በብሔርተኝነት ሜዳ ኢህአዴግ ጎል-አግብቶ ወይም ጉቦ-ሰጥቶ ያሸንፍሃል! (ክፍል-4)

ጨቋኝ ስርዓት ከስልጣን ለማስወገድ የመጀመሪያው ነገር የትግሉን ዓላማና ግብ ማስቀመጥ ነው። ባለፉት ክፍሎች በዝርዝር ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ ጨቋኝ ስርዓትን ለማስወገድ የሚካሄደው ትግል መነሻ ምክንያት የዜጎች የነፃነትና እኩልነት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ስላልተሰጠው ነው። የትግሉ የመጨረሻ ግብ ደግሞ የብዙሃኑ ነፃነትና እኩልነት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ነው። የትግሉን ዓላማና ግብ ካስቀመጥክ በኋላ በመቀጠል የራስህንና የጨቋኙን ስርዓት ልምድና ችሎታ ታጠናለህ።

በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት ከአመሰራረቱ ጀምሮ እስከ ፖለቲካዊ ስርዓቱ ድረስ በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ ነው። በዚህ ፅሁፍ የመጀመሪያ ክፍል በዝርዝር በተገለፀው የመከፋፈል መርህ (Principle of division) መሰረት፣ “ብሔርተኝነት” የሕዝብ ንቅናቄ ለመቆስቆስ (mobilization) እና ለማዳፈን (demobilization) ያገለግላል። በመሰረቱ የአንድ ሀገር ዜጎችን በብሔር የመከፋፈሉ ዓላማ የፖለቲካ ስልጣን ለመቆጣጠር ነው። በብሔርተኝነት በመቆስቆስ ወደ ስልጣን የመጣ የፖለቲካ ቡድን በተመሣሣይ ብሔርተኝነትን የሌሎች ብሔሮችን የፖለቲካ ንቅናቄ ለማዳፈን ይጠቀምበታል።

በተለይ አብላጫ ድምፅ የሌለው ብሔርተኛ ቡድን በስልጣን ላይ ለመቆየት ያለው ብቸኛ አማራጭ ተቃዋሚዎችን የጋራ የፖለቲካ አጀንዳና የተቀናጀ እንቅስቃሴ እንዳይኖራቸው መከፋፈል ነው። በዚህ ረገድ የኢህአዴግ መንግስት ከጠቅላላው የሀገሪቱ ሕዝብ አብላጫ ድምፅ ያላቸውን የኦሮሞና አማራ ሕዝቦችን የሚወክሉ የፖለቲካ ቡድኖች በመከፋፈሉ ረገድ የሚከተለው ስልት እንደ አይነተኛ ማሳያ ሊቀስ ይችላል። ነገሮችን ከተለየ አቅጣጫ እንዲታዩ በማድረግ አፍራሽ ሚና ያላቸው፣ እንደ “Bourdieu” አገላለፅ፣ “the evocative power of an utterance which puts things in a different light” የሚባሉ ዓይነት፣ ታሪካዊ ቅራኔዎችንና አለመግባባቶችን የሚቀሰቅሱ አገላለፆች በስፋት ይጠቀማል። ከእነዚህ ውስጥ ለምሳሌ፡- “ትምክህተኛ፥ ጠባብ-ብሔርተኛ፥ ነፍጠኛ፥ የደርግ ሰርዓት ናፋቂዎች፥ …” የሚሉት በዋናነት ይጠቀሳሉ።

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ ብሔርተኝነትን እያቀነቀነ ወደ ስልጣን የመጣው ሕወሃት መራሹ የፖለቲካ ቡድን ብሔርተኝነትን መልሶ የአማራና ኦሮሞ ሕዝብን የፖለቲካ ንቅናቄ ለማዳፈን እየተጠቀመበት እንደሆነ ያሳያል። በብሔር ላይ የተመሰረተ ማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ የኢህአዴግ መንግስት በቀደደው ቦይ እንደ መፍሰስ ነው። ኢህአዴግ ከአመሰራረቱ ጀምሮ እየተጫወተ ያደገው በብሔርተኝነት ሜዳ ነው። በሜዳው ኢህአዴግ ወይ ተቃዋሚዎች ላይ ጎል አግብቶ አሊያም ለተቃዋሚዎች ጉቦ ሰጥቶ ያሸንፋል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ በብሔርተኝነት ላይ በተመሰረተ የትጥቅ ትግል በስልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ ቡድን ከማንም የተሻለ ልምድና ችሎታ አለው። በክፍል ሦስት በዝርዝር ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ በብሔርተንነት ላይ የተመሰረተ የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱ አማፂ ቡድኖች ስኬትና ውድቀታቸው የሚወሰነው በሌላ ነገር ሳይሆን በስልጣን ላይ ባለው መንግስት የአፀፋ እርምጃ ነው። አማፂያኑ በመንግስት ላይ ጥቃት በፈፀሙ ቁጥር መንግስት አማፂያኑ በሚንቀሳቀሱበት አከባቢ ላይ ከቀድሞ የበለጠ የኃይል እርምጃ መውሰድ አለበት።

