የአዲስ አበባ ነገር “ሲስሟት ‘እምቢ’ ብላ ሲስቧት” ሆኗል!

ባለፈው ዓመት “ኦሮሚያን ለአመፅ፣ አዲስ አበባን ለቆሻሻ የዳረገች አንቀፅ” በሚል ርዕስ አንድ ፅሁፍ  አውጥቼ ነበር። በፅኁፉ የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) ተግባራዊ አለመደረጉ ለተጠቀሱት ችግሮች ምክንያት መሆኑን ይዘረዝራል። በዚህ አመት በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) መሰረት የኦሮሚያ ክልልን ልዩ-ጥቅም ለመወሰን የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ተከትሎ የውዝግቡ ጡዘት ከርሯል። ከሰሞኑ በኦሮሞ ልሂቃን ዘንድ እየተነሳ ያለው ጥያቄ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ አካል ናት” የሚል ነው። “ይህ ጥያቄ ከሕገ-መንግስቱ አንፃር እንዴት ይታያል” የሚለውን የዘርፉ ምሁራን ትንታኔ ሊሰጡበት ይችላሉ። ይህ ፅሁፍ ግን ጥየቄውን ከመሰረታዊ የመብት መርህ አንፃር ያለውን አንድምታ ይዳስሳል።

ከሦስት አመታት በፊት በኦሮሚያ ክልል አመፅና ተቃውሞ ሲነሳ “የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ይቁም” በሚል እንደነበር ይታወሳል። በዚህ መልኩ የተጀመረው የፖለቲካ ንቅናቄ ዛሬ ላይ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ አካል ናት” ወደሚለው ተቀይሯል። ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ለማወቅ በቅድሚያ ከአመፅና ተቃውሞ በስተጀርባ ያለውን መሰረታዊ ምክንያት መረዳት ያስፈልጋል።

በመሰረቱ፣ አዲስ አበባ ከአመሰራረቷ ጀምሮ በዙሪያዋ ካለው የኦሮሞ ማህብረሰብ ጋር ያላት ግንኙነት ኢ-ፍትሃዊ ነበር። ለብዙ አመታት ከተማዋ በዙሪያዋ ያለውን የኦሮሞ አርሶ-አደር ወደጎን እየገፋችና ከመሬቱ እያፈናቀለች መስፋፋቷ የአደባባይ ሚስጥር ነው። የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) ደግሞ ለዚህ ችግር የመጨረሻ እልባት ለመስጠት ታሳቢ ያደረገ ነው። ሆኖም ግን፣ የክልሉን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ግን ከአንድ ክፍለ-ዘመን በላይ ያስቆጠረውን ኢ-ፍትሃዊ ግንኙነትን ከማስቀጠል የተለየ ዓላማ ያለው አይመስልም።

የኦሮሚያ ክልል እንደ ዘጠኙ የሀገሪቱ ክልሎች፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የክልሉ ነዋሪዎች እንደ ማንኛውም ኢትዮጲያዊ በሕገ-መንግስቱ የተደነገገ መብት አላቸው። የኦሮሚያ ክልል ከአገልግሎት አቅርቦትና የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ግን ከላይ የተጠቀሱት ሕገ-መንግስታዊ መብቶች እንደ “ልዩ-ጥቅም” ተደርገው ቀርበዋል። ለምሳሌ፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 90(1) መሰረት የሀገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን ሁሉም ኢትዮጲያዊ የትምህርት¸የጤና አገልግሎት እና ንፁህ የመጠጥ ውሃ የማግኘት መብት አለው የሚል ሲሆን፣ በአንቀፅ 92(1) መሰረት ደግሞ መንግስት ሁሉም ኢትዮጲያዊ ንፁህና ጤናማ አከባቢ እንዲኖረው የመጣር ኃላፊነት አለበት ይላል።

ሆኖም ግን፣ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ መሰረት፤ አዲስ አበባ የሚያስፈልጋትን ንፁህ የመጠጥ ውሃ ከኦሮሚያ ከርሰ-ምድር በነፃ እየቀዳች ለነዋሪዎቿ በመሸጥ ብዙ ሚሊዮን ብር ታጋብሳለች ለኦሮሚያ ግን የውሃ መስመሩ በሚያልፍባቸው ጥቂት ቀበሌዎች የቧንቧ መስመር ይዘረጋላቸዋል፣ የከተማዋ ፅዳትና ውበት ኤጀንሲ የከተማዋን ደረቅ ቆሻሻ እየሰበሰበ ኦሮሚያ ውስጥ ወስዶ እየጣለ ከአገልግሎት ክፍያ ብዙ ሚሊዮን ብር ይሰበስባል የሰንዳፋ አከባቢ ነዋሪዎች በአከባቢና አየር ብክለት ውስጥ ይኖራሉ፣ አዲስ አበባ እያደገችና እየሰፋች በሄደች ቁጥር ተጨማሪ የመሬት አቅርቦት ከኦሮሚያ ታገኛለች የኦሮሞ አርሶ-አደር ከእርሻ መሬቱ እየተፈናቀለ በድህነት አረንቋ ውስጥ ይዘፈቃል፣ የኦሮሚያ ክልል ከ300 በሚበልጡ በአማርኛ የሚስተምሩ የአንደኛ ደረጃ ት/ት ቤቶችን በመክፈት ሕፃናት በአፍ-መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ያደርጋል በአዲስ አበባ የሚኖሩ የኦሮሞ ልጆች በኦሮምኛ ቋንቋ መማርን እንደ “ልዩ ጥቅም” ይቆጠራል፣…ወዘተ። በአጠቃላይ፣ ረቂቅ አዋጁ የአዲስ አበባን እድገትና መስፋፋት ለማስቀጠል የሚያስፈልጋትን የአገልግሎትና የተፈጥሮ ሃብትን እንደ ከዚህቀደሙ ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እያገኘች እንድትቀጥል ከማድረግ ባለፈ የክልሉን ልዩ ጥቅምን ለማክብር/ማስከበር የተዘጋጀ አይደለም።

