ወይኔ…ስድብ አማረኝ! ኢህአዴግን መስደብ አማረኝ!

እናንተ! ዛሬ በጣም ስድብ አምሮኛል። መሰደብ ለምጄዋለሁ። እኔያማረኝ መሳደብ ነው። ይሄው ከነጋ ጀምሮ፤ ስድብ…ስድብ፣ ስደብ…ስደብ ይለኛል፣ ያለ ወትሮዬ መሳደብ፥ መስደብ አምሮኛል። ችግሩ ማንን ልስደብ? “ራስህን ሰደብ” እንዳትሉኝ። ራሴን ሁሌ እንደሰደብኩት ነው። በሰራሁት ስራ አንድም ቀን ረክቼ አላውቅም። ስለዚህ፣ ሁልቀን ራሴን እንደወቀስኩ፥ እንደሰደብኩ ነው። ዛሬ ግን ያማረኝ ሌላን ሰው መስደብ ነው። እ…እ… የቀድሞ ጠ/ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ትዝ… አሉኝ።

ጠ/ሚ መለስ በአንድ ወቅት “’መለስ መላጣ’ ማለት ይቻላል፣ መላጣዬን መንካት ግን አይቻልም” ያሉትን ታስታወሳላችሁ? አቦ… ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልኝማ! አንድ የምሰድበው ሰው አገኘሁኝ! እንሆ ስድብና ተሰዳቢ በነፃ ተገኝቷል። ኑ እንሳደብ! “መለስ መላጣ፣ መለስ መላጣ፣ መለስ መላጣ፣….መሌ መላጣ፣ መልዬ መላጣ፣….መላጣ…ጣ…ጣ…ጣ” ኤጭ… ስድቡ መላ-አጣ!

አንድ ዓይነት ስድብ መሳደብ ይሰለቻል። አንድ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ስድቡ በተሰዳቢው የተፈቀደ ሲሆን ያስጠላል። የተፈቀደ ስድብ ልክ እንደ አደረ ገንፎ ቀዝቃዛ ነው። አያረካም፣ ሺህ ግዜ ቢሳደቡት ጥም አይቆርጥም። ከዚያ ይልቅ፣ ስድብ ልክ እንደ ትኩስ ገንፎ መፋጀት አለበት። ከተሳደቡ አይቀር በድንገት ሳይጠበቅ፥ ሳይታሰብ ከፍ-ዝቅ አድርጎ ሲሆን ያረካል። ስለዚህ፣ አንዲት ቃል አስፈቅዶ “መለስ መላጣ” ማለት ስድብ አይደለም። ከሰደቡ አይቀር እንደ አበበ ገላው በእልህና ቁጭት ውስጥ ሆኖ የጭቃ ዶፍ ማውረድ ነው። ወራጅ አለ!

እዚህ ሀገር ከተፈቀደው ስድብ ውጪ መሳደብ ክልክል ነው። እንደ አበበ ገላው ዲያስፖራ ካልሆንክ በስተቀር እንደመጣልህ እሳደባለሁ ብትል መከራ ይከተልሃል። እንኳን መሳደብ ስለ አበበ ገላው የአሰዳደብ ስልት ማውራት በራሱ አመት ከስድስት ወር ያሳስራል። ለዚህ ደግሞ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ቋሚ ምስክር ነው። (ጌቾ እንኳን ለቤትህ አበቃህ!) ስለዚህ፣ ሀገር ጥለህ ካልወጣህ በስተቀር ከተሰዳቢዎች ፍቃድ ውጪ መሳደብ ያስቀጣል!