መንግስት የአማፂያኑን ጥቃትና ድጋፍ ለመቀነስ በሚወስደው የኃይል እርምጃ በማህብረሰቡ ላይ የሚፈፅመው በደልና ጭቆና ከሌለ ወይም ዝቅተኛ ከሆነ የአማፂያኑ የማሸነፍ እድል በዚያው ልክ ዜሮ ወይም አነስተኛ ይሆናል። ለምሳሌ፣ የደርግ መንግስት በትግራይ ያሰማራው ሦስተኛው አብዮታዊ ጦር ከሕወሃት ታጋዮች እየደረሰበት ተደጋጋሚ ጥቃት ለማስቆምና አማፂያኑ በሽረ አካባቢ ያላቸውን ድጋፍ ለመቀነስ በሚል በሃውዜን የአየር ድብደባ ፈፀመ። ነገር ግን፣ ከሃውዜን ጭፍጨፋ በኋላ ባለው አንድ አመት ውስጥ በደረግ በደረሰበት ሽንፈት ትግራይን ለአማፂያኑ አስረክቦ ወጣ። ታዲያ ደርግ ሃውዜን ላይ በፈፀመው ስህተት ለስኬት የበቃ የፖለቲካ ቡድን ተመሳሳይ ስህተት ይፈፅማል ብላችሁ ታስባላችሁ?

ከዚያ ይልቅ፣ በትጥቅ ትግሉ ወቅት የቀሰመውን ልምድ በአግባቡ እየተጠቀመበት ያለ ይመስለኛል። በተለያየ ግዜ፥ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የትጥቅ ትግል ጀመርኩ ያለ አማፂ ቡድን ሦስት ወር ባልሞላ ግዜ ውስጥ ለሁለት ይከፈላል። ከዚያ በኋላ፣ አንደኛው ወገን በተፈጠረው ነገር ላይ እርስ-በእርሱ እንኳን ተወያይቶ ሳይጨርስ፣ ሌላኛው ወገን በቤተ-መንግስት ሲወያይ ይታያል። ስለዚህ፣ በስልጣን ላይ ያለው ቡድን ከአመሰራረቱ ጀምሮ የሚከተለው የመከፋፈል ስልት በየትኛውም የፖለቲካ መድረክ ተግባራዊ እንደሚያደርገውና በጣም የተካነበት ስልት እንደሆነ በግልፅ ያሳያል። አሁንም በድጋሜ ብሔርተኝነት የኢህአዴግ ሜዳ መሆኑን ያሳያል። በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የትጥቅ ትግል ኢህአዴግ ወይ ጎል አግብቶ አሊያም ለአማፂያኑ ጉቦ ሰጥቶ ያሸንፋል።

በአጠቃላይ፣ ብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የኢህአዴግ መንግስት በጣም የተካነበት ስልት ነው። ብሔርተኝነትን ሕዝባዊ ንቅናቄን ለመቆስቆስ ሆነ ለማዳፈን በሚገባ ተጠቅሞበታል፥ እየተጠቀመበትም ይገኛል። ስለዚህ፣ በብሔርተኝነት ላይ በተመሰረተ ማንኛውም የፖለቲካ አንቅስቃሴ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ማስወገድ ሆነ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት አይቻልም። ከዚያ ይልቅ፣ ብሔርተኝነት የሕልውና መሰረቱ ለሆነ የፖለቲካ ቡድን የሚሸነፈው በአንድነት በመደራጀት ነው። በወገንተኝነትና ጦርነት የተካነ የፖለቲካ ቡድን በነፃነትና እኩልነት መርህ ላይ ለተመሰረተ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ፍፁም እንግዳ ነው። ሁሉን-አቀፍ የሰላማዊ ትግል መርሆችና የአተገባበር ስልቶችን በሌላ ፅሁፍ በዝርዝር እንመለስበታለን።