ሕገ-መንግስታዊ መብትን እንደ “ልዩ ጥቅም”

የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ህገ-መንግሥታዊ “ልዩ ጥቅም” አስመልክቶ በቀረበው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መግለጫ “የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም” በማለት የጠቀሳቸው ነጥቦች በሙሉ የክልሉና የህዝቡ ሕገ-መንግስታዊ መብቶች ናቸው። ባለፈው ባወጣነው ፅሁፍ ከአገለግሎት አቅርቦትና የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ መካከል ያለው ግንኙነት በዋናነት በስነ-ምጣኔ (Economics) መርህ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ በዝርዝር ለማስረዳት ሞክሬያለሁ። በዚህ መሰረት፣ አዲስ አበባ ከተማ የአገልግሎትና የተፈጥሮ ሃብት ተጠቃሚ (service and natural resource consumer) ስትሆን የኦሮሚያ ክልል ደግሞ አቅራቢ (supplier) ነው። በመሆኑም፣ የኦሮሚያ ክልል ከአገልግሎት አቅርቦትና የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ሊከበርለት የሚገባው ልዩ ጥቅም “ለከተማዋ ለሚያቀርበው አገልግሎትና የተፈጥሮ ሃብት ተገቢ ዋጋ (reasonable price) ሊከፈለው ይገባል” የሚለው ነው።

ይሁን እንጂ፣ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ህገ-መንግሥታዊ “ልዩ ጥቅም” አስመልክቶ በቀረበው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መግለጫ መሰረት “ልዩ ጥቅም” በሚል ከቀረቡት ነጥቦች ውስጥ አብዛኞቹ የክልሉና የሕዝቡ ሕገ-መንግስታዊ መብቶች ናቸው። በመሰረቱ ሕገ-መንግስታዊ መብት ማክበርና ማስከበር የመንግስት ግዴታና ኃላፊነት ነው። ሕገ-መንግስታዊ መብት ከአገልግሎት አቅርቦት እና የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ጋር የተያያዘ “ልዩ-ጥቅም” አይደለም። በመግለጫው ውስጥ እንደ ልዩ ጥቅም የተጠቀሱት በሙሉ ለኦሮሚያ ክልል ብቻ ሳይሆን ለሁሉም  ክልሎችና ሕዝቦች የተሰጡ ሕገ-መንግስታዊ መብቶች ናቸው። በዚህ መሰረት፣ በዚህ ረቂቅ አዋጅ የኦሮሚያ ክልል ከሌሎች ክልሎችና ሕዝቦች ምንም የተለየ ጥቅም አልተከበረለትም። የኦሮሚያ ልዩ-ጥቅም ጉዳዩን በንፅፅር ለማየት እንዲቻል የሕገ-መንግስቱን ድንጋጌዎች እና የሚኒስትሮች ምክር ቤት መግለጫን ጎን-ለጎን አያይዘን እንደሚከተለው አቅርበናል።   

የኢፌድሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 90 (1)፡ “ ማህበራዊ ነክ ዓላማዎች”፤ “የሀገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን ሁሉም ኢትዮጲያዊ የትምህርት፥ የጤና አገልግሎት፥ የንፁህ፥ የመኖሪያ፥ የምግብና የማህበራዊ ዋስትና እንዲኖረው ይደረጋል።” የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ህገ-መንግሥታዊ “ልዩ ጥቅም” አስመልክቶ የቀረበ መግለጫ፤

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጠጥ ውሃ የሚያገኘው በአብዛኛው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚገኙ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር መገኛዎች በመሆኑ ከዚህ አኳያ ጉድጓዱ የሚቆፈርበት፣ ግድብ የሚለማበት ወይም የውሃ መስመሩ አቋርጠው የሚያልፍባቸው የክልሉ ከተሞችኛ አና ቀበሌዎች በአስተዳደር ወጪ የመጠጥ ዉሃ ተጠቃሚ  እንዲሆኑ እንደሚደረግ በሕጉ ተቀምጧል፡፡

በአዲስ አበባ ጋር በተያያዘ በዙሪያ ያሉ ወጣቶች በተቀናጀ ሁኔታ የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሌሎች በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉት አካባቢዎች አዲስ አበባ የሚሠራቸው ሥራዎች ለዙሪያ ወጣቶች የሥራ እድል እንዲያመቻች በእውቀትና በእቅድ የተመሠረተ ሥራ መሠራት ያለበት ይሆናል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ከባንኮች ጋር በመተባበር የማህበራዊ ቤቶች የሆኑትን የኮንደሚኒየም ቤቶች አስገንብቶ ከነዚህ ውስጥ በከተማው ላሉ የመንግሥት ሠራተኞትና ሴቶች በኮታ በእጣ ወስጥ ገብተው እንደወዳደሩ የደርጋል፡፡ በተመሳሳይ መለኩ ለኦሮሚያ ክልል መንግሥት ሠራተኛ ሆነው በከተማው ውስጥ ለሚኖሩትም ተመሳሳይ እድል እንዲሰጥ በአዋጁ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል፡፡

የኢፌድሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 89፡“የኢኮኖሚ ነክ ዓላማዎች”፣ (5) መንግስት መሬትና የተፈጥሮ ሃብትን በሕዝብ ስም በይዞታው ስር በማድረግ ለሕዝቡ የጋራ ጥቅምና እድገት እንዲውሉ የማድረግ ኃላፊነት አለበት። አንቀፅ 50(4)፤ “የኢትዮጲያ አርሶ አደሮች መሬት በነፃ የማግኘትና ከመሬታቸው ያለመነቀል መብታቸው የተከበረ ነው”። የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ህገ-መንግሥታዊ “ልዩ ጥቅም” አስመልክቶ የቀረበ መግለጫ፤

በከተማው ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት የኖረው የኦሮሞ አርሶአደር ቁጥሩ ቀላለ ባልሆነ ሁኔታ በልማት ምክንያት ተነሺ ነበር፡፡ አሁንም ለልማቱ ተፈላጊ እስከሆነ ድረስ በማሳመን ይህንኑ መፈፀም የሚገባን ይሆናል፡፡ ዋናው ቁም ነገር ይህ ተነሺ አርሶአደር ቢያንስ ቢያንስ ከቀድሞ ኑሮ የተሻለ ሁኔታ ሊፈጠርለት ይገባል፡፡ በልማቱ ማስፋፋት ምክንያት ተጎጂ ሊሆን በጭራሽ አይገባም፡፡ በዚህ መሠረት ለወደፊቱ በቂ ካሣና በዘላቂነት የሚቋቋምበት ሁኔታ እንዲመቻችለት፣ ከዚህ በፊት የተሠራውም ሥራ ተፈትሾ ጉድለቶች እንዲስተካከሉ፣ እነዚህን ሥራዎች የሚያስተባብር የሚመራና የሚያስፈጽም ጽ/ቤት እንዲደራጅ በአዋጁ እንዲካተት ተደርጓል፡፡

የኢፌድሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 92፡ “የአከባቢ ደህንነት ጥበቃ ዓላማዎች”፤ (1) መንግስት ሁሉም ኢትዮጲያዊ ንፁህና ጤናማ አከባቢ እንዲኖረው የመጣር ኃላፊነት አለበት። (2) ማንኛውም የኢኮኖሚ ደህንነት የሚመለከት ፖሊሲና ፕሮግራም የአከባቢውን ደህንነት የሚያናጋ መሆን የለበትም። የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ህገ-መንግሥታዊ “ልዩ ጥቅም” አስመልክቶ የቀረበ መግለጫ፤

በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ያሉ ከተሞችና ቀበሌዎች ከከተማው ከሚወጡ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎች ከሚደርሱ የአካባቢ ብክለትና ጉዳት የመጠበቅ መብት እንዳላቸው፣

ከአዲስ አበባ ከተማ በሚወጡ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎች ከሚደርሱ የአካባቢ ብክለትና ጉዳት የክልሉን ከተሞችና ቀበሌዎች ለመጠበቅ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ እንዲካሄድ እንደሚደረግ፣ ቆሻሻን መልሶ የመጠቀም ሥርዓት እንደሚዘረጋ፣

በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ያሉ ከተሞችና ቀበሌዎች ደህንነቱ ሳይጠበቅና ቁጥጥር ሳይደረግበት ከተቀመጠው ደረጃ በላይ ወደ ክልሉ በተጣሉ ወይም በፈሰሱ ቆሻሻዎች ምክንያት በሰው፣ በእንስሳትና በተፈጥሮ አካባቢ ላይ ለደረሰው ጉዳት በሕግ አግባብ ከአስተዳደሩ ካሳ የማግኘት መብት እንደሚኖራቸው፣

ለአዲስ አበባ ከተማ ልማት የግንባታ ማእድናት ማግኛ ሥፈራዎች የአየር ብክለት እንዳያስከትሉ እና ለደን ልማት ወይም ለሌሎች ልማቶች መዋል እንዲችሉ እንዲያገግሙ አንደሚደረጉ፣

ለአዲስ አበባ ከተማ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ማከሚያና ማስወገጃ ቦታዎች እንዲሁም መልሶ መጠቀሚያ ስፈራዎች አስተዳደሩና ክልሉ በጋራ ባጠኗቸወ ቦታዎችና ሳይንሳዊ መስፈርቶችን ባሟሉ ሁኔታዎች እንዲተዳደሩ አንደሚደረጉ፣