አይ አሜሪካ!… ከአሜሪካኖቹ ይልቅ ለኢትዮጲያኖች ስድብ ስትመች አኮ አይጣል! ዲያስፖራዊች፤ መለስን በስብሰባ አዳራሽ፣ ሬድዋንን በገበያ አዳራሽ፣ አቦይ ስብሃትን በሬስቶራንት፣ ግርማ ብሩን በመኖሪያ ቤት፣ …. ወዘተ እየሄዱ የፈለጉትን ባለስልጣን እንደ ይሳደባሉ። ኢትዮጲያ ውስጥ ግን እንኳን መሳደብ የአሜሪካውን ስድብ በሹክሹክታ ማውራት አትችልም።

እኔ ታዲያ የት ሄጄ ልፈንዳ፣ ማንን ምን ብዬ ልስደብ?! ለምሳሌ፣ “መለስ መላጣ” ማለት ይቻላል። ይህን የስድብ ፍቃድ ተጠቅመህ “መለስ ብሔርተኛ!” ማለት ትችል ይሆናል። ነገር ግን፣ አውቀህ ወይም አዳልጦህ “መለስ ዘረኛ” ብለህ ከተሳደብክ፣ ወይም ከጠ/ሚኒስትሩ በፊት ፓርቲያቸውን አስቀድመህ “ኢህአዴግ ሌባ፣ መለስ ዘረኛ” ብለህ ከተሳደብክ ሲዖልን በአካል ሄደህ ታየዋለህ። አቶ ኤርሚያስ ለገሰ “የመለስ ቱርፋቶች” በሚለው መፅሃፉ ገፅ 40 ላይ በካዛንቺሱ መንግስት መኖሪያ ቤት በአይኑ የተመለከተውን እውነታ እንዲህ ገልፆታል፡-

የመለስ ቱርፋቶች፡ ባለቤት አልባ ከተማ፣ ከፍል አራት፥ ገፅ 40 ላይ የተወሰደ

ታዲያ እኔ ማንን ልስደብ? ፓርቲውንና መሪውን መስደብ፥ መሳደብ ፈጽሞ አይታሰብም። ነገር ግን፣ መንግስትን ለብቻው ነጥዬ ብሰድበውስ? ሆሆይ… “ወንዴ አያሌውን ያየ መንግስትን አይሳደብም” አትሉኝም እንዴ? የወንዴ አያሌውን አድራሻ ማወቅ ለምትሹ፣ አዲስ አበባ ቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 08 የቤት ቁጥር “ጎዳና” ነው። “ወንዴ መንግስትን በመሳደቡ ምን አጋጠመው?” ለምትሉ ደግሞ ከታች በምስሉ ላይ የሚታየውን የክስ ቻርጅ እስከ መግለጫው ድረስ በጥሞና አንብቡ፡-

ከማህበራዊ ሚዲያዎች የተገኘ የክስ ቻርጅ

እሺ ታዲያ አሁን ምን ይሻለኛል? ዛሬ ስድብ—ስድብ ብሎኛል። የኢህአዴግ ፓርቲን፣ የኢህአዴግ መሪን፣ የኢህአዴግ መንግስትን መስደብ፥ መሳደብ መከራና ስቃይ ከባድ ነው። እኔ ደግሞ መሳደብ አምሮኛል። ኧ… እነአንቶኔ “ለምን ኢህአዴግን ብቻ ትሳደባለህ?” ሲሉ ይሰማኛል። ለመሆኑ ኢህአዴግን ብሰድበው ምኑ ይጎዳል? ደግሞስ ከኢህአዴግ የበለጠ መሰደብ ያለበት ከቶ ከወደየት ይገኛል? ግልፅ አይደለም? ቆይ ትንሽ ዘርዘር ላድርግላችሁ…

ኢህአዴግ የፖለቲካ ድርጅት ነው። የኢህአዴግ መንግስት ደግሞ አስተዳደራዊ መዋቅር ነው። ድርጅትና መዋቅር ልክ እንደ ሰው-ልጅ የሞራል ስብዕና የላቸውም። በእኔ ስድብ የኢህአዴግ ፓርቲና መንግስት የሞራል ስብዕናው አይነካም። እንደ ሰብዓዊ ፍጡር ክብርና ሰብዕናው አይጎዳም። ኢህአዴግን ስሰድብ ሞራላቸው የሚነካው ድርጅቱና መንግስቱ ሳይሆን በመዋቅሩ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ናቸው። የኢህአዴግ ፓርቲን ወይም መንግስትን ስሳደብ አንዳንድ አባላቱና አመራሮቹ በእኔ ስድብ ራሳቸውን ይሰድባሉ።

