሪ የሆነ የኃይል እርምጃ በተቃዋሚዎች ላይ ይወስዳሉ። በእንዱህ ያለ ሁኔታ ውስጥ የፖለቲካ ልሂቃን ሕዝባዊ ንቅናቄውን በትጥቅ ትግል ወይም በሰላማዊ ትግል ለመምራት ምቹ ዕድል ይፈጠርላቸዋል። በዚህ መሰረት፣ ምንም እንኳን አንድ ዓይነት መነሻና መድረሻ ቢኖረውም ጨቋኝ ስርዓትን ለማስወገድ የሚደረገው ትግል ሁለት አማራጭ መንገዶች እንዳሉት መገንዘብ ይቻላል፤ አንደኛ፡- በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የትጥቅ ትግል፣ ሁለተኛ፡- በነፃነትና እኩልነት ላይ የተመሰረተ ሁሉን-አቀፍ ሰላማዊ ትግል ናቸው። ከዚህ በመቀጠል የመጀመሪያውን የትግል ስልት መሰረታዊ ባህሪና ውጤታማነት እንመለከታለን።

የሕዝቡን አመፅና ተቃውሞ በትጥቅ ትግል የማስቀጠል ዝንባሌ ያላቸው የፖለቲካ ልሂቃን በዋናነት ብሔርተኝነት እና በራስ-የመወሰን መብትን ማቀንቀን ይጀምራለ። ብሔርተኘነት የሕዝቡን ንቅናቄ ለማቀጣጠል የሚያገለግል ሲሆን በራስ-የመወሰን መብት ደግሞ የትግሉ ግብ (ተስፋ) ሆኖ ያገለግላል። በአብዛኞቹ የዓለም ሀገራት የሚካሄዱ የትጥቅ ትግሎች በእነዚህ ሁለት እሳቤዎች ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ነገር ግን፣ በዚህ መልኩ የሚካሄድ የትጥቅ ትግል ከትግሉ መነሻ ምክንያትና የመጨረሻ ውጤት አንፃረ የተዛነፈ ነው።

በመጀምሪያ ደረጃ የትግሉ መነሻና መድረሻ የሕዝብ ነፃነትና እኩልነት ነው። ነገር ግን፣ የትጥቅ ትግሉን ለማቀጣጠል ሲባል በማህብረሰቡ ዘንድ እንዲሰርፅ የተደረገው የብሔርተኝነት ስሜት ከነፃነትና እኩልነት ይልቅ በራስ-ወዳድነት (egoisim) እና ወገንተኝነት ላይ የተመሰረተ ነው። ስለ ብሔርተኝነት ፅንሰ-ሃሳብና በሰው ልጅ ላይ ስለሚያስከትለው የሞራል ኪሳራ በክፍል ሁለት በዝርዝር ለመግለፅ ተሞክሯል። ስለዚህ፣ በዚህ ክፍል ዋና ትኩረታችን የትጥቅ ትግል በማህበራዊ ስነ-ልቦና ላይ በሚያስከትለው ተፅዕኖ ላይ ይሆናል። 

Skocpol (1994) and Goodwin (1994) የተባሉ የዘርፉ ምሁራን፣ የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱ አማፂያን ስኬትና ውድቀታቸው የሚወሰነው በሕዝባዊ አመፅ፥ በብሔርተኝነት፥ በውጪ ኃይሎች ድጋፍ፥ የሽምቅ ውጊያ ስልት፥ ወይም ሌላ ሳይሆን በስልጣን ላይ ባለው መንግስት ባህሪ እንደሆነ ይገልፃሉ። ጨቋኝ ስርዓት ለማስወገድ የሚደረግ የትጥቅ ትግል በአብዛኛው የሚጀምረው በሽምቅ ውጊያ ስልት ነው። ይህ ደግሞ አማፂያኑ ራሳቸውን በማህብረሰቡ ውስጥ በመደበቅ በመንግስት ላይ ጥቃት የሚፈፅሙበት ስልት ነው።

ከዚህ በተቃራኒ፣ ጨቋኝና አምባገነን መንግስታት ደግሞ ከአማፂያኑ ጥቃት በተፈፀመባቸው ቁጥር ከከዚህ በፊቱ የበለጠ የኃይል እርምጃ መውሰድ የተዋጊዎቹን ጥቃትና ድጋፍ ይቀንሳል የሚል እሳቤ አላቸው። ሽምቅ ተዋጊዎቹ በማህብረሰቡ ውስጥ ተደብቀው የሚንቀሳቀሱ እንደመሆኑ መጠን ጨቋ መንግስት በሚወስደው የአፀፋ እርምጃ በማህብረሰቡ አባላት በደልና ጭፍጨፋ ይደርሳል።በማህብረሰቡ ላይ በደልና ጭቆና በተፈፀመ ቁጥር ደግሞ የአማፂያኑ ድጋፍ ይጨምራል፣ የመንግስት ተቀባይነት ይቀንሳል። በዚህ መሰረት፣ የአማፂያኑን ጥቃትና ድጋፍ ለመቀነስ በሚል የሚወሰድ የአጸፋ እርምጃ የሽምቅ ተዋጊዎቹን አቅምና ድጋፍ እየጨመረ፣ የጨቋኙን ስርዓት አቅምና ተቀባይነት እየቀነሰ እንዲሄድ ያደርገዋል።

