ኦህዴድ ስንት “አሉላ ሰለሞኖች” አሉት?

ትላንት ከአንድ የውጪ ዲፕሎማት ጋር በኢትዮጲያ ስላለው ፖለቲካዊ ሁኔታ አንዳንድ ነገሮችን እያነሳን ተወያየን። በውይይቱ ከተነሱት ነጥቦች አንዱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የአመራር ሁኔታ ነበር። ዲፕሎማቱ “አዲሱ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) አመራር ውሳኔ ሰጪነት እና በሕዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ምን ይመስላል?” የሚል ነበር።

በእርግጥ በኦሮሚያ ክልል ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ የኢህአዴግ መንግስት ከውሳኔ ሰጪነት እና ተቀባይነት አንፃር መሰረታዊ ችግር አለበት። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ልሂቃን በፖለቲካው ውስጥ በሚፈለገው ደረጅ ንቁ-ተሳትፎ አለማድረጋቸው ነው። የፖለቲካ ልሂቃን የሚጠበቅባቸውን ሚና በአግባቡ መወጣት ከተሳናቸው በከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ውሳኔ ሰጪነት እና ተቀባይነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይፈጥራል። ከዚህ አንፃር ያለውን መሰረታዊ ችግር ከማየታችን በፊት የፖለቲካ ልሂቃን የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ በአጭሩ እንመልከት።

ኢህዴድ ከሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የበለጠ አባላትና አመራሮች እንዳሉት ይታወቃል። ነገር ግን፣ እነዚህ አባላትና አመራሮች ፖለቲከኞች እንጂ የፖለቲካ ልሂቃን (political elites) አይደሉም። ነገር ግን፣ የፖለቲካ አመራር (political leadership) እና ውሳኔ ሰጪነት (decision making) በህዝብ ዘንድ ባለ ተቀባይነት የሚወሰን ነው። በሕዝብ ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት (legitimacy) ያለው የፖለቲካ ቡድን ቁርተኛ የሆነ አመራርና ውሳኔ ሰጪነት ሊኖረው ይችላል። በተቃራኒው፣ በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት የሌለው የፖለቲካ ቡድን ፖሊሲና ዕቅዶቹን በአግባቡ ማስፈፀም ይሳነዋል። በዚህ መሰረት፣ በስልጣን ላይ ያለ የፖለቲካ ቡድን አመራርና ውሳኔ ሰጪነት፣ ብሎም የማስፈፀም አቅም የሚወሰነው አመራሩ በህዝብ ዘንድ ባለው ተቀባይነት ነው። የፖለቲካ አመርሩ ተቀባይነት (legitimacy) ደግሞ በዋናነት የሚወሰነው በፖለቲካ ልሂቃን አማካኝነት ነው።

image
ምስል-1

ከላይ በምስል-1 ላይ እንደሚታየው፣ የፖለቲካ ልሂቃን በመንግስት እና በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል መካከል ባለው ግንኙነት ላይ በሁለት መልኩ ተፅዕኗቸውን ያሳርፋሉ። አንደኛ፡- የፖለቲካ መሪዎች የሚሰጧቸውን አመራሮችና የሚያሳልፏቸውን ውሳኔዎች ደግፈው ሃሳብና አስተያየት በመስጠት በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ያስችላሉ። ሁለተኛ፡- ከብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ጋር በቀጥታ ግጭት (conflict) ውስጥ በመግባት የአመራሩን ተቀባይነት ለማስረፅ ይተጋሉ። ስለዚህ፣ የኦህዴድ/ኢህአዴግ አመራር ሰጪነት መታየት ያለበት በዋናነት ከኦሮሞ ልሂቃን የፖለቲካ ተሳትፎ አንፃር ነው።

በፅሁፉ መግቢያ ላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ ዲፕሎማቱ “አዲሱ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) አመራር ውሳኔ ሰጪነት እና በሕዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ምን ይመስላል?” ብሎ ሲጠይቀኝ የእኔ መልስ “ኦህዴድ ስንት “አሉላ ሰለሞኖች” አሉት?” የሚል ነበር፡፡ እሱም በአግራሞት እየተመለከተኝ “who is Alula Solomon?” አለኝ። በእርግጥ አሉላን የጠቀስኩት ይሄ ነው የሚባል የተለየ ምሁራዊ ብቃት ኖሮት አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ የሕወሃት/ኢህአዴግ ቀንደኛ ደጋፊና ለፓርቲው ጠቃሚ መስሎ እስከታየው ድረስ ምንም ዓይነት ተግባርና ውሳኔ ከመደገፍ ወደኋላ የማይል ስለሆነ ነው።