በእርግጥ ከላይ የተጠቀሱት አገልግሎቶችና የተፈጥሮ ሃብቶች ለከተማዋ እድገትና መስፋፋት አስፈላጊ ናቸው። ሆኖም ግን፣ የአዲስ አበባ እድገትና መስፋፋት የኦሮሚያ ክልልን መብትና ተጠቃሚነት በሚፃረር መልኩ መሆን የለበትም። ስለዚህ፣ የአዲስ አበባ እድገትና መስፋፋት በዙሪያዋ ካለው የኦሮሞ ማህብረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብትና ተጠቃሚነት ጋር አብሮ መሄድ አለበት። የአዲስ አበባ የማደግ መብት ከኦሮሚያ ክልል ሕዝብ እድገት ጋር አብሮ የማይሄድ ከሆነ ፍፁም ስህተት ነው።

በመሰረታዊ የመብት መርህ መሰረት፣ የአዲስ አበባ እድገትና መስፋፋት በዙሪያዋ ላለው የኦሮሞ ማህብረሰብ መብትና ተጠቃሚነት እንቅፋት መሆን የለበትም። ይህ ካልሆነ ግን፣ የኦሮሞ ሕዝብና መንግስት የራሱን መብት ለማስከበር ሲል የከተማዋ እንቅስቃሴን መግታት መብት ይኖረዋል። ምክንያቱም፣ እንደ “Immanual Kant” አገላለፅ፡-  

“The universal law of right may then be expressed thus: ‘Act externally in such a manner that the free exercise of [your] will may be able to coexist with the freedom of all others’…Consequently, if a certain exercise of freedom is itself a hindrance of the freedom that is according to universal laws, it is wrong; and the compulsion of constraint which is opposed to it is right, as being a hindering of a hindrance of freedom, and as being in accord with the freedom which exists in accordance with universal laws. Hence, according to the logical principle of contradiction, all right is accompanied with an implied title or warrant to bring compulsion to bear on any one who may violate it in fact.” THE SCIENCE OF RIGHT trans., W. Hastie Part-1: Page 2-3

በእርግጥ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከመሠረተ-ልማት አቅርቦት፣ ከመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ከደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ጋር፣ እንዲሁም በተፈጥሮ ሃብት ላይና በአየርና ውሃ ላይ ከሚደርስ ብክለት ጋር በተያያዘ ያላቸው ሕገ-መንግስታዊ መብት ሊከበር ይገባል። ነገር ግን፣ እነዚህ መብቶች የሚከበሩት አግባብ በከተማዋ ዙሪያ ያለውን የኦሮሞ ሕዝብ መብትና ተጠቃሚት በሚገድብ/በሚፃረር መልኩ መሆን የለበትም። በአጠቃላይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ራስን በራስ የማስተዳደር ስልጣን የኦሮሚያን ሕገ-መንግስታዊ መብት እንዳይከበር እንቅፋት መሆን የለበትም።

በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(2) ላይ “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን-በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን ይኖረዋል” በሚል ተደንግጓል።  ሆኖም ግን፣ ይህ መብት በአንቀፅ 49(5) ላይ የኦሮሚያ ክልል፤ ከአገልግሎት አቅርቦት እና የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም፣ እንዲሁም ሁለቱን በሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም አልተጠበቀለትም።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሕገ-መንግስቱ የተሰጠው ራሱን-በራሱ የማስተዳደር ስልጣን የከተማዋ ነዋሪዎችን መብት ለማረጋገጥ እንጂ በከተማዋ ዙሪያ ያለውን የኦሮሞ ማህብረሰብ መብትና ተጠቃሚነት የሚፃረር ተግባር ለመፈፀም አይደለም። የከተማዋ ስልጣን ለክልሉ መብት መከበር እንቅፋት ከሆነ ግን፤ “Right is Conjoined with the Title or Authority to Compel” በሚለው መሰረታዊ የመብት መርህ መሰረት የኦሮሚያ ክልል የከተማ አስተዳደሩን በማስገደድ ሕገ-መንግስታዊ መብቱን ማስከበር ይችላል።

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ በኦሮሚያና አዲስ አበባ መካከል ላለው ችግር ዋና መንስዔና ግንባር ቀደም ተጠያቂው አካል የከተማዋ መስተዳደር ነው። በመሆኑም፣ የኦሮሚያ ክልል የከተማ መስተዳደሩን እንቅስቃሴ ለመግታት የሚወስደው እርምጃ አግባብነት ይኖረዋል።በዚህ መሰረት፣ አዲስ አበባን የኦሮሚያ አካል በማድረግና አስተዳደሩን በመቆጣጠር የክልሉን ሕገ-መንግስታዊ መብትና ጥቅም ለማክበር/ማስከበር የሚያደርገው እንቅስቃሴ ከመሰረታዊ የመብት መርህ አንፃር ትክክልና ተገቢ ነው። ከዚህ አንፃር ሲታይ የአዲስ አበባ ነገር “ሲስሟት ‘እምቢ’ ብላ ሲስቧት” የሚሉት ዓይነት ሆኗል!