በአጠቃላይ፣ በትጥቅ ትግል የአማፂያኑ ስኬትና የጨቋኝ ስርዓት ውድቀት የሚወሰነው በዚህ ስሌት መሰረት ነው። በመሆኑም፣ በትጥቅ ትግል ጨቋኝ ስርዓት የሚወድቀው ንፁሃንን በመጨፍጨፉ ምክንያት ሲሆን፣ አማፂያኑ ደግሞ የሚያሸንፉት ንፁሃንን ዜችን በማስጨፍጨፋቸው እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ከዚህ አንፃር፣ በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የትጥቅ ትግል በንፁሃን ዜጎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ በደልና ጭፍጨፋ እንዲፈፀም ምክንያት በመሆኑ ተመራጭ አይደልም።

ከዚህ በተጨማሪ፣ የትጥቅ ትግል የመጨረሻ ውጤት በመግቢያው ላይ ከተጠቀሰው የትግሉ መነሻና መድረሻ ጋር ፍፁም ተቃራኒ ነው። የትግሉ መነሻ የሕዝብ ነፃነት እና እኩልነት ቢሆኑም በትጥቅ ትግሉ ወቅት የሰረፀው በራስ-ወዳድነት ላይ የተመሰረተው የብሔርተኝነት ስሜት በሂደት ወደ ወገንተኝነት እና የተበዳይነት ስሜት ይቀየራል። ከላይ በጦርነት ወቅት አማፂያኑ በሚንቀሳቀሱበት ማህብረሰብ ላይ የሚደርሰው በደልና ጭፍጨፋ በሕብረተሰቡ ዘንድ የጠላትነትና ፍርሃት ስሜት እንዲሰርፅ ያደርገዋል። ስለዚህ፣ የትግሉ መነሻ ምክንያት ነፃነትና እኩልነት ናቸው። የትግሉ የመጨረሻ ውጤት ግን የወገንተኝነት/ተበዳይነት እና የጠላትነት/ፍርሃት ናቸው።

ከትጥቅ ትግል በኋላ የሚመሰረተው ፖለቲካዊ ስርዓትም በእነዚህ ስሜቶች ተፅዕኖ ስር ይወድቃል። የወገንተኝነት/ተበዳይነት እና የጠላትነት/ፍርሃት ስሜት በስፋት በሚንፀባረቅበት ማህብረሰብ ዘንድ እንደ አዲስ የሚዘረጋው ፖለቲካዊ ስርዓት የአንድ ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ ይሆናል። በእንዲህ ያለ የፖለቲካ ማህብረሰብ ዘንድ የብዙሃኑን ነፃነትና እኩልነት ማረጋገጥ የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጠበቅ የዋህነት ነው። ከዚያ ይልቅ፣ ከሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎ የሚነሱ የመብትና ነፃነት ጥያቄዎችን በፍርሃትና ጥርጣሬ የሚመለከት ይሆናል። እንደ ቀድሞ ስርዓት የዜጎችን ጥያቄ በኃይል ለማፈን የሚታትር ሌላ ጨቋኝ ስርዓት ይፈጠራል።             

በአጠቃላይ፣ በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የትጥቅ ትግል በማድረግ የብዙሃን ነፃነትና እኩልነት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በፍፁም መገንባት አይቻልም። በብሔርተኝነት ላይ በተመሰረተ የትጥቅ ትግል ከስልጣን ያስወገዱት ጨቋኝ ስርዓት “አልሸሹም ዞር አሉ” የሚሉት ዓይነት ነው። ምክንያቱም፣ ነፃነትን የማያውቅ ነፃ-አውጪ ሳይውል-ሳያድር ጨቋኝነቱ ፍትው ብሎ ይታያል። ለዚህ ደግሞ ጨቋኙን የደርግ ስርዓት በመገርሰስ ወደ ስልጣን ከመጡት የኢህአዴግና የሻዕቢያ መንግስት የበለጠ ጥሩ ማሳያ ያለ አይመስለኝም። (በቀጣዩ ክፍል ደግሞ በነፃነትና እኩልነት ላይ የተመሰረተ ሰላማዊ ትግል እንዴት ማካሄድ እንደሚቻል በዝርዝር እንመለከታለን።)          

9 thoughts on “ብሔርተኝነት ጨቋኝ ሰርዓትን ለማስወገድ እንጂ ዴሞክራሲን ለመገንባት አይጠቅምም! (ክፍል-3)

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