በእርግጥ አሉላን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ለአራት አመት ያህል አውቀዋለሁ። ከእሱ ጋር የተለየ ፀብ ሆነ ግንኙነት የለኝም። ነገር ግን፣ በተደጋጋሚ እንደታዘብኩት፣ አሉላ በመንግስት አካላት የተፈፀመ ስህተት ሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለሕወሃት ጠቃሚ እስከመሰለው ድረስ ሽንጡን ገትሮ ይከራከራል። ለምሳሌ፣ ባለፈው 2008 ዓ.ም የነሃሴ ወር ላይ እኔ፥ አሉላና ግዛቸው ኢብሳ የዶች-ቬሌ ራዲዮ ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ እንደ አሉላ አገላለፅ ¨Wonderful discussion” አድርገናል። ከአንድ ወር በኋላ እኔ ስታሰር ግን “ስድና በጥላቻ” የተሞላሁ ሰው መሆኔን በመጥቀስ ያለ ምንም ጥፋትና ማስረጃ መታሰሬ “አግባብነት” እንዳለው ለማሳመን ሲታትር ነበር። ከታች ያለው ምስል ከአሉላ የፌስቡክ ገፅ የተወሰደ ሲሆን ከላይ የተጠቀሰውን ሃሳብ በግልፅ ያሳያል፡-

image
ምስል-2

አሁንም ቢሆን በአሉላ ላይ የተለየ ጥላቻ ሆነ ቂም የለኝም። ከዚያ ይልቅ፣ እኔን የሚያሳስበኝ ሌሎች የሀገራችን ምሁራን በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳብና አስተያየታቸውን እንዳይሰጡ በፍርሃት ቆፈን ተይዘው፣ የተቀሩትም ለእስርና ስደት በተዳረጉበት ሁኔታ፣ እንደ አሉላ ያሉ የፖለቲካ ልሂቃን ብቻቸውን ፖለቲካውን ከፊት መምራታቸው ነው። ለምሳሌ፣ ከታች ባለው ምስል ላይ እንደሚታየው፣ አሉላ ከሕወሃት ጋር በተያያዘ ለተነሳ ጥያቄ የፓርቲውን ርዕዮተ-አለምና የወደፊት አቅጣጫ በመተንተን ምላሽ ይሰጣል። ከጎን ባለው ምስል ላይ ደግሞ ይህ ቀንደኛ የሕወሃት ደጋፊ የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣውን ረቂቅ አዋጅ ደግፎ ሲከራከር ይታያል።

image
ምስል-3

በእርግጥ እንደ አሉላ ያሉ ሰዎች በማንኛውም ዓይነት ጉዳይ ላይ ሃሳብና አስተያየታቸውን መስጠት መብታቸው ነው። ችግሩ፣ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር፣ በሀገራዊ ሆነ ክልላዊ ጉዳይ ላይ ሃሳብና አመለካከታቸውን ያለ ገደብ የመግለፅ ነፃነት ያላቸው እነሱና እነሱ ብቻ መሆናቸው ነው። ለምሳሌ፣ አዲሱ የኦሮሚያን “ልዩ ጥቅም” ለመወሰን በወጣው ረቂቅ አዋጅ የክልሉንና የህዝቡን ጥቅም አያስከብርም። ረቂቅ አዋጁን በመቃወም ላይ ያሉት አብዛኞቹ የኦሮሞ ልሂቃን በውጪ ሀገር ያሉ ሲሆን በሀገር ውስጥ ያሉት ደግሞ ሃሳብና አመለካከታቸውን የመግለፅ ዕድል ተነፍገዋል። ጥቂቶች እንደፈለጋቸው በነፃነት እየተናገሩ ብዙሃኑ በፍርሃት ተለጉመው የሚቀጥሉት እስከ መቼ እንደሆነ አይገባኝም። ያም ሆነ ይህ፣ ሁኔታው በአዲሱ የኦህዴድ አመራር ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩ ግን ግልፅ ነው።  

One thought on “ኦህዴድ ስንት “አሉላ ሰለሞኖች” አሉት?

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