ደርግና ኢህአዴግ፡ ጨቋኝ ስርዓት የሚፈጠረው በልሂቃን መከፋፈል ነው!

ባለፈው ዓመት የቀድሞ የአየር ኃይል ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት (ጆቤ) “ድርግነት እያቆጠቆጠ – ዴሞክራሲ እየጨላለመ ነው – ሕዝቦች ጠንቀቅ በሉ” በሚል ርዕስ ማሳሰቢያ አዘል ፅሁፍ አውጥተው ነበር። ነገር ግን፣ እንደ ጄ/ል አበበ ያሉ የቀድሞ ጦር አዛዦች ራሳቸው የገረሰሱት የድርግ ስርዓት “ተመልሶ ሊመጣ ነውና ተጠንቀቁ” የሚል ማሳሰቢያ መስጠታቸው ለብዙዎች ግራ ያሰኛል። ምክንያቱም፣ በደርግም ሆነ በኢህአዴግ ዘመን በዜጎች ላይ በደልና ጭቆና የሚፈፅመው በመከላከያና ደህንነት ኃይሎች አማካኝነት መሆኑ ግልፅ ነው። ስለዚህ፣ የደርግ ስርዓት ተመልሶ ቢመጣ እንኳን በእነሱና በቀድሞ ባልደረቦቻቸው አማካኝነት እንደሆነ መገመት ይቻላል። ታዲያ እነዚሁ ሰዎች ተመልሰው “ደርግነት እያቆጠቆጠ ነው” ሲሉ መስማት ለብዙዎች ግር የሚያሰኝ ነገር ነው።

በእርግጥ ላለፉት አስር አመታት በኢትዮጲያ ፖለቲካ ውስጥ የታየውን ለውጥ በጥሞና ላስተዋለ ነገሩ ሁሉ “ከድጡ ወደ ማጡ!” የሚሉት ዓይነት እንደሚሆንበት አልጠራጠርም። በመሰረቱ፣ ፍርሃት (fear) የጨቋኝ ስርዓት መርህና መመሪያ ነው። በጨቋኝ ስርዓት ስር የሚኖሩ ዜጎች በእለት-ከእለት እንቅስቃሴያቸው ላይ ፍርሃት እንደ ጥላ ይከተላቸዋል። ፍርሃት፤ የዜጎችን ነፃነት የሚገድብ፣ የእኩልነትን የሚያጠፋ፣ ፍትህን የሚያጓድል፣ በአጠቃላይ ዴሞክራሲን የሚገድል “ጥላ-ወጊ” ነው። ዛሬ በኢትዮጲያ ላይ የፍርሃት ድባብ (climate of fear) ተንሰራፍቷል።

በተለይ ከ1997 ዓ.ም ወዲህ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የግል ሚዲያ፣ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች እና የፍትህ ተቋማት ስራና አሰራርን በዝርዝር ስንመለከት ሕገ-መንግስታዊ ዴሞክራሲ (constitutional democracy) ከስረ-መሰረቱ እየተናደ በመፍረስ ላይ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። በተጠቀሰው ግዜ ውስጥ፤ በተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎች፥ በጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋቾች ላይ የሚደርሰው እስራት፥ ስደትና እንግልት፣ በምርመራ ስም የሚደርስባቸው መከራና ስቃይ፣ እንዲሁም ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ በወጡ ሰላማዊ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ግድያ፥ አካል ጉዳት፥ እስራትና እንግልትን ስንመለከት “ደርግነት ከማቆጥቆጥም አልፎ እንደ ዋርካ ዛፍ አድጎና ተንዘርፏል” ለማለት ያስደፍራል።