ይቅርታ! እኔ እነሱን አልሰደብኩም። እኔ የሰደብኩት ድርጅቱንና መንግስትን ነው። እነሱ ግን ስድቡን ለራሳቸው ወስደው ራሳቸውን በራሳቸው ይሰድባሉ። የሰደብኩት ድርጅትና መንግስት በራሱ የሚነካ ሞራል እና የሚናገር አንደበት የለውም። አንዳንድ የበታችነት ስሜት የተጠናወታቸው ሰዎች ግን በእኔ ስድብ ራሳቸውን እየሰደቡ “መንግስትን ሰድበሃል” እያሉ ይከሱኛል። የበታችነት ስሜት የተጠናወተው ሰው በስሙ ሲጠሩት እንኳን በንቀት የሰደቡት ይመስለዋል። ኢህአዴግን እኔ ብሰድበው ምንም አይጎዳም። በተሰደብን ባዮች ላይ የደረሰው ጉዳት ግን በራሳቸው የአመለካከት ችግር እንጂ በእኔ ስድብ ምክንያት የተፈጠረ አይደለም። ስለዚህ፣ ወሳኙ ነገር የእነዚህን ሰዎች የአመለካከትና ግንዛቤ መለወጥ ነው። ይሁን እንጂ፣ ኢህአዴግና መንግስት ተሰደበ እያሉ ምስኪኖችን መወንጀል፥ ማሰር፥ መቀጥቀጥ፥ … ራስን በራስ መስደብ ነው።

ሌላው ከኢህአዴግ የበለጠ መሰደብ ያለበት ከቶ ከወደየት ይገኛል? እኔ የምለው፣ ማጅራቴን አንቆ አላላውስ ካለኝ የጭቆና ቀንበር ሌላ ማንን ልስደብ ኖሯል? ስኳር፥ ዘይት፥ ዱቄት፣…የግብር ጭማሪ፥ የበጀት ጭማሪ፥ የደመዋዝ ጭማሪ፣… መብራት፥ ውሃ፥ ኔትዎርክ፣…ኢኮኖሚ፥ ፖለቲካ፥ ትምህርት፣… በፀረ-ሽብር ሌላ ሽብር፣ በሰላምና ልማት በደልና ግፍ፣¸መብትና ነፃነትን በጉልበትና ፍርሃት፣ … ስንቱ ተዘርዝሮ ይቻላል! እንደው በጥቅሉ፣ መቼ መኖር፥ መታሰር፥ መገረፍና መሞት እንዳለብኝ በመወሰን ፈጣሪ የሰጠኝን የሕይወት ፀጋ ከቀማኝ ኢህአዴግ የበለጠ ስድብና መሰደብ የሚገባው ያለ ሌላ አካል አለ እንዴ?ይኄው ዛሬ ከነጋ ጀምሮ ኢህአዴግን ስደብ…ስደብ ይለኛል።

እንዴ…በቃ አማረኝ! ስድብ አማረኝ! ኢህአዴግን መስደብ አማረኝ! ታፈንኩ፥ አፈነኝ! ብሶት፥ ቁጭት፥ ምሬት ወስጤን አቃጠለኝ። በነፃነት ማሰብ፥ መናገርና መፃፍ ወንጀል መሠለኝ። የኢህአዴግ ስራው ቀርቶ ስሙ ራሱ አስጠላኝ። የእሱ የሆነ ነገር ሁሉ ገማኝ፥ ጠነባኝ! ነፃነት ናፈቀኝ፣ በፍርሃት መኖር ሰለቸኝ። ኢህአዴግ እጅግ በጣም አስጠላኝ! ስድብ አማረኝ! ኢህአዴግን መስደብ አማረኝ! ምን ያደርጋል ታዲያ መሳደብ ሳልጀምር ስድብ አለቀብኝ ወይስ ፍርሃት አነቀኝ?

One thought on “ወይኔ…ስድብ አማረኝ! ኢህአዴግን መስደብ አማረኝ!

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