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ ባለፉት አስር አመታት ደርግነት ከማቆጥቆጥ አልፎ ስር ሰድዶ በቅሏል። በዚህም በሁላችንም ሕይወትና እንቅስቃሴ ላይ የፍርሃት ድባብ አጥልቷል። ነገር ግን፣ “የደርግ ስርዓት እንዴትና ለምን ተመልሶ መጣ?” የሚለው ለብዙዎቻችን ግልፅ አይደለም። ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠው ምላሽ ደግሞ ስለ ፖለቲካዊ አገዛዝ ባለን ግንዛቤ ላይ ይወሰናል። ለምሳሌ፣ “ኢትዮጲያን እየገዛ ያለው ማን ነው?” ተብለን ብንጠየቅ አብዛኖቻች የተወሰነ የፖለቲካ ቡድንን፥ የመንግስት ባለስልጣናትን ወይም የጦር መሪዎችን ስም ከመዘርዘር አናልፍም። ነገር ግን፣ የፖለቲካ አገዛዝ የሚመራው በፖለቲካ ፓርቲ፥ ባለስልጣናት ወይም የጦር ጄኔራሎች አይደለም።

“በሳንጃ የፈለከውን ማድረግ ትችል ይሆናል ከላዩ ላይ መቀመጥ ግን አትችልም” (You can do everything with bayonets, except sit on them) እንደሚባለው፣ ሀገርና ሕዝብን በጦር ኃይል መግዛት አይቻልም። በእርግጥ ሀገርና ሕዝብን በጦር ኃይል ቁጥጥር ስር ማዋል ይቻል ይሆናል።  ነገር ግን፣ በወታደሮችና በጦር መሳሪያ መግዛትና ማስተዳደደር አይቻልም። ለምሳሌ፣ የፈረንሳዩ ንጉስ ናፖሊዮን “Napoleon” ስፔንን በመውረር ሙሉ-በሙሉ በቁጥጥሩ ስር አውሏት የነበረ ሲሆን ሀገሪቷንና ሕዝቡን ለአንዲት ቀን እንኳን መግዛት እንደተሳነው ምሁራን ይገልፃሉ። በፈረንሳዩ ናፖሊዮን እና በስፔን ሕዝብ መካከል የነበረው ሁኔታ በአምስት አመቱ የፋሽስት ወረራ ወቅት በሞሶሎኒ እና በኢትዮጲያ ሕዝብ መካከል ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ይመስለኛል።

ሕዝብና ሀገርን በወታደር ብዛትና በጦር መሳሪያ መቆጣጠር ቢቻልም መግዛት ግን አይቻልም። ምክንያቱም፣ ሀገርን ለመግዛት በመሪነት ቦታ ላይ መቀመጥና ህዝብን መምራት ይጠይቃል። የመሪነት ሚናን በአግባቡ ለመወጣት ደግሞ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የግድ ያስፈልጋል። በሕዝብ ዘንድ ያለ ተቀባይነት ደግሞ የሚወሰነው በብዙሃኑ አስተያየት/አመለካከት ነው። ስለዚህ፣ ሀገርን መግዛት የሚችለው በሌላ ሳይሆን በብዙሃኑ አስተያየት/አመለካከት (public opinion) አማካኝነት ነው። “THE REVOLT OF THE MASSES” በሚለው መፅሃፉ “Jose Ortega y Gasset” ፅንሰ-ሃሳቡን እንዲህ አብራርቶታል፡-   

“By “rule” we are not here to understand primarily the exercise of material power, of physical coercion. This stable, normal relation amongst men which is known as “rule” never rests on force.…It is necessary to distinguish between a process of aggression and a state of rule. Rule is the normal exercise of authority, and is always based on public opinion, to-day as a thousand years ago, amongst the English as amongst the bushmen. Never has anyone ruled on this earth by basing his rule essentially on any other thing than public opinion…. In Newton’s physics gravitation is the force which produces movement. And the law of public opinion is the universal law of gravitation in political history.” THE REVOLT OF THE MASSES፡ CH.XIV፡ Page 71 – 80 

በስልጣን ላይ ያለ የፖለቲካ ቡድን ምንም ያህል ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ ቢኖረው በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት እስከሌለው ድረስ ሀገሪቱን መምራት አይችልም። ሌላው ቀርቶ እንደ ናፖሊዮን ያሉ ጦረኛ መሪዎች እንኳን ውሳኔ ከማሳለፋቸው በፊት የብዙሃኑን ሃሳብና አስተያየት ይጠይቃሉ። በአጠቃላይ፣ ጨቋኝ ስርዓት እንዲኖር በቅድሚያ በደልና ጭቆናን አምኖ የተቀበለ ማህብረሰብ መኖር አለበት። ለዚህ ደግሞ የብዙሃኑን ሃሳብና አመለካከት ለጭቆና በደልና ጭቆናን እንዲቀበል ተደርጎ መቅረፅ ያስፈልጋል።

የፖለቲካ ኃይል ወይም የስልጣን ለውጥ (ሽግግር) ማለት በራሱ የብዙሃኑ አስተያየትና አመለካከት ለውጥ ነው። የብዙሃኑ አስተያየት/አመለካከት ለውጥ በሌለበት የፖለቲካዊ ስርዓት ለውጥ በራሱ ትርጉም የለውም። ምክንያቱም፣ ሀገርና ሕዝብን ለመምራት የሚያስችል ኃይል (ruling power) የሌለው የፖለቲካ ስልጣን ፋይዳ-ቢስ ነው። ነገር ግን፣ በደልና ጭቆናን አምኖ የሚቀበል ማህብረሰብ እንዴት መፍጠር ይቻላል?   

በመሰረቱ አብዛኛው የሀገሪቱ ዜጋ የራሱ የሆነ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት የለውም። የብዙሃኑ አስተያየት/አመለካከት (public opinion) የሚቀረፀው በጥቂት የፖለቲካ ልሂቃን አማካኝነት ነው። እነዚህ ጥቂት የፖለቲካ ልሂቃን በብዙሃኑ አስተያየት/አመለካከት ላይ የበላይነትና ቁጥጥር አላቸው። በዚህ መሰረት፣ የፖለቲካ ልሂቃን በደለና ጭቆናን አጥብቆ የሚጠየፍና የሚቃወም ወይም በተቃራኒው “በደልና ጭቆናን ባይደግፍ እንኳን አምርሮ የማይቃወም” የፖለቲካ ማህብረሰብ መፍጠር ይችላሉ።

ነገር ግን፣ የአንድ ሀገር የፖለቲካ ልሂቃን ከብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል አንፃር የተማሩና የተሻለ የፖለቲካ ግንዛቤ ያላቸው እንደመሆኑ መጠን ከጨቋኝ ስርዓት ይልቅ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲኖር ይሻሉ። በየትኛውም ማህብረሰብ ዘንድ ከመብትና ነፃነት ይልቅ በደልና ጭቆናን የሚያቀነቅን የፖለቲካ ልሂቅ ይኖራል ብዬ አልገምትም። ይሁን እንጂ፣ ልሂቃን ስለ መብትና ነፃነት እየተናገሩ ባለበት ሁኔታ በደልና ጭቆናን አምኖ የተቀበለ ማህብረሰብ ለምን ይፈጠራል?

በመሰረቱ ጨቋኝ ስርዓት ሕዝብና ሀገርን ለመምራት የሚያስችለው ምቹ ሁኔታ የሚፈጠረው በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነት ያለው የፖለቲካ አመለካከት ሳይኖር ሲቀር ነው። ይህ ደግሞ የሚፈጠረው የሀገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን እርስ-በእርስ የሚጋጩ/የማይስማሙ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት በሚያራምዱበት ወቅት ነው። የፖለቲካ ልሂቃን እርስ-በእርስ የሚጋጩ አቋሞችና አጀንዳዎችን በሚያራምዱበት ወቅት የዜሮ-ድምር ጨዋታ ይጀመራል።

በዜሮ-ድምር ፖለቲካ አንደኛው ወገን የሚሰጠው ሃሳብና አስተያየት የሌላኛውን ወገን አቋምና አመለካከት ውድቅ በማድረግ ላይ ያነጣጠረ ነው። ይህ ደግሞ በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ወጥ የሆነ የጋራ አመለካከትና ግንዛቤ እንዳይፈጠር ያደርገዋል። በብዙሃኑ ዘንድ ወጥ የሆነ የፖለቲካ አመለካከት በሌለበት ሀገር ለማስተዳደር የሚያስችለው ኃይል (ruling power) ሊኖር አይችልም። የፖለቲካ ልሂቃን የብዙሃኑን አመለካከትና ግንዛቤ ከመቅረፅ አንፃር ድርሻና ኃላፊነታቸውን መወጣት ሲሳናቸው ሀገርና ሕዝብ መምራትና ማስተዳደር የማይቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል። በዚህ መሰረት፣ ጨቋኞች የተፈጠረውን ክፍተት ተጠቅመው በምሁራኑ/ልሂቃኑ ቦታ ራሳቸውን ይተካሉ። ይህን ሂደት “Jose Ortega y Gasset” እንደሚከተለው ይገልፀዋል፡-    

“What happens is that at times public opinion is nonexistent. A society divided into discordant groups, with their forces of opinion cancelling one another out, leaves no room for a ruling power to be constituted. And as “nature abhors a vacuum” the empty space left by the absence of public opinion is filled by brute force. At the most, then, the latter presents itself as a substitute for the former. Consequently, if we wish to express the law of public opinion as the law of historical gravitation, we shall take into consideration those cases where it is absent, and we then arrive at a formula which is the well-known, venerable, forthright commonplace: there can be no rule in opposition to public opinion.” THE REVOLT OF THE MASSES፡ CH.XIV፡ Page 71 – 80 

በ1960ዎቹ አጋማሽ ላይ የኢትዮጲያ የፖለቲካ ልሂቃን በዋናነት “በኢህአፓ” እና “መኢሶን” አማካኝነት ለሁለት ጎራ ለይተው እርስ-በእርስ ሲጠዛጠዙ የተፈጠረውን ክፍተት ተጠቅሞ ወታደራዊ ደርግ ስልጣን ተቆጣጠረ። በድጋሜ በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ የኢትዮጲያ የፖለቲካ ልሂቃን “በአህዳዊ አንድነት” እና “በብሔር እኩልነት” ጎራ ለይተው እርስ-በእርስ ሲጠዛጠዙ የተፈጠረውን ክፍተት ተጠቅሞ አምባገነናዊ የኢህአዴግ መንግስት ተፈጠረ።

በመጀመሪያ ደርግ በኢህአፓ የተቃጣበትን የነጭ ሽብር ጥቃት ለመመከት መኢሶን ወደ ራሱ አስጠግቶ በቀይ-ሽብር ዘመቻ ኢህአፓ አባላትና አመራሮችን አጠፋ። ኢህአፓዎችን አጥፍቶ ሲጨርስ ከስሩ ያስጠጋቸውን የመኢሶን አባላትና አመራሮች አጠፋ። በተመሣሣይ፣ የኢህአዴግ መንግስት በ1997ቱ ምርጫ ከቅንጅት የተቃጣበትን የሕልውና አደጋ ለማስወገድ እንደ ሕብረት ያሉ ብሔርተኛ የፖለቲካ ቡድኖችን ወደ ራሱ አስጠግቶ የቅንጅት አባላትና አመራሮችን በእስርና በስደት ደብዛቸው እንዲጠፋ አደረገ። ከዚያ በመቀጠል፣ ቅንጅቶችን አጥፍቶ ሲጨርስ ከስሩ ያስጠጋቸውን ብሔርተኛ ቡድኖችን በፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ አማካኝነት ደብዛቸውን በማጥፋት ላይ ይገኛል። በደርግ የቀይ-ሽብር ዘመቻ ሆነ የኢህአዴግ ፀረ-ሽብር አዋጅ ዓላማቸው አንድና አንድ ነው – በሕዝብ ላይ ፍርሃትና ሽብር መፍጠር ነው። ምክንያቱም፣ ሕዝብ በደልና ጭቆናን ተቀብሎ የሚኖረው በፍርሃትና ሽብር ውስጥ ብቻ ነውና።